ግርማ መንግሥቴ
በአሁኗ አገራችን እንኳን «የፍልስፍና ክበባት» ቀርቶ እራሱ «ክበብ» የሚለው ቃል ስለመኖሩ አይደለም ስለመፈጠሩም ማንም ምንም መናገር አይችልም፤ «ፍልስምና» እያለ በየምናምኑ የሚለጥፈውን እንቁጠረው ካልተባለ በስተቀር። ግን ደግሞ ወደድንም ጠላን፤ «ሙሉ ሰው» መሆን እስከፈለግን ድረስ «የፍልስፍና ክበባት»ም ይሁኑ ሌሎች ያስፈልጉናል።
(ተጓዳኝ የትምህርት አካል ስለሆነው «የፍልስፍና ክበብ/ባት» ስናወራ ግን እራሱ «ፍልስፍና» የሚለው በአገራችን ስለመወደዱም ይሁን መፈቀዱ የምናውቀው ነገር ይኖር ይሆን? አአዩ (AAU) ውስጥ በአንድ ወቅት ዜና ሆኖ የነበረው የክፍለ-ትምህርቱ «ይዘጋ» (የ«ታሪክ» እና «ፎክሎር» የጥናት መስኮችንም ጨምሮ) ትርምስ ምን ላይ ደረሰ? ለመሆኑ አንድ ጋዜጣ ላይ እንኳን «በፍልስፍና ትምህርት ቢኤ/ኤምኤ/ፒኤችዲ ያለው/ያላት …» የሚል የሥራ ማስታወቂያ ያየም ሆነ ያነበበ አለን? ችግሩም ሆነ መፍትሄው እነዚህን ከማወቅም ሆነ ከመረዳት የሚጀምር ቢሆንም ይህ ጽሑፍ ወደ እነዚህ ጉዳጉዶች ውስጥ አይዘልቅም።)
በመጀመሪያ ደረጃ «ክበብ» ማለት እንደ አንድ ድርጅት ሊቆጠር የሚችል፤ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች አነሳሽነት ወይም መስራችነት የሚመሰረት፤ በአብዛኛው በአንድ «ነጠላ ጉዳይ» (ዲሲፕሊን) ላይ የሚመሰረትና በእሱው ዙሪያ የሚሽክረከሩ ሀሳቦችን የሚያስተናግድ፤ ያለ ምንም ዓይነት ልዩነት አባላትን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ወዘተ መሆኑ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ሲሆን፤ አባላቱም – ከመስራች እስከ ተባባሪና የክብር አባላት ድረስ ያሉት ተመሳሳይ ፍላጎት፣ ስሜት፣ ሙያ፣ የሕይወት ልምድ ወዘተ ያላቸው መሆናቸውም እንዲሁ አንድን ክበብ ከሌላው የተለየ ያደርገዋል። («የፍልስፍና ክበብ» ብለን ስንነሳም ይህንኑ መሠረታዊ አስተሳሰብ ይዘን ነው።)
«ክበብ» ወይም «ክበባት» በትምህርት ተቋማት፣ በተለይም በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች እንደየፍላጎታቸውና ችሎታቸው ተሳትፎ የሚያደርጉባቸው ሲሆኑ ይህም በትምህርት ሙያዊ ቋንቋ «ተጓዳኝ ትምህርት» (Co-curricular activity) በመባል ይታወቃል።
«የፍልስፍና ክበብ» (የዛሬ ዘመናዊ ስሙን ከመጎናፀፉ በፊት በጅምላ «ክበብ» ወይም «የውይይት ክበብ» በሚል መጠሪያ ይታወቅ ነበር። ከዚያ በፊትም እጅግ ጠቅላይና ጀማይ በሆነው በ«ውይይት» ይታወቅ የነበረ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፤ «ውይይት» ታክሲን በታሪካዊ ማስታወሻነት በመጥቀስ ለእኛ አዲስ እንዳልሆነ፤ ነገር ግን የመጣው ሁሉ እየነቀለ እየጣለውና መከራ ውስጥ የገባን መሆኑን በእልህና ድፍረት የሚያብራሩ ብዙዎች ናቸው። ያም ሆነ ይህ የብዙዎቹ ገራገር አስተያየት ሲጠቃለል «ነበር»፣ «የለም»፤ «ይኖራል» የሚል ነው። («ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን» ሲባል ያልገባኝ እዚህ ጋ «የለም» ተብሎ መምጣቱን ልብ አልኩት።)
«ፍልስፍናን ከመደበኛው ትምህርት ባለፈ በክበብ ወይም ክበባት ደረጃ ማስተናገዱ ምን ፋይዳ አለው?» ብለው የሚጠይቁ ነበሩ፤ አሉም። ጥያቄው ልክና መሠረታዊ ስለሆነ ሊስተናገድ የሚገባው ነው።
ከዚህ አኳያ የዓይን ምስክር የሆኑትንና በውስጡም ተሳትፈውና ተጠቅመው ያለፉትን አቶ አስፋው ዳምጤን የምናገኝ ሲሆን እሳቸውም በ«ማህበራዊ ጥናት መድረክ» ህትመት (1998 ዓ.ም) አማካኝነት በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበረውን እውነታ ሲገልፁ ጃንሆይ ለጥበብና ፈጠራ ያላቸውን ፍቅርና ትጋት፤ ማበረታታት ከጠቀሱ፤ በአደጉት አገራት ለምሳሌ በእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሌለ የክበብ ዓይነት እንደሌለ ካስረዱ በኋላ «አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አባል ሆኜ ከመደበኛው ትምህርት ኮርሶች ያልተናነሰ ጥቅም ያገኘሁባቸው ሁለት ማህበሮች ነበሩ።
እነርሱም፣ በዶክተር ሳማ-ሐና ይመከርና ይደገፍ የነበረው፤ ፖኤትሪ ሶሳይቲ (የሥነ ግጥም ማህበር ወይም ክበብ) እና በሚስተር ሆይናስኪ መሪነት ይንቀሳቀስ የነበረው የኤንትሮፖሎጂ ሶሳይቲ ነበሩ።» (በርካታ ቁም ነገሮችንና አገራችን የነበረችበትን፣ ያለፈችበትንና አሁን ያለችበትን በውል ለመረዳት መጽሐፉን ማንበብ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመን ማለፍ እንፈልጋለን።) ይህን የአስፋው ዳምጤን ሀሳብ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምም የሚጋሩት ሲሆን በአንድ ወቅት የብሔራዊ ትያትር ንግግራቸው ይህንኑ በሚገባ ማብራራታቸው («አፍሪካ አፍሪካ አገራችን …» የሚለውን ዘመን አይሽሬ መዝሙር ማበርከቱን ጭምር) ይታወሳል።
ይህ ሁሉ ዛሬ የመንግሥት ብቻ ከ50 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ባሉበት አገር አንዱ ጋር እንኳን ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑ፤ ወይም እየተደረገ ካለም አለመሰማቱ ከመግረም አልፎ ቢያሳዝን የሚገርም አይሆንም።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ ይህ «ክበብ» ወይም «ክበባት»ን የተመለከተ እንቅስቃሴ ከመደበኛው ትምህርት (Curricular activity) እኩል ለመባል ምንም ባልቀረው ደረጃ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የተማሪዎችን መልካም ሰብእና ከመገንባት፤ እውቀትን ከማስረፅና የወደፊቱ ማንነታቸውን ከወዲሁ ፈልገው ከማግኘት አኳያ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ከአቶ አስፋው ምስክርነት መረዳት እንችላለን። በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደነ ኮከበ ጽባሀ ዓይነቶቹ በክበባት እንቅስቃሴ የትና የት ደርሰው እንደነበርም አስፋው አብራርተዋል።
«የፍልስፍና ክበብ» ከግለሰብ እስከ ዓለም ማህበረሰብ ድረስ የሰዎችን ንቃተ-ህሊና ማዳበርና ምክንያታዊና ኃልዮታዊ ትውልድን መፍጠር፤ እንዲሁም ሕይወትንና ተግባርን ከመመርመር አኳያ ፋይዳው ከዚህ መለስ የሚባል አይደለም። ለዚህም ነው በርካታ የአውሮፓና አሜሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፍልስፍና ክበባት መምሪያዎች (ጋይድላየንስ) ላይ የሶቅራጥስ ያልተፈተነ ሕይወት ከንቱ መሆኑን የምታስገነዝበው “The unexamined life is not worth living.” ሳትጠቀስ የማትታለፈው ብቻ ሳትሆን እንደ መርህም የምትከበረው።
ፍልስፍናን በክበብ ደረጃ በማዋቀር ፍላጎት ያላቸው እንዲሳተፉ ማድረግ ተገቢ መሆኑን የተገነዘቡ አገርና ዓለም አቀፍ ተቋማት በርካቶች ሲሆኑ አንዱም በዓለም አቀፍ ደረጃ የፍልስፍና ክበባትን መመስረትና መንቀሳቀስን የሚያበረታታውና በፋይናንስ ጭምር የሚደግፈው (UN) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት በድረ-ገፁ ላይ ካሰፈራቸው ተግባራት እና እንቅስቃሴዎቹ መካከል አንዱ ይኸው የፍልስፍና ክበባት እንቅስቃሴና ያሉበት ሁኔታ፤ እንዲሁም አጠቃላይ ፋይዳቸውን የተመለከተ ሲሆን ለተግባሩም አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታም እንደሚያደርግ የተገለፀው መልዕክት ነው።
ዩኤን እንደተገነዘበው የአሁኗ ዓለማችን ቀድሞ ከነበረችበት በሁሉ ነገሯ የተለየች ስትሆን አለመግባባቶች፣ ግጭቶች፣ የማንነት ጥያቄዎች፤ ባጭሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ ወዘተ ጉዳዮች በከፍተኛ ደረጃ እያወዛገቧት ይገኛሉ። ይህን ለመግታት ደግሞ መፍትሄው የነቃ፤ ምክንያታዊና በኃልዮት የሚመራ ትውልድን መፍጠር ሲሆን ይህ ሊሆን የሚችለው የፍልስፍና ክበባት በየአካባቢው ሲደራጁና ዜጎች እንደየፍላጎትና ዝንባሌያቸው በተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦች፣ እሳቤዎችና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነው።
ይህ አስተሳሰብ በአፍሪካም የነበረ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ሕዝቦችን በሙሉ ወደ አንድነት እንዲመጡ፤ እንዲሰባሰቡ ጥሪ የሚያደርገው «ኡቡንቱ» (Ubuntu) ፍልስፍና፤ መላው ጥቁር ሕዝብንና አፍሪካን ከነጭ የበላይነት ይላቀቅ ዘንድ ለትግል ያነሳሳው ኢትዮጵያዊነት (Ethiopianism) እና ሌሎች (Negritiued, Pan-Africanism, African Nationalism፣ አሁን በጠ/ ሚ/ር «የተዋወቀው»፤ እየተስተጋባ ያለውና ኢትዮጵያውያን ወደ አንድ መምጣት ያለባቸው መሆኑን የሚያሳስበው «መደመር» (“Synergy”)፤ እና ሌሎችም ያሉ ሲሆን፤ ይህ አገርን መሠረት ያደረገ ፍልስፍናም የራሱ የሆኑ ተግባራዊ መገለጫዎች አሉት።
ኢትዮጵያዊው «አገር ፍቅር ትያትር”፤ አገርና እናትን በአንድ የሚመለከተው ኢትዮጵያዊው አገርን የተመለከተና «እናት አገር» ወዘተ የመሳሰሉ አገላለፆች የአንድ አገር ፍልስፍና ከሚገለጽባቸው ጽንሰ-ሀሳቦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በየአገሩ ያለውን ከእሴት፣ ትውፊትና አገር በቀል እውቀቶች ጋር እያያያዝን ብንመለከተው ደግሞ ጉዳዩ ከዚህም ልቆ ነው የምናገኘው። (ባለፈው ሳምንት «ኢትዮጵያና ‘የፍልስፍና ወግ’ አቅጣጫዋ» በሚል ርእስ በዚሁ አምድ ላይ የወጣውን ጽሑፍ ይመለ ከቷል።)
በአደጉት ዘንድ «የፍልስፍናና ክበብ» (“Philosophy Group”, “Philosophy Association” ሌላም ሌላም በሚል የተቋቋሙም አሉ) ጉዳይ መሰረቱን ጥሎ፣ ተደራጅቶና አሳታፊነቱ ጎልቶ ነው የሚገኘው። በተለይ መሪና ሥርዓቱ በተቀያየሩ ቁጥር ፍልስፍናቸው አብሮ በማይቀያየርባቸው ሥልጡን አገራት እና ተቋሞቻቸው ውስጥ ክበቡ ስር ሰድዶና ተደላድሎ ለታሪክ ምስክርነት የበቃ ሆኖ የሚገኝ ሲሆን፤ ከእነዚህም አንዱ በሮያል የፍልስፍና ተቋም (The Royal Institute of Philosophy) የሚደገፈው የባርንስ ፍልስፍና ክለብ (The Barnes Philosophy Club) ተጠቃሽ ነው። (በነገራችን ላይ በዚህ በተደራጀ ክበብ በኦንላይን መሳተፍ ይቻላል።)
የአሜሪካው ኮሌጅ ኦፍ ሊበራል አርትስ (College Of Liberal Arts) የፍልስፍና ክበብ የክበቡን መጠነ ርእይና የክንውኑን የሽፋን አድማስ፤ አጠቃላይ ተፈጥሮን ዓይን ከሰበከት እያገላበጠ የሚመለከት፤ ውስጣዊና ውጫዊ ክፍሎችም ሳይቀሩ የሚበረብር መሆኑን “Philosophy club is a place where people get together to discuss issues ranging from inner space to outer space.”) በማለት የገለፀው ሲሆን ይህም በክበቡ ምንም የማይዳሰስም ሆነ የማይነካ፤ የማይተችም ሆነ የማይደነቅ፤ የማይመረመርም ሆነ የማይፈተሽ ነገር እንደሌለ ፍንትው አድርጎ ያሳያልና ከሌሎቹ ሁሉ የተነሳንበትን ርእሰ-ጉዳይ ስለሚያብራራልን በጥቅስ አስቀምጠነዋል።
በዚህ የፍልስፍና ክበብ ውስጥ የማይነሳ፤ ወይም የተከለከለ ነገር የሌለ ሲሆን በዋናነትም ሥነ ውበት፣ ሥነ ምግባር፣ ጥንታዊው ፍልስፍና፣ ዘመናዊ የየአህጉራት ፍልስፍናዎች፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ፍልስፍና፣ የሙዚቃ ፍልስፍና፣ እና እራሱ «ፍልስፍና ምንድን ነው?» የሚለውና የመሳሰሉት፤ እነ ፍራንሲስ ቤከንን የመሳሰሉ ሰብእናዎችና ሥራዎቻቸው ሁሉ በርእሰ ጉዳይነት ተነስተው ውይይትና ክርክር የሚደረግባቸው የእውቀት ዘርፎች በተለይም ክበቡን ከሌሎች ለየት የሚያደርገው እጅግ የተቃረኑ ሀሳቦች ያለምንም ችግር የሚስተናገዱበት መሆኑ ነው። (እዚህ ላይ ምናልባት እነዚህ ክበባት መፍረሳቸው በምትኩ ተማሪዎች ክበባቸው «ብሔር»፤ ተግባራቸው እርስ በ’ርስ መተላለቅ እንዲሆን አስተዋፅኦ አድርጎ ይሆን የሚል ጥያቄ ብጤ ሳያጭር አይቀርምና ጉዳዩ ያወያያል።)
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፍ አንድ አቢይ ጉዳይ ቢኖር ለፍልስፍና ክበባት መመስረት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ነው። በበርካታ ጥናቶች እንደተረጋገጠው በትምህርት ተቋማትም ይሁን በአካባቢና ሰፈር ሁሉም፤ በተለይም ወጣቶች በእንደነዚህ ዓይነት ክበባት (የሥነጽሑፍ፣ ጋዜጠኝነት – – – እና የመሳሰሉት) ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው። (መንግሥታትን አልጨመርንም፤ በተለይ የአፍሪካዎቹ «ይህን ዓይነቱን እንቅስቃሴ እንደ ድፍረት ይቆጥሩታል፤ የተናቁ አድርገው ሁሉ ያስቡታል» ይባላልና የእነሱን በሌላ ጽሑፍ መዳሰሱ የተሻለ ይሆናል።)
ከዚህ አንፃር አፄ ኃይለሥላሴ በዘመነ ሥልጣናቸው፤ በተለይም ለወርዱ ለአካባቢ በወቅቱ የአአዩ ተማሪዎች በእሳቸው ላይ ሲያሴሩ፤ በግልፅም በሥነጽሑፍ ሥራዎችና ሰልፎች፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የህትመት ውጤቶች አማካኝነት እሳቸውን ሲያብጠለጥሉ «ተዋቸው —» ማለታቸው «ከጊዜው የቀደሙ መሪ» እንዳስባላቸው ታሪክ ያስረዳል። ከእሳቸው ወዲህ ከመጡት ጋርም በንፅፅር እየታዩ የሳቸውን «የተሻለ» እሚሉም በርካቶች ናቸው።
ሌላው ምቹ ሁኔታ የፍልስፍና ክበብን ለማቋቋም የሚቋቋምበት ተቋም የግድ የፍልስፍና ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም መሆን የሌለበት መሆኑ ሲሆን በየትም ቦታና ተቋም ውስጥ ክበቡን አቋቁሞ መስራት መቻሉን እንደ አንድ ትልቅ መደላድል መውሰድ እንደሚቻል ከበርካታ ተቋማት ልምድ መረዳት ይቻላል።
ሌላው በከፍተኛና ዓለም አቀፍ (የትምህርት፣ የዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብቶች ወዘተ) ተቋማት ጭምር የሚበረታታና አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር የሚደረግለት መሆኑ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የጠቀስነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።
እንደ ዩኤን አተያይ ዓለማችን በነውጥ እየተናጠች የምትገኘው በዋናነት በማንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ነው። ይህ ደግሞ በቀጥታ ከፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ወዘተ ውስብስብ ዘርፎች ጋር ይያያዛል። ይህንን ችግር ለመፍታትም ሆነ ለመቋቋም ደግሞ ውይይቶች፣ ሙግቶች፣ ክርክሮች፣ እራስን ማወቅና ሌላውንም መረዳት ላይ ያተኮሩ የንቃተ-ህሊና መዳበርን የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች፣ አካባቢንና የዓለምን ሁኔታ መረዳትን፤ ካለፈው ትውልድ ጋር ልምድ መለዋወጥን ወዘተ ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ በየተቋማቱም ይሁን አካባቢዎች የውይይት ክበባትን ማቋቋምና እርስ በእርስ (በተለይም ወጣቱ)፤ ያለ ምንም ስጋት መማማር ይገባዋል። ለዚህ ደግሞ «የፍልስፍና ክበብ» ቀዳሚውና ከሁሉም በላይ አስፈላጊው አነስተኛ «ተቋም» ነው። በመሆኑም በማንኛውም አካባቢ «የፍልስፍና ክበብ» አቋቁመው እርዳታና ድጋፍን ለሚሹ ወገኖች ዩኤን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። (ለዝርዝሩ የተቋሙን ደንብና መመሪያ ይመርምሩ።)
ሌሎው «በክበቡ ምን ምን ተግባራት ይከናወናሉ?» የሚለው ሲሆን በአብዛኛው «በፍልስፍና ክበብ ከዚህ በመለስ የሚባል ነገር የለም» በሚለው የሚስማሙ ሀሳቦች ናቸው ያሉት። ይህ ማለት ግን ከደረጃ በታች የሆኑ ሥራዎችን ሁሉ ያካትታል ማለት አይደለም። የማይመጥኑ ሥራዎች የማስተማርም ሆነ ማወያየት አቅማቸው ብዙም የሚያወላዳ ባለመሆኑ ለዚህ ክበብ ይታጩ ዘንድ አይመከርም።
«የፍልስፍና ክበብ» እንደማንኛውም ክበብ (ምንም ዓይነት ልዩነትን በማያስተናግድ መልኩ የተሰባሰቡ) አባላት የሚመሰረት ሲሆን የሚመራውም ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በአባላቱ ነው። የፋይናንስ ድጋፍን በተመለከተም በራሳቸው ሲሆን በሰለጠነው ዓለም ባለሀብቶች በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።
ጥንት በእነሶቅራጥስ ዘመን መጀምሩ የሚነገርለትና ዘመናዊ ትምህርት እያደገ በመጣበት ፍጥነት ጎን ለጎን እየተስፋፋ የመጣው «የፍልስፍና ክበብ» ዋና አላማው የገባው፣ የነቃ፣ የተረዳና የተገነዘበ፤ እራሱን ያወቀ፣ ሌሎችንም የተረዳ፤ ከአካባቢውም ባለፈ የዓለምን አጠቃላይ ሁኔታ፣ ይዞታና እይታ የተገነዘበ ግለሰብ፤ ከዚያም ባለፈ ማህበረሰብ መፍጠር ነው። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ በተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ከመነጋገር፣ መከራከርና የጋራ ግንዛቤ ላይ ከመድረስ ጀምሮ የታላላቅ ፈላስፎችን ሥራዎች፣ የመንግሥታትን (እንደ ሕገ መንግሥት ያሉ) ሰነዶች፣ የፈጠራ ሥራዎችን በመነሻነት መጠቀም የአሰራር ዘዴው ሲሆን፤ «ዘር»፣ «ብሄር»፣ «ፆታ»፣ «ቋንቋ»፣ «ብሄረሰብ»፣ «እኩልነት»፣ «ዲሞክራሲ»፣ «ኃይማኖት»፣ «ፍትህ»፣ «እውነት»፣ «ሞራል»፣ «እሴት»፣ «ባህል»፣ «ሥነምግባር» እና የመሳሰሉ ጠንከርና ጠጠር ያሉ ጽንሰ ሀሳቦችን በመወያያ ርእስነት በማንሳት ተወያይቶ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነው። ይህ ከተቻለ ሲሆን ካልተቻለ ከእነልዩነት መጓዝ፤ በሂደትም ልዩነቶች የሚገቱበትንና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሂደትን በመከተል ወደ መግባባት መምጣት። በእዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ የሰው ልጅ ምን ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ/እድገትና የዳበረ ንቃተ ህሊና ባለቤት ሊሆን እንደሚችል ይታወቃልና ከዚህ በላይ ወደ ዝርዝር መሄዱ ስለማይበረታታ እዚሁ ላይ ገትተነዋል።
ባጠቃላይ፤ የፍልስፍና ክበብም ሆነ ሌላ ከላይ በአገራችን እንደነበረውና ተጠቃሚ የሆኑት (ከላይ የጠቀስናቸውን እነ አቶ አስፋው ዳምጤን ያስታውሷል) እንደሚናገሩት ፋይዳቸው ቀላል አይደለም። የአገር ታሪክ፣ የተሰወሩ እሴቶች፣ ያልተገለጡ የቆዩ የሥነጽሑፍ ሥራዎች፣ የአገርና ሕዝብ የአኗኗር፣ አሰራርና አስተዳደር ፍልስፍናዎች ወዘተ ሁሉ ተፈልገው የሚወጡት፤ ተመርምረው የሚደረስባቸው ከባለሙያዎች ባለፈ በእነዚህ ክበባት ነው። በመሆኑም ያስፈልጉናል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 5/2013