አስመረት ብስራት
ወይዘሮ ሰራ ዘመኑ ሰናይ በጋዜጣችን ለወላጆች ምክር የሚያካፈሉ እናት ናቸው። የህክምና ባለሞያ ሲሆኑ ልጆቻቸውን አሳድገው ለቁምነገር አብቅተዋል። ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ነው ለወገኖቼ የተወሰነ ነገር ከልምዴ ባካፍል ብለው በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መዕክቶችን ያስተላልፋሉ። ለዛሬም ካካፈሉን ውስጥ እነሆ።
እኛ ወላጆች በልጆቻችን ላይ ዘለቄታ ያለው የመማር ፍላጎት እንዴት ማሳደር እንችላለን? በተለያዩ መንገዶች ይህንን የማድረግ አቅም አለን አቅሞቻችንን የምንጠቀምባቸውን ሶስቱን መንገዶች እንደሚከተለው እንመልከት።
አንደኛው መንገድ ልጆቻችን ለሚጠይቁን ጥያቄዎች በምንችለው አቅም አጥጋቢ መልስ መስጠት ነው ልጆች በትንሽነት ዕድሜያቸው በተፈጥሮአቸው የማወቅ ጉጉት ይዘው ነው የሚወለዱት ስለዚህም ትንሽ ከፍ ማለት ሲጀምሩ ብዙ ጥያቄዎች በየጊዜው መጠየቅ ይጀምራሉ ።
በዚህን ጊዜ ሳንሰለች ጥያቄያቸውን ካደመጥንና አጥጋቢ መልስ ከሰጠናቸው የማወቅ ጉጉታቸው እየዳበረ ይሄዳል በአንጻሩ ደግሞ የተሰላቸ መንፈስ ካሳየናቸው የማወቅ ጉጉታቸውን ቀስ በቀስ እንገድብባቸዋለን ይህ እንዳይሆን በተቻለን አቅም አጥጋቢ መልስ በመስጠት የማወቅ ጉጉታቸውን ማበረታታት ይኖርብናል።
ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ልጆች በተለይ በትንሽነታቸው ዕድሜ ዕውቀታቸውን የሚያዳብ ሩበትን መንገድ በማያጨናንቃቸው ሁኔታ ይልቁንም በሚያስደስታቸው መልክ ለማድረግ መሞከር ነው ለምሳሌ በጣም ጨዋታ የሚወድን ልጅ አስቀምጠን መጽሐፍ አንብብ ብለን ብናስገድደው ይህ ልጅ የማንበብ ፍላጎትን አያዳብርም
በዚህ ፋንታ የጨዋታ የሚመስል ብዙ ስዕሎችና እንቅስቃሴዎች ያሉበት የኮሚክ መጽሐፍ ብናቀርብለት ግን እሱን ደስ ብሎት ስለሚያነበው ቀስ በቀስ የማንበብ ችሎታውንና ፍላጎቱን ያዳብራል ይህንንም በሚያነብ ጊዜ አንዴ ቁጭ ብሎ ለረጅም ጊዜ እንዲያነብ መግፋትም የለብንም ምክንያቱም ልጆች በትንሽነታቸው ትኩረት አድርገው አንድ ቦታ ላይ የመቀመጥና ሥራቸውን የመከታተል አቅማቸው ውስን ስለሆነ ስለዚህ እንደፈለጉ እየተነሱ በሚፈልጉበት ጊዜ እንዲያነቡ መፍቀድ ይገባናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ ማንበብን ጥፋት ሲያጠፉ እንደመቅጫ መጠቀም የለብንም ማንበብን ከቅጣት ጋር ካያያዙት የማንበብ ፍላጎት በውስጣቸው አያዳብሩም ።
ልጆቻችን ላይ ዘለቄታዊ የመማር ፍላጎት ለማሳደር ልንጠቀምባቸው ከምንችላቸው መንገዶች መካከል ሶስተኛው እኛ ራሳችን የማናውቀውን ነገር ለማወቅ ጥረት ስናደርግ ማሳየት ነው ለምሳሌ ልጄ መጥታ አንድ መልሱን የማላውቀውን ጥያቄ ጠየቀችን እንበል።
በዚህ ጊዜ ዝም ብሎ አላውቀውም ከማለት ወይም አለማወቄን እንዳታውቅ ለመሸፈን ከመሞከር ፋንታ፤ ይህንን እኔም አላውቀውም፣ እስቲ መልሱን እንፈልግ በማለት ያሉትን መንገዶች ተጠቅሞ መልስ ማግኘትን ማሳየት ለልጆቻችን በጣም ይጠቅማቸዋል::
በዚህ ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን ይማራሉ የማይታወቅን ነገር በጥረት ማወቅ መቻሉን ይማራሉ ዕውቀትን ማዳበር የዕድሜ ገደብ እንደሌለው ይማራሉ የእኛንም የማወቅ ጉጉት ሲመለከቱ እነሱም ተመሳሳይ የማወቅ ጉጉታቸውን ያዳብራሉ።
እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ሶስት መንገዶች በመጠቀም ልጆቻችን ላይ ዘለቄታዊ የሆነ የመማርና የማወቅ ፍላጎትን ማዳበር እንችላለን ትኩረታችንም ከዛሬ ትምህርታቸው ውጤት ላይ ከማተኮር፤ በተለይ በልጅነታቸው ዕድሜ፤ የትምህርት እና የዕውቀት ፍቅር በውስጣቸው እንዲሰርጽ ማድረግ ላይ ማተኮር ለሕይወታቸው የበለጠ ይጠቅ ማቸዋል ።
ወላጅነት የትውልድ ባለአደራ መሆኑን በመገንዘብ ልጆቻችንን በጥበብ ማሳደግ ባህላችን ልናደርገው ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013