በዶሚኒካን ሪፐብሊክ አዘጋጅነት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ እንደሚካሄድ ይታወቃል። በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው ይህ የዓለም ዋንጫ ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ የሚከናወንም ነው። ከየአህጉራቱ በዚህ መድረክ መሳተፍ የሚችሉ ሀገራትም የማጣሪያ ጨዋታዎችን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሚመራው ማጣሪያ ሦስተኛው ዙር ከቀናት በኋላ ይደረጋል። በዚህ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ከኬንያ አቻው ጋር ይጫወታል።
በዓለም ዋንጫው ከስድስቱ አህጉራት የተወጣጡ 16 ቡድኖች ሲካፈሉ፤ አፍሪካ በሦስት ሀገራት ትወከላለች። ቡድኖቹን ለመለየትም 25 ሀገራት ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን ካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ አንስቶ በማጣሪያው ጨዋታ በማሳተፍ ላይ ይገኛሉ። አራት ዙር ባለው ማጣሪያም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን በመርታት ለሦስተኛ ዙር ማለፉ የሚታወስ ነው። አዲስ አበባ እና ፕሪቶሪያ ላይ በነበሩት ጨዋታዎች አጠቃላይ ውጤት 3 ለምንም የሆነ ውጤት ያስመዘገበው የወጣት ቡድኑ ከቀናት በኋላ በሚያደርገው ሦስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከኬንያ ጋር ይገናኛል።
የመጀመሪያው ጨዋታ በተያዘለት መርሀ ግብር መሠረት አዲስ አበባ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያደርግ ሲሆን፤ ከዚህም የሚሆነውን ዝግጅት አስቀድሞ ጀምሯል። በአሰልጣኝ ራውዳ አሊ እየተመራ ከሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም አንስቶ በመሰባሰብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ክፍል የጤና ምርመራ ተደርጎለትም ነው ወደ ዝግጅቱ የገባው። የሜዳ ላይ ተግባር ልምምዱንም በአዲስ አበባ እና አበበ ቢቂላ ስታዲየሞች እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር ሜዳ ላይ እያከናወነ ይገኛል። ዝግጅቱን ተከትሎም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ረውዳ አሊ በ29 ተጫዋቾች የተጀመረው ዝግጅቱ ወደ 23 በመቀነስ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቁማለች። የወዳጅነት ጨዋታን በሚመለከት ሁለት የታቀደው ሁለት ጨዋታ ለማድረግ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የሴት ቡድኖች ወደ ዝግጅት ባለመመለሳቸው እርስ በእርስ ለማድረግ ተገደዋል። ተጋጣሚው የኬንያ ብሄራዊ ቡድን በቅጣት ላይ የቆየ በመሆኑ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ ያልተቻለ መሆኑ ዝግጅቱ በምን መልክ ሊሆን ይገባል የሚለውን አዳጋች ቢያደርገውም ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም እየተሞከረ ነው። ከዚህ በኋላ በሚኖሩት ቀናትም የቡድን ውህደትና ቅንጅት ላይ ያተኮረ ዝግጅት በማድረግ 11ዱን ተጫዋቾች የመለየት ሥራ ይቀጥላል። ቡድኑን በቅርቡ የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ያሉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም የሚተዋወቁ በመሆናቸው የቡድን ስሜት የመገንባቱን ሂደት ቀላል ያደረገው መሆኑንም አሰልጣኟ ታስረዳለች።
የቡድኑ አባላትም ይህንኑ የአሰልጣኟን ሃሳብ ይጋራሉ። አምበሏ ሂሩት ተስፋዬ በሁለተኛው ዙር ጨዋታ ላይ ያልነበሩ አዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን ቢቀላቀሉም በአግባቡ ተግባብተው ዝግጅታቸውን እያደረጉ መሆኑን ገልጻለች። ከአሰልጣኞቻቸው የሚሰጧቸውን የልምምድ አቅጣጫ በመከተል በአንድ የቡድን ስሜት ለውጤታማነት እስከ ጨዋታው ያሉትን ቀናትም ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል።
አጥቂዋ ማህሌት ምትኩም የቡድኑ አባላት በሞራልና በወኔ ሀገራቸውን ለማገልገል እየተጉ መሆናቸውን ነው የምትጠቁመው። በዚህ ዙር አዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን የተቀላቀሉ ቢሆንም ዝግጅቱ አስቀድሞ የተጀመረ መሆኑ ለመግባባት አዳጋች አልነበረም። በአሰልጣኞቻቸው በኩል ከሜዳ ልምምድ ባለፈ በሥነ ልቦናም ዝግጅት ማድረጋቸውም ለውጤታማነት በእጅጉ የሚያግዛቸው እንደሆነም አብራርታለች።
በማጣሪያው ምድብ ሁለት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ተደልድሎ የነበረው የኬንያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው እንደማይሳተፍ ባሳወቀው ተጋጣሚ ምክንያት በፎርፌ ወደ ሦስተኛ ዙር ማለፍ ችሏል። በአዲስ አበባ እና ናይሮቢ በሚኖሩት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አሸናፊ የሚሆነው ቡድንም በመጨረሻው ዙር ጨዋታ ከጅቡቲና ብሩንዲ አሸናፊ ጋር የሚጫወትም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም