በሀገራችን ወቅታዊና አንገብጋቢ ከሆኑት ቀዳሚ ጉዳዮች መካከል የኑሮ ውድነት አንዱ ሆኗል። በነጋ በጠባ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት ኅብረተሰቡን ለቁሳዊ ችግር አልያም ለመሰረታዊ ፍላጎት መጓደል ከመዳረግ ባለፈ በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው እንዳይረጋጋ በማድረግ ለተለያዩ ስነ ልቦናዊ ችግሮች እያጋለጠው የኖረ አብሮነቱንም እየሸረሸረበት ይገኛል። ለመሆኑ ይህ አልቀመስ ያለ የኑሮ ውድነት የሚያሳድረውን ማህበራዊ ጫና እንዴት መቋቋም ይቻላል ስንል የስነልቦና ባለሙያ የሆነችውን ወይዘሪት ሀናን ሁሴን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ወይዘሪት ሀናን እንደምታብራራው በኮቪድ እየታመሰች ያለችው ዓለማችን ያለፉትን ዓመታትን አልፋ እዚህ እስከትደርስ ብዙ እጦቶችን አስተናግዳለች። ወደ መደበኛ ሂደቷ ለመመለስ የምታደርገው ጥረት በተለያየ መልኩ የሁሉንም ቤት አንኳኩቷል። በዚህ ላይ ደግሞ የሰላም መደፍረስ ሲጨመር እሳት ላይ ጋዝ እንደማርከፍከፍ ይሆናል። በኢኮኖሚ ባለሙያዎች እይታ ለኑሮ ውድነት ምክንያት ከሚባሉት ምክንያቶች ውስጥ የምርት እጥረት፤ ሰው ሰራሽ የዋጋ መናር (በተለይ ምርቶችን ሆን ብሎ በመደበቅ) የውጪ ምንዛሬ መጨመርና ተያይዞ የሚመጣው እንደ የነዳጅ መወደድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይህን ተከትሎ ተያያዥነታቸው ግልፅ በሆኑም ባልሆኑም ጉዳዮች የሚጨምሩ ምርቶች በመኖራቸው የሁሉንም ሰው ሕይወት የሚነካ ነገር ይፈጠራል።
የኑሮ ውድነት የከተማ ነዋሪ ላይ ቢጠነክርም የገጠሩንም ክፍል የሚነካው ሲሆን በሁለቱም ቦታዎች ላይ የሚንጸባረቀው የኅብረተሰቡን አንድነት የሚገዳደር መሆኑ ነው። ስለ ነገ ማቀድ አስቸጋሪ ይሆናል። የገበያ መቀዛቀዝ የሥራ ፍላጎትን፣ በመንግሥት ላይ የሕዝብ አመኔታ ማጣትን ያስከትላል። የኑሮ ውድነት ከጊዜያዊ ጫና ባለፈ ዘላቂ የሚባል ጉዳት ያሳርፋል። የብዙ ጉዳዮች ድምር ውጤት እንደመሆኑ መጠን ለመፍታት የሚወሰደው እርምጃ እንደ ኅብረተሰቡ የኢኮኖሚ አቅምና የስነ ልቦና ዝግጅት የሚወሰን ይሆናል።
የስነ ልቦና ምላሹ በጥሩም ይህን በክፉ የሚጀምረው ደግሞ መረጃ በመለዋወጥ ነው። ሕዝብ የኑሮ ውድነትን ቡናና ሻይ እየጠጣ ይወያይበታል ያለውንም መረጃ ይቀባበለዋል። የተቀባበለውን መረጃ መሰረት ከፊሉ የነበረው ርህራሄ ሲጨምርና ለሌሎች መጨነቅ ውስጥ ሲገባ ገሚሱ ደግሞ ወደ አላስፈላጊ ተግባር ብሎም ወደ ወንጀል ያመራል። በዚህ መልኩ ችግሩን በሌላ ችግር ለመፍታት የሚጥረው ሰው ቁጥር እየበዛ ሲመጣ በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን ባህልና እሴት እየሸረሸረ ወደ አዲስ ማንነት ይወስደዋል። ለምሳሌ የጤፍ ዋጋ መጨመር ሲሰማ እንደ ማህበረሰብ ለችግሩ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ባእድ ነገርን የሚቀላቅል ካለ፤ ሌላውም እንዲሁ የመሰለውን በሚችለው ልክ በመስራት ሊያካክስ ስለሚሞክር ተያይዞ መውደቅን ያመጣል።
ባጠቃለይ ማህበራዊ ለውጦች የጊዜን ዋጋ ይተምናሉ፤ ጊዜ ደግሞ ግብይትን። ገበያ ላቦትን ሚዛን ላይ ጥሎ የኅብረተሰብን መንፈስ ይመዝናል። የግለሰቦችን ጥምር አቋም ስብስብን እንዲወክል ሁሉ የእያንዳንዱ ግለሰብ የስነልቦና ንቃት የኑሮን ውድነት ይወስናል። በዚህ ዓይነት ኅብረተሰባችን የተቋቋመበት መርሆች በተረበሸ ቁጥር መተሳሰብን የሚያርቁ ነገሮች ይፈጠራሉ። ባጠቃለይ የዘይት ዋጋ መጨመር፣ የስኳር ከገበያ መጥፋት፣ የቤት ኪራይ መናር ብሎም የገበያ መቀዛቀዝ በማህበረሰቡ ስነ-ልቦና ይገልፃል ለማለት ይቻላል። ብዙውን ጊዜ የኑሮ ውድነትን ለመናገር ትኩረት የሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቢሆኑም ቁጥር ባለፈ የሚፈጥረውን ተጽእኖ ለመገንዘብ ከስነ ልቦና አንጻር ከግለሰብ ጀምሮ መታየት ያለባቸው ጉዳዮችም አሉ።
ከግምት ውጪ የሆኑ ድንገተኛ ለውጦች በተለያዩ መልኩ ኅብረተሰቡን በየደረጃው ይጫኑታል። የተጨነቀ ማህበረሰብ በአካባቢው በሚስተዋሉ ለውጦች ተገፋፍቶ የተለያዩ ተገቢ ያልሆኑ ውሳኔዎችንም ሊያደርስ ይችላል። የኑሮ ውድነት የሚያደርሰውን ማህበራዊ ተፅዕኖ ተከታትሎ ለመመዝገብ እጅጉን ከባድ ቢሆንም ከላይ ከላይ ሲታይ ማህበራዊ ኑሮን ያቀዘቅዛል፤ ትዳርን ከማመሰቃቀል አልፎ ቤተሰብን እስከማወክ እና ቀስ በቀስ እስከ መበተን ሊያደርስ ይችላል።
ያልተረጋጋ ኅብረተሰብ የኑሮን ውድነት እና የኑሮም ውድነት ያልተረጋጋ ኅብረተሰብን ያፈራሉ። ዜጎችም በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ስርቆትና ማጭበርበር ለመከወን እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል። የኑሮ ውድነትን ከሕዝብ የራስ መተማመን እንዲሁም ራስን የመቻል አቅም ጋር ብናዛምደው የሚነግረን ነገር የራስን ዋጋ መተመን ከሕዝብ የማምረት አቅም ጋር ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለው ነው። በመሆኑም ከጥገኝነት ስሜት ለመላቀቅ ከፍተኛ የሆነ የማህበረሰብ ስነልቦናዊ ንቃት ይፈልጋል።
ሁሉም ነገሮች በዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ተገዢ እንደመሆናቸው መጠን የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ በማምረትና በመግዛት አቅም የዳበረ፤ ለሚፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ራሱ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር ይጠበቃል። ለዚህም ዕቅዶችን በመንደፍና በመግበርም ያልተነቃቃ ሕዝብን ማነሳሳትና ጥሪት ይዞ እንዲጠብቅ ማድረግ የመሪዎች የመጀመሪያው እና ዋና ሥራቸው ሊሆን ይገባል።
ይህም ሆኖ ለኑሮ መወደድ ጥቂት ግለሰቦችን ወይንም አመራርን ብቻ ለይቶ ተጠያቂ ማድረግ የዓለምን ውስብስብነት ካለመረዳት የሚመጣ ሲሆን መፍትሄ ለማፈላለግም እንቅፋት የሚሆን ሀሳብ ነው። በመሆኑም ራስን የመፍትሄው አካል ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በየወቅቱ በፍጥነት የሚለዋወጥ በመሆኑ በአንድ ወገን የሀብት አቅምን ማደርጀት። በሌላ በኩል አንዳንድ ሰዎች ችግሩ እነሱ ላይ ብቻ የሚደርስ አድርገው በመመልከት ራሳቸውን ለከፋ ጭንቀት ሲዳርጉ ይስተዋላል። ነገር ግን ችግሩ በተለያየ ደረጃና ሁኔታ በመላው ዓለም የሚከሰት በመሆኑ ሳይታሰብ ለሚፈጠሩ ነገሮች ራስን በማዘጋጀት የተረጋገጠ ውሳኔ ለማሳለፍ መዘጋጀት ከእያንዳንዱ የሚጠበቅ ይሆናል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014