ይበል ካሳ
ዘቢ ሞላ ሐድራ በጉራጌ ዞን ውስጥ ቀቤና ወረዳ ከዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የአንድ መቶ አስራ አንድ ዓመት ዕድሜ ጠገብ ታሪካዊ የሃይማኖት፣ የባህልና የቅርስ ማዕከል ነው፡፡ በ1902 ዓ.ም በታላቁ ሸክ ሱሩር ኦብዮ የተመሰረተችው የዘቢ ሞላ ሃድራ በመጀመሪያ የእስልምና ሃይማኖት ማዕከል ሆና አገልግላለች፡፡ የዘቢ ሞላ ሐድራ ጥንታዊ የታሪክ፣ የቅርስና የባህል ማዕከል መስራች የታላቁ ሸክ ሱሩር ኦብዮ የልጅ ልጅና የማዕከሉ አስተዳዳሪ የሆኑት ሸክ ሙሐመድ አሚን ሐጅ በድረዲን ከአንድ መቶ አስራ አንድ ዓመታ በፊት በአያታቸው የተመሰረተውንና ለአባታቸው የተላለፈውን ታሪካዊውን ቦታ እርሳቸውም ከአባታቸው ተቀብለው ቅርሱን ለትውልድ የማስተላለፍ ስራውን በኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
በዚህም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በመጣው በታሪካዊው የዘቢሞላ ሃድራ አሁን ላይ የተከፈተው ዘመናዊ የእስልምና ቤተ መጻህፍት ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሃድራው ከዚህ ቀደምም ትልቅ የእስልምና ማዕከል የነበረ መሆኑን የጠቀሱት ሸክ ሙሐመድ አሚን በታላቁ ሼክ ሃጅ ሱሩር መስራችነትና በአባታቸው ሐጅ በድረዲን አሁን ደግሞ በእርሳቸው አማካኝነት በትውልድ ቅብብሎሽ እስካሁኑ ዘመን ድረስ የተጠበቀውን የማዕከሉን ቅርስና ታሪክ የበለጠ አጠናክሮ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያግዝ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ለዚህም መንግስት በሰጠው ትኩረትና ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ብሔራዊ ቤተ መጽሃፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ላደረጉት ታሪካዊ ሥራ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ለሥራው ትብብር ያደረጉ ሌሎች አካላትንም አመስግነዋል፡፡ ታሪካዊ መዛግብቶችንና ቅርሶችን በዘመናዊ መንገድ በመሰነድና በማደራጀት በአንድ ሁለገብ የቤተ መጻህፍትና መዛግብት ማዕከል በማስቀመጥ የጀመረው ማዕከሉን የማዘመንና የማጎልበት ሥም የዘቢሞላ ሃድራን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ታላቅ የእስልምና ማዕከል ለማድረግ ለሚከናወኑ ቀጣይ ሥራዎች መሰረት የሚጥል ጅማሮ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የቀቤና ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብዱልመሊክ አብደላ የዘቢሞላ ሃድራ ከ1902 ዓ.ም ጀምሮ ከሰሜኑ ነጃሽ እስከ ዳና ያሉትን ስመ ጥር የሃገራችን የእስልምና ማዕከላትን በማስተሳሰር እንዲሁም የዕውቀት ማዕከል ሆኖ በማገልገልና በሸሪአ ዕውቀት ከማስተሳሰር በአሻገር በኦሮሞ፣ በቀቤና፣ በጉራጌና በወለኔ ሕዝቦች መካከል ማህበራዊና ሃይማኖታዊ አብሮነትን በማስተሳሰር ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ሚና ሲጫወት የቆየ ታሪካዊ ማዕከል ነው፡፡ በመሆኑም ማዕከሉ በውስጡ ካቀፈው ሰፊ የታሪክ፣ የቅርስና የመዛግብት ሃብት አኳያ የጥናት፣ የምርምርና የቱሪስት መስህብ ማዕከል ለማድረግ ያለሰለሰ ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም እንደ ሃገርም በተዋረድ በሚገኙ መንግስታዊ መዋቅሮችም ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡
በዚህ ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሃድራውን ዕምቅ የታሪክ፣ የቅርስና የመስህብነት አቅም በማጥናት ትውልድ ተሸጋሪ የታሪክ፣ የጥናትና ምርምር፣ የቅርስና የቱሪዝም መስህብ ማዕከል እንዲሆን በማሰብ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ ቤተ መጽሃፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተጀመረው ማዕከሉን የማዘመንና የማጎልበት ሥራ እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በዕለቱ የተመረቀው የዘቢሞላ ሁለገብ የጥናትና ምርምር ቤተ መጽሃፍት ማዕከልም የጥረቱ አንድ ፍሬ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ለሥራው ግብ መምታት የተቻላቸውን ያደረጉና በማድረግ ላይ የሚገኙ አካላትን፣ ተቋማትን፣ ምሁራንን፣ ሰራተኞችንና ግለሰቦችን አመሰግነዋል፡፡
በዘቢ ሞላ ሃድራ የቅርስና የመዛግብት ማዕከል ተምረው ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱ በርካታ ሸኮችና ኡለማዎች መካከል የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ሸክ ሱልጣን አማን አንዱ ናቸው፡፡ በእስላማዊው የቤተ መጽሃፍት ማዕከል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የታሪካዊው የዘቢ ሞላ ሐድራ ዕውቀት፣ ታሪክና ባህል ትኩረት ተሰጥቶት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመዝግቦ ዕውቅና እንዲያገኝ የማድረጉ ሥራ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የዘመናት ምኞት እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡
ይህንን የተገነዘበው የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ብሔራዊ ቤተ መጽሃፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ከሁለት ዓመታት በፊት ማዕከሉን በታሪኩ ግዝፈት ልክ መዝግቦ ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል ግዙፍ ዘመናዊ ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጦ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የዘገየ ቢሆንም አሁን ላይ በሃድራው ውስጥ ተገንብቶ ለምረቃ የበቃው ሁለገብ ዘመናዊ እስላማዊ ቤተ መጻህፍት የዚሁ ዕቅድ አካል በመሆኑ እርሳቸውን ጨምሮ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ከፍተኛ ደስታ የፈጠረ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ምክንያቱም የቤተ መጽሃፍቱ መገንባት በሃድራው ውስጥ የሚገኙ በርካታ ታሪካዊ መጻህፍቶችንና መዛግብቶችን መያዝ በሚገባቸው ልክ በዘመናዊ መንገድ ጠብቆ ለመያዝና ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ “የሁላችንም አባት የሆኑት ታላቁ ሸክ ሱሩር ኦብዮ ከአንድ መቶ አስራ አንድ ዓመታት በፊት ወደዚህ መጥተው የዘቢ ሞላ ሐድራን ከማቋቋማቸው በፊት በቦታው ምንም አልነበረም፤ አካባቢው ባዶ ጫካ ብቻ ነበረ” የሚሉት ሐጅ ሱልጣን፤ ከዚያ በኋላ ግን ዘቢ ሞላ የብዙ ነገሮች ማዕከል ሆና መመስረቷን ያስታውሳሉ፡፡ “ዘቢ ሞላ” ማለት በቀቤናኛ “የመድሐኒት መንደር” ማለት ነው፡፡ ይህም ከመስራቿ ሸክ ሱሩር ኦብዮ መድሐኒት አዋቂነት ጋር ተያይዞ ለመንደሪቷ የተሰጣት ስም መሆኑንም ነው የአካባቢው ተወላጅና የማዕከሉ ተማሪ የሆኑት ሸክ ሱልጣን የሚያብራሩት፡፡
በዚህም ሸክ ሱልጣን እንደሚሉት በማዕከሉ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ትምህርት ተካሂዶበታል፡፡ ከጉራጌ እስከ ስልጤ፣ ከስልጤ እስከ ሐላባ፣ ከባሌ እስከ አርሲና ጅማ ድረስ በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ውስጥ እስከ ከፍተኛው ደረጃ የደረሱ በርካታ ኡለማዎችና ኸሊፋዎች ከማዕከሉ የወጡ ናቸው፡፡ እነርሱም በበኩላቸው ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኡለማዎችን፣ ኡስታዞችንና ሼኮችን አስተምረው ለሃይማኖታቸው አበርክተዋል፡፡ በመሆኑም ዘቢሞላ ሃድራ በእስልምና የሃይማኖት ትምህርት ኢትዮጵያን ጫፍ እስከ ጫፍ ያዳረሰ ወሳኝ ማዕከል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ሁሉ ታሪካዊ ሃይማኖታዊ ትምህርት መጽሐፍትን በመጻፍ፣ ማእከሉን በመቋቋምና አስተማሪዎችን በማሰባሰብ የማዕከሉ መስራች የሆኑት ታላቁ ሸክ ሱሩር ኦብዮ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ሚና ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ መስራች የሆኑት ታላቁ ሸክ ሱሩር ኦብዮ የጻፉት “ኢፏደተሊፏን” የተባለ የተውሂድ መጽሐፍና ልጃቸው ሐጅ በድረዲን የጻፉት “ኢፋኸአልመአን” የተባሉ መጽሐፎች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ መጽሐፎቹ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው ለዓለም ሁሉ ደርሰዋል፡፡ “እናም የዘቢ ሞላ ሐድራ እንዲሁ ሲያይዋት ቀላል ትመስላለች ነገር ግን በእስልምና ውስጥ ትልቅ ታሪክ ያላት ትልቅ ቦታ ናት” ይላሉ የሐድራው መስራች ሸክ ሱሩር ኦብዮ ልጅ የሐጅ በድረዲን ደረሳ የሆኑት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸክ ሱልጣን አማን፡፡
በዘቢ ሞላ ሐድራ የታሪክና የቅርስ ማዕከል ውስጥ በተገነባው የ “ሸክ ፉትሁዲን ሁለገብ ዘመናዊ እስላማዊ ቤተ መጽሐፍት” የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርን ወክለው የተገኙትና መልዕክት ያስተላለፉት ወይዘሪት ሙሉእመቤት ጌታቸው ናቸው፡፡ እንደ ተወካይዋ ንግግር ኢትዮጵያ የበርካታ ዕውቀቶችና ሥነ ጽሁፎች ባለቤት ናት፡፡ እነዚህ ጽሁፎች በየዕምነት ተቋማቱ በገዳማቱና በየመስጊዱ እንዲሁም በየግለሰቦች ቤቶች ተበታትነው ይገኛሉ፡፡ “አባቶቻችን በየዘርፉ የነበራቸውን ዕውቀቶች፣ ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን በትጋት ጽፈው በሥርዓት ከትበው አስቀምጠውልናል” ያሉት ወይዘሪት ሙሉእመቤት ሆኖም ትውልዱ ይህንን ሃብት አውጥቶ ሊጠቀምበትና ትልልቅ ቁምነገሮችን ሊሰራበት አልቻለም፡፡ አባቶች የጻፏቸውን መጽሃፍትና መዛግብት በየዕምነት ተቋሞቻቸውና በየቤታቸው እንዲቀመጡ ያደረጉት ባላቸው ዕውቀት ተጠቅመው ከጥፋትና ከውድመት ጠብቀው ለማቆየትና ለትውልድ እንዲተላለፉ በማሰብ ነበር፡፡ ሆኖም ዘመኑ እየተለወጠ ሲመጣ ግን እንዲህ በተበታተነ መንገድ በየጓዳው ተቀምጠው የሚገኙ የጽሁፍ ሃብቶችን አውጥቶ ለመጠቀም አስቸጋሪ በመሆኑ ትውልዱ አባቶቹ ባስተላለፉለት ዕውቀት እንዳይጠቀም ምክንያት ሆኗል::
እናም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ቀደምት አባቶች ጽፈው ለትውልድ ያስተላለፏቸው ድንቅ ጥበብና ዕውቀትን የተሸከሙ የመጻህፍትና የመዛግብት ቅርሶች እየተጎዱና እየጠፉብን መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ “ይህም ልጆቻችን ትልቁን ዕውቀት በጉያቸው ታቅፈው፣ ወርቁን በእጃቸው ይዘው ሌላ ዕውቀት ፍለጋ ወደ ውጭ እንዲያማትሩ እያደረገብን ነው” ይላሉ፡፡ ስለሆነም በዛሬው ትውልድ ውስጥ የሚገኙ ታላላቆችና መንግስት ይህንን ሁኔታ የማስተካከል ግዴታ አለበት፡፡ ለዛም ነው ከዛሬ ሰባ ሰባት ዓመታት በፊት ገደማ ንጉሱ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ “ወመዘክር” በሚል የአሁኑን ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሃፍት ኤጀንሲ እንዲቋቋም ያደረጉት፡፡ ከላይ የተገለጸውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ለጥፋትና ለብልሽት ተጋላጭ በሚያደርግ ሁኔታ በየዕምነት ተቋማቱና በየግለሰቦች ቤት ተበታትኖ የሚገኘውንና አባቶች ለትውልድ ያስተላለፉትን የሃገሪቱን የዕውቀት ሃብት ጠብቆ አንድ ላይ አሰባስቦና አደራጅቶ ለትውልዱ ለማዳረስና የሃብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው ኤጀንሲው የተቋቋመበት ዋናው ምክንያት፡፡
በዚህ ረገድ ንጉሱ ባበረከቷቸው ጥቂት መጽሐፎች በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራ የጀመረው ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሃፍት ኤጀንሲ ጥንታዊ መዛግብቶችንና መጻህፎችን ከያሉበት በማሰባሰብና በአንድ ማዕከል ተጠብቀው እንዲቀመጡ በማድረግ ወደ ማዕከል መምጣት ያልቻሉትን ደግሞ በዘመናዊና በሳይንሳዊ መንገድ በያሉበት ተጠብቀው እንዲቀመጡ በማድረግ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የዘቢ ሞላ ሃድራ የታሪክና የቅርስ ማዕከልን በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት የታሰበውም ጥንታዊ ሃብትን በሥርዓት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍና ተጠቃሚ ማድረግ ከሚለው ከዚሁ የኤጀንሲው ዓላማ በመነሳት መሆኑን ተወካይዋ ያብራራሉ፡፡ ጥያቄው ቀድሞ የመጣው ከማዕከሉ መሆኑም የዘቢ ሞላ ሃድራን የሚያስመሰግንና ሌሎችም በአርዓያነት ሊከተሉት የሚገባ የሰለጠነ አካሄድ መሆኑንም ነው ወይዘሪት ሙሉእመቤት ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከሁለት አመታት በፊት ሙሉ ማዕከሉን በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡ ዋናው ግንባታ የዘገየ ቢሆንም በማዕከሉ ውስጥ የነበሩ ጥንታዊና ታሪካዊ መዛግብትና መጻህፍትን በማሰባሰብ ለትውልድ እንዲተላለፉና ትውልዱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ በአሻገር የጽሁፍ ቅርሶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመዝግበው እንዲተዋወቁና የቱሪስት መስህብም እንዲሆኑ የሚያስችል ዘመናዊ ሁለ ገብ እስላማዊ ቤተ መጽሃፍት ገንብቶ ማስመረቅ ችሏል፡፡
ይህም ለቀጣይ ሥራዎች ትልቅ እርሾ የሚጥል መሆኑን ነው የኤጀንሲው ተወካይ የጠቆሙት፡፡ ቤተ መጽሃፍቱ ከሃይማኖታዊ ይዘቶች በአሻገር የአካባቢው ማህበረሰብ ከዓለምአቀፍ የዕውቀትና ጥበብም ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርጉ፣ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች አጋዥና ማጣቀሻ ሆነው የሚያገለግሉ ሃምሳ ሺህ ብር የሚያወጡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጽሃፎችን ኤጀንሲው አበርክቷል፡፡
የቤተመጽሀፍቱ መገንባት ለእስልምና ሃይማኖት ከሚያበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እና በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከሚሰጠው ላቅ ያለ ዋጋ ባሻገር እንደ ሃገርም ቦታው ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የዘቢ ሞላ ሃድራ ጥንታዊ ታሪክና የባህል ማዕከል ለማዘመንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የተጀመረው ሥራና በማዕከሉ ውስጥ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ዘመናዊ እስላማዊ ቤተ መጽሃፍት ታሪካዊውን ስፍራ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2013