ፍሬህይወት አወቀ
ቦታው አዳማ ከተማ አመዴ ወይም ጨፌ የገበያ ማዕከል ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ነው። በአካባቢው ከ20 የሚበልጡ የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቆች አሉ። አብዛኞቹ በማህበራት የተደራጁ ሲሆኑ በግላቸው የግለሰብ ሱቅ ተከራይተው የሚያመርቱና የሚሸጡም አልጠፉም። በየሱቁ የሚታዩት ባህላዊ አልባሳትና የተለያዩ ባህላዊ ቁሳቁሶች ዓይን ይይዛሉ። በየሱቁ የሚታዩት ሰዎች በሥራ የተጠመዱ ናቸው። ነጫጭ የተቆራረጡ ጨርቆችን በስፌት ማሽን የሚሰፉ፤ የተሰፋውን የሚዘመዝሙ፤ ቁልፍ የሚተክሉ፤ የሚተኩሱ፤ ደንበኞችን የሚያስተናግዱ እንዲሁም በተመስጥኦና በትዕግስት አንገታቸውን አቀርቅረው አልባሳቱን በጨሌ የሚያስጌጡ ወጣት እንስቶችም ለቁጥር የበዙ ናቸው።
እንስቶቹ ግንባራቸው ላይ ካጠለቁት ጨሌ ጀምሮ በባህላዊ አልባሳት ተንቆጥቁጠው ጨሌዎቻቸውን በተመስጥኦ በወግ በወጉ ይደረድራሉ። ጉልበታቸው ላይ የታቀፉት የተለያየ ቀለም ያላቸው ጨሌዎች በቅደም ተከተላቸው መሰረት ደርድረው ሲጨርሱ እንደ አስፈላጊነቱ በባህላዊ አልባሳቱ ላይ በተለይም በልብሱ አንገት አካባቢ ይሰፋሉ። ጨሌዎቹም ሆኑ የባህል አልባሳቱ በተለያዩ ቀለማት የተንቆጠቆጡ ሲሆን ከቀለማቱም መካከል ነጭ፣ ቀይና ጥቁር ጎልተው ይታያሉ።
በአካባቢው የሚታየው እንቅስቃሴ ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም በርካታ አልባሳቶች ያሉበትና በተሻለ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያገኘነው ፊራኦል የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት መሸጫ ሱቅ አንዱ ነው። እኛም ፊራኦል የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት መሸጫ ሱቅ ከየት ተነስቶ የት ደርሷል፤ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴው ምን ይመስላ፤ ዘርፉ ባህልን ከማስተዋወቅ አንፃር ምን አበርክቶ አለው፤ የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ለሌሎች ተሞክሮ ይሆን ዘንድ የስኬት አምዳችን እንግዳ ልናደርገው ወደድን ።
ትውልድና ዕድገታቸው ከአርሲ የሆነው አቶ ፍጹም አያሌው የመምህር ልጅ ናቸው። በመምርነት ሞያቸው አማካኝነት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ አዳማ ከተማ የመጡት ወላጅ አባታቸው አቶ አያሌው ኑሯቸው አዳማ ከተማ ላይ ሲሆን፤ አቶ ፍጹምም ትምህርታቸውን በአዳማ ከተማ የማጠናቀቅና በከተማዋ የመቆየት ዕድል አግኝተዋል። ከትምህርታቸው በመቀጠልም በባህላዊ አልባሳት ዘርፍ ተሰማርተው ወደ ሥራው ዓለም ተቀላቅለዋል። ወደ ባህላዊ አልባሳት ሥራ ለመግባትም ምክንያት የሆኗቸው የባለቤታቸው ቤተሰቦች እንደሆኑ በማስታወስ እርሳቸውም ለሙያው ትልቅ አክብሮትና ፍቅር የነበራቸው ሰው መሆናቸውን አጫውተውናል።
አቶ ፍጹም፤ ኢትዮጵያዊ የሆነው ባህላዊ አልባት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን አንስተው እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ በባህሉ መሰረት ባህላዊ አለባበሱን፣ አመጋገቡን አጠቃላይ የባህል እሴቱን በሚገባ መጠቀም ከቻለ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይቻላል። የኢትዮጵያ ባህል በራሱ ሰፊና ጥልቅ እንደመሆኑ በስፋት ልንጠቀምበትና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በሀገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለውን ድርሻ እንዲወጣ ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ።
አቶ ፍጹም፤ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቀጥታ በሸማ ሥራና በሀገር ባህል አልባሳት ወደ ተሰማሩት ቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለው ሥራ ጀምረዋል። ሥራ የጀመሩትም በመዘምዘም፣ ጥልፍ በመጥለፍና አልባሳቱ የሚጠይቀውን የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ ነው። ሙያውን ከዕለት ዕለት በማሻሻል ሥራውን በራሳቸው አቅም ባለቤታቸውን ደጋፊ በማድረግ መሥራት ጀመሩ። በአንድ የሲንጀር መኪና የተጀመረው የሀገር ባህል ልብስ ስፌትም ዛሬ ላይ በአዳማ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የባህል አልባሳት አምራችና ሻጭ ነጋዴዎች መካከል ስመጥር ለመሆን አስችሏቸዋል።
አቶ ፍጹም ከአራት ዓመታት በፊት ከቤተሰቦቻቸው ተቀብለው የጀመሩት የባህል አልባሳት ምርት ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ ቤተሰብ ያስተዳድራሉ። ከእርሳቸው አልፎም 100 ከሚደርሱ የዘርፉ ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በትብብር ይሰራሉ። የኦሮሞ ባህል በራሱ ትልቅና ሰፊ ነው የሚሉት አቶ ፍጹም፤ ሥራው አንድ ሰው ብቻውን የሚሰራው እንዳልሆነና በቅብብሎሽ የሚሰራ ሥራ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይም ሸማኔው ለባህል አልባሳቱ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ከሸማኔው ጋር በትብብር መሥራትና የሸማኔውን ጥበብ መጠቀም የግድ መሆኑን ይናገራሉ።
በተለይም በአሁን ወቅት በተለያዩ ዲዛይነሮች ተውበው የሚታዩት የሀገር ባህል አልባሳቶች በዲዛይነሮች አማካይነት እና በርካታ የእጅ ሥራዎችን የሚጠይቅ በመሆኑ ዋጋው ውድ ቢሆንም ነገር ግን ተገቢውን ክፍያ ለሸማኔው መክፈል የሚገባ ነው። ሸማኔው ያልሸመነውን ሸማ ሰፊው ወይም ጠላፊው ምንም ሊያደርግለት አይችልም። ስለዚህ ሸማኔው ካለበት ቦታ ሸማውን በመግዛት የተለያዩ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳትን ያመርታሉ። ያመረቷቸው አልባሳቶችም በተለያዩ ጨሌዎች ባህሉን በሚገልፁ ምልክቶች ተንቆጥቁጠው ይታያል።
አቶ ፍጹም የባህል አልባሳቱን በሚያመርቱበት ሱቅ ውስጥ ግብይቱንም የሚፈጽሙ ቢሆንም በርካታ ሥራዎቹ ወይም ዝግጅቶቹ ከየቦታው ተዘጋጅተው የሚመጡ እንደሆነ አጫውተውናል። በዋናነት ሸማው ሸማኔው ካለበት ቦታ ተዘጋጅቶ የሚመጣ ሲሆን ሌሎች ሥራዎችንም ሠራተኞች ሥራውን ከለመዱት በኋላ በተለይም ጥልፎችን በየቤታቸው ጠልፈው የሚያቀርቡ መሆኑን ይናገራሉ።
ሥራው በርካታ ሰዎችን የሚፈልግና በቅብብሎሽ የሚሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍጹም፤ ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በልምምድ መሥራቱ ውጤታማ የሚያደርግ ስለመሆኑ እኔ በራሴ ጥሩ ምሳሌ ነኝ ይላሉ። ምክንያቱም እርሳቸው ከቤተሰብ የወረሱትን ሞያ አብረዋቸው ለሚሰሩ ሠራተኞች በማጋራት በሰጡት የሥራ ላይ ሥልጠና በርካቶችን አብቅተዋል። የበቁት ሠራተኞችም የተወሰነ ጊዜ ከእርሳቸው ጋር ከሰሩ በኋላ ወጥተው በራሳቸው ማምረት የጀመሩ ስለመኖራቸውም ይመሰክራሉ።
ማንኛውም ሠራተኛ እርሳቸው ጋር ሥራ ፈልጎ ሲመጣ በቀላሉ ዝምዝም፣ ቁልፍ መትከልና መተኮስ ከመሳሰሉት ሥራዎች የሚጀምርና ሥራው ሲሰራ በመመልከት የሥራ ላይ ሥልጠና ያገኛል። ሠራተኞቹ የተመለከቱትን ማንኛውንም ሥራ በተግባር እየሰሩ በሚያደርጉት ልምምድ በስፌት ማሽን ላይ መሥራት የሚያስችል ብቁ ሞያተኛ ያደርጋቸዋል የሚሉት አቶ ፍጹም፤ በቴክኒክና ሞያ ትምህርትና ሥልጠና ተምረው ከሚያገኙት ክህሎት በበለጠ በሥራ ላይ በልምድ የሚያገኙት ዕውቀት ፈጣንና በተጨባጭ መታየት የሚችል እንደሆነም በተግባር ያረጋገጡት ስለመሆኑ አጫውተውናል።
ከአራት ዓመታት በፊት በጥቂት ገንዘብ ወደ ሥራው የገቡት አቶ ፍጹም፤ ያን ጊዜ የነበረው የማህበረሰቡ አቀባበልና አሁን ላይ ያለው ሁኔታ እጅግ የተራራቀ መሆኑን ጠቁመው በአሁን ወቅት ግን ተጠቃሚው በርካታ ነው ይላሉ። ከዚህ ቀደም የባህል አልባሳት በባህላት ወቅትና በተለያዩ ፕሮግራሞች ብቻ ይለበስ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ሰዎች ለሠርግ፣ ለልደትና ለተለያ ፕሮግራሞች የባህል አልባሳቱን ተመራጭ ያደርጋሉ።
በኦሮሚያ አካባቢ አብዛኛው ማህበረሰብ በተለይም ወጣቱ ወደ ባህላዊ አልባሳት እየመጣ ነው። ከጊዜ ወደ ገዜ እየጨመረ የመጣው የባህል አልባሳት ገበያም አዋጭና ተመራጭ ነው። ስለዚህ ዘርፉን አጠናክሮ በመያዝ በተሻለ ጥራትና መጠን ለአለባበስ ምቹ አድርጎ የማምረትና የመሸጥ ሰፊ ዕቅድ ያላቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
የማምረት አቅማቸውን በተመለከተም እንደ አልባሳቱ አይነት የሚለያይ ሲሆን፤ በአብዛኛው አልባሳቱ በሚፈለግበት የባዓላት ወቅት ለቁጥር የበዙ አልባሳትን ያመርታሉ። በተለይም የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ወቅት የተለያየ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት የሚፈለግበት ወቅት በመሆኑ ሰፊ ገበያ አለ። በዚህ ጊዜም ከፊራኦል የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ማምረቻና መሸጫ ሱቅ ጋር በጋራ ከሚሰሩ 100 ሠራተኞች በተጨማሪ ለሌሎች ሠራተኞችም የሥራ ዕድል ይፈጠራል።
ለአብነትም በአንድ ወቅት ለተዘጋጀ መድረክ የባህል አልባሳት እንዲያቀርቡ በተደረገላቸው ጥሪ በ10 ቀናት ውስጥ ለ480 ሰዎች ልብሱን አዘጋጅተዋል። ይህ ትልቅ አቅም ነው። አልባሳቱ በስፌት መኪና ከሚሰራው በበለጠ በእጅ ሥራ የሚጠለፍ ሥራ ስላለው ጊዜ የሚወስድ ይሆናል። እንደ ፋብሪካ በርካታ ተመሳሳይነት ያላቸውን አልባሳት በአንድ ጊዜ አምርቶ ማውጣት የሚቻል አይደለም። በእጅ የሚሰራ ጥልፍ ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅና ውበትና ጥራት ያለው ነው። ይህም ባህሉን በማስተዋወቅ ረገድ ተመራጭ ያደርገዋል።
ከገቢ አንፃር ፊላኦር የኦሮሞ ባህል አልባሳት ማምረቻና መሸጫ ይህን ያህል ካፒታል ደርሷል ብሎ በቁጥር ለመግለጽ ቢቸግርም በሱቅ ውስጥ ያሉት በርካታ ምርቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ ያወጣል። ከዚህም በላይ በርካታ ቁጥር ካላቸው ሠራተኞችና ግብዓት አቅራቢዎች ጋር በትስስር የሚሰሩ መሆናቸውና አጠቃላይ ሥራው የተደራጀና መስመር የያዘ መሆኑ በራሱ ትልቅ ሀብት ነው። ከምንም በላይ ሥራው የተደራጀና መሥመር የያዘ በመሆኑ ማንም ሰው ቢመጣ በቀላሉ ማስቀጠል የሚቻል እንደሆነም አጫውተውናል።
ለዚህም ከአዲስ አበባ ከተማ ጀምሮ የሥራ ሰንሰለት ያለው በመሆኑ ትዕዛዝ ሲኖር ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ባይኖሩ እንኳን ግብዓቱ ካላቸው ደንበኞች ከአዳማም ይሁን ከአዲስ አበባ ድረስ በማስመጣት እንደሚያመርቱ ይናገራሉ። ስለዚህ ሥራው በዘርፉ ከተሰማሩ የተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራና አገርን የሚያስተዋውቅ በመሆኑ መሰረት ጥሎ መሥራት ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው።
የባህል አልባሳት ሥራውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስተው እስካሁን ለመጡበት መንገድ መንግሥት ትልቅ ድርሻ እንደነበረው አቶ ፍጹም አንስተዋል። ከዚህ ቀደም ለዘርፉ የተሰጠው ቦታ አነስተኛ ከመሆኑም ባለፈ የባህል አልባሳት በየጊዜው የሚለበሱ አልነበሩም። ነገር ግን በአሁን ወቅት ለባህል ዘርፉ መንግሥት እየሰጠ ያለው ትኩረት የሚያበረታታ ነው። ማህበረሰቡም ባህሉን የመከተልና የማድነቅ ግንዛቤው ከዕለት ዕለት እየጨመረ በመምጣቱ ሥራው አዋጭና ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ሆኗል።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የአዳማ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለዘርፉ ዕድገት ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ሲሆን እርሳቸውም ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ አጫውተውናል። በተለይም የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲቻል በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ ተሳታፊ ሆነው የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩና መሸጥ እንዲችሉ በማመቻቸት ሰፊ እገዛ ሲያደርግላቸው መቆየቱን ይጠቅሳሉ።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለዘርፉ እየሰጠ ያለውን ትኩረት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የራሳቸውን ፈጠራና ተነሳሽነት ደምረው በባህል አልባሳቱ የተሻለ ሥራ እየሰሩ የሚገኙት አቶ ፍጹም፤ አልባሳቱን በስፋት አምርቶ ለገበያ በማቅረባቸው ከእርሳቸው አልፎ አገሪቷም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንደምትሆን በማመን ወደፊት ሥራውን በስፋት ለመሥራት ዕቅድ አላቸው።
በፊራኦል የኦሮሞ የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ ከሚመረቱ የባህል አልባሳት መካካል ሱሪ ከ800 ብር ጀምሮ የሚሸጥ ሲሆን ቀለል ያሉ ጥልፍ የተጠለፈባቸው ቲሸርቶችም እንዲሁ ከ700 ብር ጀምሮ ቀርበዋል። ቀሚስ፣ ሸሚዝና ሌሎች አልባሳትም በየደረጃቸው ተመርተው ለገበያ የሚቀርቡ ሲሆን በተለይም የሙሽራ አልባሳትን በስፋት ያመርታሉ።
ማንኛውም ባህላዊ አልባሳት ለሙሽራም ይሁን ለተለያዩ ዝግጅቶች እንዲሁም በአዘቦት የሚለበስ ደንበኞች በሚፈልጉት ዲዛይን መሰረት የሚዘጋጁ ናቸው። ከትዕዛዝ ውጭም የተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ተዘጋጅተው ለገበያ የሚቀርቡ በመሆናቸው ማንኛውም ሰው የፈለገውን መርጦ መግዛት ይችላል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013