መርድ ክፍሉ
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን አቅመ ደካሞችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሁሉም ቦታዎች እየተቀጣጠለ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው።መንግስትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩ በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው።ይህም እንቅስቃሴ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው።የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራት ማህበራት እየተበራከቱ ይገኛል።በተለይ የህብረተሰቡን ችግር ከስሩ ለመፍታት ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት እንዳልጠፉ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በተለይ በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን። ዛሬ ጉኑኖ ሓሙስ ከተማ በጎዳና የሚገኙ ልጆችንና በልመና የሚተዳሩትን ሰዎች የሚደግፈው ሀልቹዋ በጎ አድራጎት ማህበርን እንቃኛለን።ሀልቹዋ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ሰብሳቢ ወጣት ስንታየሁ በቀለ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ማህበሩን መስርቷል።ከወጣት ስንታየሁ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተው አቅርበነዋል።
የማህበሩ አመሰራረት
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ሀልቹዋ በጎ አድራጎት ማህበር ሲመሰረት ቅድሚያ የማህበሩን ስያሜ ለመምረጥ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል።በስተመጨረሻም ‹‹ሀልቹዋ›› የሚለው እንዲመረጥ ተደረገ።‹‹ሀልቹዋ›› የሚለው ቃል ወላይትኛ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹አላማ›› ማለት ነው። አላማ የተባለበት ምክንያት በዓለም ውስጥ የሚገኘውን ብዙ ውጣ ውረድ ለማለፍ የሰው ልጅ ያለ ዓላማ ሲጓዝ ወይም ሲሰራ ከንቱ ልፋት ይሆናል።ነገር ግን በአላማ ሲሰራ ፍሬን ወይም ለውጡን ያገኛል።ስለዚህ ዓላማ የሌለው ወጣት ወደ ሌላ ቦታ ማለትም ወደ ሱሰኝነት፣ ሌብነት፣ ተንኮል ወዘተ…. አልባሌ ቦታ ላይ እንዲውል ምክንያት ይሆናል።ነገር ግን ዓላማ ያለው ወጣት ለምክንያት እንጂ ለስሜት ቦታ አይሰጥም ምክንያቱም በዓላማ ስለተነሳ ነው ።
ማህበሩ ከተመሰረተበት አራት ዓመት ሆኖታል።ማህበሩ ሀምሌ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ቀደም ብሎ የማህበሩ ሊቀመንር በራሱ ተነሳሽነት ሰዎችን ይረዳ ነበር።ለዚህም ያነሳሳው አንድ ሰፈር በሄደበት ወቅት አንዲት እናት ስትቸገር አየ። በወቅቱም የአቅሙን ያክል ድጋፍ አድጎላት ለቀጣይ ቀን ሌሎች በጎ አድራት ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን በማሰባሰብ ማገዝ አለብኝ ብሎ ወሰነ።በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችን በማሰባሰብ ትምህርት ሲዘጋ ክረምት ወራት ላይ ምን መስራት እንዳለባቸው ውይይት ማድረግ ጀመሩ።
በውይይቱ በክረምቱ ወራት ምን ማድረግ ይሻላል ብለው ተማከሩ።ከዛም ‹‹አንድ ነገር ብንሰራ ይሻለናል በማለት›› ምንም ገንዘብ ሳይኖራቸው በማሰባሰብ ለራሳችን ማንፀባረቂያ ልብስ አሰፍተው ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙትን አረጋውያን ወይም የተቸገሩትን ለመረዳት ወደ ስራ ገቡ። ወደ ስራ በገቡበት ወቅት በገንዘብ የመርዳት አቅም ባይኖር እንኳን ውሃ ቀድቶ መስጠት እንደሚቻል አምነው ስራውን ጀመሩ። በዚህም ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየታቸው የከተማው ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ተወካዮች ከጠሯቸው በኃላ ዕውቅና ተሰጣቸው።ከዛም በአንድ ላይ ለመስራት አሰቡ።ማህበሩ የራሱ የሆነ እቅድ ስላለው በክረምት ወራት ትምህርት በነፃ ለማስተማር ቦታውን ጠይቀው ትምህርት ቤት ተፈቀደላቸው።እነዚህን ማከናወን ጀመሩ። ከዛም ሰኔ ሁለት ቀን 2010 ዓ.ም ላይ ለማህበሩ ስም በማውጣት በይፋ ከህብረተሰቡ ጋር ችግኝ በመትከል ስራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ በርካታ ተግባራቶች አከናውነዋል። ከነዚህም ውስጥ መጀመሪያ መኖሪያ ቤት ላጡ፣ በጎርፍ እየተቸገሩ ላሉት ሰዎች የቤት ጥገና በየዓመቱ የተደረገ ሲሆን በዚህም በርካታ ቤቶች ተሰርተዋል። በተጨማሪም ብርድ ልብስ፣ ምግብ እንዲሁም የቁሳቁስ ማሰባሰብ ሥራ ተከናውኗል። ትምህርት ለመማር ድጋፍ ላጡ ልጆች ደብተርና እስክሪብቶ በማሰባሰብ እና በበዓላት ጊዜ ምግብ ፣ ዱቄት፣ ዘይት ፣ ከሰል፣ ጨው ፣ ስኳር እና ቡና የመሳሰሉት ከጥሬ ገንዘብ ጋር እዲሰጣቸው ተደርጓል።ሌላው ደግሞ በጎዳና ላይ ያሉትን በማሰባሰብ ምግብ በማብላት እና ኮሮና ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የመከላከያ መንገዶችንና ግንዛቤ በመስጠት ስራ ሲሰሩ ቆይቷል።
የክረምት ወራት የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ ደም የመለገስ ስራ ተሰርቷል።እንደ ማህበረሰቡ የዕድገት ደረጃና የአከባቢ ሁኔታ የተለያዩ አገልግሎቶች ለመስጠት ወጣቶች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን በጎ አመለካከታቸውን የሚያውሉበት በምላሹም ትምህርትና ልምድ የሚቀስሙበት ተግባር ተከናውኗል።
በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ውስጥ ማህበሩ የተሳተፈ ሲሆን በማሳ ላይ በጎርፍ የሚቸገሩ ሰዎችን ለማገዝ እርሻ ቦታ በመሄድ የድች ቦይ በመሥራትና በጋና ክረምት ደረቅ ቆሻሻን የማቃጠል ሥራ ተሰርቷል። በመንገድ ደህንነት ደግሞ ማህበረሰቡን ዜብራ አጠቃቀም በማሳየት፣ ትራፊክ ማብራት በማሳየት እንዲሁም ተማሪ ከትምህርት ቤት ሲወጣ እና ሲገባ ትራፊኩን የማገዝ ሥራ ተሰርቷል። ትምህርት በማስተማር ረገድ ደግሞ በክረምት ወራት ለተማሪዎቹ ማጠናከርያ ትምህርት በየክፍል ደረጃ ማለትም ከ5 እስከ 12 ክፍል ትምህርት ተሰጥቷል።
በችግኝ ተከላ ስራ የተለያዩ ችግኝ በከተማ ውስጥ እና ለማህበረሰብ አረንጓዴ ልምላሜ እንዲንሆንና ሰው ለማረፍ እንዲመች የችግኝ ተከላ ሥራ ተከናውኗል።የቤት ጥገና ሥራ ደግሞ ለአረጋውያን ቤት ጥገና እና ጉልበት ሥራ በመሥራት ማህበሩ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል። ልብስ የማሰባሰብ ስራ ቤት ለቤት በመሄድ ትርፍ ልብስ በመሰብሰብ በጎዳና ላይ ለሚገኙ ልጆች የመስጠት ሥራ ተከናውኗል። ምግብ የማብላት ስራ በተለያዩ ጊዜያት የተከናወኑ ሲሆን ምግብ አጥተው ለሚሰቃዩ የጎዳና ልጆች እና አቅም ለሌላቸው አረጋውያን በየበዓላት ጊዜ በምግብ እጦት እንዳይሰቃዩ በየጊዜው ምግብ የማብላት ስራ ተሰርቷል። የትምህርት ቁሳቁስ በማሰባሰብ ማለትም ደብተር፣ እስክርቢቶ እንዲሁም ሌሎች ቁሰቁሶችን ለችግረኛ ተማሪዎች እንዲሰጡ ተደርጓል።
የኮሮና ወረርሽኝን በሀገሪቱ ከተከሰተ በኋላ በየመንገዱ ውሃ እና ሳሙና በማስቀመጥ እንዲሁም ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተከናውኗል። በየከተማ መግቢያ ቦታ እና ሆቴሎች ላይ የግንዛቤ ትምህርትና በጤና ጥበቃ የተደገፉ ጹሁፎችን የመለጠፍ ስራ ተሰርቷል። እንዲሁም በመኪና መናሃሪያ አካባቢ እና ባንክ ቤቶች እና ሰው የሚበዛበት ቦታ ላይ አልኮልና እጅ የማስታጠብና የማስተማር ስራ ተከናውኗል።
የህብረተሰቡ አቀባበል
ህብረተሰቡ የማህሩን ጥንካሬንና ብርቱ ቀና አመለካከት አይተው ተደስተው በማመስገንና ከማህበሩ ጎን በመቆም የቤት ጥገና ሲደረግ በራሳቸው ጊዜ እንጨት፣ ሚስማር፣ ቆርቆሮ፣ ማገር፣ በርና መስኮት በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል።በተጨማሪ ደግሞ እናቶች ከቤታቸው በሥራ ሰዓት ላይ ቁርስ፣ ምሳ እያመጡ እገዛ ያደርጉ ነበር።
ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች ብዙ ናቸው።በተለይ ብር ማሰባሰቢያ ሰዓት ላይ ለራሳቸው ብለው ነው በማለት ብዙ ቦታ ላይ የመሰደብ ሁኔታዎች ነበሩ።በሌላ በኩል ‹‹ሥራ አጥተው ወጣቱ ለልመና ወጥተዋል›› የሚሉ ወሬዎች ነበሩ።በበዓላት ጊዜ ለጎዳና ተዳዳሪ ልጆች እና የቤት ጥገና በሚደረግበት ጊዜ የገንዘብ አቅም ጠፍቶ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ ነበር። ገንዘብ ለማግኘት ችግሮች ገጥመው የነበረ ሲሆን ቤት ለቤት በመሄድ መጠየቅ አስቸጋሪ ነበር። በአቅም ችግር የተነሳ የተጀመሩ ቤቶች እንዲቋረጡ ይደረግ ነበር።ችግሮቹን ለመፍታት ከህንፃ መሳሪያ መሸጫ ቦታ በብድር መልክ በመውሰድ ያለደመወዝ እና ያለ አበል፣ ራበን፣ ጠማን ሳይሉ በብዙ ውጣ ውረድ አላማቸውን ለማሳካት ተግተዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ማህበሩ ከብዶት የነበረው የሚሰጠውን የጥንቃቄ ምክር ሰው ተግባራዊ እንዲያደርግ ተከታታይ የሆነ ትምህርት መስጠት ነበር። በተጨማሪም ለራሳቸው ጥንቃቄ ለማድረግና ግንዛቤ መስጠት ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ፈጥሮባቸው ነበር። በወቅቱ የኮሮና መከላከያ መንገዶቹን ለማስተማር ሲወጣ በእጃቸው ምንም አይነት ገንዘብ አልነበረም።ሳሙና፣ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ወይም ማስክ መግዣ ገንዘብ አልነበራቸውም።
ቀጣይ እቅዶች
ማህበሩ በቀጣይ በርካታ ዕቅዶችን ያሰበ ሲሆን የተቸገሩትን ለመርዳት ለምሳሌ ማህበሩን የሚያግዝ ወይም የሚደግፍ ድርጅት ቢኖር ለጎዳና ልጆች ትምህርት ቤቶች በመክፈት የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል እና ለጎዳና ልጆች እንደ አቅማቸው ሥራ ለመስጠት ሀሳብ አላቸው። የማህበሩ አባላት ያላቸውን አቅም በመጠቀም በጎ ተግባራትን በማከናወን ለቀጣይ ትውልድ አሻራቸውን አሳርፈው የማህበሩን ስም ሁሌም እንዲኖር የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን እቅዶች አሉ።
ማህበሩ በቀጣይ ለመስራት ካሰባቸው ነገሮች ውስጥ ቀደም ብሎ ሲያከናውናቸው የነበሩ ስራዎች ይገኙበታል። የአረጋውያን ቤት ጥገና ማከናወንና አቅም አጥተው በብርድ በዝናብ ለሚቸገሩት አረጋውያን ደግሞ ቤት ሠርቶ ለመስጠት አቅደዋል። እየተማሩ አቅም አጥተው የተመለሱትን፣ ስራ አጥተው የተቀመጡትን በማገዝና በመደገፍ እንዲሁም በሰው ቤት እየሰሩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ያለትምህርት በሰው ኩሽና የሚንከራተቱትን ወደ ትምህርት ዓለም ለማስገባት እቅድ አላቸው። ደግሞ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ገቢ ማስገኛ ቦታዎችን ከመንግሥት ጋር በመነጋገር የወጣቶች መዝናኛ ለመክፈት አቅደዋል። በተጨማሪም ጎዳና ተዳዳሪዎች ከጎዳና ህይወታቸው ወጥተው ራሳቸውን ችለው በስራ ላይ እንዲሆኑ ለማድረግ ታቅዷል። በጎዳናው ላይ የተወለዱትን ከመንግሥት ጋር በመሆን ለማሳደግ እና ለማንሳት ማሰባቸውም ታውቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013