ኢትዮጵያ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በምታደርገው ትግል ውስጥ ሙስና አንዱ ተግዳሮት ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደተናገሩት ሙስና የብሔራዊ አደጋ ስጋት
እስከመሆን ደርሷል። ሙሰኞችም እንዳይታለፍ የተሰመረውን ቀይ መስመር ቀይ ምንጣፍ አድርገው
እየተመላለሱበት ስለመሆኑ አስረግጠው ተናግረው ነበር።
በኢትዮጵያ በዚህ መልኩ የሚገለጸው ሙስና ታዲያ፣ የሕዝብ ሃብት እንዲበዘበዝ እና ላልተገባ ጥቅም
እንዲውል በማድረግ የልማት ጉዞን ወደኋላ ይጎትታል። በሌላ በኩል ሙስና ስር እየሰደደ በሄደ ቁጥር ዜጎች
ከመንግሥት ሊያገኙ የሚገባውን አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግር በመሆን
ሕዝቦችን ለከፋ ችግርና ምሬት ይዳርጋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን መተማመን
ይሸረሽራል፤ ሰላምና መረጋጋትን በማጥፋት የፖለቲካ ምሕዳሩን ይረብሻል።
ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ነገ አሳካዋለሁ ብላ ወደመዳረሻዋ በምትጓዝበት የብልጽግና ጉዞ ላይ ትልቅ
እንቅፋት ሆኖ በመገኘቱ፤ ችግሩን ከወዲሁ ፈር ለማስያዝ የሚያስችል ሥራ እንደሚከናወን ጠቅላይ
ሚኒስትሩ ቃላቸውን ሰጥተው ነበር። በቃላቸው መሠረትም ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል የፀረ-ሙስና
ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁመው ወደሥራ እንዲገባ አድርገዋል። ኮሚቴውም ኅብረተሰቡን ደጀንና
አጋር አድርጎ ሙሰኞችን የመለየትና በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር የጀመረ ሲሆን፤ ከኅብረተሰቡ በደረሰው
ጥቆማ መነሻነት እና በተለያየ አግባብ በደረሰባቸው መረጃና ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ ተጠርጣሪ
ሙሰኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ ፋይል ከፍቷል።
ሰሞኑን ደግሞ ብሔራዊ የፀረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴው እስካሁን የሠራቸው ሥራዎች ጠቅላይ
ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የገመገመ ሲሆን፤ በግምገማውም እስካሁን ከኅብረተሰቡ 800
የሚጠጉ ጥቆማዎች እንደደረሱት፣ 110 የሚሆኑ ጥቆማዎች ወደ ምርመራ መግባታቸውንና ክስ የቀረበባቸው
መዝገቦች ብዛት 65 መድረሱን አስታውቋል።
የዚህ ግምገማ ውጤት እንደሚያሳየው፣ ሙስና የሀገር አደጋ ከመሆኑ አኳያ ችግሩን ከመከላከል አንጻር
ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎም ሆነ ኮሚቴው እየወሰደው ያለው ርምጃ መልካም ጅምር መሆኑን
ነው። ይህ ማለት ግን ሥራው ከችግሩ ስጋትነት አንጻር በሚፈለገው ልክ ተጉዟል ማለት አይደለም።
ሙስና እያደረሰ ካለው ጉዳት እና ከችግሩ ስፋት አንጻር ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ገና ብዙ መሥራት
ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ጥቆማዎችን በማስረጃ
ላይ አስደግፎ ሊያቀርብ፤ ጥቆማውንም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በሌላ በኩል፣ ኮሚቴው የሚደርሱት ጥቆማዎችን በሕግ አግባብ እንዲጣሩ በማድረግ መዝገቦችን
የማደራጀት እና የምርመራ ፋይል የመክፈት፤ እንዲሁም በተደራጁ ፋይሎች ክስ ተመስርቶ ተገቢውን
ውሳኔ እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ ተጠናክሮ መሥራት ይኖርበታል።
በሌላ በኩል የሕዝብ ጥቆማ በደረሰ ቁጥር ቶሎ ተጣርቶ ወደ ርምጃ ካልተገባ፤ አንድም ጥቆማ ሰጪው
ሕዝብ በሂደቱ ተስፋ በመቁረጥ ከተባባሪነት ራሱን ሊያቅብ የሚችልበት እድል ይኖራል። በሌላ በኩል፣
ሙሰኞች በወቅቱ እንዲታረሙ እና እንዲጠየቁ ካልተደረገ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሉ እዚህም እዚያም
የሚፈጥሯቸው ችግሮች ሀገርና ሕዝብን ዋጋ እያስከፈሉ መቀጠላቸው፤ ሌሎችም ወደ ሙስና እያማተሩ ያሉት የሚያስተምራቸውን ርምጃ ስለማያዩ በድፍረት ወደ ሙስናው መድረክ እንዲቀላቀሉ እና ችግሩ የበለጠ ሰፊ እና ውስብስብ እንዲሆን ማድረጉ አይቀሬ ነው።
በመሆኑም የተጀመረው የሙስና ትግል የታለመለትን ግብ እንዲመታ፤ ሥራዎች በተናበበ እና በተቀናጀ
መልኩ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሊከናወኑ ይገባል፤ ኅብረተሰቡም ይህንን የልማት ነቀርሳ ነቅሎ
ለመጣል ሙሰኞችን በማጋለጥ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 5/ 2015 ዓ.ም