አዲስ አበባ (ኢዜአ)፡-የተመድ የአቢዬ ሰላም አስከባሪ ልኡክ የሆኑት ሦስት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የሞቱበትና ሌሎች የቆሰሉበት የሄሊኮፕተር አደጋ መንስኤ እየተጣራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የተመድ የአቢዬ ሰላም አስከባሪ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ገብሬ አድሃነ የአደጋው መንስሄ እየተጣራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
በሱዳን አቢዬ ግዛት የመንግሥታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ልኡክ አባል የሆኑትና ህይወታቸው በአደጋ ያለፈው ሦስት ኢትዮጵያውያን አስክሬን ኢትዮጵያ መድረሱም ታውቋል፡፡
በሰላም አስከባሪ ልኡክ አባላቱ ላይ አደጋው የደረሰው ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን፣ አደጋው የደረሰው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አባላትን ጭኖ የተለመደ እለታዊ ተግባሩን በማከናወን ላይ እያለ ሄሊኮፕተር በድንገት ተከስክሶ ነው።
በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ 10 የልኡኩ አባላት ላይም ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ክፉኛ ጉዳት የገጠማቸው ሦስት አባላት ለከፍተኛ ህክምና ወደ አዲስ አበባ መላካቸው ታውቋል። ሰባቱ ግን እዛው ህክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በስፍራው የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሰላም አስከባሪ ልኡክ አባላት ለአስከሬኑ የክብር ወታደራዊ ሽኝት እንዳደረጉለት ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኖዬ ጉታሬዝ ከትናንት በስቲያ 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተከፈተበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ለሞቱት የሰላም አስከባሪ አባላት የተሰማቸውን ኀዘን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ አወዛጋቢ በሆነችው የሱዳኗ አቢዬ ግዛት ወደ አራት ሺ 500 ያህል የሰላም አስከባሪ አባላትን በመንግሥታቱ ድርጅት አማካኝነት አሰማርታለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011