በወንጀል የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የዜጎች በአፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት (The right to speedy trial) መሰረታዊ የሆነ መብት መሆኑ የሚታወቅ ነው።በመሆኑም በዚህ አጭር ጽሑፍ አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ምንነትና በአገራችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስላለው የሕግ ማዕቀፍ በወፍ በረር እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን።
አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ምን እንደሆነ ከማየታችን በፊት የፍትህን ትርጓሜ ማየት ያስፈልጋል። ፍትህ ምን ማለት ነው የሚለው ጥያቄ እንደ አካባቢውና ጥያቄው ከተነሳበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተዛምዶ የሚታይ በመሆኑ የፍትህ ወይም የፍትሐዊነት ትርጉም ወጥ በሆነ አገላለጽ ሁሉንም የሚያግባባ ትርጉም ማግኘት ያስቸግራል።
ቢሆንም የተለያዩ ዘርፎች ከራሳቸው አኳያ የፍትህን አስፈላጊነት ይሁን የፍትህን ምንነት ያስቀምጣሉ። ለአብነትም በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የሚገኙ አዋቂዎች ፍትህን የሚመለከቱት ከማህበረሰባዊ እኩልነት አኳያ በመሆኑ ከዚህ አንጻር ፍትሕ ሲባል በግለሰቦች ይሁን በማህበረሰቦች መካከል ሊኖር የሚችለውን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በእኩልነት ሊስተናገዱ እና ማህበራዊ ተሳትፏቸውም በእኩልነት ሊረጋገጥላቸው እንደሚገባ እና እኩል ሆነው እንዲታዩ ከማድረግ አኳያ ትርጉም ይሰጡታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከኢኮኖሚ ዘርፍ አኳያ የሚመለከቱት ሰዎች ፍትሐዊነትን የሚመለከቱት ከሃብት አያያዝና አጠቃቀም ጋር በማቆራኘት በመሆኑ ፍትሐዊነት ሲባል ተቀራራቢነት ያለው የሃብት አጠቃቀም ወይም ደግሞ ሚዛናዊ የኑሮ ደረጃ መምራት የሚለውን ትርጉም እንዲይዝ አድርገው ይመለከቱታል። በሕግ ሰዎች ዘንድ ደግሞ ፍትሕ በአብዛኛው በፍርድ ሂደት ያለውን ሚዛናዊነትን ከማስጠበቅ አኳያ የሚመለከቱት በመሆኑ ሰዎች በሕግ እኩል ሆነው ፍርድ ማግኘት በሚገባቸው ጉዳይ ላይ ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ እንዲሰጣቸው የሚያመለክት ትርጓሜ ይሰጡታል።
አፋጣኝ ፍትሕ የማግኘት መብት ጽንሰ ሀሳብና ያለው የሕግ ማዕቀፍ ሲታይ ደግሞ አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ጽንሰ ሃሳብ በመሰረቱ በሕጉ መሠረት የተከሰሱ ሰዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ግልጽ እና ፍትሃዊ በሆነ ሂደት የመዳኘት እና ተቀባይነት ባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ማግኘት እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው::
እጅግ የተራዘመና የዘገየ የፍትህ ወይም የዳኝነት አሠጣጥ ሂደት ተከራካሪ ወገኖች ላይ ጥርጣሬ እና እምነት ማጣትን ከማሳደሩ እንዲሁም የፍትሕ ስርዓቱን ውጤታማነት እና ብቃት አጠያያቂ ማድረግ ከመቻሉም በላይ “የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል” ከሚለው የሕግ ምሁራን አባባል አንጻር ፍትሕ እንደተከለከለ ወይም እንደተነፈገ ሊወሰድ ይችላል፡፡
አፋጣኝ ፍትሕ የማግኘት መብት በሕግ ጥበቃ ያለው መሰረታዊ መብት ሲሆን በተለያዩ አገራት ሕጎችም ተደንግጎ ይገኛል።በአሜሪካ (The Sixth Amendment to the U.S.Constitution) በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንጓል።በአፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ከጥንት ጀምሮ የነበረ መሰረታዊ መብት ሲሆን በእንግሊዝ በንጉስ ሄነሪ ሁለተኛ (1154-1189) ጊዜ እንግሊዛውያን አፋጣኝ ፍትሕ ማግኘት እንዳለባቸው በሕግ ተደንግጎ ነበር።እ.ኤ.አ በ1215 ደግሞ ንጉሱ በእጁ የሚገኙ የፍትሕ ጥያቄዎችን ማዘግየት እንደማይችል በማግና ካርታ (Magna Charta) በግልጽ ደንግጎ ነበር፡፡
ይህ ፍትሕን በአፋጣኝ የማግኘት መብት በተለያዩ ዓለም አቀፍ፣ አሕጉር አቀፍ እና በአገራችን የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተረጋገጠ ሲሆን ሁሉም ድንጋጌዎች የፍትሕ ጥያቄ ተገቢና ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡
ለምሳሌ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን (ICCPR) በአንቀፅ 14 (3) (ሐ) ላይ በወንጀል ጉዳይ ተከሶ የቀረበ ሰው “አግባብ በሆነ ሁኔታ ሳይዘገይ የመዳኘት” መብት ያለው መሆኑን የደነገገ ሲሆን፤ ከአህጉራዊ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ ደግሞ የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች ቻርተር (ACHPR) በአንቀፅ 7 (1) (መ) ላይ ማንም ሰው የደረሰበትን በደል ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ አድሎአዊ ባልሆነ ፍርድ ቤት ወይም የፍርድ አካል የመዳኘት መብት እንዳለው አስቀምጧል።
ወደ አገራችን የሕግ ማዕቀፍ ስንመጣ አፋጣኝ ፍትሕ የማግኘት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት በአንቀፅ 20 (1) ስር የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት የመስማት መብት ያላቸው መሆኑ ተመልክቷል።ከዚህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ እንደምንረዳው የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት መረጋገጥ ያለበት እንደየጉዳዩ ሁኔታ ግልጽ በሆነ ችሎት ሲሆን፤ ይህ ሲባል ከተከሳሹ በተጨማሪ ማህበረሰቡም ስለ ጉዳዩ ሂደት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ፍትህ ሲሰጥ ለመታዘብ ወይም ለማየት እድል ይሰጠዋል።
በሕገ መንግስቱ ከተደነገገው ድንጋጌ በተጨማሪ የወ/መ/ስ/ስ/ሕጉ ላይም ይህንን መሰረታዊ መብት አፈጻጸም የሚያረጋግጡ የተለያዩ ድንጋጌዎች ይገኛሉ።ለምሳሌ ከጊዜ ቀጠሮ ጋር በተገናኘ፣ ከምርመራ ጊዜና ሪፖርት አደራረግ ጋር በተገናኘ እንዲሁም ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላም በአቃቤ ህግ በኩልም ሆነ ከፍርድ ቤት በኩል በጉዳዩ ላይ በጊዜ ውሳኔ መስጠት ስለማስፈለጉና ፍትሕን በጊዜ ከመስጠት ጋር የሚገናኙ ድንጋጌዎች ይገኛሉ (የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ አንቀጽ 59፣37፣109 እና አንቀጽ 94 እና ተከታዮቹ)።
በአፋጣኝ ፍትሕ የማግኘት መብት ዳኝነት ወይም የፍትሕ ጥያቄ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ያለመዘግየት ምክንያታዊ በሚባል አጭር ጊዜ ውስጥ ዳኝነት ወይም ፍትሕ የማግኘት መብት ነው። ይህ መብትም አላስፈላጊና ያልተንዛዙ ቀጠሮዎች እንዲኖሩ በማድረግ ዳኝነት ጥያቄ በቀረበበት ጉዳይ ላይ ውሳኔ የማግኘት መብትን ይጨምራል።በተጨማሪም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት የሚረጋገጠው በሕግ የተዘረጋን ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ጉዳዩን ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ መምራት ሲቻል ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በአፈጻጸም ክፍተቶች ወይም በሕግ የተዘረጋን ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ተከትሎ ባለመሄድ ምክንያት የዜጎች በአፋጣኝ ፍትሕ የማግኘት መብት ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ይስተዋላል።እ.ኤ.አ በ2014 በተደረገው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ላይ በአብዛኛው የፍርድ ሂደት መጓተት የሚከሰተው በተራዘሙ የሕግ ሥነ-ሥርዓቶች፣ በታራሚዎች ብዛት፣ በፍትሕ ሥርዓቱ የቅልጥፍና ማነስ ችግር እና በሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ መሆኑ ተጠቅሷል።
ቀልጣፋና ፈጣን ዳኝነት የማግኘት መብት በዋናነት የተከሳሹ መብት ቢሆንም የተጐጂዎችና የሕብረተሰቡ ጥቅሞችንና ፍላጐቶችን የሚጠብቅ ነው።ተከሳሹ ጉዳዩ በተቻለ ፍጥነት ውሳኔ እንዲያገኝለት እንደሚፈልግ ሁሉ ተበዳዮች/ተጐጂዎችም ጉዳዩ በጊዜ እንዲወሰንላቸው ይፈልጋሉ።
ሕብረተሰቡም ቢሆን ጉዳዩ በተራዘመ ቁጥር የህዝብ እና የመንግሥትን ወጪና ጉልበት የሚያባክን በመሆኑ ቶሎ እልባት እንዲያገኝ ይፈልጋል።በመሆኑም የቀልጣፋ እና የፈጣን ዳኝነት መርህ እጅግ በጣም ጠቃሚና ወሳኝ የሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ምንጭ:- ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013