
ፍሬህይወት አወቀ
ሀዋሳ፡- በሲዳማ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ ፡፡ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫም በክልሉ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቆሙ ፡፡
አቶ ደስታ ትናንት ለክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 1ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የዘጠኝ ወር ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት፣ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካው ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በኤክስቴንሽን የተደገፈ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም 238 ሺ 246 ሞዴል አርሶ አደሮችን መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል፡፡
በ2012/13 ዓ.ም የመኸር ወቅት ደግሞ አጠቃላይ 102 ሺ 353 ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር ለመሸፈን መታቀዱን ጠቁመው ፣ ከዚህ ውስጥም 97 ሺ 24 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
በማህበራዊ ዘርፍ መሠረተ ልማት ከማሟላት አንጻር ነባርና አዳዲስ መንገዶች ግንባታ ተጠናክሮ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል።ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የህብረተሰቡን የጤና ልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማት ግንባታ የማስፋፋትና ውስጣዊ አደረጃጀታቸውን የማጠናከር ስራ መሰራቱን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚህ ቀደም በየጤና ተቋማቱ ይስተዋሉ የነበሩ የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች እጥረቶችን ማቃለል መቻሉን አስታውቀዋል።
በተለይም በአሁን ወቅት በክልሉና በአካባቢው እያገረሸ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን መዘናጋትን ለማስቀረት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክረው የቀጠሉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የክልሉን የውስጥ ገቢን የማሳደግ ሥራ ከመስራት አንጻር የተለያዩ የገቢ ምንጮችን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ አቅምን የማጎልበት ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።በክልሉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ በተለይም በፐብሊክ ሰርቪሱ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚፈጸሙ ቅጥሮች፣ የደረጃ ዕድገትና ዝውውሮችን በመገምገም የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
ክልሉ በበጀት ዓመቱ ከመቶ ሺ በላይ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 84 ሺ ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰራጨው የገንዘብ በብድር እና ለማዳበሪያ የተሰጠ ብድር አመላለስ ላይ ውስንነት መኖሩ የጠቆሙት አቶ ደስታ ፣ በቀጣይ የተጠናከረ ሥራ በመስራት ውዝፍ ብድር ለማስመለስ በየደረጃው ያሉ አካላት ትልቅ የቤት ሥራ የሚጠብቃቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫም በክልሉ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስትና ህዝብ በጋራ እንዲሰራና አስፈላጊውን ሁሉ ከወዲሁ እያከናወነ የሚገኝ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ያለው የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 1ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የሚቀጥል ሲሆን ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽ ይሰጣል ፣ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ ያጸድቃል፤ ሹመቶችንም ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም