አንተነህ ቸሬ
ከ60 ዓመታት በላይ በሩጫ ውስጥ ኖረዋል። ስፖርት፣ በተለይ ሩጫ፣ እስትንፋሳቸው ነው። ‹‹እኔን ከስፖርት የሚለየኝ ሞት ብቻ ነው›› በሚለውና ለስፖርት ያላቸውን ፍቅር በሚገልፁበት ንግግራቸው ይታወቃሉ። የተሳተፉባቸውን ውድድሮች በበላይነት በማጠናቀቅ ለቁጥር የበዙ ሜዳሊያዎችንና ዋንጫዎችን አሸንፈዋል።
በሮም ኦሊምፒክ ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰንን በማሻሻል ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈው የዝነኛው ኢትዮጵያዊ የአትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ደማቅ ድል የእርሳቸው አሻራ አለበት። በፈታኝ ልምምዶችና በጥብቅ ዲስፕሊን የታጀበው የአሰልጣኝነት ተግባራቸው በርካታ ተተኪዎችን ለማፍራት አስችሏል … የሩጫው አድባር ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ!
ዋሚ የተወለደው በቀድሞ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ መናገሻ አውራጃ፣ ሱሉልታ ወረዳ፣ በ1909 ዓ.ም ነው። በልጅነቱ ከብት በሚጠብቅበት ወቅት የተለያዩ የዱር እንስሳትን እያባረረ ይይዝ ነበር። ከፈረስ ጋር ሩጫ ይጀምርና ከጥቂት ርቀት በኋላ ዋሚ ፈረሱን ጥሎት ይከንፋል። ይህ ተግባሩም ሩጫን ከልጅነቱ ጀምሮ እንዲካንበት አስችሎታል።
ዋሚ በሩጫ ስፖርት ታዋቂ መሆንና የአገርንም ማስጠራት እንደሚቻል ያወቀው በአጋጣሚ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን እናቱ ወይዘሮ ወርቄ አያና ከገበያ የገዙትን እቃ የጠቀለሉበትን ጋዜጣ ሲመለከተው የታዋቂ ሯጭ ፎቶ ይመለከታል።
ሜዳውንና ተራራውን በሩጫ ሲያቆራርጠው የሚውለው ዋሚም ‹‹እኔ አውሬ እያባረርኩ ሚዳቋ፣ ጃርት፣ ጥርኝና ቆቅ እየያዝኩ ከሰንጋ ፈረስ ጋር ተሽቀዳድሜ እያሸነፍኩ ይህ ሰውማ አያቅተኝም:: እኔም በምችለው በሩጫ ብወዳደር ታዋቂ እሆናለሁ ማለት ነው?›› ብሎ ራሱን ጠየቀ።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ዋሚ ወንድሙን ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ባለበት ወቅት አዳዲስ ወታደሮች ሲመለመሉ ተመለከተ። አንድ የሃምሳ አለቃ ምልመላውን ሲመለከት ለነበረው ዋሚ ‹‹ለምን ወደ ውትድርና አትገባም›› ብለው ጠየቁት። ዋሚም ጥያቄውን ለመቀበል ቢያመነታም ከጥቂት ማግባባት በኋላ ጥያቄውን ተቀብሎ ከመስከረም 5 ቀን 1945 ዓ.ም ጀምሮ ወታደር ሆኖ ተቀጠረ።
ስልጠናውን ሲጨርስ ሁለተኛ ክፍለ ጦር ተመድቦ ወደ አስመራ ሄደ። በወቅቱ ምልመል እና ነባር ወታደሮች በአንድ ላይ ሆነው ሩጫ ይወዳደሩ ነበር። አዲሱ ምልምል ወታደር ዋሚ ቢራቱ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቀቀ። ይህ ድሉም በጦሩ ስፖርት ክፍል እንዲመደብ አስቻለው።
በ1947 ዓ.ም የሜልቦርን ኦሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና በብስክሌት ስፖርት ውድድሮች ስትሳተፍ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ከተመረጡ አትሌቶች መካከል ዋሚ አንዱ ነበር። ይሁን እንጂ ከአለቆቹ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከቡድኑ ጋር ወደ አውስትራሊያ ሳይጓዝ ቀረ። ከውድድሩ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የማራቶን ሩጫ (42 ኪሎ ሜትር) ያሸነፈው ዋሚ ነበር። ቤተሰቦቹን ለማየት ፈቃድ ጠይቆ ሳይፈቀድለት የቀረው ዋሚ ከጦር ኃይሎች በመልቀቅ ክብር ዘበኛን ተቀላቀለ።
ከሜልቦርን ኦሊምፒክ መልስ የጦር ኃይሎች የስፖርት ውድድር ሲካሄድ ጦር ኃይሎችን ለቆ ክብር ዘበኛን የተቀላቀለው ዋሚ፤ የአምስት ሺ እና የ10ሺ ሜትሮች እንዲሁም የማራቶን ውድድርን በበላይነት አጠናቀቀ። ለድሉም ከልዑል መኮንን ኃይለሥላሴና ከክብር ዘበኛ ዋና አዛዡ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ እጅ የዋንጫና የገንዘብ ሽልማቶችን ተቀበለ።
እነዋሚ በወቅቱ ይህንን ሁሉ ስኬት ሲያስመዘግቡ ፌዴሬሽንም ሆነ አሰልጣኝ እንዲሁም የስፖርት ትጥቅ አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ዋሚ ራሱንም ሆነ አበበ ቢቂላን እያሰለጠነ አዲስ ታሪክ መስራቱን ቀጠለ።
በወቅቱ በኦሊምፒክ ህግ መሰረት አንድ ሰው በአንድ ጊዜ አሰልጣኝም ተወዳዳሪም መሆን ስለማይችል አሰልጣኝ መቅጠር ግድ ሆነ። ስለዚህም ስዊዲናዊው ስካነን አበበን እና ዋሚን ለማሰልጠን ተቀጥረው ለሮም ኦሊምፒክ ውድድር ዝግጅታቸውን ቀጠሉ።
ስዊዲናዊው አሰልጣኝ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የዓለም ምርጥ አትሌቶች የሚሆኑ ብላቴናዎችን እያሰለጠኑ መሆናቸውን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም። እኚህ የባህር ማዶ አሰልጣኝ በአበበ እና በዋሚ ኢትዮጵያ አማካኝነት በረጅም ርቀት ሩጫ ድል እንደምታስመዘግብ እርግጠኛ ሆነው ነበር። ይህንንም ለንጉሱ በወቅቱ ቀርበው ተናግረው ነበር።
በወቅቱ ዋሚ በማራቶን የአገሪቱ ቁጥር አንድ ሯጭ ስለነበረ በሮም ኦሊምፒክ እንደሚወዳደር ጥርጣሬ አልነበረም። ይሁን እንጂ ያ ሁሉ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ዋሚ ቢራቱ በድንገት ታመመ። የሮም ኦሊምፒክ ውድድር ስድስት ቀን ሲቀረው ኢትዮጵያ የተማመነችበት ጀግና ሕመም አሸነፈው፤ በሰውነቱ 19 የተለያዩ ቦታዎች ላይ ብጉንጅ ወጣበት።
አሰልጣኙ ኃላፊነቱን ለሌላኛው ምርጥ አትሌታቸው አበበ ቢቂላ ለመስጠት ተገደዱ። አበበም በሮም ጎዳናዎች ታላቁን ተልእኮ ለመሸከም ኃላፊነቱን ተረከበ። አደራውን ተቀብሎ የተሰለፈው ጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ እጅግ ደማቅ ታሪክ ፃፈ።
እዚህ ላይ የአበበን ድል ለማስታወስ ያህል ከአበበ ደማቅ የድል ታሪክ መዝገብ በጥቂቱ እንጨልፍ። ከ83 አገራት የተውጣጡ ከአምስት ሺ በላይ አትሌቶች በተካፈሉበት የሮም ኦሊምፒክ ላይ የዓለም ሕዝብ ትኩረት በአውሮፓውያን አትሌቶች ላይ ነበር። ስለኢትዮጵውያን አትሌቶች በተለይም ስለ አበበ በቂላ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አበበ ቢቂላ ወይም ሌላ አፍሪካዊ አትሌት ሊያሸንፍ እንደሚችልም አልተጠበቀም፤ ከዚያ በፊት አንድም አፍሪካዊ በኦሊምፒክ ታሪክ ሜዳሊያ አግኝቶ አያውቅምና።
አሰልጣኙ ኒስካነን የሞሮኮው ራህዲ ቤን አብዴሰላም፣ የኒውዚላንዱ ባሪ ማጊ፣ የሶቭዬት ኅብረቶቹ ኮንስታንቲን ቮሮብዮቭ እና የወቅቱ የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት የነበረው ሰርጌይ ፖፖቭ (2:15:17.0) እንዲሁም የብሪታንያው ዴኒስ ኦጎርማን የጊዜውን ምርጥ ማራቶን ተወዳዳሪዎች እንደነበሩ ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሯጮች በጥብቅ ነግረዋቸዋል።
ይሁን እንጂ የሞሮኮው ራህዲ ቤን አብዴሰላም ይለብሰዋል የተባለው የመለያ ቁጥሩ 26 የነበረ ቢሆንም የለበሰው መለያ ግን በአስር ሺ ሜትር ውድድር ላይ ለብሶት የነበረውን መለያ ነበር። ስለሆነም አበበ የሞሮኮው ሯጭ የትኛው እንደሆነ አላወቀም ነበር።
ውድድሩ ተጀመረ። ታላቅ ሕልም ያነገበው አበበ ማንም ሳይጠብቀው መሪዎቹን እየተከታተለና በመጨረሻም ቀድሟቸው ውድድሩን በአስደናቂ ብቃት በአሸናፊነት አጠናቀቀ … ያውም በባዶ እግሩ! … ያውም የዓለም ክብረ ወሰንን በመስበር! አበበ ቢቂላ ውድድሩን በሁለት ሰዓት፣ ከአሥራ አምስት ደቂቃ፣ ከአሥራ ስድስት ነጥብ ሁለት ሴኮንድ (2:15:16.2) በማጠናቀቅ የዓለምን ክብረ ወሰንን ሰብሮ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ።
ራህዲ ሁለተኛ፣ ባሪ ማጊ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን አገኙ። የአበበ ፍላጎትና ሃሳብ ራህዲ እስከሚያጋጥመው ድረስ ጉልበቱን ለመቆጠብ ነበር። በዚህ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ክብረ ወሰኑን በተሻለ ውጤት ይሰብር እንደነበር አሰልጣኝ ኒስካነን ጥርጣሬ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።
የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ውጤት የዓለምን ታሪክ ቀየረ። ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካና ለዓለም ጥቁር ህዝብ ድል ያበሰረ ችቦ አቀጣጣለ። ኢትዮጵያዊያው አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ታላቁን የኦሊምፒክ ማራቶን በአንደኛነት ከማሸነፉም በተጨማሪ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዘገበ። በኦሊምፒክ ታሪክ የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ስፖርተኛ ሆኖ ስሙ በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቃማ ቀለም ሰፈረ።
አበበ ቢቂላ የማራቶንን ርቀት ሮጦ ያሸነፈውና ሪከርድ ያስመዘገበው በባዶ እግሩ መሆኑ ደግሞ የመላ ዓለም ስፖርት አፍቃሪዎችን በእጅጉ ያስደነቀ …የአበበ በቂላን ስምና የኢትዮጵያን ዝና በመላው ዓለም ተቀርፆ እንዲቀር ያደረገ ነበር። ጋዜጠኞች አበበ ለምን ያለ ጫማ በባዶ እግሩ እንደሮጠ ጠይቀውት ‹‹ … እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው…›› ብሏል።
በውድድሩ ማግሥትም፣ የኢጣሊያ ጋዜጦች በትልልቅ ፊደሎች ጎልቶ የሚታይ ርእስ በመፃፍ ‹ሮምን የወረረ ኢትዮጵያዊ› የሚል አዲስ ስም አወጡለት። አበበ የክብር ዘበኛ ወታደር እንደሆነ ጋዜጠኞቹ ስለሚያውቁ ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ግዙፍ ጦር አዝምቶም ነበር።
ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው …›› የሚል ጽሁፍ ይዘው ወጡ። ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው። ይህም አጋጣሚ ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ።
በሮም ባስመዘገበው ድል እጅግ ተደናቂ መሆን የቻለው አበበ ‹‹ … እኔ የዓለም አንደኛ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ነኝ። አንደኛው ዋሚ ቢራቱ በመታመሙ አልመጣም እንጂ ዋሚ ባይታመምና ቢመጣ ኖሮ ከዚህም በላይ ተአምር ታዩ ነበር …›› በማለት በአስተያየቱ ዓለምን ይበልጥ አስደነቀ።
ሻለቃ ባሻ ዋሚ በሜልቦርንና በሮም ኦሊምፒኮች ላይ አለመሳተፋቸው እጅግ ያስቆጫቸዋል። የቁጭታቸው መንስዔ ደግሞ ‹‹እኔም በውድድሩ ላይ ብሳተፍ ኖሮ ኢትዮጵያ አገራችን ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን ታገኝ ነበር›› የሚል የአገር ወዳድ ዜጋ እሳቤ ነው። በተለይ በሮም ኦሊምፒክ ላይ አለመሳተፋቸው ቢያስቆጫቸውም እርሳቸው እያበረታቱ ያሳደጉት ሌላው ጀግና ሻምበል አበበ ቢቂላ ወርቃማ ድል አስመዝግቦ ኢትዮጵያን ማኩራቱ ቁጭታቸው በመጠኑም ቢሆን ቀለል እንዲልላቸው አድርጓል።
አትሌት ዋሚ ከሕመማቸው ሙሉ በሙሉ ባያገግሙም ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ሦስት ዓመታት ቀደም ብሎ በተካሄደው የኦሳካ ማራቶን ውድድር ላይ ለመሳተፍ ግን ቆርጠዋል። ውድድሩን በባዶ እግራቸው የሮጡት ዋሚ፤ አበበ ቢቂላን ተከትለው ሁለተኛ ሆነው አጠናቀቁ። ሰራዊቱ በምሳ ሰዓት ዜና ያዳምጥበት የነበረው ሬዲዮም ዋሚ ከውድድሩ የተሸለሙት ነበር።
ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በተለያዩ የሩጫ መድረክ ላይ አገራቸውን ያስጠሩበት ድል አስመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከል በአንድ ሺ 500፣ በሦስት ሺ፣ በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትሮች እንዲሁም በ21፣ በ25፣ በ32 ኪሎ ሜትሮች እና በአገር አቋራጭና በተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ 51 የወርቅ፣ 44 የብር እና 30 የነሀስ ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 21 ሰርተፍኬት፣ አራት ዲፕሎማዎችንና ከ40 በላይ ዋንጫዎችን ወስደዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በ2011 ዓ.ም ባዘጋጀው ሦስተኛው የኢቢሲ (EBC) ስፖርት ሽልማት አንጋፋው አትሌት ‹‹የሕይወት ዘመን ተሸላሚ›› በመሆን የእውቅናና የ50ሺ ብር ሽልማት አግኝተዋል።
ሻለቃ ባሻ አትሌት ዋሚ ቢራቱ በተለያዩ ምክንያቶች በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ሳይችሉ ቢቀሩም በሌሎች ውድድሮች ግን ደማቅ የአሸናፊነት ታሪኮችን አስመዝግበዋል። ለአብነት ያህል በቼኮዝሎቫኪያ፣ በኡጋንዳ እና በግብጽ በተደረጉ ውድድሮች አሸንፈው የኢትዮጵያን ስም አስጠርተዋል።
አበበ በቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ ስለሺ ስህን፣ ገንዘቤ ዲባባና ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የሻለቃ ባሻ ዋሚን መንገድ የተከተሉ እንቁዎች ናቸው።
ሻለቃ ባሻ ዋሚ በርካታ ተተኪ አትሌቶችንም ማፍራት ችለዋል። በጥብቅ ዲስፕሊን የተገራው የአሰልጣኝነት ስራቸው ተተኪ አትሌቶች ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። እርሳቸው ያሰለጠኗቸው አትሌቶችም ‹‹… ጥብቅ ዲስፕሊንን ይከተላል። ተስፋ እንዳንቆርጥ በተደጋጋሚ ይመክረናል፤ ሁላችንንም በእኩል ዐይን ነው የሚያየን›› ብለዋል።
የሶምሶማ ሩጫ በኢትዮጵያ እንዲለመድ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል። ምንም እንኳን እኚህ አንጋፋ አትሌት እድሜያቸው ቢገፋም በተለያዩ ጊዜያት በውድድሮችና በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ ይታወቃሉ። ለአብነት ያህል በእርጅና ዘመናቸው በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ሆነው ያለምንም ችግር ማጠናቀቃቸው ተጠቃሽ ነው። ለጠንካራ ተክለ ሰውነታቸውና በጤንነት ረጅም እድሜ የመቆየታቸው ምስጢርም ይኸው በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፋቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ታላቁ የጽናት ተምሳሌት ‹‹እኔን ከስፖርት እንቅስቃሴ የሚለየኝ ሞት ብቻ ነው›› ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት የ104 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ የ11 ልጆች አባት ናቸው። በርካታ የልጅ ልጆች ያሏቸው ሲሆን፣ ቅድመ አያትም ሆነዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013