
በጽጌሬዳ ጫንያለው
አዲስ አበባ፡- በሰሜን ሸዋ ዞን በታጣቂ ኃይሎች በደረሰ ጥቃት ከአጣዬ ከተማ ተፈናቅለው በመሀልሜዳ ለሚገኙ ከ10ሺህ እስከ 15 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ድጋፍ ለማድረስ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ አስታወቁ፡፡
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ በተለይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ታጣቂ ሀይሉ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ፡፡ ችግሩን ለክልሉና ለዞኑ ብቻ የሚተው አይደለም ።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአካባቢው ነዋሪ ራሱን ለማዳን በመረጠው አጋጣሚ ሁሉ ወደ አጎራባቹ አካባቢዎች ተሰዷል ያሉት አቶ ታደሰ፣ በአጣዬ አካባቢ
ብቻ የተፈናቀሉ ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ የሚደርሱት ዜጎች መሀልሜዳ መግባታቸውን ጠቁመዋል ፡፡ ከተማዋ ተፈናቃዮቹን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ስለሌላት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል ፡፡
አጣዬ ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ በተደጋጋሚ ችግር የተከሰተበት በመሆኑ አብዛኛው በሚባል ደረጃ የነዋሪው
ንብረት ወድሟል ፣ሲሰደድም በእጁ የሚይዘው ነገር የለም ፤ስለዚህ ዞኑ በተቻለው ሁሉ ድጋፉን እያደረገ ነው :: እንደ መንግሥት ከሰላምና ጸጥታው በተጓዳኝ የድጋፉ ሥራ ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል ::
ሸዋሮቢት እንደአጣዬ ከተማ እንዳትሆን በብዙ መንገድ አመራሩ ጭምር በመሳተፍ ታድጓል:: በተለይም ደግሞ የክልሉ፣ የዞኑ ጸጥታ ኃይል በጋራ በመሆን በሰራው ሥራ ሸዋሮቢት ላይ ችግሩ ብዙም እንዳይገዝፍ አድርጓል:: አሁንም ከፌዴራል ከተጨመረው ኃይል ጋር በመሆን ሰላምና ጸጥታው የተረጋጋበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ህዝቡ ወደ ቤቱ የሚመለስበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው ብለዋል ::
መኪና ጭምር ተመድቦ ተፈናቃዮቹ ወደቤታቸው የሚገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: የተፈናቀለው ወደነበረበት
መመለሱ ደግሞ ከተማዋ ወደነበረ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰች እንድትመጣ አድርጓታል:: አሁንም ቢሆን ትልቅ ሥራን ይጠይቃል:: ሰላምና ደህንነቱን የሚያረጋግጥ አካልም በተጠንቀቅ መቆም አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል::
በአጣዬ ከተማ ያለውን ሰላም ለማረጋገጥ ሳይቻል ህዝብን ወደነበረበት ለመመለስ አዳጋች እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ታደሰ፤ ብዙሀኑ ማለትም ከ10 ሺ እስከ 15 ሺ የሚሆኑ ዜጎች በመሀልሜዳ ከተማ ሰፍሮ የሚገኘው ሰላም በማጣቱ ነው:: ሀብት ንብረቱም ጠፍቷል:: ህይወቱንም ከማትረፍ ውጪ አማራጭ አልተሰጠውም:: ስለሆነም ህብረተሰቡን በደንብ አወያይቶና አረጋግቶ እንዲሁም ጸጥታና ሰላሙን አረጋግጦ እንዲመለስ ይደረጋል ብለዋል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013