
-የተፈናቀሉ ሰዎችን የመመለስና የማቋቋም ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተጠቆመ
በዘላለም ግዛው
አዲስ አበባ:- በአጣዬና አካባቢው የመሸገውን ታጣቂ ኃይል ለማጽዳት የክልሉ የጸጥታ መዋቅር፣ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት በቅንጅት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የአማራ ክልል አስታወቀ፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎችን የመመለስና የማረጋጋት፣ የማጽናናትና የማቋቀቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገለጸ ።
የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤በአጣዬና አካባቢው በንጹኃን ላይ ጥቃት አድርሶ የመሸገውን ታጣቂ ኃይል ለማጽዳት የክልሉ የጸጥታ መዋቅር፣ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት፣ በቅንጅት እየተንቀሳቀሱ ነው። ተጨማሪ የጸጥታ ኃይልም ወደ አካባቢው ገብቷል።
‹‹በአካባቢው አንጻራዊ መሻሻሎች አሉ፣ የተኩስ
ድምጽ ቆሟል፣ ነገር ግን ከአካባቢው አሁንም የጠላት ኃይል አልጸዳም፣ መሽጓል›› ያሉት አቶ ግዛቸው ፣ ይህን ኃይል የማጽዳት ስራ በተቀናጀና በተጠናከረ መንገድ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ የተከሰተባቸውና ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች በፌዴራል ደረጃ በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደሩ መደረጉን ያስታወሱት አቶ ግዛቸው፣
ጥቃት አድራሾቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ለፍርድ ለማቅረብ ፤ አልያም ለመደምሰስ እርምጃ እየተወሰደ ነው፣ እርምጃውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል::
የአማራ ክልል ጥቃት እየደረሰበት ያለው በአንድ አቅጣጫ ብቻ አይደለም ያሉት አቶ ግዛቸው፤ በአጎራባችና በተለያዩ ክልሎች ላይ ተወላጆችን መሠረት ያደረገ ጥቃት እየደረሰ ነው ብለዋል::
በተመሳሳይም በሰሜን በኩል የትህነግ እንቅስቃሴዎች አሉ፣ በክልሉ ብጥብጥ ለማስነሳት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሉ ፣ ይህንን ለመቀልበስ በተለያዩ አካባቢዎች ልዩ ኃይል ተከፋፍሎ እንደሚገኝ ጠቁመዋል:: በዚህም ፈጥኖ ኃይል አንቀሳቅሶ ችግሩ ወደተከሰተበት አካባቢ በማድረስ ፣ ጉዳቱን መቀነስ አልቻልንም ብለዋል::
የጠላት ኃይል አሰፍስፎ ክልሉን ለማተራመስ እየሰራ መሆኑን አውቆ የክልሉ ህዝብ ከመንግሥት ጎን ሊሰለፍ ይገባዋል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ አጋጣሚውን በመጠቀም መነገድ የሚፈልጉ አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ከድርጊታቸው ርቀው በሰከነ ሁኔታ መንግሥትን ሊያዳምጡና ሊተባበሩ ይገባቸዋል ብለው አሳስበዋል::
በሁሉም አካባቢዎች ላይ ልዩ ኃይል ማስቀመጥ አንችልም፣ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ለአንድ ዓመትና በላይ በአካባቢው ሰላም ሰፍኖ በመቆየቱ ያለው ሁኔታ ተረጋግቷል ብለን ባሰብንበት አጋጣሚ ነው ችግሩ የተፈጠረው ሲሉ ገልጸዋል::
የጠላት ኃይል አዘናግቶ ልዩ ኃይሉን ከጀርባው በመውጋት ጥቃት እንደሰነዘረበት ያስታወቁት አቶ ግዛቸው ፣ ልዩ ኃይል መስዋዕት እየከፈለና ክልሉን እንደ ክልል እያስቀጠለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::
አሁን ተጨማሪ ኃይል መግባቱን፣ ችግሩም በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው፤ ችግሩ ተፈቷል ወደ ዕርቅ ገብተዋል ብለን ባሰብንበት ወቅት የጥፋት ኃይሉ ያለ የሌለ ኃይል አሰባስቦ እና ከባድ መሳሪያ ታጥቆ መንቀሳቀሱን ጠቁመዋል::
‹‹አሁንም የትህነግ ፍርስራሽ ቡድን አልጸዳም:: ከአማራ ክልል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል:: እዚህ አገር ላይ የተከሰቱና እየታዩ ያሉ የትኛውም አይነት ግጭቶች በሙሉ የትህነግ የስራ ውጤቶች ናቸው›› ብለዋል::
ትህነግ ላለፉት 50 ዓመታት አልሞ የሰራቸው ስራዎችና የረጨው መርዝ አሁን አብቅሎ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ይህንን ህብረተሰቡ ሊገነዘበው እንደሚገባም ጠቁመዋል::
የጥፋት ቡድኑ እንደፈለገና በነጻነት ለመንቀሳቀስ እንዲመቸው በአካባቢዎቹ የትርምስ ስትራቴጂውን ለመተግበር እየተጋ እንደሚገኝ ፣ በአንጻሩ መንግሥት ለማምለጥ የሚንቀሳቀሰውን የጥፋት ኃይል በመደምሰስ አካባቢዎቹን ከጠላት ነጻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል::
የተፈናቀሉ ሰዎችን የመመለስና የማረጋጋት፣ የማጽናናትና የማቋቀቋም ስራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው ፣ ከተፈናቃዮቹ ብዙዎቹ መኖሪያቸው የተቃጠሉባቸው፣ ኃብት ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው በመሆኑ አካባቢውን ከጠላት ኃይል ከማጽዳት ቀጥሎ ማቋቋምና ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ስራ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል:: የሰሜን ሸዋ ዞንና የየአካባቢዎቹ አመራሮች ቦታው ድረስ በመሄድ አካባቢውን የማረጋጋት ስራ እየሰሩ እንደሆኑም አመልክተዋል::
መላው የክልሉ ህዝብ በተለይ ወጣቶች ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝና ወደነበረበት እንዲመለስ እንዲተባበሩ፣ በስጋት አካባቢ ያሉት ከተቻለም በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲከላከሉ:: በአካባቢያቸው የመሸገ የጠላት ኃይል ካስተዋሉም መረጃ በመስጠት ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርበዋል:: ስለደረሰው የጉዳት መጠን አጠቃላይ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን በማመልከትም፤ ስራው ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል::
የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት ሰላምና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀና በመኪና እየተጫነ የመጣ የታጠቀ የኦነግ ሸኔ ኃይል በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን በመግለጽ በጥፋት ኃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
በቅርቡ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባወጣው መግለጫው መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማ በተከሰተው ግጭት የሞቱ ንጹኃን ዜጎች ቁጥር 303 መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል ::
369 ዜጎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ፤ ከሁለቱ ዞኖች በተገኘው መረጃ መሰረት ከ50 ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ፤ ከአንድ ሺ 539 ቤቶች በላይም መቃጠላቸውን ገልጿል ::
የችግሩን ባለቤት በመለየት ተጠያቂ ለማድረግ 81 ተጠርጣሪ ግለሰቦች ቢያዙም ከበላይ አካል በተሰጠ ትእዛዝና ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲለቀቁ ተደርገዋል፤ በተመሳሳይ በ2010 እና 2011ዓ.ም በተከሰቱ ችግሮች አጥፊዎች ተለይተው ህጋዊ እርምጃ አለመውሰድ ለህግ የበላይነት አለመከበር የራሱ ድርሻ ይኖረዋል ማለቱም ይታወሳል ::
በተያያዘ ዜና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የፌደራል መንግስት በአማራ ሕዝብ ላይ በአማፂ ኃይሎችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመሸጉ የሽብር ተኮር ተግባር ተባባሪ አካላት የጋራ ቅንጅት እየተፈፀመ ያለውን አማራን የማጥፋት ዘመቻ በቁርጠኝነት አልተከላከሉም፣ የዘር ማጽዳት ወንጀሉን በአደጋው ልክ ባለማውገዛቸውም በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የምሁራን መማክርት ገልጿል።
እየተፈፀመ ያለውን አማራ ተኮር እልቂት የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ሊያውቁት ይገባል፣ የክልሉ መንግስትና ሚዲያው መሽፋፈንን እንደ ስልት መከተል መምረጣቸው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የቀጠለው አማራ ተኮር የዘር ማጽዳት በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ጠቅሷል።
የክልሉ መንግሥት አማጺ ኃይሎችን ከጥፋት ተልዕኳቸው መግታት አለመቻሉ አሳስቦኛል ያለው ምሁራን መማክርቱ፤ የፌዴራሉና የክልሉ መንግሥት የዜጎች ደኅነንት የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ዜጎች በሥርዓቱ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርግና የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ተገልጿል።
በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጽዳት ወንጀል ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ የዴሞክራሲ ኃይሎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የግፉዓን ድምጽ እንዲሆኑ ጥሪውን አቅርቧል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013