
በሞገስ ተስፋ
አዲስ አበባ፡- የኮቪድ-19 ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የሚሰጡ የመደበኛ ህክምና አገልግሎት ላይ ጫና መፍጠሩ ተገለፀ::
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና፣ የስርዓተ ምግብ ዳይሬክተርና ብሔራዊ የኮቪድ ክትባት ማስተባበሪያ ግብረ ኃይል ፅኃፊ ዶክተር መሰረት ዘላለም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች በየቀኑ በኮቪድ -19 ታማሚዎች እየተጨናነቁ ነው ፤ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ ነው:: በመደበኛ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ላይም ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል::
ጤና ተቋማት በኮቪድ-19 ህሙማን በተጨናነቁ ቁጥር እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሂደው የወሊድ አገልግሎት እንዳያገኙ ያደርጋል ያሉት ዶክተር መሰረት ፣ ሌሎች ተጓዳኝ የህክምና አገልግሎት የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በአግባቡ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ኃይልና ቦታ የማይገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል ::
መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለሚፈልገው የህብረተሰብ ክፍል በአግባቡ መስጠት እንዲቻል የኮቪድ የጥንቃቄ መንገዶችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል::
የምኒሊክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬከተር ዶክተር ሽመልስ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉ በመደበኛ የህክምና አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው:: ነገር ግን አሁን ላይ የኮቪድ-19 ቫይረሱ ስርጭት በመጨመሩ ለመደበኛ ታካሚዎች የፅኑ ህሙማን ማከሚያ የሚውሉ 20 የሚደርሱ አልጋዎችን ለኮሮና
ታካሚዎች አገልግሎት እየዋሉ ነው::
በሁሉም ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የህሙማን ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና የማስተናገጃ ቦታ በመጥበቡ የምኒሊክ ሆስፒታልም እየተፈተነ መሆኑን ያስታወቁት ዶክተር ሽመልስ ፣ በምቹ ሁኔታ አንቡላንስ ተጠርቶ ወደ ማዕከላት የሚወሰዱበት ሁኔታ ውስን በመሆኑ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ በማሰብ የተወሰኑ ማሽኖች ተዘጋጅተው ህክምና እየሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል::
ኮሮና ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ስለመጣ በሆስፒታሉ በመደበኛ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ሽመልስ፣ ለኮቪድ -19 ታካሚዎች ለይቶ ማቆያ የሚሆን ቦታ የሚያስፈልግ ከመሆኑም ባሻገር የህክምናው ባህሪ እንደ ሌሎች የህመም አይነቶች ባለመሆኑ ህሙማኑን የሚከታተሉ በርካታ ባለሙያዎችን ይፈልጋሉ ብለዋል ::
በዚህ ሳቢያም በመደበኛው የህክምና ዘርፍ አገልግሎት የተሰማሩ ባለሙያዎችን ስለሚወስድ መደበኛ ታካሚዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ በአግባቡ ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ በሚጠበቀው ልክ ባለመሆኑ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያስከተለ እንደሚገኝ ገልፀዋል::
በሆስፒታሉ ቀዶ ህክምና የሚደረግላቸው የአይን፣ የከፍተኛ ቀዶ ህክምና፣ የማህፀንና ሌሎች ቀዶ ህክምና ታካሚዎች የኮቪድ ምርምራ ተደርጎላቸው ነፃ ሲሆኑ ቀዶ ጥገናው እንደሚከናወንላቸውም ጠቅሰዋል:: ናሙና ተወስዶ ውጤቱ እስኪመጣ በሚወስደው ጊዜ ከፍተኛ መስተጓጎል እየተከሰተ መሆኑንም አመልክተዋል::
በአሁኑ ወቅት ከኮቪድ -19 መስፋፋት ጋር በተያያዘ መደበኛው የህክምና አገልግሎት ባይቋረጥም ወረርሽኑ በመደበኛ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሯል ጫናው እየበረታ ነው ብለዋል ::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013