ማህሌት አብዱል
ተወልደው ያደጉት ጎንደር ከተማ ነው። በዚያው ከተማ በሚገኙት ፃድቁ ዮሃንስ እና እድገት ፈለግ በተባሉ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን በንግድ ስራ ህግ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። በፌዴራል የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ውስጥ የምርመራና የአቤቱታ ክትትል ኤክስፐርት ሆኖ ለስድስት ወራት አገልግለዋል። በመቀጠልም በቀድሞው አጠራሩ ፍትህ ሚኒስቴር በአሁኑ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሚባለው ተቋም ውስጥ ደግሞ ለስድስት ዓመታት በከፍተኛ አቃቢነት ሰርተዋል። ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የህግ አማካሪና ጠበቃ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ከአቶ ሃይለማርያም ተመስገን ጋር በስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫና ከዚህ ጋር ተያይዞም ከአገራዊ የሰላም፣ የፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– መንግስት በህወሓት ላይ የወሰደውን ህጋዊ እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶች ቀንሰው እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭትና አለመረጋጋቶች በየአካባቢው እየተበራከቱ ይገኛሉ። እርሶ የዚህ ምንጭ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ኃይለማርያም፡– እውነት ነው፤ በትግራይ ክልል ከተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ በኋላ በተወሰነ ደረጃ ግጭቶችና በንፁሃን ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ቀንሰው ነበር። በእርግጥ ጊዜው አጭር ነው። እናም ለተወሰ ጊዜ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አንፃሪያዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት ታይቶበት እንደነበር ማስተዋል ይቻላል። ግን ይህም ቢሆን በጣም አጭር ጊዜ ነው የቆየው። እንዳልሽው በቅርብ ጊዜ ደግሞ በበርካታ የሀገራችን አካባቢዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እየተበራከቱ ነው የመጡት። ይህ ለምንድን የሆነው? ከዚያ በፊት በዋነኛነት የህወሓት ረጅም እጆች በግጭቶቹ እና በብጥብጦቹ ውስጥ ይኖራል ተብሎ ግምት የሚወሰድ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወሳኝ በሆነ መልኩ ከተመታና የቡድኑ ህልውና ችግር ውስጥ በገባበት ሁኔታ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ለምን አልቆሙም ? የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ በእርግጥም ከራሱ ከምርጫው ጋር ሊያያዝ ይችላል። በከፊል ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ግቦች እና ፍላጎቶች ለማራመድ ሲባል የተለያዩ ታክቲኮችንና ስልቶችን የሚጠቀሙ ሃይሎች እንዳሉ ይታወቃል። ስለዚህ ያነሳሽው ጥያቄ ከዚህ ነገር ሊነሳ ይችላል።
በተለይም ‹‹ምርጫው መደረግ የለበትም›› የሚል አቋም ያላቸው ሃይሎች የሚፈጥሩት ችግር እንዳለ ይታወቃል። እነዚህ ሃይሎች እንግዲህ ተነጥለው በደሴት ላይ የሚኖሩ አይደሉም። በራሱ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሰሚነትም፣ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይህንን ሃሳብ ሊጋሩ የሚችሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ እሙን ነው። ምክንያቱም በአንድ አገር አስተዳደር ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ አሰላለፎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይኖራሉም። ስለዚህ እነዚያ ፍላጎቶችን ለማሳካት በቀላሉ ለመፈፀም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን የመጠቀም እድሎች እየተፈጠሩና እየሰፉ ነው የሄዱት። በዚህ ምክንያት ይመስለኛል እነዚህ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ያሉት።
እንደእኔ እምነት እስከምርጫው መዳረሻም ሆነ ምንአልባትም በምርጫው ማግስት መንግስት እስከሚቋቋም ድረስ እነዚህ ችግሮች ሊቀጥሉ የሚችሉበት እድል አለ። ስለዚህ መንግስት ይህንን ታሳቢ አድርጎ በተለይም በመንግስት እና ከገዢው ፓርቲ ውስጥ ለተሻለ ግብ የሚሰራው ሃይል እነዚህን ነገሮች ታሳቢ አድርጎ የመንግስትንም ሆነ የፓርቲውን መዋቅር መፈተሽና ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠቅበታል። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ጥቃቶች ከመንግስት መዋቅር እይታ፣ ድጋፍና ፍላጎት ውጪ የሚሆኑበት እና በዚህ ደረጃ ሊፈፀሙ የሚችሉበት እድል ጠባብ ነው። ስለዚህ መንግስት ራሱን ሊፈትሽ ይገባል ብዬ አስባለሁ። ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ባይቻል እንኳን ቢያንስ ለጊዜው መከላከል እንዲቻል ጊዜያዊ የሆኑ እርምጃዎች በጣም ያስፈልጋሉ።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አኳያ ታዲያ የግጭቶቹ እልባት አለማግኘት በምርጫው ላይ የሚያጠላው መጥፎ ነገር ምንድን ነው?
አቶ ኃይለማርያም፡– የዚህ ችግር መቋጫ አለማግኘት በምርጫውም ሆነ በአገር ህልውና ላይ የሚያሳርፈው መጥፎ አሻራ መኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም። በተለይም ምርጫው ላይ በጣም ከፍተኛ ስጋት ነው የሚፈጥረው። ምርጫው እንደሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ከስጋት ነፃ አይደልም። አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታና በዋነኝነት ደግሞ ስራ ላይ ባለው ስርዓት ፣ የምንተዳደርበት ህግ፣ ስራ ላይ ያሉ ተቋማት፣ያለው አስተዳደር በጣም ብዙ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ነው ያሉት። ስለዚህ በዘላቂነት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መዋቅራዊ የሆነ ወይም ስርዓታዊ የሆነ ሽግግር ያስፈልጋል። ዋናው የችግሩ ምንጭ እዚሁ ስለሆነ ማለት ነው። አንዱ ህዝብ ሌላኛውን ህዝብ፣ አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል ሌላኛውን የህብረተሰብ ክፍል በጥርጣሬ እና በስጋት እንዲያይ፤ የጋራ ከሆኑ ግቦቻችን ይልቅ የግል ብለን የምናስባቸው ፍላጎቶችና ጥቅሞች ላይ ያተኮርንበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ በዘላቂነት መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው የጋራና ሊያግባቡን በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መስራት ስንችል ነው።
በነገራችን ላይ እኔ በግሌ የምርጫው ውጤት ዘለቄታዊ የሆኑ ለውጦች ያስከትላል ብዬ አምናለሁ። በእኔ እምነት ምርጫውን ተከትሎ መሰረታዊ የሆኑ ሽግግሮችን የምናገኝባቸው መንግስታዊ ውሳኔዎች ይወሰናሉ ብዬ እገምታለሁ። ባለፉት ሶስት ዓመታት የመጣንበትን ሂደት ስናይ መንግስት ትልልቅ የሚባሉ እርምጃዎችንና ውሳኔዎችን ሲያስተላለፍ ነው የቆየው። ይህንን መሰረት አድርገን በቀጣይ የተሻለ ውሳኔና ለውጦች ይመጣሉ ብዬ አምለሁ። በእርግጥ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ መንግስት ወደ ፊት ምንአይነት ፍኖተ ካርታ ሊኖረው እንደሚችል በግልፅ አያሳይም ወይም አያሳውቅም።
አዲስ ዘመን፡– ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ኃይለማርያም፡– ይህም ማለት ለምሳሌ ‹‹ምርጫውን ብናሸንፍ በዚህ ሀገር ውስጥ ስራ ላይ የምናውለው ስርዓት ተግባራያዊ የምናደርገው ነገር ይህ ነው›› የሚል ነገር ከዶክተር አብይ መንግስት አንሰማም። በእኔ እምነት ህገ-መንግስታዊ ጥያቅዎች ምላሽ ማግኘት መቻል አለባቸው። ስርዓቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ የመንግስት ወይም የዶክተር አብይና የፓርቲያቸው አቋምና ግብ ምንድን ነው? የሚለው ነገር በግልፅ ለህዝብና ለውይይት የቀረበ አይደለም። ለምሳሌ በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት ቋንቋን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር ስርዓት ላይ የተመረኮዘ ነው። ይህም አሁንም ድረስ ያላባራ ችግር ውስጥ እንደከተተን ይታወቃል። በዚህ ላይ የገዢው ፓርቲ አስተዳደር አቅጣጫ እና ግብ ምንድን ነው ስለሚለው ነገር ምንም የተነገረን ነገር የለም።
በእርግጥ ይህንን ግልፅ ማድረግ ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም አሁን ባለንበት ሁኔታ አንድ አቋም ይዞ መውጣት የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ያስቀይማል ወይም ድጋፍ ያሳጣል ተብሎ ስለሚወሰድ ቀላል አይሆንም። ስለዚህ ግልፅ ያልተደረገበት ምክንያት በቂ ነው ብዬ አምናለሁ። ግን እስካሁን ከተወሰዱ እርምጃዎችና ውሳኔዎች አንፃር የተለየ ነገር የሚሆን ይመስለኛል። ለምሳሌ ስራ ላይ ካለው ህገ-መንግስት ጋር ተያይዞ ፣ ከምንመራባቸውና ከምንተዳደርባቸው የአስተዳደር መርሆች ፣ መዋቅሮች አንፃር ለውጥ ሊኖር ይችላል ብዬ እገምታለሁ። ከህወሓት ጋርም የነበረው ትልቅ ልዩነት እና መካሰስ ስርዓቱ ላይ ለውጥ ይመጣል የሚል ነው። ስለዚህ በዘላቂነት ከመፍታት አንፃር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ ሊኖር የሚችልበትና በሚኖርበት አካባቢ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር ወይም ባለቤት የሚያደርግ ስርዓትና ህገ-መንግስት መኖር መቻል አለበት። ይሄ በዘላቂነት በየአካቢው ያሉ ግጭቶችን ለማስቆም ያስችላል። የጥቃቶቹ ዋነኛው ምክንያት በየአካባቢው የሚኖረው ህዝብ ፖለቲካዊ ውግንና በሚኖርበት አካባቢ በአስተዳደርና በፀጥታ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። እስከዚያ ድረስ ምርጫው ራሱ በተመሳሳይ ችግር ከተዘፈቀ የአደጋ ስጋት ይኖረዋል። ለዚህ የሚመጥን ዝግጅት በመንግስት በኩል መደረግ መቻል አለበት።
በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ምርጫው መካሄድ እንዳለበት ጥሪ ሲያደርጉ የነበሩት፣ ሲቀሰቅሱ የነበሩና አቋም ወስደው የነበሩ አሁን ደግሞ ‹‹ምርጫው መደረግ የለበትም›› የሚል አቋም ይዘው ብዙ ስራዎች እየሰሩ ነው የሚገኙት። እንግዲህ ይሄ በወቅቱ ምርጫ መደረግ አለበት ሲሉ የነበሩት የተሻለ የሀይል ሚዛን ስለነበራቸው እና የተሻለ ውጤት ማምጣት እንችላለን የሚል ስሌትና ትንተና ስለነበራቸው ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ከራሳቸው የፖለቲካ ግብና ፍላጎት አኳያ ብቻ ተነስተው ነበር ሲሞግቱ የነበሩት። አሁን ደግሞ ካለው የሃይል ሚዛን ትንተና አኳያ ተነስተው አሁን ምርጫው ቢደረግ ‹‹የእኛን የፖለቲካ ግብና ፍላጎት ሊያሳካ የሚችል ውጤት አይኖርም›› የሚል ትንታኔ ይዘው ነው የቀረቡት። ስለዚህ ከዚህ ተነስተው በአደባባይ ነው ‹‹ምርጫው መካሄድ የለበትም›› ሲሉ ሲሞግቱ የታዩት። ይሄ ጥረት የሚዲያና የፕሮፖጋንዳ ስራ ሊሆን ይችላል። ከዚያም አልፈው በተጨባጭ ምርጫው እንዳይካሄድ የፀጥታ ችግሮች እንዲፈጠሩ ያደርጉ ነበር።
ለዚህ ችግር መፈጠር ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩት እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ያሉ አይደሉም። በራሱ በመንግስት መዋቅር ሆነ በፓርቲ ውስጥም ያለ የሆነ የሃይል አሰላለፍ ያለ ሲሆን ድጋፍም የሚደረግለት መሆኑ መገመት ይቻላል። በየትኛውም ፓርቲ ውስጥም ይሁን በየትኛውም መንግስት ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶችና ግቦች አሉ። አንደኛው አንደኛውን አሸንፎ ለመውጣት ሁሉንም አይነት ጥረቶች ያደርጋሉ። የቅስቀሳ፣ የፕሮፖጋንዳ እና የመሳሰሉት ስራዎች እንዳሉ ሆነው አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ሃይል የተቀላቀለበትም ችግሮች በመፍጠር ለማደናቀፍ ሲሰሩ ይስተዋላል። ስለዚህ ይህንን ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀት ይጠይቃል። ለዚህ የሚመጥን ዝግጅት እስካለ ድረስ ችግሩ ቢፈጠርም እንኳን የተፈለገው ውጤት ሳይደርስ ማስቆም ይቻላል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ በመነሳት እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንወክለዋለን ለሚሉት ህዝብ ከማሰብ የመነጨ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ኃይለማርያም፡– እኔ እያንዳንዱ የፖለቲካ ግብና በዚያ ግብ ዙሪያ የሚሰባሰቡ ሰዎች እንወክለዋለን የሚሉት የህብረተሰብ ክፍል ጥቅምና ግብ ‹‹እኛ በያዝነው አቋም ነው የሚመነጨው›› ከሚል እምነት የመጣ እንደሆነ ነው የማስበው። ይሄ በየትኛውም የፖለቲካ ጎራ ወይም ደግሞ ካምፕ ውስጥ ያሉ እና የፖለቲካ ግብ ይዘው የሚሰሩ ግለሰቦች ቡድኖች በዚህ አስተሳሰብ ነው የሚደራጁትም ሆነ የሚንቀሳቀሱት። በተጨባጭ እነዚያ የፖለቲካ ግቦችና አስተሳሰቦች እንወክለዋለን የሚሉትን
የህብረተሰብ ክፍሎች ይጠቅማሉ ፤ አይጠቅሙም፤ የሚለው ነገር ሌላ ጉዳይ ነው። ባለፈው 50 ዓመት በተለያየ መንገድ የፖለቲካ ቡድኖች በተለያየ የፖለቲካ ሃሳብ ላይ ተደራጅተው እንደነበር ይታወቃል። ለምሳሌ የንጉሳዊውን ስርዓት መውደቅ ተከትሎ በተለያየ ርዕዮተ ዓለም የተሰለፉ ሃይሎች ብቅ ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለምም ይዘው የተለያየ ቡድን ሆነው የያዙት ሃሳብ እና ርዕዮት አገር ይጠቅማል ብለው ብዙ ግብ ግብ የፈፀሙበት ፣ ብዙ መስዋትነት የከፈሉበት፣ በተጨባጭ ግብ ግቡን አሸንፈው የፖለቲካ ስልጣን የያዙ ሃይሎችም በነበሩበትም ሆነ በዚያ ሂደት ውስጥ አገር ተጠቅሟል ወይ? እንደታሰበው በአገራችን የዘውድ ስርዓቱን መውደቅ ተከትሎ የተፈጠረው ስርዓት አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ አድርሷል ወይ? ብንል ያው ውጤቱን በተጨባጭ ያየነው ነው የሚሆነው። በመሆኑም በነበሩት የፖለቲካ ስርዓቶች ብዙ ቁልቁል የወረድንበትና ብዙ ውድቀት ውስጥ የገባንበት ነው ማለት ነው። ስለዚህ አንድ የፖለቲካ ግብ ወይም አስተሳሰብ የያዘ ሃይል ያንን ግብ ለህብረተሰቡ ማረጋገጥ አይቻልም። ምክንያቱም በተጨባጭ ተሞክሮ የሚታይ ስለሆነ ማለት ነው።
እንደዚህ አይነት የፖለቲካ አቋም ይዘው ስልጣን ላይ ያሉ ሃይሎችም ቢሆን እንወክለዋለን ላሉትም ሆነ ለሀገርም ብዙ ውድቀትና ችግር አስከትለው አልፈዋል። ስለዚህ አሁን ደግሞ ካለፈው የፖለቲካ ታሪካችን የሚመዘዙ የተለያዩ የፖለቲካ አሰላለፎች አሉ። ይሄ የሃይል አሰላለፍ ከገዢው ፓርቲ ውጪ ብቻ አይደለም ያለው፣ በራሱ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ሃሳብን መሰረት ያደረገ የተለያየ አሰላለፍ አለ። በተለይም አሁን ስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስትና ስራ ላይ ያለው ስርዓት መቀጠል አለበት ብሎ እስከመጨረሻው ድረስ ጥረት የሚያደርግ ሃይል አለ። በሌላኛው በኩልም ብዙ ነገሮች መለወጥና መሻሻል አለባቸው ብሎ የሚሰራ ሃይል ደግሞ አለ። ስለሆነም እኔ በግሌ የማምነው አሁን በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት ፣ የአስተዳደር መዋቅሮች የተተከሉበት፣ የተደራጁበት ማህበረሰባችን፣ ህዝባችን የተደራጀበት መርሆዎች በማያቋርጥ ግጭት ውስጥ እንዳስገቡን ነው። ለየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅሙ አይደሉም። ብዙ ችግሮችን አይተናል፣ብዙ ውድቀቶችም አጋጥመውናል። ከዚህ በኋላ ቢቀጥል እንደ ሀገርም ለመቀጠል ፈተና ውስጥ የሚከተን ነው የሚሆነው። በመሆኑም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያማከለ ፣ ለሁሉም ዋስትና የሚሰጥ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠቅመው ይሄ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ግን ብንቀጥል ወይም አሁን ያለው የክልል አስተዳደር እና ህገ-መንግስት የእኛን የህብረተሰብ ክፍል ይጠቅማል ብሎ የሚያስብ ሰው እንደሚያስቡት እንወክለዋለን ለሚሉት የህብረተሰብ ክፍልም የሚጠቅም ነገር አይደለም። ደግሞም ለየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ዋስትና የማይሰጥ ስርዓት ለሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ሊሰጥ አይችልም። እንደእኔ እምነት የመገዳደል፣የመጠቃቃት ፣ የመገፋፋት አዙሪት ውስጥ ከመግባት በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ምክንያቱም ሌላኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቃበት ፣ የሚጎዳበት ሁኔታ ባለበት የሠላም ዋስትና ሊኖረን አይችልም። ስለዚህ ስርዓታዊ ሽግግር ያስፈልገናል። ለውጥ ያስፈልገናል። መለወጥ ያለባቸው ነገሮች መለወጥ መቻል አለባቸው። ይህንን መሰረት አድርጎ የሚሰራ ማንኛውም ፖለቲካ ሃይል ወይም ቡድን ካለ ይህንን መደገፍ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ይህንን ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ የሃይል አሰላለፍ አለ ብዬ አምናለሁ። ይሄ የእኔ ግምት ነው። የፖለቲካም ሆነ የመንግስት መዋቅር ውስጥ አይደለሁም። ምን እንደሚያስቡና እንደሚወስኑ አላውቅም። እስካሁን እየተወሰኑና እየተተገበሩ ካሉ ስራዎች አንፃር ፍላጎቱ እንዳለ እገምታለሁ።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ ጊዜ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳና ክርክር ወቅት የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን የሚጎዱ ሃሳቦችን ሲሰነዝሩ ይስተዋላል። በዘንድሮ ምርጫ ይህንን ነገር ታዝበዋል? ከዚህ አኳያ ሊደረግ ይገባል የሚሉት ጥንቃቄ ምንድን ነው?
አቶ ኃይለማርያም፡– እንዳልሽው ስጋቱ አለኝ። ምክንያቱም ከዚህ ቀደምም በነበሩት ምርጫዎች በገዢው ፓርቲም በተፎካካሪዎችም በጣም ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ፣ ለግጭት የሚገፋፉ ቅስቀሳዎችን አይተናል። ይሄ ጠቃሚ አይደለም። ለራሳቸው ለፓርቲዎቹም ቢሆን የሚጠቅም አይደለም። አንደኛ ነገር ፓርቲዎቹ መወዳደር መቻል ያለባቸው በሃሳብ ጥራት ላይ መሆን ነው ያለበት። እንደፓርቲ የሚመሩባቸው ሃሳቦች በሃገር አስተዳደርና በሀገር ልማት ደግሞ ሊኖራቸው የሚችለውን ውጤት መሰረት አድርገው ሃሳባቸውን መሸጥ መቻል አለባቸው። ይህም ከፍተኛ የሆነ ጨዋነት ይጠይቃል፤ በጣም ስክነት ይፈልጋል። የትኛውም ህዝብ መሪዎቹ በሚያራምዱት አቋምና የፖለቲካ አቋማቸውን ለማራመድ የሚጠቀሙበት ስልት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ስለዚህ የመጀመሪያው ሃላፊነት የፓርቲዎቹ ነው። ምክንያቱም በግጭትና በትርምስ ውስጥ ማንም ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም። ራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ቢሆኑ አንፃራዊ በሆነ ነፃነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት አንፃራዊ የሆነ ሰላም ሲኖር ነው። ሰላምና መረጋጋት በሌለባቸው አካባቢዎች የተቃዋሚዎች እና የገዢውን ፓርቲ አመራሮችና ተወዳዳሪዎች የተገደሉበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ስሜት ቀስቃሽና የሚያጋግሉ የቅስቀሳ ስልቶች ለጊዜው አጭር የሆነ መፍትሄ ሊሰጡ ይችላሉ። ጉዳቱ ግን በዘላቂነት የሚቀጥል እና ለሁሉም ነው የሚሆነው። ስለሆነም ከገዢው ፓርቲ ከተቃዋሚዎችም ከፍተኛ የሆነ ሃላፊነት፣ ጨዋነት እና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ማለት ነው። የእንሸነፋለን ስጋት ወይም ፍርሃት አላስፈላጊ የሆነ የመጨረሻ አማራጮችን መጠቀም አካሄዱ ውስጥ ሊከተን ይችላል። ሥለዚህ በጣም ራስን መግዛትና መቆጠብ ይጠይቃል ማለት ነው። ምክንያቱም የሁሉም ጥቅምና ፍላጎት ሊረጋገጥ የሚችለው በዚያ መልኩ ነው። እናም ሃገርንና ህዝብ ካሰብን እነዚህን ነገሮች በጣም በተረጋጋ ሁኔታ ማራመድ ከባድ አይሆንም ብዬ አስባለሁ። በአንፃራዊነት አብዛኛው በውድድር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃላፊነት የሚሰማቸው ይመስለኛል። በድምሩ ግን አልፎ አልፎ ከሚታዩ አደገኛ የሆኑ ቅስቀሳዎችና ስሜትን ከሚያነሳሱ አጋጣሚዎች በስተቀር በአብዛኛው የተሻለ መረጋጋት ያለ ይመስለኛል። ያው ችግሮች አሉ፤ ይቀጥላሉም። ከችግር ነፃ መሆን ቀላል አይደለም። በአንፃራዊነት ግን የተሻለ ይመስለኛል። ከፓርቲዎቹ የሚመጣው ቅስቀሳ በላይ የፀጥታና አለመረጋጋት የሚመጣው ስጋት በጣም ከፍተኛ ነው።
አዲስ ዘመን ፡– በሀገሪቱ ከተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ቁጥሩ ቀላል የማይባለው የሕብረተሰብ ክፍል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባቱና ይህም ሁኔታ በምርጫው ላይ መጥፎ የሆነ አንድምታ ይኖረዋል የሚል ስጋት ያለባቸው አካላት አሉ። በእርሶ እምነት ህብረተሰቡ ከገባበት ተስፋ መቁረጥ አውጥቶ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው አካል እንዲሆን ምን መሰራት አለበት ?
አቶ ኃይለማርያም፡– እውነት ነው፤ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሁልጊዜ ህዝቡ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ አለ። ይህም ሊፈጠር የቻለው መጥፎ ተሞክሮዎች በመኖራቸው ነው። በተጨባጭ እንደህዝብም ያለፍናቸው በጣም መጥፎ ተሞክሮዎች ስላሉ እና በዚያ ምክንያት ከተፈጠረው ሰቀቀን መምጣቱ አይቀርም። ፍርሃቱ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም። እንዳልሽው የሁሉም ሰው ጥያቄ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ያለስጋት ወጥቶ መግባት ነው። አየሽ አንዳንድ ጊዜ ምርጫዎቻችን ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ከሰላምና መረጋጋት በላይ ማንም የሚያሳስበው የለም። አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት ቁጥር አንድ የህዝባችን፣ የሃገራችንም ጥያቄ ነው። በዚህ ውስጥ ሆኖ ተጨማሪ ቀውስና ችግር የሚፈጥር ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማንም ሰው ፍላጎት የለውም። በእኔ እምነት ቢያንስ ሰባትና ስምንት ወራት የተሰሩት ስራዎች ምርጫውን የበለጠ አደገኛ ሊያደርጉ የሚችሉና ለከፍተኛ ቀውስ ሊከቱ የሚችሉ የፖለቲካ ሃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች ከሂደቱ ውጭ ነው የሆኑት፡ ህወሓትን ጨምሮ ሌሎች በጥባጭ ሃይሎች በመወገዳቸው የምንሰጋውን ያህል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንገባለን ብዬ አላስብም። ነገር ግን ሁልጊዜም ቢሆን ስጋቱ አለ።
በምርጫው ወቅት፣ በቅስቀሳው ውስጥ ሆነን አንዳንድ ምልክቶችን አይተናል። ለዚህ ደግሞ አስቀድሜ የጠቀስኩልሽ በተፎካሪ ፓርቲዎችም ሆነ በገዢው ፓርቲ በኩል ተወዳዳሪ የነበሩ ሰዎች ሞተዋል። እነዚህ ነገሮች በምን ደረጃ ያድጋሉ? የሚለው ነገር እጅግ አሳሳቢ ነው። በተለይም ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ እንዲሁም የምርጫው ውጤት ይፋ ሲደረግ ደግሞ ምንድን ነው የሚሆነው? መንግስት ቢሸነፍ ውጤቱን አምኖ በፀጋ ይቀበላል? የሚለው ነገር አሁም የሚያሰጋ ነው። ስለዚህ አስቀድሜ እንዳልኩሽ በየጊዜው ትርምስና ግጭትን ሁነኛ የፖለቲካ መታገያ ያደረጉ አካላት በተለያዩ ምክንያቶች ከሂደቱ ውጭ መሆናቸው ለሁላችንም የሚያፅናና ነው። በአንፃራዊነት በፉክክር ላይ ያሉት ሀገራዊ ሃላፊነትና ግብ የሚጋሩ ናቸው ብዬ ነው የማምነው።
አደጋው ከዛሬ አመት ከነበረበት ሁኔታ የከፋ ነው ብዬ አስባለሁ። ግን ገዢው ፓርቲም ተቃዋሚዎችም የሚጠቀሙት ቋንቋና ድምፀት ወሳኝነት አለው። ስለዚህ ማስተካከል ከተቻለ አደጋውን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መቀነስ ይቻላል። ይሄ ሃላፊነት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሚዲያዎቹም እነዚህን ነገሮች ክርክሮች በሚደረግበት ጊዜ በሚያተላልፉት ነገሮች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። በጣም ስሜት ቀስቃሽ ከሆኑ ቅስቀሳዎችና አቀራረቦች መታቀብን ይጠይቃል። መንግስት ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ መዋቅሮቹን፣ የፀጥታ ተቋማቱን በደንብ መፈተሽ መቻል አለበት። ምክንያቱም የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ከራሱ የመንግስት መዋቅር ነፃ ላይሆኑ የሚችሉበት እድል በመኖሩ ነው። ስለዚህ የመንግስት መዋቅር ቢያንስ ከፀጥታ ችግር ነፃ ከሆነ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን ማረጋገጥና ጉዳት መቀነስ ይቻላል። የመንግስት መዋቅር በዚህ ችግር ውስጥ ተጠልፎ ከገባ ግን ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ከአሁኑ መንግስት መዋቅሩን መፈተሽ መቻል አለበት። ይህም ሁሉን አቀፍ ጥረት ይጠይቃል።ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማስተባበር እና ወጥ በሆነ መንገድ ከሰራን ችግር ቢፈጠር እንኳን ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– እንደሚታወቀው በዘንድሮ ምርጫ በርካታ ፓርቲዎች ናቸው የሚወዳደሩት፣ መጨረሻ ላይ ግን ውጤቱን አምኖ ተቀብሎ በሰላም ከመሄድ አኳያ ምን ያህሎቹ ዝግጁ ናቸው ብለው ያምናሉ? ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተስማሙበት መርህ አኳያ ከማን ምን ይጠበቃል ብለው ያምናሉ?
አቶ ኃይለማርያም፡– እንግዲህ አሁን ላይ ሆኖ አሸናፊው ስንት እና የትኛው ፓርቲ እንደሆነ አይታወቅም። መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምፅ አንድ ፓርቲ ብቻ ላያገኝ ይችላል። ከአንድ እና ከዚያ በላይ ፓርቲ ጋር ጥምረት መፍጠር ይጠበቅበት ሊሆን ይችላል። ሥለዚህ ውጤቱን በፀጋ መቀበል ከሁሉም ይጠበቃል። ሆኖም አስቀድመን እንደጠቀስነው ገዢው ፓርቲ ቢሸነፍ ስልጣኑን ሊለቅ ይችላል ወይ ? ሌሎቹስ ገዢው ፓርቲ ቢያሸንፍ አምነው ይቀበላሉ ወይ? የሚለው ነገር አጠያያቂ ነው። ለዚህ ትልቁ ችግር የእምነትና መተማመን ነው። በተቋሞቻችን ላይ ያለን እምነትና መተማመን ነው የሚስተዋለው። ይህ ችግር ብዙ ጊዜ የሚስተዋለው በታዳጊ አገራት ብቻ አይደለም፤ በኢኮኖሚም በጣም በበለፀጉ አገራትም ጭምር ነው እየተስተዋለ ያለው። እነዚያ አገራት ‹‹እኔ ነኝ.. .እኔ ነኝ›› ያሸነፍኩት በሚል ውዝግብ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ አለ። የህይወት መስዋትነትም ጭምር የሚያስከፍልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ስለዚህ የምርጫው ውጤት ሳይሆን ወሳኙ በተቋሞቻችን ላይ ያለን እምነት እና መተማመን ምን ያህል ነው የሚለው ነው የሚያሳስበው። ምርጫ ቦርድ ይሄኛው ፓርቲ አሸንፏል ቢል ምርጫ ቦርድን እናምናለን ወይ? ወይም ደግሞ ሂደቱ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ የተለያዩ አካላት ይታመናሉ ወይ? እንደኛ ባለ ሀገር ውስጥ ይሄ እምነትና መተማመን ማምጣት በጣም ከባድ ነው። ምርጫው ከግጭትና ከሁከት የፀዳ የማይሆንበትና፣ በመንግስት ወይም በፀጥታ ተቋማት ላይ የማንተማመንበት ሁኔታ መፈጠር መቻል አለበት። በምርጫው ወቅት ቅሬታዎች ሊመጡ ይችላሉ፤ ሂደቱ ላይ ችግር ከተፈጠረና ውጤቱን በሚወስን ስህተት ተሰርቷል የሚል ቅሬታ ሊመጣ ይችላል። በዚህ ምክንያት ፓርቲዎቹ አስቀድመው ስጋት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ስህተት ባይኖር እንኳን ስህተት ተፈጥሯል ብለን ልናምን የምንችልበት እድል አለ። ገዢው ፓርቲ ውስጥ ራሱ ስጋት ውስጥ ሊገባ ይችላል።
ስለዚህ ውጤቱ ከመገለፁ በፊት አስቀድሞ ተፅዕኖ የመፍጠር ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ ማለት ነው። በኋላ ውጤቱ ሲገለፅ ያንን ውጤት በተለያየ መንገድ የመረዳት እድል ይኖራል ማለት ነው። በአጠቃላይ ስጋቱ አለ፣ ይህ ደግሞ የሚመነጨው አስቀድሜ ካልኳቸው ነገሮች የተነሳ ነው ። ወሳኙ ነገር እንዴት እንሻገረው የሚለው ነው።በዚህ ሁሉ እምነትና መተማመን ማጣት በተቋሞቻችን የአቅም ውስንነት አለ፣ አንዳንዴ ሆን ተብለው የሚሰሩ ጥፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ እነዚህ ስህተቶችና ጉድለቶች ቢኖሩ እንኳን እንዴት እንቀበላቸው እንዴት እናስተናግዳቸው የሚለው ነገር ወሳኝነት አለው።
በሌላ በኩል ‹‹በህዝብ ድምፅ ስልጣን መያዝ አይቻልም›› የሚሉ ሃይሎች አስቀድመውም በአመፅና በትጥቅ ትግል ጥረት ውስጥ መግባታቸው በራሱ በምርጫው ፍትሃዊነት እና ዲሞክራሲያዊነት ላይ የራሱን ጥላ ማጥላቱ አይቀርም። በአብዛኛው ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብ ድምፅ ባሉት ተቋማት ተማምነን የመንግስት ስልጣን መያዝ እንችላለን በሚል እምነት ነው። ስለዚህ በሂደቱ ላይ ችግሮች ሊፈጠሩ ቢችሉ እንኳን ያለን አማራጭ ውጤቱንም ሆነ ውሳኔውን አምኖ መቀበል ነው። ምቾት ባይሰጥም ቅሬታ ቢኖርም፣ ቢያስከፋም ለአገርና ለህዝብ ሲባል መቀበል ያስፈልጋል። ደግሞም በተነሳንበት መንገድ እስከታመንን ድረስ የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚፈጥሩትን አደጋ መቀነስና ለሀገርና ለህዝብ ማሰብ ይገባል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በዘንድሮ ምርጫ ሲቪክ ማህበራት ተሳትፎም ሆነ እንቅስቃሴ እምብዛም አይታይም፤ ይህ በምርጫው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ አለ ወይ?
አቶ ኃይለማርያም፡– በትክክል፤ አስቀድሜ እንደገለፅኩትም ለምርጫው በሰላም መጠናቀቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል። ምርጫውንም የተሳካ የሚያደርገው የእነዚህ አካላት በተሟላ ሁኔታ መሳተፍ ነው። ሚዲያው ራሱን ችሎ ባለድርሻ ነው፣ የሲቪክ ተቋማቱም ትልቅ ሚና አላቸው። አንቺም እንዳልሽው የሲቪክ ማህበራቱ ተሳትፎ እኔም እያየሁኝ አይደለም። እንዳውም ከዚያ ይልቅ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን መንግስታዊ ድርጅት ቢሆንም በምርጫው ላይ በጎ ተፅእኖ ለማሳደር የራሱን ጥረቶች ሲያደርግ አይቻለሁ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የማበረታታትና የመቀስቀስ ስራ ሲሰራ ተመልክቻለሁ። ይሄ በጣም ተገቢ ነው።
ስለዚህ እነዚህ የሲቪክ ማህበራት ሚና ወሳኝና ጠቃሚ ነው። የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም እንዲወስዱ የመወትወት ፣ የማግባባትና ጫና የማሳደር ሚና አላቸው። በዚህ ረገድ ትርጉም ያለው ስራ ሰርቷል ሊባል የሚችል ስራ አልሰሩም። ጠንካራ የሲቪክ ማህበረሰብ ቢኖሩን የምርጫውን ሰላማዊነት፣ የተረጋጋ በማድረግ በኩል በጣም ትልቅ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችል ነበር። እንግዲህ ይህ የሚያሳየው ሀገር
በቀል የሲቪክ ማህበራት እንደሌሉን ነው። ያሉትም ተቋማት ደግሞ ከስጋት ነፃ አይደሉም። በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ብንሳተፍ ፣ ቅስቀሳ ብናደርግ በመንግስት በኩል በበጎ አንታይም የሚል ፍርሃት ያለባቸው ይመስለኛል። በኋላም ደግሞ በነፃ ለመንቀሳቀስ እንቸገራለን የሚል ስጋት የሚኖርባቸው ይመስለኛል።
ስለዚህ እነዚህ ነገሮች የራሳቸውን ጥላ አጥልተውባቸው ሊሆን ይችላሉ። በውጭ አካላት የሚደረገው እንቅስቃሴ ደግሞ የራሱ የሆነ ተፅእኖ ይኖረዋል። ምክንያቱም ማንኛውም ተቋም የሚያገለግለው የሚከፍለውን ነው። ኢትዮጵያ የምታቋቁማቸው የሲቪክ ማህበራት ኢትዮጵያን ነው የሚያገለግሉት። ነገር ግን አገር በቀል ተቋማት ገንዘብ ለማሰባሰብ የራሱ ፈተና አለው። ከዚህ ባሻገር በፖለቲካ ጉዳይ ለመሳተፍ በጣም የመሸማቀቅና የመፍራት ነገር ስላለባቸው ፈተናው ቀላል አይደለም። ግን ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ላለው ይቻላል። ዞሮ ዞሮ የሲቪክ ማህበራት ስራ ህብረተሰብ የማገልገል ተልእኮ ስለሆነ ሁልጊዜ መስዕዋትነት ይጠይቃል። በዚህ ረገድ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለው ተሳትፎ የሚያደርጉ ማህበራትን እያየን አይደለም። በቀረው ጊዜና ወደ ፊት በሚደረጉ ምርጫዎች ግን ጉልህ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎች ምንም እንኳን ምርጫዎቹ ነፃና ፍትሃዊ ነበሩ ለማለት ባይቻልም የውጭ ታዛቢዎች በመጋበዝና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ የተሻለ እንደነበር ይጠቀሳል። የእርሶ ግምገማ በዚህ ረገድ ምንድን ነው?
አቶ ኃይለማርያም፡– እኔም አላስተዋልኩም። ከዚህ በፊት የነበሩት ምርጫዎች እንዳልሽው ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ሲደረግ እናስታውሳለን። እግዲህ ውጤቱ ሊወስኑ የሚችሉ ስራዎች አስቀድሞ የመስራት ሰፊ ዝግጁነት ስለሚኖር አሁንም ያለስጋት ታዛቢ ለማሳተፍ ችግር የለም ብዬ አስባለሁ። አሁን መንግስት እንዲህ አይነት ጥሪዎች እያደረገ አይደለም። መንግስት ይህንን የማያደርግበት የራሱ ምክንያት ሊኖረው ይችላል። አሁን ባለንበት በተጨባጭ ሁኔታ በጣም ብዙ የውጭ ሃይሎች እጃቸውን በኢትዮጵያ ለማስገባት ስፋት ጥረት እያደረጉ ነው።
ትግራይ ላይ የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ አለም አቀፉ ሚዲያ፣ አለም አቀፍ በሰብአዊ መብት ጉዳይ የሚሰሩ በጣም ወገንተኛ የሆኑና ኢትዮጵያ እንደ አገር መንግስትንም ደግሞ ያላአግባብ አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገቡ ዘገባዎችንም ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችንም፣ ሰፊ የሆኑ ቅስቀሳዎችንም ሲሰሩ ቆይተዋል። ብዙ ጊዜ የአውሮፓና የአሜሪካ ተቋማት ናቸው በፋይናንስ ድጋፍ የሚያደረጉትና በቀጥታም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚቆጣጠሯቸው። እንደውም አደገኛ የሚባሉ በመንግስት በኩል በጣም በጥንቃቄ በመያዙ እንጂ ብዙ ችግር ውስጥ ሊያስገቡን የሚችሉ ጥረቶችን በተከታታይ ሲያደርጉ ቆይተዋል። መንግስት ከእዚህ ስጋት የተነሳ ለመጋበዝ ፍላጎት ሊኖረው አይችልም ብዬ አስባለሁ። ግን አልተጋበዙም የሚለው እውነት ነው። እኔም ብሆን በግሌ አገር በቀል ሲቪክ ተቋማት፣ በምርጫው ውስጥ ለመታዘብ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች መቀስቀስ አለባቸው፤ መጋበዝም ይኖርባቸዋል፤ ዕድሉ መመቻቸት አለበት ብዬ አስባለሁ። ከውጭ የሚመጡትን በሚመለከት ግን እኔም ብሆን በግሌ ለተሳካ የዴሞክራሲ ሙከራ አጋዥ ይሆናሉ ማለት አይቻለኝም። የራሳቸውን ፍላጎት ይዘው ስለሚመጡ በትክክል ሚናቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት የለኝም።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የውጭ ታዛቢዎችን መጋበዝ ማለት ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል እያሉኝ ነው?
አቶ ኃይለማርያም፡– እንዳልኩሽ በግሌ በውጭ ተቋማትና በውጭ መንግስታት ስለሚደገፉ በቀጥታም በተዘዋዋሪ መንገድ በውጭ ሃይሎች የሚዘወሩ የውጭ ታዛቢዎች ለተሳካ አገራዊ ምርጫና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የግድ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። ለአገር ውስጥ ግን በእዚህ ጉዳይ ላይ ለሚሳተፉና አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ አገር በቀል ተቋማት ነጻነቱ እንዲኖራቸው ሊወተውቱ፣ እድሉ ሊመቻችላቸው፣ ሊጋበዙና ዋስትናም ሊሰጣቸው ይገባል። ወደ ውስጣችን ማየት ነው የሚጠቅመን ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የግብጽና ሱዳን እጅ ተጽእኖውን በግልጽ እየታየ ባለበት ሁኔታ ከእዚህ አንጻር ምርጫው ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ? ተጽዕኖውን
ከመከላከል አኳያስ ምን መሰራት አለበት?
አቶ ኃይለማርያም፡– የህዳሴው ግድብ ምናልባት ከምርጫው ባልተናነሰ ስትራቴጂክ የሆነ ጥቅም አለው። ምርጫው ከጸጥታ ስጋትና ከመሳሰሉት ነጻ እንዲሆን መጠንቀቅ ያለብንን ያህል የህዳሴው ግድብ እንዳይደናቀፍ፣ በታቀደለት መልኩ እንዲቀጥልና እንዲሳካ ጥረት ማድረግ በጣም አስፈላጊና ግዴታ ነው ማለት ነው። ይሄንን ተከትሎ ደግሞ ግንባታውን ለማደናቀፍና እንዳይሳካ ለማድረግ የሚሰሩ በግልጽ የሚናገሩ አሉ። ለምሳሌ የግብፁ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከቅርብ ቀናት በፊት ነው አካባቢውን እንዳይረጋጋ ማድረግ እንችላለን በሚል በአደባባይ የተናገሩት። በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውም ፖሊሲ የሚታወቅ ነው። አንዱ በማያቋርጥ ነውጥና ትርምስ ውስጥ ኢትዮጵያን ማስገባት የሚለው ፖሊሲያቸውም ይታወቃል። በእዚህ ሂደትም ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት በጣም ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ስለዚህ ስጋቱ አለ፤ እውነተኛ ስጋት ነው ማለት ነው። ሱዳንም ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ጋር የራሷን ጥቅም መሰረት ጥሩ ግንኙነት የነበራት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለግብፅ ፍላጎት እና እቅድ የመንበርከክ ዝንባሌዎችን እያሳየች ነው።
ስለዚህ ጥቅምም ባይሆን እንኳን የኢትዮጵያ አለመረጋጋትና የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲደናቀፍ ሲባል በስልጣን ላይ ያለው የሱዳን መንግስት ለግብጽ ፍላጎት ተንበርክኳል የሚል እምነት ነኝ። ስለዚህ ከሱዳን መንግስትም በኩል የሚመጣው ተጽእኖና ስጋት ቀላል አይደለም። ድንበር ጥሶ ደግሞ በመግባት ወረራን ፈጽሟል። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጉዳዩ የተያዘበት አግባብ በጣም በጥንቃቄ መሆኑ እንጂ ለከፍተኛ ቀውስና ችግር ሊያጋልጠን ይችል ነበር። ይህንን መመከት ያስፈልጋል። እስካሁን ጥሩ የመመከት ስራ እየተሰራ ቆይቷል። ምናልባትም በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶችና ችግሮች እጃቸው የለበትም ማለት አይቻልም። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ ከሱዳን ጋር ብዙ በድንበር የምንጋራቸው ማህበረሰቦችም አሉ። በእዛ በኩል ተጋላጭ የሚያደርገን ነገር አለ። ስለዚህ ያለውን አደጋ ለመመከት ብዙ ስራ ይጠይቃል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ጠላቶች ምርጫውን እንደ ጥሩ አጋጣሚና ዕድል ተጠቅመው ኢትዮጵያን የማተራመስና ቀውስ ውስጥ የመክተት ፍላጎታቸውን ለማስፈጸምና ለመፈጸም እንደ ዕድል ሊያዩት ይችላሉ። ስለዚህ ምርጫው ከውጭ ሃይሎች ተጽዕኖ ነጻ መሆኑን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለብን፣ ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችንም መከላከል ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡– በዚሁ አጋጣሚ እስቲ ሶስቱ ሀገራት በህዳሴ ግድቡ ላይ በሚያደርጉት ድርድር ኢትዮጵያ የያዘቻቸው አቋም ምን ያህል አዋጭ ነው ይላሉ?
አቶ ኃይለማርያም፡– በድርድሩ ላይ የግብፅና የሱዳን አቋም ይታወቃል። ድርድሩን ከአፍሪካ ህብረት እጅ አውጥተው እነሱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተፅዕኖ ማሳደር በሚችሉ ሃይሎች እጅ እንዲወድቅ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል። ባለፈውም ድርድሩ በአሜሪካ እጅ እንዲገባ ያደረጉበት አጋጣሚም ነበር። ምክንያቱም ምዕራባውያኑ ጋር በተለያየ መንገድ የጥቅም ተስስር ስላላቸው እነሱ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉበት እድሉ አላቸው። በእርግጥ እስካሁን አልተሳካላቸውም። አሁን ከአፍሪካ ህብረት እጅ ለማውጣት ብዙ ዛቻም ፣ ማስፈራሪያም፣ የመሳሰሉትን ነገሮች ሲጠቀሙ ነው የቆዩት። እስካሁን የኢትዮጵያ መንግስት በጣም በተሳካ ሁኔታ ጉዳዩ ከአፍሪካ ህብረት እጅ እንዳይወጣ ማድረግ ችሏል። ከዚህ በኋላም ጥረታቸውን ያቆማሉ ብዬ አላስብም። ግን አጠቃላይ ሁኔታዎች ሲታይ የኢትዮጵያ መንግስት የዲፕሎማሲ የበላይነቱን እና እያየዘ ይመስላል። ሰሞኑንም የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ካይሮ ተገኝተው በጉዳዩ ላይ ያራመዱት አቋም ለኢትዮጵያ መንግስት ዲፕሎማሲ ተጨማሪ ድልን ያረጋገጠ ነው። ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት ሊታይና ሊያዝ እንደሚገባው አስረግጠው ነው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ እዛው ካይሮ ላይ ይህንን አቋም ያራመዱት። ሩሲያ የያዘቻቸው አቋም ለኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። ስለዚህ ማስፈራሪያውና ዛቻው እየሰራ አይደለም ማለት ነው። የሚፈልገፉትን ውጤት አላመጣም። አሁን ደግሞ ተመልሶ ወደ ድርድር ለመመለስ የተለያዩ መግለጫዎችን እያወጡ ነው። ስለዚህ መንግስት ጉዳዩን የያዘበት አግባብ በግሌ በጣም የተሳካ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– እንደአጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ምን ጉድለቶች አሉበት?
አቶ ኃይለማርያም፡– የህግ የበላይነትን ከማረጋጋጥ አንፃር በእኔ እምነት አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ- መንግስትም ሆነ ስርዓት በብዙ መልኩ ሊቀየር ሊለወጥ ይገባል። አሁን ባለንበት ህገ-መንግስት እና ስርዓት ውስጥ ሆነን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም ራሱ ስርዓቱ ብዙ ህዝቦችን መሰረታዊ በሆነ መልኩ ማረጋገጥ በማይችል ሁኔታ የተቀረፀ ስላልሆነ ማለት ነው። በየአካባቢው ያለው ማህበረሰብ አንደኛው ባለቤት ሌላኛው ደግሞ መጤ እና እንግዳ ሆኖ የሚበየንበት። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሚኖሩበት አካባቢ በአስተዳደር ውስጥ ለመሳተፍ በፀጥታ ጉዳዮች ውስጥ የራሱን ድርሻ ለመወጣት እንደአንድ ሙሉ ዜጋ መብቱን ሊጠቀም የሚያስችል እድል የማይሰጥ ነው። ስለዚህ ከዚህ መውጣት ያስፈልጋል። ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዋስትና የሚሰጥ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ያማከለ ህገ-መንግስት መቅረፅ ያፈልጋል። ይህንን ማድረግ ከተቻለ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ማዕቀፍ ሲኖር ነው ። በግሌ አሁን ስራ ላይ ያለው ህገመንግስት ያንን ማዕቀፍ በበቂ ሁኔታ የሚያዘጋጅ ነው ብዬ አላምንም። ባለፉት አመታት በየአካባቢው ብዙ መፈናቀሎች፣ ግድያዎች ፣ ጥቃቶች ደርሰዋል። በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ደግሞ የበለጠ ብዙ ችግሮች አይተናል። ከዚህ ሁሉ ቀውስ ውስጥ ጉዳት ያደረሱ፣ ሰው የገደሉ፣ የጨፈጨፉ አካላት ምን ያህል በህግ ጥላ ስር እንዲጠየቁ ተደርገዋል? ብትዪ በጣም ጥቂት ነው። ምክንያቱም ራሱ ስርዓቱ ፈቃድ የሚሰጣቸው እና ጥበቃ የማይሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ ነው። ምንም ወንጀል ቢፈፅሙ የማይጠየቁ ሰዎች አሉ። በአንድ አካባቢ ሄደሽ መጤነሽ ተብለሽ በምትገደይበት፣ በምትፈናቀይበት ፣ በምትዘረፊበት፣ አጥቂው እንደመብቱ ተቆጥሮለት እንዲገድል እድል የሰጠ ስርዓት እያየን ነው። የአስተዳደር መዋቅሮቹ ሁሉም እንደዜጋ መብት የሚሠጡ አይደሉም። በመሆኑ ለሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከህዝቡ ስነልቦና ታሪክም ሆነ ባህል ታሳቢ ያደረገ የፌደራል ስርዓት ሀገራችን ላይ መፈጠር መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ። በዚህ መልኩ የህግ የበላይነት ትርጉም ባለው ሁኔታ ስራ ላይ ማዋል ይቻላል፤ የዜጎችን ዘላቂ መሰረታዊ መብቶች ማረጋጥ ያስፈልጋል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መፃኢ እድል ምን ተስፋና ስጋት አለው ብለው ያምናሉ?
አቶ ኃይለማርያም፡– እኔ በግሌ በጣም ተስፋ ነው የሚታየኝ። እርግጥ ነው በየአካባቢው እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን፣ እየጠፋ ያለው የሰው ህይወት ፣ ንብረት መውደምን መሰረት አድርጎ ተስፋ መቁረጥ ፣ ከፍተኛ የሆነ ተስፋ የመቁረጥ ሥሜት እና የመረበሽ ስሜት ውስጥ መግባቱ የሚታወቅ ነው። እኔ ግን በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ብዙ ችግሮችን እያስተናግድን ብንመጣም ለውጡ ከመጣ ወዲህ በየአመቱ ትልልቅ እና ትርጉም ያላቸው ለውጦችን እያየን መጥተናል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ህወሓት ከስልጣን የተወገደበት አንድ ምዕራፍ ነው፣ ከዚያ አልፎ ደግሞ በሀገራችን ትርጉም ያላቸው እርምጃዎችና ውሳኔዎች የተወሰደባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል ተሳትፎ እንዲያርጉ እድል ተሰጥቷል። በእርግጥ አንዳንዶቹ ይህንን ለክፋት ተጠቅመውበታል።
አንዳንድ ጊዜ በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥና የጨለመ የሚመስልበት ሁኔታ ቢኖርም በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋ የሚሰጡ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በሁለት ሳምንት ውስጥ ህወሓት እንዲህ እንክትክቱ ይወጣል የሚል የፖለቲካ ተንታኝ የለም። ሁሉም በከፍተኛ ስጋት ውስጥና ጭንቀት ውስጥ ነው የነበረው። ምክንያቱም ራሱን ያደራጀበት፣ የታጠቀው ትጥቅና ያደራጀው ሰራዊትም ብዙ ጥፋትና ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ነበር። ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንን አደጋ መቀነስ ተችሏል። በእርግጥ እሱን ተከትሎ በብዙ አካባቢዎች ብዙ ጉዳት ደርሷል። በትግራይ ውሥጥም ብዙ የሰብአዊ መብት ጥቃቶች ደርሰዋል፣ ያ የሚያሳዝን አጋጣሚ ነው። ጉዳቱ እንዳይቀጥል መስራት ይጠይቃል። ህብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ መደበኛ ማህበራዊ ህይወቱ እንዲመለስ መጣር ያስፈልጋል። እንዲህም ሆኖ ግን እነዚያን አደጋዎች የተሻገርንበት መንገድ የፈጣሪ እገዛ እንደታከለበት መረዳት ትቺያለሽ። ከዚያ አልፎ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎችም እንደዚሁ አመፅ ፣ብጥብጥና ትርምስን ሁነኛ የፖለቲካ መታገያ አድርገው የያዙ የፖለቲካ ሃይሎችም ከዋናው ፖለቲካ እየተገፉ ጥግ እንዲይዙ የተደረገበት መንገድም ተስፋ የሚሰጥ ነው። እናም ብዙ ችግር አለ፤ ብዙ ጉዳት አለ፤ ስጋት አለ፤ አሁንም ግን እነዚህን ችግሮች እየተሻገርን የመጣንባቸው መንገዶች ተስፋ እንድንሰንቅና የተሻለ አገር ለማየት እድል የሚሰጥ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼ እና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ኃይለማርያም፡– እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013