የአንድ አገር ልማትና ዕድገት እንዲሁም የመንግሥት ዴሞክራሲያዊነት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ የተረጋጋ መንግሥት መኖር ነው። የተረጋጋ መንግሥት ደግሞ በዜጎቹ እምነት የተጣለበትና ይህንንም ከግብ ለማድረስ የሚተጋ መንግሥት ማለት ነው። የተረጋጋና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የሚፈጠረው በምርጫና በምርጫ ብቻ ነው።
በእርግጥ መንግሥት በሁለት ዓይነት መንገድ ሊመሰረት ይችላል፤ በኃይል ወይም በሰላማዊ መንገድ። በኃይል ሥልጣን ላይ የሚወጡ መንግሥታት በአብዛኛው ለዜጎቻቸው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ፍላጎት ዋነኛ ግባቸው አይደለም። የነዚህ መንግሥታት ዋነኛ ፍላጎት በማንኛውም መንገድ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችሉ የኃይል አማራጮችን ማካሄድ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ውስጣዊ ችግር ሁሉ በጉልበት ለማፈን ይጥራሉ፤ ከውጭ የሚመጣ ተፅዕኖ ካለ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መስለው ለመታየት የውሸት ምርጫ እስከማካሄድ ድረስ ሊሄዱም ይችላሉ።
በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን ላይ የሚወጡ መንግሥታት ግን በባህርያቸውም ሆነ ዓላማቸው ከመጀመሪያዎቹ ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። እነዚህ መንግሥታት ሥልጣንን የሚፈልጉት ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ለአገር ልማትና ዕድገት እንዲሁም ለዜጎቻቸው ብልጽግና ነው። ስለዚህ ይህ እውን እንዲሆን በቅድሚያ ለሕዝባቸው ምን መስራት እንደሚፈልጉና እንዴት እንደሚሰሩ፤ ለዚህም የያዙት አማራጭ ምን እንደሆነ እና ኅብረተሰቡ ምን እንደሚፈልግ በመረዳት አብረው ለመስራት ዝግጁ ይሆናሉ። ስለዚህ ይህንን ለማድረግ በቅድሚያ የሕዝባቸውን እምነት ማግኘት ይሻሉ።
አገራችንም ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተለያዩ ምርጫዎችን ስታካሂድ ቆይታለች። በዘመነ ኢህአዴግም አምስት ያህል ምርጫዎችን አካሂዳለች። ነገር ግን እነዚህ ምርጫዎች በአብዛኛው ኅብረተሰብም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅቡልነት ነበረው ለማለት አይቻልም። ለዚህ አንዱና ዋነኛው መነሻ ደግሞ የምርጫው አካሄድና ከምርጫው በኋላም ምርጫውን ለመቀበል የነበረው ዝግጁነት ማነስ ናቸው።
ከ2007ቱ ምርጫ በኋላም ኅብረተሰቡ በነበረው መንግሥት ላይ ሙሉ ለሙሉ እምነት በማጣቱ አዲስ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል። ወደሥልጣን የመጣው የለውጥ መንግሥት ደግሞ ይህንን የቀደመውን የተዛባ የምርጫ አካሄድ ለማስተካከል በርካታ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ወደሥልጣን በመጡበት ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃል ከገቡበት ጉዳይ ውስጥ አንዱ ነፃ፣ ሰላማዊና፣ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ነው። በዚህም መሠረት ላለፉት ሦስት ዓመታት ይህንን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ ሥራዎች ተሰርተዋል።
ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ዋልታና ማገር ናቸው ተብለው ከሚታመንባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ይህንን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን መፍጠር ነበር። በዚህ መሠረት ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም ከማንም የማይወግን ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ተደርጓል።
እነዚህ ተቋማት ከላይ የተባለውን ዴሞክራሲዊ ምርጫ ለማካሄድ ጠቃሚ ናቸው። እነዚህ ተቋማት ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮም የጎላ ቅሬታና ትችት ሲቀርብባቸውም አልታየም። ይህም ተቋማቱ ለማንም የማይወግኑና ለህሊናቸው የሚሰሩ ስለመሆናቸው አንድ ማሳያ ነው።
ምንም እንኳ አንዳንዶች በራሳቸው ጊዜ ምክንያት በመፍጠር ከምርጫ ቢወጡም እስከመጨረሻው ድረስ ግን በምርጫው ላይ እንዲሳተፉ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይህ ደግሞ መንግሥት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ፓርቲዎች ወደሜዳው ገብተው እንዲሳተፉና አማራጮቻቸውን ለሕዝብ አቅርበው እንዲፎካከሩ ዕድል መስጠቱን ያሳያል።
ያም ሆኖ ግን ይህ ምርጫ እውን እንዳይሆን የሚፈልጉ ኃይሎች ዛሬም አልጠፉም። ለአብነትም የምርጫውን መቃረብ ተከትሎ በአገሪቷ ሰላም የለም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እዚህም እዚያም ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላት አሉ። እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ዋነኛ ዓላማቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ሁኔታ ባለመኖሩ ምርጫ መካሄድ የለበትም ስለዚህም በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ እንችላለን ብለው ማሰባቸው ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በምርጫው ዋዜማ የታላቁን ህዳሴ ግድብ መሠረት በማድረግ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ ወደሰላማዊ ምርጫ እንዳትገባና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዳይኖር ለማድረግ የራሳቸውን ጥረት ከማድረግ አልቦዘኑም። ለዚህ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የዘንድሮ ምርጫ ሲቃረብ የሚደረጉ ተፅዕኖዎች መጨመራቸው ማሳያ ነው።
ከዚህም ጎን ለጎን በዘንድሮ ምርጫ ላይ ዜጎች በስፋት እንዳይሳተፉ ለማድረግ የሚፈጠሩ ሴራዎችም ምርጫውን ለማደናቀፍ ከሚሰሩ ሥራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። ይህ ደግሞ በተለይ በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ ካርድ እንዳይወስድ ከማድረግ ጀምሮ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙ እስከማድረግ የዘለቀ የማደናቀፍ ጥረቶችንም ያካትታል።
ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ዜጋ በዚህ ወሳኝ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምዕራፍ ወቅት ንቁ በመሆን ዴሞክራሲን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱን አሻራ ለማኖር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ለዚህ ደግሞ ወሳኟን ካርድ መውሰድ የግድ ነው። እናም በእጃችን ያለውን መብት በአግባቡ ልንጠቀምበት ግድ ይለናል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም