የደም መርጋት በብዛት የደም አጓጓዥ በሆኑትና “ብለድ ቬዝል” የተሰኙት የደም ክፍሎች ግድግዳ ላይ በሚደርስ ጉዳት የሚከሰት ነው። ጉዳቱ በአይን የሚታየውና እንደ መቆረጥ ያለ አደጋ ሲደርስ የሚከሰት ይሆናል። አልያም በአይን የማይታይ ይሆንና በደም ሴሎቻችን ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ይጨምራል።
በተጨማሪም ደም በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት መዘዋወሩን ሲያቆም የደም መርጋት እክል ሊከሰት ይችላል። የደም መርጋት ችግር በአብዛኛው ጊዜ የሚታየው ደምን ከሰውነት ወደ ልብ በሚመልሱ ደም መላሽ የደም ስሮች ውስጥ የተቋጠረ ደም መርጋት ሲፈጠር ነው። ብዙ ጊዜ በታፋና በጭን ውስጥ ገባ ብለው በሚገኙ ተለቅ ባሉ ደም መላሽ የደም ስሮች ውስጥ ነው የሚከሰተው ።
የደም መርጋት መነሻ ምክንያቶች
• ለረዥም ግዜ የአልጋ ቁራኛ መሆን በተለይም እንቅስቃሴ የሌለበት ውሎና አዳር
• በዘር የሚተላለፍ በቤተሰብ አባላት ላይ የሚታይ ከሆነ
• ከወሊድ በኋላ እስከ ስድስት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ
• ከመጠን በላይ ውፍረት
• በቅርብ ጊዜ ቀዶ ጥገና ህክምና መደረግ
• በተለያዩ ምክንያቶች ከመጠን በላይ የደም ሴሎች መፈጠር
ሊከሰትባቸው የሚችሉ ምክንያቶች
• ካንሰር
• በተፈጥሮ የገዛ ሰውነትን የሚፃረሩ በሽታዎች – ሲጋራ ማጨስ
• የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኒኖች መውሰድ
• ለረጅም ሰዓታት በመቀመጥ ደም መርጋት ከላይ እንደተጠቀሰው በታፋ እና በጭን በሚገኙ ተለቅ ባሉ ደም መላሽ የደም ስሮች የሚፈጠር ሲሆን በብዛት የሚታየው በአንድ በኩል ብቻ ነው። የተፈጠረው የደም መርጋት ደም ዝውውርን ስለሚዘጋ የሚከተሉት ስሜቶች ይታያሉ።
በእጅ ወይም እግር አካባቢ ድንገት የሚከሰት እብጠት፦
የደም መርጋት በእግር ወይም እጅ ውስጥ ደም እንደልቡ እንዳይዘዋወር በማድረግ ደም ወደ ኋላ እንዲመለስ የሚያደርግ ሲሆን፥ በዚህ ምክንያትም እብጠት ይከሰታል። በእጅ ወይም እግራችን ላይ በድንገት ህመም ያለው እብጠት ካጋጠመንም ትኩረት ልንሰጠው ይገባል።
የእግር ወይም የእጅ ህመም በብዛት የደም መርጋት ምልክት ናቸው ከሚባሉት ውስጥ እብጠትና የሰውነት መቅላት ተጠቃሽ ቢሆኑም፤ ከዚህ የተለየ ምልክቶች አሉ። በደም መርጋት ምክንያት በእጅ እና በእግር ላይ የሚከሰት የህመም ስሜትን በርካቶች የጡንቻ መሸማቀቅ ይመስላቸዋል።
በዚህ ምክንያትም በርካቶች ህክምና ሳያገኙ ይቀራሉ። ስንራመድ ወይም እግራችንን ወደ ላይ እና ወደ ታች በማድረግ በምናንቀሳቅስበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜት የሚሰማን ከሆነ የደም መርጋት ምልክት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ወደ ጤና ተቋም ብንሄድ መልካም ይሆናል።
በደረት አካባቢ የሚከሰት ህመም፦
ብዙ ጊዜ ደረታችን አካባቢ የህመም ስሜት ሲያጋጥመን የልብ ህመም ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን ከደም መርጋት ምልክቶች ውስጥ ደረት አካባቢ የሚሰማ የህመም ስሜት ተጠቃሽ ነው። ብዙ ጊዜ የደም መርጋት ምልክት ነው ተብሎ ከሚጠቀሰው የደረት አካባቢ ህመም ውስጥ ትንፋሽ ወደ ውስጥ ስንስብ ደረታችንን ቀስፎ የመያዝ እና የመውጋት ስሜቶች ተጠቃሽ ናቸው።
የትንፋሽ ማጠር ወይም የልብ ምት ፍጥነት መጨመር በሳምባችን ውስጥ የሚከሰት የደም መርጋት የኦክሲጅን በብዛት እንዳይዘዋወር ያደርጋል። የኦክሲጅን ዝውውር አነስተኛ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ልባችን የኦክሲጅን እጥረቱን ለማካካስ ሲል በፍጥነት መምታት ይጀምራል።
በደረታችን አካባቢ ግራ የሚያጋባ ስሜት ከተስተዋለብን እና ትንፋሽ ወደ ውስጥ በምናስገባበት ጊዜ የሚያስቸግረን ከሆነ በሳምባችን ውስጥ የደም መርጋት ለመከሰቱ ምልክት ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ በርካቶች ራሳቸውን እንዲስቱ የሚያደርግ ሲሆን፥ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላልም ነው የተባለው። ስለዚህ እንዲህ አይነት ችግር በብዛት የሚስተዋልብን ከሆነ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ መታከም ይመከራል።
የቆዳ መቅላት፦
ከደም መርጋት ምልክቶች ውስጥ የሰውነት ቆዳ መቅላት በዋናነት ይጠቀሳል። እንዲሁም የቆዳ በመለዝ ወይም ቀያይ ሰንበሮችን ማውጣትም ምልክቶቹ ሊሆኑ ይችላሉ። አጣዳፊና ደረቅ ሳል፦
በምን ምክንያት እንደተከሰተ ያልታወቀ አጣዳፊ የሆነ ደረቅ ሳል የደም መርጋት ምልክት ሊሆን ይችላል። በተለይም በምናስልበት ጊዜ የትንፋሽ ማጠር፣ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የልብ ምት እና ደረታችን አካባቢ የህመም ስሜት የሚሰማን ከሆነ የደም መርጋት ምልክት መሆኑን ሊያረጋግጥልን ይችላል። እንዲህ አይነት ምልክቶች የሚስተዋልብን ከሆነ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የጤና ባለሙያዎችን ማማከር እና ተገቢውን ህክምና ማድረግ ይገባል።
ምርመራዎቹ
• የደም ምርመራ
• እግር ላይ የተቋጠረውን ደም ለማየት ዶፕለር የአልትራሳውንድ ምርመራ ይደረጋል
• የደም መርጋት መኖሩ እንዳለ ከታወቀ የደም መርጋት ለመፈጠሩ ምክንያቶችን ለማወቅ ተጨማሪ የደም ምርመራዎች ይደረጋሉ።
ህክምናው
• ደም ማቅጠኛ (Anticoagulant) መድሀኒቶች ይታዘዛሉ፤
• ከመድሀኒት በተጨማሪ በእግር ውስጥ የደም ዝውውርን ለመጨመር ስቶኪንግ ሊታዘዝ ይችላል፤
• ለረዥም ሰዓታት የሚቀመጡ ከሆነ እግርዎን በየጊዜው ማንቀሳቀስ ተገቢ ነው።
• በተጨማሪም የረጋው ደም ወደ ላይ ወደ ሳንባ እንዳይሄድ ለመከላከል በደም ስር በኩል የማጣሪያ ወይም የማጥለያ ወንፊት ሊቀበር ይችላል። አንዳንድ ጊዜም የረጋውን ደም ለማስወገድ ወይም ለመበተን የሚያስችሉ መድሀኒቶች በቀጥታ ደሙ ወደረጋበት ቦታ በመርፌ በኩል ሊሰጡ ይችላሉ።
ምንጭ፦ www.menshealth.com
ይረዳል። ከዚህ አንጻርም በሳምንት ለ150 ደቂቃዎች መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው። //
ምንጭ፡- www.eufic.org/en
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 7/2013