የማስታወስ ብቃት መቀነስ የአብዛኛው ሰው ችግር እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል። ችግሩ በግለሰብ ደረጃ የሚከሰት ቢሆንም የሚያስከትለው ተጽእኖና የሚፈጥረው ጫና የሚንጸባረቀው ግን በማህበረሰብ ደረጃ ነው። ጥሩ የማስታወስ ችሎታ ባላቸው ሰዎች የሚፈጠር ማህበረሰብ ያለፉ ነገሮችን ስለሚያስታወስና በቀላሉ ስለሚማርባቸው ስህተትን ከመድገም የተቆጠበ ይሆናል። በመሆኑም እንደ ግለሰብ የሚጀመረው ውጤታማነት ድምር በማህበረሰብ ደረጃ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ ይረዳል ማለት ነው። ለመሆኑ የማስታወስ ብቃት ምንድን ነው? እንዴትስ ልናዳብረው እንችላለን ስንል የማህበራዊ ሳይንስና አመራር ባለሙያ የሆኑትን አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አቶ ዘላለም እንደሚያብራሩት የማስታወስ ብቃት የተገኘውን መረጃ አቁሮ፣ አቆይቶና በኋላ ላይ መልሶ መጠቀም የመቻል ሂደት ነው። የሰው የማስታወስ ችሎታ ሁለት ዓይነት ሲሆን የተማረውንም ሆነ የተለማመደውን መረጃ መጠበቅንና መልሶ ማግኝትን ያካትታል። ይህም በአዕምሮ ውስጥ የማይቋረጥ ሂደት ነው። በአጠቃለይ የማስታወስ ብቃት የሰው ልጅ ያወቀውን ለወደፊት ለመጠቀም በአዕምሮው የማስቀመጥ ልዩ ስርዓት ወይም ሂደት ነው ማለት ይቻላል።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የሰው ልጅ ገና በእናቱ ማህጸን በጽንስ ደረጃ ካለበት ጊዜ ማለትም ከተጸነሰ «ከሁለት ሳምንት ጀምሮ» ማስታወስ የሚጀምር ሲሆን፤ ገደብአልባ መረጃን የማቆር አቅምም አለው። የሰው ልጅ የአጭር ጊዜ ትውስታና የረጅም ጊዜ ትውስታ ባለቤትም ነው። ተጨማሪም አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሥራ ትውስታና የማጣቀሻ የትውስታ ዓይነቶች የሚባሉም አሉት። የአጭር ጊዜ ትውስታ የሚባለው ከ20-30 ሴኮንድ ብቻ መረጃን ማቆየት መቻልና በፍጥነት አስቦ መረጃን ከትውስታው ማምጣት የሚችል ሲሆን፤ ከሌላው ዕድሜ በተሻለ ደግሞ ከ20 ዎቹ ዕድሜ አካባቢ ጀምሮ እስከ 48 ዓመት ድረስ ይህንን በደንብ መከወን ይችላል። ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ግን ማስታወስ መቻልም አብሮ እየቀነሰ የሚሄድ ተፈጥሯዊ አካሄድ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።
የማስታወስ ጠቀሜታዎች
1ኛ. ከውድቀት ከኪሳራ ትምህርት ለመውሰድ ይረዳል። የማስታወስ አቅማችን ዝቅተኛ ከሆነ የጣለንን፣ ያደናቀፈንንና ያሰናከለንን ስለምንዘነጋ ደጋግመን መውደቃችን የማይቀር ይሆናል። በመሆኑም ከውድቀታችን ተምረንና የሚያስፈልገንን ተሞክሮ ይዘን ወደ ስኬታችን መሄድ የምንችለው ያለፈውን ስናስታውስ ብቻ ነው።
2ኛ. “እኔ ማን ነኝ?” የሚለውን የግል ጥያቄ ለመመለስና ራሰን ለማወቅ ይረዳል። ራሳችንን ማወቅ የምንችለው ማስታወስ ስንችል ብቻ ነው። ከተወለድን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለፈውንና ያለውን ማስታወስ ስንችል ብቻ ራሳችንን እናውቃለን ማለት እንችላለን። እናም መርሳት ራስን ያለማወቅ አንዱ ችግር ሲሆን፤ ማስታወስ ደግሞ ራስን የማወቂያ መንገድ ነው።
3ኛ. ለተፈጠርንበት ምክንያትና ዓላማ ኑረን ለማለፍ ይጠቅመናል። ማስታወስ የሚችል ሰው ባለራዕይ ይባላል። እንዲህ ዓይነት ሰው የተነሳበትን ዓላማ ሳይዘነጋ ዕለት ዕለቱን በማስታወስ መፈጸም የሚያስችል ብቃትን የሚጎናጽፍ ይሆናል። በአንጻሩ የሚረሱ ሰዎች የቅርብ የዛሬዋን ብቻ እያለሙ ኑረው በዘልማድ ብቻ ኖረው ለማለፍ ይገደዳሉ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በራሳቸው ህይወት ወስጥም ሆነ በማህበረሰቡ የሚኖራቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ይሆናል። የሚያስታውሱ ግን መነሻ መድረሻቸውን አውቀው በህይወት ጊዜያቸው ሁሉ ለሚፈጽሙት ዓላማና ራእይ ብቻ ይንቀሳቀሳሉ። ይህም ህይወትን ትርጉም ለመስጠት ይረዳቸዋል። ለሚኖሩበትም ማህበረሰብ አንዳች ረብ ያለው ሥራ ሠርተው የማለፍ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
4ኛ. ትርጉም ያለው ህይወት ለመምራት ያስችላል። ትርጉም ያለው ህይወት ማለት ለምን? እንዴት? በምን? ወዴት? ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች አውቀው እየመለሱ መኖር ማለት ነው። ይህም በሃሳባችን ፍቃድ የሳልነውን የኑሮ ካርታ ባለቤት እንደመሆን ማለት ሲሆን፤ በስርዓት፣ በመርህ፣ በአመክንዮ፣ በእውቀት መኖር መቻል ማለት ነው። በዘፈቀደ፣ በደሳለኝ፣ በገጠመኝ፣ በተመቸኝ፣ በቀናኝ፣ ባማረኝ ወዘተ ያለትርጉም የሚኖሩ ሁኔታዎች እነሱን ያዟቸዋል እንጂ በእነሱ ኃይል አውቀት የሚሠሩት ነገር አይኖርም።
5ኛ. ውሳኔ ለመወሰን ይረዳል። የሚረሳ ሰው ማስታወስ የማይችል መወሰን ላይ ይቸገራል። ምክንያቱም መወሰን የሚያስችለን ምክንያት የሚገኘው ያለፈው ከማስታወስና የሚቀጥለውን ከማወቅና ከመገመት በመነሳት ስለሆነ ነው። እናም ለምን እንደምንወስን ካስታወስን መወሰን የመቻላችን ዕድል ሰፊ ስለሆነ አቋም ያለው ሰው ለመሆን ያስችለናል። የብዙዎቻችን እያነከስን የመኖራችን ትልቁ መነሻ ትላንታችንን ስለምንረሳ እንዴት እንዳለፍን ስለማናስታውስ ዛሬና አሁን ላይ በርትተን መወሰን አለማቻላችን ነው።
የማስታወስ ችሎታችንን ለማጠናከር
1ኛ. የምንፈልገው ጉዳይ ላይ ነጥለን ትኩረት ማድረግን መለማመድ፣
2ኛ. መረጃን ወይም ልናስታውሰው የፈለግነውን በአዕምሯችን ሰብስበንና ሰድረን ለማስቀመጥ መሞከር፣ በዘርፍ፣ በዓይነት፣ በይዘት ወዘተ…።
3ኛ. ለማስታወስ የሚረዱ ምልክቶችን መጠቀም።
4ኛ. ልናስታውሰው የፈለግነውን ሥዕላዊ በሆነ መልኩ ለመገንዘብ መሞከር።
5ኛ. የምናውቀውን አዲስ መረጃ ቀድመን ከምናውቀው ጋር ማዛመድ።
6ኛ. ልንመዘግበው የምንፈልገው ነገር በጽሑፍ የሰፈረ ከሆነ ድምፅ በማውጣት ጮክ ብሎ ማንበብን መለማመድ።
7ኛ. በቂና ጥሩ እንቅልፍን ማግኘት።
8ኛ. ልናስታውሰው የወደድነውን በማብራራት ደጋግመን መለማመድ።
9ኛ. ሽምደዳን ማስወገድን። በተጨማሪም በአመጋገባችን ስኳር በምግባችንም ሆነ በመጠጣችን ውስጥ በጥቂቱ መጠቀም፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተርና ውፍረትን መቀነስ፣ ተመካሪ ብልሐቶች ናቸው።
በሌላ በኩል የማስታወስ አቅማችን በጣም የተዳከመ ከሆነና የለት ተለት ኑሯችንን እስኪረብሽ ድረስ ማስታወስ አለመቻል ካጋጠመን በሽታ ነው። ይህም በሽታ አልዛይመር ወይም ዲሜንቲያ በሽታ በመባል የሚታወቅ ነው። አልዛይመር የአንጎል በሽታ ሲሆን፤ ቀስ በቀስ የማስታወስ፣ የማሰብና የምክንያታዊነት ክህሎታችን ይቀንሳል። በዋነኝነት ከዕድሜ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ቢሆንም፤ የምንጠቀመው መድሃኒት የጎንዮሽ ጉዳት፣ እጅግ አሰቃቂ ገጠመኝ፣ ቫይታሚኖች እጥረት፣ የአንጎል ካንሰር ወይም የአንጎል ማመርቀዝ፣ ስትሮክ፣ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትና ድባቴ እንዲሁም ሌሎችም ህመሞችና በሽታዎች የአልዛይመርን በሽታ ሊያመጡብን ይችላሉ። ይህ በሽታ ከ10 በላይ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ያሉት ሲሆን፤ አንዳቸውም ከገጠሙን በፍጥነት ባለሙያ ልናማክር ይገባል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013