ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ምርጫ ነው:: ምርጫ ዜጎች ይበጀኛል፤ ያስተዳድረኛል፤ ይወክለኛል፤ ችግሮቼን ይቀርፍልኛል፤ ሰላምና ድህንነቴን ያረጋግጥልኛል፤ ልማትና ብልጽግና ያጎናጽፈኛል ብለው ለሚያምኑበት ፓርቲ ወይም ተወካይ ድምፃቸውን የሚሰጡበት ሂደት ነው::
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 38 በተደነገገው መሰረትም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያውያን አምስት ምርጫዎችን ያካሄዱ ሲሆን ስድስተኛውን ምርጫ ከእስካሁኑ በተለየ ሁኔታ ለማካሄድ ትኩረታቸውን ሁሉ ምርጫው ላይ አድርገዋል:: የምርጫው ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ ጋር በመምከር ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 28/2013 እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳድሮች ምርጫ ሰኔ 5/2013 እንዲሆን በተወሰነው መሰረት ወደ ሥራ ገብተዋል::
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ መንገዱን ከጀመረች ወራት የተቆጠሩ ሲሆን የመጨረሻው የምርጫ ቀን ሊደርስም ከሰባት ሳምንት ያነሰ ጊዜያት ብቻ ቀርተዋል:: በምርጫ ቦርድ ሰሌዳ መሰረት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በይፋ የተጀመረው የካቲት 8/2013 ሲሆን እስካሁን ባሉት የሁለት ወራት ጊዜያት ውስጥም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምልክት ማጽደቅ፤ የዕጩዎች ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ ይገኛል::
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 28/2013 ቢካሄድም ምርጫ ውጤት ብቻ ሳይሆን ሂደትም ጭምር ስለሆነ በምርጫው ሂደት ላይ የሚታዩ አንዳንድ ስንክሳሮችን ከወዲሁ በማረም ምርጫውን ሰላማዊ፤ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነትን ያተረፈ ማድረግ ይገባል:: እስካሁን ባለው ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምልክት ማጽደቅ እንዲሁም የዕጩዎች ምዝገባ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል:: ከዚህ በተቃራኒ ግን በምርጫ ጣቢያዎች ዝግጅትና በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ግን በርካታ ችግሮች ይታያሉ::
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በ673 የምርጫ ክልሎች የሚደረግ ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል 49,407 የምርጫ ጣቢያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ:: ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው መራጮችን መመዝገብ ሲገባቸው በአጠቃላይ 50 ሺህ ከሚጠጉት የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ያለው በ25,151 የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ነው:: ይህ ደግሞ የመራጮችን ምዝገባ የሚያውክና በምርጫ ሂደቱ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው::
በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ የቀረው ሰባት ቀናት ብቻ ናቸው:: በእነዚህ ውስን ቀናት ደግሞ በመላ ሀገሪቱ በሚባል መልኩ ዝግጁ ያልሆኑትን ከ25 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን ከፍቶ ለመራጮች ምዝግባ ዝግጁ ማድረግ ከፍተኛ ትጋትንና ከጊዜ ጋር መሽቀዳደምን የሚጠይቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በምርጫው ሰኬት ላይ ተግዳሮት የሚሆን ነው:: ምንም አይነት ሰላም መደፍረስ የማይታይበትን የአዲስ አበባን ከተማ እንኳን ብንመለከት ካሉት 1 ሺህ 848 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ የጀመሩት 1 ሺህ 662 ናቸው:: ይህንን ስንመለከት የምርጫ ጣቢያዎችን ከፍቶ ለመራጮች ምዝገባ ክፍት ማድረግ ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀረው በቀላሉ ለመረዳት ይችላል:: እንደ አፋር እና ሶማሌ የመሳሰሉት ክልሎች ደግሞ ምዝገባ የጀመረ አንድም ጣቢያ ያለመኖሩ ችግሩን የበለጠ የተወሳሰበ ያደርገዋል::
ምርጫ እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት የምርጫ ጣቢያዎች በዚህን ያህል መጠን ዝግጁ አለመሆን አሳሳቢ ቢሆንም ለምርጫ ጣቢያዎቹ አለመከፈት እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው የፀጥታ ጉዳይ በመሆኑ ችግሩን በተቀናጀ ጥረት መፍታት ካልተቻለ የምርጫ ጣቢያዎቹ መቼ እንደሚከፈቱ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም:: ስለሆነም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ዋነኛ ኃላፊነት የተጣለበት የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ሥጋቶችን በማስወገድ ባሉት ውስን ቀናት የምርጫ ጣቢያዎቹ የሚከፈቱበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል:: የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ቢሆኑ የምርጫው ሂደት የተሳካ መሆኑ ዞሮ ዞሮ ጠቀሜታ ለእነሱ በመሆኑ በተቻለ መጠን በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና መራጮች እንዲመዘገቡ የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል::
ከምርጫ ጣቢያዎች አለመከፈት ጎን ለጎንም የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማድረስ የትራንስፖርት ችግር መኖር፤ ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች በምርጫው ታሳተፊ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት የተፈናቃዮቹን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልጽ በቂ መረጃ አለመኖር፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች መታሰር እና በቅስቀሳ ሂደት የሚያጋጥሙ የተለያዩ ሳንካዎች መፈጠር በምርጫ ሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው::
ስለሆነም ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በብዙዎች እንደሚጠበቀው ነፃ፤ ፍትሃዊ፤ ሰለማዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነትን ያተረፈ እንዲሆን በምርጫ ሂደቱ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች ከወዲሁ መፈታት ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013