በዓልን ከአረጋውያን ጋር – በመቄዶንያ

‹‹ሰውን ለመርዳት ፤ሰው መሆን በቂ ነው!›› በሚለው መሪ ሃሳብ የሚታወቀው “መቄዶንያ” የአረጋውያን እና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል›› ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን በተለይም ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ፣ መመገብ እና መጸዳዳት የማይችሉ የአልጋ ቁራኛ የሆኑና የሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያንን እና የአእምሮ ህሙማንን ከወደቁበት ጎዳና በማንሳት ወደ ማዕከሉ በማምጣት ድጋፍ የሚያደርግ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ7 ሺ 500 በላይ የሚሆኑ ተረጂዎችን ከተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከሚያገኘው ድጋፍ መልሶ እየደገፈ የሚገኘው ማዕከሉ ትናንት በጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ አረጋውያን እና የአእምሮ ሕሙማን ዛሬ ላይ ሕይወታቸው ተቀይሮ በጉልበታቸው እና በእውቀታቸው የደገፏቸውን ማእከል እያገለገሉት ይገኛሉ።

የማዕከሉ መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ እንደሚገልጹት፤ ሁሌም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም ለማዕከሉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ‹‹ሚያዝያን ለመቄዶንያ›› በሚል መሪ ቃል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር አመቻችቷል። በዚህም የኢትዮ ቴሌኮም የማህበራዊ ትስስር ገፆችን ለሚቀላቀሉ አዳዲስ ተከታዮች፣ ልጥፎችን በማጋራትና ላይክ በማድረግ የሚገኘው ገቢ ለማዕከሉ እርዳታ ይውላል።ሕብረተሰቡም የኢትዮ ቴሌኮምን ገጽ በመቀላቀል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም የማህበራዊ ትስስር ገፆች ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም፣ ዩትዩብ፣ ሊንክዲን እና ቴሌብርን በመቀላቀል፤ እያንዳንዱ ሰው ሰብስክራይብ ሲያደርግ አስር ብር አዳዲስ ተከታዮች ሲቀላቀሉ ደግሞ ሠላሳ ብር ለመቄዶንያ ገቢ እንደሚደረግ በመረዳት ቀላል የሚመስል ነገር ግን ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውን እርዳታ እንዲያደርጉ መሥራቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ማዕከሉ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን ደሴ፣ ድሬዳዋ፣ ሻሸመኔ፣ አድዋ፣ ባህርዳር፣ ሐረር፣ ጋምቤላ፣ ጎሬ፣ መቱ ፣ጅማ፣አምቦ ሀዋሳ እና አርባ ምንጭን ጨምሮ በ25 ከተሞች ውስጥ እየሠራ ይገኛል።በቀጣይም በተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀ ሲሆን፤ በወሊሶ፣ ሱሉልታ፣ ሰበታ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሆሳዕና እና ሌሎች ከተሞች ላይ ለመሥራት ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምሯል። አገልግሎቱን ወደ 20ሺህ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ሲሆን፤ እየተሠራ የሚገኘው ባለ 15 ወለል ሕንፃ ግንባታ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ድርጅቱ ላለፉት አስርት ዓመታት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚመሰገን ነው።

ማዕከሉ ያለ ምንም የውጭ እርዳታ እና ድጋፍ ለተረጂዎች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በሙያ፣ በጉልበት፣ በሃሳብ፣ በገንዘብ እና በበጎ ፈቃድ ማገልገል ብዙዎችን መርዳት ነው። እንደ ሠርግ፣ ልደት፣ ኒካ እና መሰል ድግሶች ያሉባቸው ዜጎች ማንኛውንም ፕሮግራማቸውን ከአረጋውያን ጋር በመሆን ማሳለፍ ማህበራዊ ኃላፊነትን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ኃላፊነትን መወጣትም ጭምር ነው።

ሥራ አስኪያጁ እንደሚያብራሩት፤ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ያለው የማዕከሉ ሕንፃ ሆስፒታል እንዲሆን በማሰብ እየተገነባ ነው። ሕንፃውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። ስለዚህ ሁሉም የቻለውን እና የአቅሙን በማድረግ ጎዳና ላይ የወደቁትን አረጋውያን እንዲሁም የአእምሮ ሕሙማንን ለመርዳት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ሊያግዝ ይገባል።

ለመቄዶኒያ እዚህ መድረስ የብዙዎች ድጋፍ አለበት። ከግለሰቦች ጀምሮ የተለያዩ ማህበራት፣የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑት ተቋማትን ጨምሮ ድርሻቸው ከፍተኛ የሚባል ነው። ይህንን ድጋፍ መሠረት በማድረግ ዛሬም ቢሆን ወደ መቄዶኒያ በቀን በትንሹ እስከ አስር ሰው ከጎዳና ተነስቶ ወደ ማዕከሉ ይገባሉ።

‹‹ብዙ ሰዎች መቄዶኒያ አቅም ያለው ይመስለዋል ነገር ግን በጣም ብዙ ወጪ ነው ያለብን።›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ ለምሳሌ በቀን ከ70 በላይ የሚሆኑ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ታካሚዎች ወደ ህክምና ተቋማት ይወሰዳሉ። ለህክምና ብቻ ብዙ ወጪ ያወጣል።በተመሳሳይ አልጋ ቁራኛ ለሆኑ ታማሚዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እና መሰል ነገሮችን ለመግዛት ወጪዎችን ያወጣል። ሌላው የተሽከርካሪ እጥረት ፣ሕንፃውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እና ግብአቶችን ለማሟላት በአጠቃላይ ብዙ የጎደሉ ነገሮች ያሉት መሆኑን ሕብረተሰቡ ተገንዝቦ ያለውን መርዳት ይጠበቅበታል።

ከሁለት ቀናት በኋላ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓልን በተመለከትም የተለያዩ የምግብ ፍጆታዎች፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ለበዓል የሚሆን የእርድ ከብት እና አቅማቸው የፈቀደውን ይዞ በመምጣት በዓሉን ከአረጋውያን ጋር በደስታ እና በምርቃት እንዲያሳልፉ ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You