አስመረት ብስራት
ልጆች እንዴት ናችሁ። የመጀመሪያ ወሰነ ትምህርት ተጠናቆ ፈተና እየተፈተናችሁ መሆኑን አውቀናል። በደንብ አጥንታቸኋል አይደል? ጎበዘ ልጆች። ከፈተና በኋላ ባለችው አጭር ጊዜ ማንበብን መለማመድ አለባቸሁ እሺ። ለዛሬ በሀገራችን በጉራጌ ዞን ከሚነገሩ ተረቶች በካፒቴን ደጀኔ ዋሻካ የተተረከውን በዚህ መልኩ አቅርቤላችኋለሁ፤ መልካም ንባብ።
በአንድ ወቅት አንድ ድሃ ሰው ነበር:: ሰውየውም ወንድ ልጁ የአንድን ሃብታም ሰው ሴት ልጅ እንዲያገባ ፈልጎ ጋብቻውን ይጠይቃል:: ሃብታሙም ሰው የሰውየውን ድህነት አይቶ ከለከለው:: እንዲህ እያለም ይፈትነው ጀመር::
“እንቆቅልሾችን መፍታት ትችላለህ?” ሲለው ሰውየውም “አዎ፣ እችላለሁ::” አለ::
ሃብታሙም ሰው “እንግዲያውስ ሶስት እንቆቅልሾችን አሰጥሃለሁ:: መልሶቹን እስከ ነገ ድረስ እንድታመጣ::” ብሎ የሚከተሉትን ሶስት እንቆቅልሾች ጠየቀው፤
“አንድ ገበሬ ሶስት ላሞች ሲኖሩት አንደኛዋ ላም የምትታለበው በተለመደው ሁኔታ ቆማ ሲሆን ሁለተኛዋ ላም ግን ተንበርክካ ነው የምትታለበው:: ሶስተኛዋ ላም ደግሞ የምትታለበው ተኝታ ነው:: ይህ ምን ማለት ነው?”
ድሃው ሰውየውም ይህንን መመለስ አልቻለም::
“እስኪ ሚስቴን ልጠይቃት::” ሲል ሃብታሙም ሰው “እሺ ሄደህ ጠይቃት::” አለው::
ሆኖም ሚስቱም አልቻለችም:: በዚህ ጊዜ ሃብታሙ ሰው “ሄደህ ለሶስትና ለአራት ቀናት ጠይቀህ ለመምጣት ሞክር::” ብሎ በቀጠሮ ሲልከው ወዲያው አንዲት የእኔ ቢጤ ሴት መጥታ “ስለእግዚአብሔር፣ እባካችሁ የምበላው ነገር ስጡኝ::” እያለች መለመን ጀመረች::
ድሃውም ሰው “ለአንቺ ምግብ የምንሰጥበት ጊዜ የለንምና እባክሽ ሂጂልን:: የሃብታሙን ሰው እንቆቅልሽ ለመፍታት እየሞከርን ነውና ሂጂልን::” አላት::
የእኔ ቢጢዋም ሴትዮ “እንቆቅልሹን ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?” ስትላቸው እነርሱም “አንቺ ምስኪንና የምትበይው እንኳን የሌለሽ ድሃ የእኔ ቢጤ ነሽና እንቆቅልሹን እንዴት ልትፈቺ ትችያለሽ?” አሏት::
እርሷም “ግዴለም እመኑኝና ልስማው::” ብላ ተማፀነች:: ሰውየውም ነገራት::
እርሷም “ይህማ ቀላል ነው:: የመጀመሪያው፣ ላሟ የሃብታም ሰው ንብረት ናት:: ድሃ ሰው የሃብታሙን ሰው ላም ወደ ግጦሽ፣ ወደ ውሃና ወደመሳሰሉት ነገር እየወሰደ ይጠብቃታል:: ስትወልድም በማዋለድ ለሰራው ስራ የላሟን ወተት ለልጆቹ ይወስዳል:: ታዲያ ይህ ሰው አንድ ቀን ሃብታሙ ሰው መጥቶ ላሟን ይወስዳታል ብሎ ሁልጊዜ ይሰጋል:: ስለዚህም ነው ሃብታሙ ሰው ሳይወስዳት በችኮላ በቆመችበት የሚያልባት:: ሁለተኛው ሰው ደግሞ በከፊል እምነት ያለው ነው:: ሃብታሙ ሰው ላሟን ሊወስዳትም ላይወስዳትም ይችላል:: ምክንያቱም ላሟ የጋራ ንብረታቸው ናት:: ላሟን በጋራ ነው የገዟት:: ሶስተኛው ሰው ላሟ ተኝታ የሚያልባት ላሟ የራሱ ንብረት ስለሆነች ማንም ሰው መጥቶ አይወስዳትምና ተረጋግቶ በሠላም ያልባታል::” በማለት የእኔ ቢጤዋ ሴት ነገረችው::
ሆኖም ድሃው ሰው መልሱን ራሱ የማያውቀው መሆኑን ለሃብታሙ ሰው ነግሮት ስለነበረ የእኔ ቢጤዋን ሴት ወደ ሃብታሙ ሰው ዘንድ ይዟት ሄዶ መልሱን እርሷ እንደነገረችው ነገረው:: ሃብታሙም ሰው “ወንድ ልጅ አለሽ?” ብሎ ጠየቃት:: እርሷም “አዎ” አለችው::
እርሱም “ልጄን ለልጅሽ ነው የምሰጠው::” ብሏት የእኔ ቢጤዋ ሴት የሃብታም ሰው ቤተሰብ መሆን ቻለች።
ልጆች ጥበበኛ ሰው ሁሌም መጥፎ ነገሮችን ወደ መልካም እድል መቀየር ይችላል። እናንተም የጥበብ ሰው ከሆናችሁ መጥፎን በመልካም ነገር መለወጥ ትችላላችሁ። ስለዚህም ጉዟችሁ በጥበብ ይሁን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2013