አስመረት ብስራት
ወይዘሮ ሳራ ዘመኑ በአሜሪካን ሃገር የሚኖሩ የህክምና ባለሙያ ናቸው። ወይዘሮ ሳራ የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ፤ ልጆቻቸውን በተገቢው መልኩ አሳድገው ለከፍተኛ ትምህርት ያበቁ ሴት ናቸው። የልጆች አስተዳደግ ላይ ቪዲዮዎችን እየሰሩ ህብረተሰቡን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያስተምሩት እኚህ እናት ሁለተኛ ፅሁፍ ለወላጆች ምክር ይሆን ዘንድ ያደረሱንን እነሆ።
ልጆቻችን ላይ ስም መለጠፍ በብዙዎቻችን ዘንድ በጣም የተለመደ ነው:: ለምሳሌ ከልጃችን ጋር መንገድ ላይ እየሄድን ከሌላ ሰው ጋር ስንገናኝ ልጁ ያገኘነውን ሰው ሰላምታ ከመስጠት ይልቅ የመሸሽ ዝንባሌ ሊያሳዬን ይችላል። በዚህ ጊዜ ለእንግዳው ሰው ምላሽ ለመስጠት ያህል “አዬ – ልጄ አይን አፋር ነው” ብለን ልጁ አይናፋር ባልሆነበት ሁኔታ “አይን አፋር” የሚለውን ስም እንለጥፍበታለን። እንደዚህ አይነት ልጅ ላይ ስም መለጠፍ ከባድ መዘዝ አለው።
ለሰው ሰላምታ መስጠት ያላስተማርናትን ልጅ እሷ “አይን አፋር” ናት እንላለን:: ወዲያ ወዲህ የሚሮጠውን ልጅ፣ እሱ “ቀዥቃዣ” ነው እንላለን። ተረጋግቶ ዝም ብሎ የተቀመጠውን ልጅ ደግሞ እሱ “ጅል” ነው እንላለን። ይህንን እና እነዚህን የመሳሰሉ መጥፎ ስሞች ልጆቻችን ላይ ስንለጥፍ ልጆቻችን ይሰሙና በተፈረጁበት ነገር ተወስነው ይቀራሉ።
ልጆች ወላጆቻቸውን ስለሚያምኑ እኛ የምንለጥፍባቸውን ስም አምነው ይቀበሉታል። ይህ ስም የመለጠፍ አባዜም በልጆቹ ላይ ከባድ መዘዝ ያመጣል። እኛ ልጄ ጅል ነው ስንል የሰማን ልጅ እኔ ጅል ነኝ ብሎ ማመን ይጀምራል። በዚህ መንገድ ልጁ ራሱን የሚያይበት መነጽር የተበላሸና የተዛባ ይሆናል። በእንደዚህ አይነት በተዛባ መነጽር እራሱን የሚመለከት ልጅ በህይወቱ ላይ ብዙ ጉዳት ይደርስበታል።
የዚህ የስም መለጠፍ መዘዝ በመጥፎ ስሞች ብቻ አይወሰንም። ጥሩ ናቸው ብለን የምንገምታቸውም ስሞች የራሳቸው መዘዝ አላቸው። ለምሳሌ በትምህርቷ ጥሩ የምትሰራውን ልጃችንን እሷ “ጎበዝ” ናት ብለን ስም እንለጥፍባታለን። ሌላውን ልጃችንን ደግሞ እሱ “ደፋር” ነው እንላለን። እነዚህ ጥሩ የሚመስሉ ስሞች ግን የራሳቸው መዘዝ አላቸው። ለምሳሌ ራሷን ጎበዝ ነኝ ብላ የምታምን ልጅ በትምህርቷ ችግር ሲገጥማት የስነልቦና ጭንቀት ውስጥ ልትወድቅ ትችላለች። ምክንያቱም ጥሩ ውጤት ካላመጣች እኛ ከለጠፍንባት ስም ያነሰች ስለሚመስላት። ልጃችንን አንቺ “ጎበዝ” ነሽ ብለን ስም ከመለጠፍ ፋንታ ግን “አንቺ በትምህርትሽ ጥሩ እየሰራሽ ነው፤ ምክንያቱም ጊዜሽን በሚገባ እየተጠቀምሽ ስለሆነ፣ የሚያስቸግርሽን አስተማሪሽን ስለምትጠይቂ ነው፣ ወዘተ” እያልን በዝርዝር ብናስረዳት ችግር ሲደርስባት ያንን ለማሻሻል ነው የምትሞክረው። በዚህም ለህይወቷ ሙሉ የሚጠቅም ትምህርት ሰጠናት ማለት ነው።
በአጠቃላይ እኛ ወላጆች ልጆቻችንን በምናሳድግበት ጊዜ ልጆቻችን ላይ ስም ከመለጠፍ ራሳችንን እንቆጥብ። ሌላም ሰው፣ አስተማሪንም ጨምሮ፣ ስም እንዳይለጥፉባቸው እንከላከል፡፡ ምክንያቱም ልጆቻችን እኛን ስለሚያምኑን የምንለጥፍባቸውን ስም እንደ እውነት ስለሚቀበሉት፡፡ ይህም ራሳቸውን የሚያዩበትን መነጽር የተዛባ ያደርገዋል፡፡ በልጆቻችን ላይም ብዙ ጉዳት ያስከትላል ሲሉ ወይዘሮ ሳራ መክረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2013