– ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር ፈረደ
በይበል ካሳ
ኢትዮጵያ አዲሱን የለውጥ ምዕራፍ ማጣጣም ከጀመረች እነሆ ሶስት አመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ዓመታት በርካታ አወንታዊና ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተለይ በሀገሪቱ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በተንሰራፋው ዘረፋና ሌብነት እንዲገታ፣ ቆመው የነበሩ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች በአዲስ መልኩ እንዲጀመሩ፤ አዳዲስ የልማት ውጥኖች ተግባራዊ እንዲሆኑና ሀገሪቱ ተስፋ እንዲኖራት ከማድረግ አንጻር ተስፋ ሰጪ ሥራዎች መከናወናቸውን ምሁራኑ ይገልጻሉ፡፡ ለ20 ዓመታት ተዘግቶ የቆየው የኢትዮ- ኤርትራ ግንኙነት በአዲስ መልኩ በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም የቻለውም ከለውጡ በኋላ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በተለይ ሀገራዊ አንድነትን ለመሸርሸር ለዓመታት የተሄደበትን መንገድ በመቀልበስ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ባለፉት ሶስት ዓመታት የተሄደበት ርቀት ከፍተኛ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በርካታ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በተለይ የህወሓት ጁንታ ጥሎ ያለፋቸው በርካታ የችግር የቤት ሥራዎች እየተመነዘሩ ሀገሪቷ ወደልማት እንዳትጓዝ እንቅፋት ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከዚሁ ኃይል ጋር የጥቅም ትስስር የነበራቸው እና የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎችም በኢትዮጵያ ላይ የፈጠሩት ጫና ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ግን ወደፊት መሄዷን ቀጥላለች፡፡ እኛም በነዚህና መሰል ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ከሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር ፈረደ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ ፓለቲካ እንዴት ይገለጻል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- በመጀመሪያ “ለውጥ” በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ አልስማማም። ምክንያቱም ለውጥ በፖለቲካል ሳይንስ በተለይም ንጽጽራዊ ፖለቲካ ለውጥ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ስናስተምር ነገሮች ሥር ነቀል በሆነ መንገድ እስካልተለወጡ ድረስ “ለውጥ” ሊባሉ አይችሉም። ነገር ግን ብዙ “ለውጥ” ከሚለው ደረጃ ላይ ከመደረሱ በፊት ብዙ ሂደቶች አሉ። ከ2010 ዓ.ም በኋላ አሁን በእኛ ሃገር ያለው “ለውጥ” እየተባለ የሚጠራውም ከእነዚህ አንዱ ነው ብየ አምናለሁ፤ እኔ በግሌ የተፈጠረው “ለውጥ” ሳይሆን “ታላቁ ተሃድሶ” ነው የምለው። ስለታላቁ ተሃድሶም ስናነሳም ቢሆን ምን ላይ ነው ትኩረት ያደረገው፣ ምን ምን ነገሮች ናቸው የተለወጡት፣ ድሮ የነበረው ምንድነው? ምንድነው የተቀየረው፣ የትኞቹ እሳቤዎች ወይም የትኞቹ ተቋማት ወይም የትኞቹ የአሰራር ሥርዓቶች ናቸው የተቀየሩት፣ ምን ውጤቶችን አምጥቷል፣ መዳረሻው ምንድነው፣ ወደምንስ እወሰደን ነው፣ የለውጥ ሂደቱስ አልቋል ወይ፣ ተቋማዊ መሰረትስ ይዟል ወይ የሚለው በጣም ሰፊና ጥልቅ ጉዳይ ይመስለኛል። በእኔ እምነት እነዚህ ሁሉ ነገሮች በሂደት ላይ ያሉ ናቸው ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡- “ታላቁ ተሃድሶ” ወይንም “ግራንድ ሪፎርም” በሚለውም ቢሆን ከእርሱ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ፓለቲካ እንዴት ይገለጻል? ከዚያ በኋላ ያለውስ? እስኪ በማነጻጸር ይግለጹልኝ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- ሪፎርሙ ትኩረት ያደረገባቸው ሦስት ነገሮች አሉ። አንደኛው የፓርቲ ሥርዓቱ ነው፣ ሁለተኛ የምርጫ ህጉ፣ ሦስተኛ የምርጫ ቦርዱ ናቸው። ዞሮ ዞሮ ግን ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ስናነሳ ስሪቱና ሥርዓቱ በሁለት ጎራዎች የተከፈለ ነው፤ በዘውጌ ብሄርተኝነትና በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት። ይህን መሰረት አድርገን ከለውጡ በፊትና በኋላ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስንመለከተው በዘውጌ ብሄርተኝነትና በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የተከፈለው እንቅስቃሴ አሁንም አለ፤ በአንዴ ሊጠፋ ሊሞትም አይችልም፣ የሚታወቅ ነው፤ አሁንም በህይወት አለ። እርግጥ ነው፣ ከለውጡ በፊት በነበረው ሥርዓት ተደፍቆ የነበረውና በአንዳንዶቹ እሳቤ ሞቷል ተብሎ ይታሰብ የነበረው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ወይንም ሃገራዊ ብሔርተኝነት ከለውጡ በኋላ እንደገና ተመልሶ እያንሰራራ መሰረትም እየያዘ የምናይበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህንን አንደኛው ለውጥ ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን። ምክንያቱም ከለውጡ በፊት በነበረው በዚያኛው ጠቅላይና አፋኝ አምባገነን ሥርዓት ውስጥ አብዛኛው የፖለቲካ አስተሳሰቡና ስሪቱ በዘውጌ ብሔርተኝነት ላይ ያተኮረ ነበር። ይህንንም “የማይታረቁ ህልሞች” የሚል ትርክት በመፍጠር የዘውጌ ብሔርተኝነቱን አስተሳሰብና አካሄድ ከኢትዮጵያዊው ብሔርተኝነት ወይንም ሃገራዊ ብሔርተኝነቱ ጋር ፍጹም የማይታረቁ አስመስሎ የሚያቀርብና በተቃርኖ ላይ የቆሙ አድርጎ በሚያስብ ትርክት ላይ የተንተለጠለ ነበር።
ከ2010 ዓ.ም በፊት ስለነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ስንነጋገር እንግዲህ ዋናው ነጥብ አፋኝ ነበረ የሚለው ነው። ወይንም ዲሞክራሲን በአፍጢሙ የደፋ ሥርዓት ነበረ የሚለው ነው ዋነኛው ጭብጥ። ፍትህ፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ የህግ የበላይነት… የዲሞክራሲን እሴቶች ብቻ እንዲህ አድርጓል፣ በዚህ በኩል ይህንን አድርጓል ብቻ ሳይሆን ከናካቴው ዲሞክራሲን በአፍጢሙ የደፋ ሥርዓት ነበረ። በአጠቃላይ የዲሞክራሲ ፕሮጀክት አንድ ቀን ይለወጣል ብለህ ምንም ነገር የማትጠብቅበት፣ ቅንጣት ተስፋ የማትጥልበት ተስፋ አስቆራጭ የተዘጋ ምዕራፍ ነበረ። ከዚህ አኳያ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ስለመጣው ስለሪፎርሙ ሂደት ስናወራ መጀመሪያ የምናነሳው የፖለቲካ መከፈት (Political liberalization) የምንለውን ነው። ይህም የሽግግር ተስፋን ይዞ መጣ። ከምን እንሸጋገራለን ያልን እንደሆን ከጠቅላይ አፋኝ አምባገነን ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንሸጋገራለን የሚል ተስፋ ይዞ መጣ። ተስፋው ወደ ተግባር እንዴት ይቀየር ሲባል “በፊት የነበሩትን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዋነኛ የሥርዓቱ መገለጫ ባህሪያት በመተው ራሴን አስተካክዬ ወደ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት አሸጋግራችኋለሁ” የሚል ሃሳብ ይዞ የለውጥ ኃይል የምንለው አካል ብቅ አለ ማለት ነው”። ይህ እንግዲህ የለውጥ ኃይሉ የተፈጠረበት ሂደት ነው። ከዚያም ሕዝባዊ እንቅስቃሴውም ዕምነቱን ሙሉ በሙሉ በለውጥ ኃይሉ ላይ ጥሎ፣ የነበሩትን ጥያቄዎች ለለውጥ ኃይሉ በአደራ አስረክቦ ወደ ዕለት ተዕለት መደበኛ እንቅስቃሴው ተመለሰ።
በዚህ ሂደት የተለያዩ ሪፎርሞች ተካሄዱ። የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ፣ የብሔራዊ ደህንነትን የመሳሰሉ ሪፎርሞች ተከናወኑ። አሁን እንግዲህ ስለ ለውጥ ለማውራት በዚህ ሂደት የተከናወኑ እነዚህ የሪፎርም ሥራዎች ምን ዓይነት ለውጥ አስገኙ? ድሮ ከነበረው በምን ይለያሉ? ምን ደረጃ ላይስ እንገኛለን? የሚሉትን ጉዳዮች ማየትና መመዘን ያስፈልጋል። ቅድም እንደነገርኩህ ሪፎርም ማለት ደግሞ ድሮ የነበሩ የመጫወቻ ህጎችን በአዲስ የመጫወቻ ህጎች መተካትና አሠራራቸውንም ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያ የፖለቲካ ለውጥን ስንመለከት ለምሳሌ የፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓትን ስንመለከት መሠረታዊ ለውጥ የለም። በብሔር “መደራጀት አይቻልም፣ በብሔር የሚደራጁ ፓርቲዎች ይህን ይህን ማድረግ የለባቸውም” የሚል አዲስ መሰረታዊ ህግ ወይም አሠራር አልመጣም። ድሮ የነበረው አሁንም እንዳለ ነው። ነገር ግን ቅድመ ሁኔታዎች መጥተዋል። አንድ የፖለቲካ ድርጅት የፖለቲካ ፓርቲ ተብሎ እውቅና እንዲያገኝ ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠዋል። ህጋዊ እውቅና የሚያገኙባቸውና ህጋዊነታቸው የሚረጋገጥባቸው ርምጃዎች ተወስደዋል። ይህም እንደፈለጉ በየመንደሩ እየተሰባሰቡ ሄደው ፈቃድ የሚያገኙበትንና በአንድ ሰው ብቻ እየተመሩ ፖለቲካ ፓርቲ ነኝ የሚሉ አካላትን የሚከስሙበትን ዕድል ፈጥሯል። ሆኖም አሁንም ቢሆን ያልተቀረፉ ችግሮች አሉ። በአንድ በኩል በዚህ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲነትን የማያሟሉ ድርጅቶች እየተራገፉ መሆናቸው መልካም ሆኖ እያለ በሌላ በኩል ግን ከሃገረ መንግስት እሳቤ በተቃራኒው የተደራጁና የህወሓት አስተሳሰብና ውርስ ያላቸው ለፖለቲካ ፓርቲነት የሚያበቃውን መስፈርት የማያሟሉና ስሙን ማግኘት የሌለባቸው ድርጅቶች እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተቆጥረው እንደ አዲስ በፖለቲካው እየተሳተፉ የሚገኙበት አሠራር ተፈጥሯል።
ከሁሉም…ከሁሉም በመልካም የሚታየው የሪፎርሙ አካል ግን ማናቸውም የፖለቲካ ተዋናይ ሃሳቡን የሚገልጽበት፣ የፖለቲካ ፕሮግራሙን የሚያንቀሳቅስበትን የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱ ነው። እዚህ ጋር ሥር ነቀል ለውጥ ባይባልም ብዙ መሻሻሎች አሉ። መሠረታዊ ነው ያላልንበት ምክንያት ይህን ያህል መሻሻል ቢኖርም አሁንም በፖለቲካዊ አቋማቸው የታሰሩ የህሊና እስረኛ የፖለቲካ ተሳታፊዎች ስላሉ ነው። የምርጫ ህጉን በሚመለከትም እንደዚሁ በርካታ መሻሻሎች ቢኖሩም የህገ መንግስቱን መሻሻል የሚጠይቁ ሁኔታዎች በመኖራቸው አንዳንዶቹ መሰረታዊ ጉዳዮች ደግሞ አሁንም በይደር የተቀመጡ ምንም ያልተነኩ ለውጥ የሚፈልጉ ነገሮች አሉ።
የምርጫ ቦርድን በተመለከተም በፊት ከነበረው በጣም የተሻለ ቁመና ላይ የሚያስቀምጠው መሻሻል በማድረጉ የለውጡ አንዱ አካል ሆኖ ሊጠቀስ የሚገባው ነው። በአጠቃላይ በፊት የነበረውን ሥርዓት አሁን ካለው ጋር ስታነጻጽረው የተወሰኑ መሻሻሎች ለውጦች አሉ። ነገር ግን ማስተዋል የሚገባን የሪፎርም ሂደቱ አሁንም ያላለቀ በሂደት ላይ ያለ መሆኑን ነው። በተለይም ለውጡን ተቋማዊ ቅርጽ በማስያዝ ረገድ ትልቅ ክፍተት አለ። እነዚህን መሰረታዊ ትንተናዎች ግምት ውስጥ አስገብተን “ለውጡ በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህል አምጥቷል ወይ? የሚለውን ጉዳይ ስንመለከተው በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለው ለውጥ ለማምጣት የተኬደበት መንገድና የተደረገው ሙከራ ነው። ከ1966 ዓ.ም አብዮት የፈነዳበት ከሚባለው ጊዜ ጀምሮ በሃገሪቱ ውስጥ የተከናወኑትን በደምና በኃይል ላይ የተመሰረቱና ሁሉን አጥፍቶ እንደ አዲስ ከዜሮ በመጀመር የሚያምኑትን ሥር ነቀል የለውጥ ሂደቶች አካሄድ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ቀስ በቀስ በሚመጣና የነበረውን እንዳለ በማጥፋት ሳይሆን መልካም መልካሙን ማስቀጠል በሚል አካሄድ ለመተካት መሞከሩ ነው። ነገር ግን ሙከራ ነው እንጅ ተሳክቷል የሚል እምነት የለኝም።
ሰላማዊ የለውጥ ሂደቱ እንዳይሳካ ካደረጉት ነገሮች መካከል በህወሓት ጁንታ አማካኝነት የተፈጠረውና የለውጥ ኃይሉ ወደተለመደው የኃይል አካሄድ እንዲገባ ያስገደደው ክስተት ዋነኛው ነው። በአጠቃላይ ግን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ለውጡን ተከትለው ከመጡ መልካም መሻሻሎች ጎን ለጎን ከውስጥና ከውጭ በተነሱ ችግሮች ከምንጊዜውም በላይ በፈተና ውስጥ ብትሆንም ሙሉ በሙሉ ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። በጨለማና በብርሃን መካከል ናት ብዬ አስባለሁ። ነገዋ ከጨለማው ባሻገር ከሩቅ በሚታይ ብርሃንም የታጀበ መሆኑ ይታየኛል።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ይነገራል። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋና ጉዳዮችን ቢጠቅሱልን፤
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- እነዚህን ተግዳሮቶች በተለያዩ ዘርፎች ከፍሎ ማየት ይቻላል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የአገር ውስጥ ፖለቲካው ነው። በአገር ቤት ፖለቲካው ውስጥ የበላይነትን አግኝቶ የቆየው ጠቅላይ አምባገነን አፋኝ ኃይል የአፋኝነት፣ የአልጠግብ ባይነትና ሁሉን ነገር ጠቅልሎ ለብቻ የመያዝ ባህል በሃገሪቱ ላይ ክፉ ውርስ ጥሎ አልፏል። ዴሞክራሲን በአፍጢሙ የደፋው የዚህ አፋኝ ኃይል ክፉ ውርስ አሁንም በሃገሪቱ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ሁኔታ በተለያየ መንገድ ሰፊ ቦታ ይዞ ቀጥሏል። የአፋኝ ኃይሉ ክፉ ውርስ ዛሬም በሁሉም አካባቢዎች በተቋማትና በሥርዓቱ ውስጥ በነበሩ ካድሬዎች ውስጥ ሰርጾ እንደቀረ ነው። አሁን ባለው የፖለቲካ ኃይል አስተሳሰብ ውስጥም በተለያየ መንገድ አስተሳሰቡ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል። ይህም ለአዲሱ የለውጥ አስተሳሰብ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ የብርሀን ኃይል የምትለው ወደ ለውጥ፣ ወደ ዴሞክራሲ፣ ወደ ትንሳኤ እመራለሁ የሚለው ኃይል አለ። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ግብግብ መሃል ነው የምትገኘው። ይኼ ግብግብ ደግሞ የውጭ ተፅዕኖ ጭምር እየደረሰበት ነው። እናም ሪፎርሙ አፋኝነትን አጥፍቶ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት እየሞከረ ቢሆንም ሂደቱ ቀጥተኛ ያልሆኑ ወይም ከዓላማው ጋር አብረው የማይሄዱ ያልተፈለጉ ውጤቶችንም እየፈጠረ ነው። ይህም የሪፎርሙ ህልም የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመትከል ቢሆንም በተግባር ስትሄድ ግን በሂደቱ በተፈጠሩ ያልተፈለጉ ውጤቶች የተነሳ ሃገሪቱን ከባድ ፈተና ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል። እንዲያውም ሃገሪቱ የቆመችባቸውን ምሰሶዎች እያነቃነቀ ነው። ሃገረ መንግስቱ የሚቆምባቸው አራት አምዶች የሚባሉትን እየሰበረም ጭምር ነው። በመሆኑም የሪፎርም ሂደቱ ይህን አቻችሎና የድሮውን አፋኝ አምባገነን የፖለቲካ ውርስ አስቀርቶ የሚፈልገውን አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚዋለድበትን ሁኔታ ለማምጣት የሚሄድበትን መንገድ ካሁኑ አስተካክሎ ካልቀየሰ ለሃገሪቱ ሌላ ችግር ይዞ ነው የሚመጣው።
ይሁን እንጅ ትግሉ እየተካሄደ ያለው አፋኙን አምባገነኑን የፖለቲካ ባህል እንዲቀጥል በሚሹና አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት በሚጥሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወይንም የለውጥ ኃይል በሚባለውና በአሮጌው የአፋኝ አምባገነን አስተሳሰብ መካከል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በሕዝቡና በሃገሪቱ መንግስታዊ ባህል መካከልም ነው። እንደምታውቀው በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ ያሉብን ችግሮች ሁለት ናቸው። ይኸውም የሃገረ መንግስት-ሕዝብ ተቃርኖ ነው። ማለትም በአንድ በኩል ጠንካራ መንግስት በሌላ በኩል ደካማ ሕዝብ መኖሩ ነው። እናም ሕዝቡ ሃገረ መንግስቱን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ አልቻለም፤ ሃገረ መንግስቱ በበኩሉ መሰረታዊ ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም፤ ሕዝቡን ማሸጋገር አልቻለም። አሁን ላይ እንደሚታየኝ ሕዝቡ ሃገረ መንግስቱን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እየታገለ ነው። ሉላዊነት የፈጠረለት ምቹ ሁኔታም ተጨምሮበት የፖለቲካ ምህዳሩም እየሰፋ በመምጣቱ ከታች ከመሰረቱ ጀምሮ ሕዝቡ ግዙፍ የፖለቲካ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። ስለሆነም የለውጥ ኃይል በሚባለው ብቻ ሳይሆን እንደ ሕዝብ በመሰረታዊ ደረጃ የሃገሪቱ ዋነኛ ችግር በሆነው የሃገረ መንግስት-ሕዝብ ግንኙነት ባህሉ ላይም ትግል እየተካሄደ በመሆኑ ፈተናው ምንም ያህል ቢከብድም በፖለቲካው መድረክ እየታየ ያለው ግዙፉ የሕዝብ ተሳትፎ ሃገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያሸጋግራታል የሚል ተስፋ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች መንስኤ ምንድነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- የችግሩ ዋነኛ መንስኤ የለውጥ ኃይል የተባለው አካል የችግሩን ፈጣሪ የችግሩ መፍትሔ አድርጎ ማሰቡ ላይ ነው። አንድን ችግር የፈጠረ አካል ተመልሶ የዚያ ችግር መፍትሔ ይሆናል ብሎ ማመን አንድን ዲ.ኤን.ኤውን የተበላሸ እንስሳ ወይም ህይወት ያለው ነገር የተበላሸውን ዲ.ኤን.ኤውን ማስተካከል ይችላል ብሎ እንደማሰብ የሚቆጠር ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ከለውጥ ኃይሉ ጋር በተያያዘ አንደኛውና ዋነኛው ችግርም ይኼ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም መጀመሪያውኑ የለውጥ ኃይል ነን ብለው ከተነሱት ኃይሎች ግማሾቹ መንገድ ላይ ቀርተዋል፣ ግማሾቹ አቋማቸውን ቀይረዋል፣ ግማሾቹ ችግሩ ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል፣ ሌሎቹ ችግሩን የተረዱበት ጥልቀትና ወደፊት የታያቸው ራዕይ የተወላገደ ነው፣ ቀሪዎቹ ብቻቸውን ቆመዋል። ስለዚህ አነሳሳቸው በደንብ ታስቦበት የተደራጀ አልነበረም። ልክ እንደ 1970ዎቹ ማለት ነው።
አሁን ላይ የምናያቸው ሁኔታዎች ሁሉ በ1970ዎቹ ተፈጥሮ ከነበረው ጋር ይመሳሰላሉ። በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ላይ የሚታው ደግሞ አጠቃላይ በትልቁ ዴሞክራሲን የሚመኝ ግን ደግሞ የዴሞክራሲን እሴቶች የማይተገብር ሆኖ ታገኘዋለህ። ለምሳሌ ፍትህን ብትወስድ ፍትህ ፍትህ እንድትሆን ለፍትህ ዋጋ የማይሰጥ ህብረተሰብ ታያለህ። በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት የኢህአዴግ መወገድ ማዕከላዊ ተደርጎ የነበረውን ግጭት ያልተማከለ እንዲሆን ስላደረገው ማህበረሰባዊ ግጭት ትመለከታለህ። መገለጫዎቹም ማህበረሰቡ ውስጥ ግዙፍ መፈናቀሎችን ታያለህ፣ ብዙ ጅምላ ግድያዎችን ትመለከታለህ። እነዚህ መሰረታዊ ችግሮች ናቸው። ከዚህ በተረፈ ግን ከላይ እንደገለጽነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋናውን ችግር የፈጠረው የአፋኝ አምባገነናዊ ስርዓቱ የአስተሳሰብ ውርስ ነው። ማለትም በሌላ አባባል እኔ “ታላቁ ተሃድሶ” ብዬ የጠራሁት የለውጥ ኃይል የሚባለው አሁን ላይ ለከፍተኛ ፈተና ያጋለጠውና ሪፎርም እንጅ ለውጥ ሊባል አይችልም እንድንል የሚያስገድደን እነዚህን ክፉ የአምባገነን ውርሶች ከሥር መሰረታቸው መንግሎ አለመጣሉ ነው፤ አሁንም አሉ እየቀጠሉ ነው። ለውጡ ኃይል ቀስ በቀስ በሂደት ይቀየራሉ በሚል አስተሳሰብ ነው የሚመራው። ነገር ግን እነዚህ ውርሶች መልሰው ራሱን እየፈተኑት ነው። የተጀመረውን ዴሞክራሲን የማዋለድ ምጥን በከፍተኛ ደረጃ እየፈተነ ያለውና የምጡን ጊዜ እንዲረዝም እያደረገ ያለው ከጨቋኝና አምባገነኑ አፋኝ ሥርዓት የተወረሱት የአስተሳሰብ ውርሶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የሠላም ማስከበሩ ዘመቻውና የዓለም አቀፉ ተፅዕኖን እንዴት ይመለከቱታል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- የውጭ ተጽዕኖ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ጅኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። የዓባይ ፖለቲካም በለው፣ የአፍሪካ ቀንድም በለው፣ የቀይ ባህር ፖለቲካም በለው ኢትዮጵያ በምታደርገው ዴሞክራሲን የማዋለድ የውስጥ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰበት መሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህ ሁለቱ የአፋኝ አምባገነናዊ ስርዓቱ የአስተሳሰብ ውርስና ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ጅኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ የመጣው የውጭ ተፅዕኖ የለውጡ ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው ብዬ እወስዳለሁ።
በእኔ ዕይታ ዓለም አቀፉ ተፅዕኖ የጀመረው ከህግ ማስከበር ዘመቻውም በፊት ጭቆናዎችና አፈናዎች እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የአምባገነኑን ሥርዓት ለመታገል ከተፈጠረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴና ተቃውሞ ጊዜ ጀምሮ ነው። የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ማስገባት የጀመሩት ያኔ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ተጥሎ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጀምሮ ነው። ከዚያ በኋላ በ2010 ዓ.ም ዶክተር አብይ ከተመረጠ በኋላ ደግሞ አጠቃላይ ከእነርሱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍላጎት በመነሳት በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት መንግስት ነው የሚመሰረተው የሚለውን ለመከታተልና ለእነርሱ በሚመች መንገድ ቅርጽ ለማስያዝ በማሰብና በተለይም ሃገሪቱን ወደ ሥር ነቀል ሊበራል ኢኮኖሚ ለመውሰድ ጣልቃ ገብነቱ ይሞከር ነበረ። ለአብነት አይ.ኤም.ኤፍና የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ የነበራቸውን ተፅዕኖ መዘንጋት የለብንም። በተለይም ቀጠናው ላይ አተኩሮ በቻይናና በአሜሪካ መካከል የሚደረገውና አዲሱ የዓለም የንግድ ጦርነት የሚባለው እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ ለተፅዕኖው መጨመር ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎቱ አመዛኙን ድርሻ ይይዛል። በቀጠናው ላይ በሁለቱ ኃያላን መካከል ያለው የንግድ ጦርነት እየተጠናከረ መጥቶ የቀዝቃዛው ጦርነት ዓይነት ቅርፅ እየያዘ ሲመጣ የቻይናን የንግድና የምጣኔ ሀብት ተፅዕኖ ከአፍሪካ ለመቀነስ በቀዝቃዛው ጦርነት ኮሚዩኒዝም ላይ እንዳደረጉት እነ አሜሪካ “መገደብ” የሚለውን ስትራቴጅ በስፋት መጠቀም በመፈለጋቸው ተፅዕኖው እያየለ መጣ። በዚህ ላይ አጠቃላይ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ አካሄድና በተለይም የባህረ ሰላጤው የአረብ ሃገራት በአፍሪካ ቀንድ በኩል የሚያደርጉትን ወታደራዊ ቀጠና የመመስረትና የማስፋፋት እንቅስቃሴ ለመገደብ እነ አሜሪካ በሚከተሉት ስትራቴጅ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ሃገራት ላይ የሚያደርጉት ተፅዕኖ ቀደም ብሎ የጀመረ ነው። በእርግጥ አሁን ላይ አይን አፍጥቶ በመውጣቱ አሁን የጀመረ ሊመስለን ይችላል እንጅ ተፅዕኖው የቆየ ነው። ከዓባይ ውሃ ጋር ተያይዞ የእነ ግብጽ የሚያደርጉት ተፅዕኖም የሚታወቅ ነው።
ሆኖም ፀረ ለውጥ ሆኖ በወጣው የህወሃት አፋኝ ቡድን ላይ በተወሰደው ህግ የማስከበር ወታደራዊ ርምጃ የቡድኑ የውጭ ክንፍ ሙሉ በሙሉ ያልተነካ በመሆኑ ከፍተኛ የጥቅምና የፖለቲካ ትስስር ፈጥሮባቸው ከነበሩ “የነጭ ጁንታዎች” ጋር በመሆን በሠራው ሰፊ የሳይበር ፕሮፓጋንዳና የቀድሞ ዲፕሎማቶችን በመጠቀም ባደረገው የገጽ ለገጽ ዘመቻ በፊት ከነበረው የበለጠ የውጭ ተፅዕኖ እንዲፈጠር አድርጓል። የመንግስት ዲፕሎማቶች የጁንታውን ያህል አለመስራታቸውም ችግሩን የራሱ የመንግስት ድክመት የፈጠረው ያደርጉታል።
ሌላውና ሁለተኛው ኮቪድ-19 በፈጠረው ከፍተኛ ተፅዕኖ የተነሳ የምዕራባውያን ምጣኔ ሀብት በከባዱ በመመታቱ እጃቸውን ወደ አፍሪካ በስፋት ማስገባታቸው አይቀርም። ከአፍሪካ ደግሞ በቅኝ ያልተገዛችውና የተፈጥሮ ሀብቷ በእነርሱ ያልተበዘበዘው ኢትዮጵያ በመሆኗ ለውጭ ተፅዕኖው የበለጠ ተጋላጭ እንድትሆን የሚያደርጋት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- የአሜሪካን ጣልቃገብነትና ወገንተኝነትስ እንዴት ነው የሚመለከቱት?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በስፋት ጣልቃ እንድትገባ እያደረጋት ያለው ምክንያት ህወሃት የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ለማጥፋት የፈጠረችውና አዝላ ቤተ መንግስት ያስገባቸው የራሷ ፍጥረት በመሆኑ እንዳይጠፋባት ስለምትፈልግ ነው። ሁለተኛ በአባይ ውሃ ላይም አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ፍላጎት የላትም ብሎ መደምደም አይቻልም። በጣም ሳይንሳዊ ይሆናል እንጅ በ “ቨርቹዋል ዋተር” እሳቤ መሰረት ማንኛውንም ምርት አምርተህ ወደ ውጭ ስትልክ ውሃ እየሸጥክ ነው። አሜሪካም በአባይ ተፋሰስ ሃገራት ላይ በምታካሂደው ኢንቨስትመንት በአባይ ውሃ ላይ የውሃ ፍላጎት አላት ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይህንንም ማየት ያስፈልጋል። ሦስተኛ የአባይ ተፋሰስ የላይኛው ሃገራት የሚባሉት በተለይም ኢትዮጵያና ሱዳን በአባይ ውሃ ላይ ከፍተኛ ግድቦችን እየገነቡና በከፍተኛ ደረጃ የግድብ ብሔርተኝነትን እየገነቡ በመሆናቸውና ይህም ምጣኔ ሀብታቸውን ትራንስፎርም እንዲያደርግ የሚያግዝ በመሆኑና ወደ ኃያልነት የሚያመጣቸው በመሆኑ ይህ ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍን ለዘላለሙ የሚቀይረው በመሆኑ ነው። ማለትም ግብጽ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የሚወሰነው ኃያላን ሃገራት በአባይ ሸለቆ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ በማድረግ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያና ሱዳን ኃያላን ከሆኑ ኃያላን አገራት ወደ አባይ ተፋሰስ ገቡ አልገቡ የሚለው ዋጋ ያጣል፤ የግብጽንም ዋጋ ያሳጣል። ለዚያም ነው አሜሪካ ለአፍሪካ ከምታደርገው እርዳታና ድጋፍ ስድሳ በመቶውን ለግብጽ የምትመድበው። ለእኔ አሁናዊ ግብጽ ሙሉ በሙሉ አሜሪካዊ ሰራሽ ናት። አሜሪካ ይህንን የምታደርገው ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያላትን ፍላጎት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ነው። እናም ግብጽ በአባይ ውሃ ላይ የሚኖራት በተዘዋዋሪ በአሜሪካኖች ብሔራዊ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያደርገዋል። በአጭሩ በቀጠናው እያደረገችው ያለው ተፅዕኖ ከውሃም በላይ የኃይል ፖለቲካን መሰረት ያደረገ ነው ማለትም ኢትዮጵያ በግድቡ ምክንያት በቀጠናው ኃያል ሆና ብትወጣ አሜሪካ ግብጽን ስለምታጣ ያን ለመቆጣጠር ነው በኢትዮጵያ ላይ ለግብጽ አድልታ የምትሰለፈው። የግብጽም ከዚህ የተለየ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ የፖለቲካ ምሁር ከላይ ለተነሱ በርካታ ችግሮች ምን አይነት የመፍትሄ ሃሳቦችን ይጠቁማሉ ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- ሁሉም አገር የራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ነው የሚሯሯጠው። የግብጽንም ሆነ የአሜሪካን ተፅዕኖ ለመቋቋም ኢትዮጵያም እጅግ ጥበብ የተሞላበት ዴፕሎማሲ መከተል ያስፈልጋታል። ሆኖም እውነቱን ለመናገር ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ምንም መስራት አልቻለችም፣ እንቅስቃሴዋ ዜሮ እየሆነ ነው ማለት ይቻላል። የጎረቤት ኬንያን የሰሞኑንና ባለፈው ጅቡቲ በአረብ ሊግ ያሳዩትን አቋም ለዚህ ማሳያ ይሆናል።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ወዳጆቿን አስጠብቆ ለማስቀጠልና ጠላቶቿን ደግሞ ተጽዕኗቸውን ለማኮላሸት በሚያስችል መንገድ፤ ቀጠናዊ ወይንም ጋርዮሻዊ በሆነ ሳይሆን ራሷንና የራሷን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር በሚያስችል መልኩ ፖሊሲዋን ከልሳ መተግበር ያስፈልጋታል። ለዚህም የቀይ ባህር ቀጠናን ወደ አንድ ለማምጣትና መተላለፊያውን በመቆጣጠር አንድ ሆኖ የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ ከአረብ ሰላጤ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ከባህልና ከፀጥታ በላይ በምጣኔ ሀብት ትስስር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር የመሰረተ ልማትና ኃይል ትስስር በመፍጠር በተለይም ደግሞ ሁለተኛውን የአፍሪካ ነጻነት ጉዳይ የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ እንዲሆን ጫና ፈጥራና ትኩረት አድርጋ በማንቀሳቀስ፣ በወዳጅና በጎረቤት ሀገራት ላይ ሳትተማመን ሁሌም የራሷን ጥቅም የሚያስጠብቅላትን ብልሃት የተሞላበት ስልት ነድፋ መንቀሳቀስ ይጠበቅባታል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፤
ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም