የገበጣ መጫወቻ ከመሰለው አስፋልት ዳር ቆማ ታክሲ እየጠበቀች ነው። ምንም ክረምት ቢሆን፣ ምንም የገበጣ ቆሬ ከመሰለው አስፋልት ላይ ውሃ ቢያቁር፣ አንድም ለካፊ ሾፌር ፣ ተሸቀዳድሞ እድፍ ውሃ አላከናነባትም። ይህም ስላልሆነ ክፉኛ አዘነች። ተብከነከነችም። እንደዚያ ‹‹ደግ ዘመን›› መለከፍ እንደቀረባት ዘግይታም ቢሆን ደረሰችበት።
‹‹ሴትን ልጅ ለካፊ ወንዶች እማይለክፏት በሶስት ምክንያት ነው›› ይላት ነበር መላኩ። ሰባተኛ ፍቅረኛዋ። ሾፌር ነበር። የላዳ ታክሲ ሾፌር።
መላኩ ሴትን ልጅ ለካፊ ወንዶች የማይለክፉበትን ሶስት አንቀጾች ሲዘረዝርም፣
አንቀጽ አንድ፣ ጠመንጃ አንጋች ከሆነች፤
አንቀጽ ሁለት፣ መነኩሴ ከሆነችና ፤
አንቀጽ ሦስት፣ ካራቲስት ከሆነች ነው ይላል።
(የባለታሪካችን ስም በዚች ያጭር አጭር ተረክ ላይ ቢነሳም ባይነሳም ምንም ስለማያመጣ በስምምነት እንተወዋለን)
እሷም ‹መላኩዬ አንተኮ ታክሲ ሳይሆን መንኮራኩር ነጂ መሆን ነበረብህ›፤ ትለው ነበር ስለሴት ልጅ አለመለከፍ ሶስቱን ምክንያቶች ተመራምሮ ስለደረሰበት።
ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን ለካፊዎች እሷን መልከፍ እንዳቆሙ ዕለቱንና ሰዓቱን በውል በማታስታውስበት ጊዜ አወቀች።
ለመሆኑ ለካፊዎቹ መልከፋቸውን ለምን አቆሙ? . . . በሰባተኛው ፍቅረኛዋ መላኩ መርህ መሠረት፣ ጠመንጃ ማንገት ጀምራ ነው? . . . አይደለም።
መንኩሳ ነው? . . . አይደለም።
ጁዶ ጀምራ ነው? . . . አይደለም።
ታዲያ ምን ሆና ነው? . . .
ሰባተኛው ፍቅረኛዋ መላኩ ያልደረሰበት፣ ወይም ሆን ብሎ ያልነገራት አራተኛ አንቀጽ ቢኖር ነው። አንድ ወደፊት የሚመጣ ሳይሆን ወደኋላ የሚሄድ የሚመስል ላዳ ታክሲ፣ ሲንገታገት መጣና አጠገቧ ቆመ።
አንገቱን በተከፈተው መስኮት አስግጎም ሾፌሩ፣ ‹‹ትሄጂያለሽ?›› አላት፣
አንዳችም ሳትመልስለት ወደኋለኛው በር አመራች።
በሩ አልከፈት አላት።
‹‹ቆይ እንደሱ አይደለም›› ብሎ ሾፌሩ በሲባጎ ገመድ የታሰረውን እጀታ ከውስጥ ሲስበው ተከፈተ።
ገባች።
ተቀምጣም ዙሪያገባዋን ትቃኝ ገባች። ታክሲዋ የቀበሌ ቤት ትመስላለች። ሾፌሩ የታክሲዋን ቤልት ቆርጦ ሱሪውን አስሮበት ሳይሆን አይቀርም ቤልቷ የለም። ወንበሩን እየነቀለ ቤቱም ይቀመጥበታል መሰለኝ አለቅጥ ወደኋላ ተለጥጦ ጥጋበኛ አስመስሎታል። የተቀመጠችበት ወንበር ተላልጦ፣ ስፖንጁ አፈትልኮ ስፕሪንግ ሽቦው ይታያል። ታክሲዋን ባዲስነቷም ባይሆን በጥሩ ይዞታ ላይ ሆና ታውቃታት ነበር። ሰባተኛው ፍቅረኛዋ መላኩ ነበር የሚሾፍራት።
መድረሻዋ እስክትደርስም ያቺ ታክሲ ከሰባተኛው ፍቅረኛዋ መላኩ ጋ ሳለች ያሳለፈቻቸውን አያሌ ትዝታዎች እንደማግ ጎልጉላ አወጋቻት። ትለከፍበት ስለነበረው ‹‹ደግ ጊዜ››
ቤቷ ስትደርስ አንገቷን ጉልበቶቿ ውስጥ ቀብራ ስቅስቅ ብላ አነባች።
አራተኛውን አንቀጽ ሰባተኛ ፍቅረኛዋ መላኩ ሳይሆን ይነዳት የነበረችው ታክሲ ነግራት ነበርና።
ቁሶች በርጅና መስታወታቸው ማርጀታችንን ሲያሳዩን እንደሰው ይሉኝታ አያውቁም።
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም