– ለውጥ ያመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው!
– ሠራዊቱ በነበረው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ረክቶ የሚኖር ሠራዊት አልነበረም
– የሀገሪቱን ሕዝብ እንዲመስል የማመጣጠን ሥራዎች እየተሠሩ ነው
አዲስ አበባ፣ አሁን በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ያመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑንና የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎትና ማእበል የለውጥ አመራር መፍጠሩን የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የዘመቻና መረጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ፡፡ የዘንድሮው ሠራዊት ቀን የሀገር መከላከያን ሪፎርም ዳር ለማድረስ በወኔ የምንነሳሳበት ሲሉም አመልክተዋል፡፡
ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በአደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይንም አክቲቪስቶች የየራሳቸው ሚና ቢኖራቸው በወሳኝነት ለውጡን ያመጣው ሕዝቡ ነው፡፡
ሥርዓት የሚቀይረው ሕዝብ ነው ያሉት ጄኔራሉ፣ የለውጥ አመራሩ ደግሞ ‹‹ሕዝቡ ልክ ነው›› ብሎ ከሕዝቡ ጋር ወግኖ ሕዝቡ የሚፈልገው ነው መደረግ ያለበት ብሎ ከሕዝቡ ጋር ቆሟል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ለለውጥ ያደርገው የነበረውን ትግል ልክ አይደለም የሚሉ አመራሮች በብዛት እንደነበሩ ያስታወሱት ጄኔራል ብርሃኑ፣ ሕዝቡ ልክ ነው ይሉ የነበሩትና ከሕዝቡ ጋር የወገኑት በጣም ጥቂቶች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡
የለውጥ አመራሩም በጥሩ ሁኔታ እየተራመደ ነው የሚል እምነት አለኝ ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ፣ ‹‹ሕዝብ እያዳመጠ፤ መጥፎ አሰራሮችንና ብልሹ አዋጆችን እየቀየረ፤ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እየታተረ፣ ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና አፈና እንዳይኖርም እየሠራ ነው›› ብለዋል፡፡ የለውጥ አመራሩ ሕዝቡን እያቀራረበ አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት እየሠራ በመሆኑ ይሄንን የለውጥ አመራር ማገዝ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑም አመልክተዋል፡፡
‹‹ሠራዊታችን ራሱ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ሠራዊቱ የሕዝቡ ልጅ ፤ ከሕዝቡ ውስጥ የወጣ ኃይል ነው፡፡ በነበረው ሁኔታ በሙሉ ረክቶ የሚኖር አልነበረም፡፡ በሠራዊቱ ውስጥም ጥያቄዎች ነበሩ›› ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ ለአብነትም በመከላከያ ውስጥ የብሔራዊ ተዋጽኦ ጉዳይ ጠንካራ ጥያቄ እንደነበረ አንስተዋል፡፡
ከሠራዊቱ ውስጥ የሚደረጉ ስምሪቶችን ትክክል አይደሉም፤ የሕዝቡ ጥያቄ በዶሞክራሲያዊ መንገድ መስተናገድ አለበት ፡፡ ሙስና ሀገር እያጠፋና እያወደመ ነው›› የሚሉ ሌሎች ጥያቄዎችም እንደነበሩ የጠቀሱት ጄኔራሉ፣ ይህም በሠራዊቱ ውስጥም የከረረ ትግል እንደነበር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ለውጡ አንተ ያመጣኽው ለውጥ ስለሆነ በዓይነ ቁራኛ ቀን ከሌሊት ነቅተህ ጠብቀው›› የሚል መልእከት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፉት ጄኔራሉ፣ ‹‹ሞተህ ለውጡን እንዳመጣኽው ሁሉ ለአደናቃፊዎች እድል ሳትሰጥ ልትጠብቀው ይገባሃል›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የሠራዊት ቀን “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንጠብቃለን፤ ሕዝባዊ ባሕሪያችን የተጠበቀ ይሆናል፤ የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን” በሚል መሪ ቃል መከበሩ፣ የሀገር መከላከያ ሪፎርምን ዳር ለማድረስ በወኔ የምንነሳሳበት ነው ሲሉ የገለጹት ጄኔራል ብርሃኑ፣ የሀገር መከላከያ ሪፎርም አስራ ሁለት ፕሮግራሞች ያሉት ሲሆን አደረጃጀቶቹም ተቀይረዋል ብለዋል፡፡
ሪፎርሙ በጥቂት ወራት የሚቋጭ ሳይሆን የሚቀጥልና ዓመታትን የሚፈጅ መሆኑን አንስተው፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች መሠራታቸውን በመካከለኛው ጊዜ የሚሠሩት ደግሞ ዝግጅት እየተደረገባቸው እንደሆነና ከረዥም ጊዜ አንጻር የሚሠሩ ሥራዎች ደግሞ ስትራቴጂክ ፕላን ወጥቶ በመሠራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሠራዊቱ በኑሮው፣ በልማቱ፣ በቴክኖሎጂና በአዳዲስ አደረጃጀቶች የታጀበ እንዲሆን ከመደረጉም በተጨማሪ የሀገሪቱን ሕዝብ እንዲመስል የማመጣጠን ሥራዎች እየተሠሩ ነውም ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ወንድወሰን መኮንን