ክፍለዮሐንስ አንበርብር
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ግድቡ ግንባታ እየተከናወነና ድርድም እየተካሄደ ቢሆንም በርካታ እክሎች መፈጠራቸው አልቀረም። በተለይም ደግሞ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሆኑት ግብፅ እና ሱዳን በየጊዜው አቋማቸውን በመቀያየርና ድርደሩ ላይ እክል በመፍጠር ሁኔታውን እያወሳሰቡት ይገኛሉ። በእነዚህ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የምሥራቅ ናይል የቴክኒክ የቀጣና ጽሕፈት ቤት (Eastern Nile Technical Regional Office/ENTRO) ዋና ዳይሬክተር፤ በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ተደራዳሪ ከሆኑት አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ያደረገው ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- ያለፉትን 10 ዓመታት የድርድር ሂደቶች እንዴት ይገነዘቡታል?
አቶ ፈቅአህመድ፡- ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመታት ሞልቶታል። ግብፅ እና ሱዳን ስጋታቸውን ከገለፁ ጊዜ ጀምሮ በጣም በርካታ የቴክኒክ ውይይቶች እና በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። በሂደቱ በርካታ ውጣውረዶች ነበሩ። የመጀመሪያው የታችኛው የተፋሰስ ሀገራት የፈጠሩት ነው። በግብፅ በኩል የነበረውና የራሳቸው ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት የፈጠሩትና የነደፏቸው ስልቶች ዋንኛ ችግሮች ነው። በዚህ ላይ ሱዳኖችም አሉበት።
ሁለተኛው ችግር የራሳችን የኢትዮጵውያን ችግር ነው። ሀገር ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ እና የተቋራጮች በተለይ የሀገር ውስጥ ተቋራጭ ያስከተለው የሥራ መዘግየት የፈጠረው ችግር አለ። ከዚህ ውጭ ግን የሦስተኛ አካላት ጣልቃ ገብነት ማንሳት ይቻላል። እነዚህ በአንድ ላይ ተደማምረው የፈጠሩት ጉዳዩን በጣም ያወሳሰቡት መሆኑ ይታወቃል። ሀገራቱም ወደ ስምምነት እንዳይመጡ አድርጓል። አልፎ አልፎም ወደ አላስፈላጊ ቃላት መወራወር እንዲገቡ ነው ያደረጋቸው።
አዲስ ዘመን፡- በእነዚህ ውጣ ውረዶች ውስጥ የኢትዮጵያ የመደራደር ፍላጎት እና ሂደት እንዴት ይታያል?
አቶ ፈቅአህመድ፡- በኢትዮጵያ በኩል በተቻለ መጠን በቴክኒክ ውይይት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የቴክኒክ ጉዳይ እንጂ የፖለቲካ ወይንም የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ በግብጽ ጉዳዩ ወደ ፖለቲካ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ብሄራዊ ደህንነት እንዲሄድ የማጦዝ ሥራዎች ከተሰሩ በኋላ እነርሱን ሥራ ለማካተት በተወሰነ ደረጃ በኢትዮጵያ በኩል የፖለቲካ ሥራዎች ሲሰሩ የነበረ ሲሆን የዲፕሎማሲ ሥራዎች በዚያው ልክ ሲከናወኑ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ መጨረሻው አካባቢ ሦስተኛ አካላትን እንዲገቡ በመጋበዝ በግብጽ በኩል ጫና ከተፈጠረ በኋላ በተወሰነ ደረጃ ኢትዮጵያን የማትቀበለው ስለነበርና የሦስተኛ አካላት መግባት ሁኔታውን ስላወሳሰበው እንዲቋረጥ ተድርጓል።
በድርድሩ ላይ የነበረው ሁኔታ ውጣ ውረድ የበዛበት በጣም አስቸጋሪ፣ አሰልቺ እና እልክ አስጨራሽ ነበር። ሆኖም ግንባታው ላይ ምንም ጫና አልፈጠረም። በተለይም የግንባታው ሂደት ቢዘገይም ጥሩ እየሄደ ነው። ስለዚህ አሁንም እስከ ፍፃሜ ብቻ ብዙ መሰራት ይገባል። ህዝቡም ለሚጠብቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከግብፅ በድርደሩ ላይ ጫና ከመፍጠር በዘለለ ወታደራዊ የጦር ጉሰማዎች እየተሰሙ ነው። ይህ ምን ያመለክታል?
አቶ ፈቅአህመድ፡- ይህ በፊትም ይታወቃል። ወደኋላ ተመልሰን ለማስታወስ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትርት አቶ መለስ ዜናዊ የግብፆችን የጦርነት ጉሰማ አስመልክቶ ግንባታው ሲጀመር ግብጾች ዝም ብለው ይመለከታሉ ወይ ተብለው ከህዝብ እንደራሴዎች ፓርላማ ላይ ተጠይቀው እንደመለሱት ‹‹ዝም ብለው አይመለከቱም ያስፈራራሉ። ለዚህም መፍትሄው አለመፍራት ነው። አለመፍራት ማለት ደግሞ ገብቶ መተኛት ሳይሆን በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው ብለው›› ነበር። እንደተባለውም ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ወደ ስልጣን የመጡት የግብጽ መሪዎች የማስፈራራት ሥራ እየሰሩ ነው። በወቅቱ ግድቡ ሲጀመር ስልጣን ላይ የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ የራሳቸውን ጥረት አድርገዋል። እርምጃ እንወስዳለን ብለውም ነበር።
በመቀጠል ደግሞ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሙርሲ በተመሳሳይ እ.ኤአ ሰኔ 2013 ለደጋፊዎቻቸውም ባደረጉት ንግግር በግድቡ ግንባታ መካሄዱ አግባብ አይደለም ብለው ዛቻ አድርገው ነበር። አንድ ጠብታ ውሃ መቀነስ የለበትም ብለው ማስፈራራታቸው ይታወሳል። ከሁሉም በላይ ግን በተደጋጋሚ ፕሬዝዳንት አልሲሲ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ጦርነት ይነሳል ይላሉ። አሁን የሚታየው የዚሁ አካል ነው። ሰሞኑንም ይህ ነው እየሆነ ያለው። በእኛ በኩል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ነው። በሁሉም መልኩ ህብረተሰቡን ለግድቡ ማሰለፍ እና አንድነትን መፍጠር ነው። እኛ ከተጠናከርን የሚመጣ ነገር የለም። ስለዚህ ፈተናውን ከሆነ የሚመጣውን ሁሉ በፅናት ማለፍ አለብን።
ምናልባት የሚመጣው የዲፕሎማሲ ጫና እና በሦስተኛ አካል ጫና መፍጠር ነው። በኢኮኖሚ ረገድ ብድር ማስከልከል እና በሌሎች ሀገራት የኢትዮጵያን ሥም ማጠልሸት ነው። እነዚህን ከግምት ውስጥ በማስገባትና ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ስልትና ታክቲክ ቀይሶ መንቀሳቀስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ግብፅ እና ሱዳን ሰሞኑን ለሁለተኛ ዙር ጊዜ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ይታወቃል። ነገሩን ወደ ከረረ አዝማሚያ የመውሰድ ፍላጎት ይኖራቸው ይሆን?
አቶ ፈቅአህመድ፡- ይህ የማስፈራራት አንዱ አካል ነው። ከዚህ ያለፈ ወደ ሌላ ነገር ይሄዳሉ የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ‹‹በዓለማችን ላይ ውሃ እሳት ሲያጠፋ እንጂ እሳት ሲያቀጣጥል አይተን አናውቀም።›› እንዲሁም በውሃ ላይ ያለ ልምድ እንደሚያሳየው የውሃ ፍጥጫ ፍቅርና ትብብር ጎን ለጎን ይሄዳሉ። በትይዩም ይሄዳሉ ይባላል። መጀመሪያ ሀገራት ኃይለ ቃል ይለዋወጣሉ፤ ወደ ፍጥጫና ወደ ሃሳብ ግጭት ያመራሉ። ከዚያ ወደ ድርድር ይመለሳሉ። ወደ ሠላም መምጣት አይቀሬ ነው። ኃላፊነት የጎደለው መሪ ካለ እና ታሪክ የማያውቅ ከሆነ አዋጭነቱን መተንተን ነው። በዚያ መንገድ ከታሰበ ዘርፈ ብዙ ችግር ያመጣል። በፖለቲካ፣ ድፕሎማሲ እና ኢኮኖሚው አዋጭነቱን ያልተነተነ እና ወደፊት ይህ ጉዳይ የሚያስከትለውን ችግር ካለገናዘበ ወደ ግጭት ማምራት ይችላል። ነገር ግን እኛ ወደዚያ እናመራለን ብዬ አላስብም። 99ነጥብ9 በመቶ ይህ የመሆን ዕድል የለውም። ምናልባት 0ነጥብ1 በመቶ ሥራ ላይ ቢያውሉና ወደዚያ ከገባን እንኳን የውሃ ፍሰት አቅጣጫ መቀየር እንደማይችሉ ማወቅ አለባቸው። ግጭት በሀገራቱ መካከል ያለውን መረዳዳት ለአንዴ እና መጨረሻ ጊዜ ስለሚቀይረውና በተግባራቸው የዕድሜ ልክ ሰለባ ስለሚሆኑ ይህንን ደግሞ ጠንቅቀው ሊያውቁ ስለሚችሉ ወደዚያ ይሄዳሉ የሚል እምነት የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያው የግድቡ ግንባታ ሂደት ከኢትዮጵያ ተቀራራቢ ሃሳብ የነበራት ሱዳን አሁን የአቋም መለዋወጥ እና ወደ ግብጽ ማዘንበል ከምን የመነጨ ነው?
አቶ ፈቅአህመድ፡- ይህንን በተለያየ አቅጣጫ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው አሁን ሱዳን ውስጥ አዲስ መንግስት ነው የመጣው። ከኦማር አልበሽር መንግስት በኋላ ወታደራዊ ስልጣን መንግስት ላይ አለ፤ ከጎን ያለው ሲቭል መንግስት ቢሆንም ሁለቱ አልተጣጣሙም። ሲቪል መንግስቱ ብዙም ጥርስ የለውም። ወታደራዊ ደግሞ ወደ ግብፅ ነው ማዘንበል የፈለገው። ወታደራዊ መንግስት ነገሮችን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫና መስመር መቀየሩ እና የአልበሽርን ሥራዎችና አካሄድ ማጠልሸትና ማዳከም ነው። ሱዳኖች ከግብፅ ደግሞ ብዙ ድጋፍ አግኝተዋል። ግብፅ ሱዳን እያስተዳደረ ለሚገኘው ወታደራዊ መንግስት ብዙ ቁሳዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል። ስለዚህ አሁን የመጣው መንግስት በግድቡ ላይ ያለውን አቋም ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር ተገዷል።
ሁለተኛው በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ሲሠሩ የነበሩ ባለሙያዎችን ጭምር ከድርድር እና ሥራው እያስወጡ ነው። እንደ አዲስ ሌላ ሥራ መጀመርና የኦማር አልበሽር ሥራ ማዳከም ላይ ተጠምደዋል።
ሦስተኛው የሱዳን መንግስት ከምዕራቡ ጋር ያለውን ፍጥጫ አቁሞ ወደ እርቅ መሄድ ይፈልጋል። ቀደም ሲል ሱዳንን ያስተዳድር የነበረው የአልበሽር መንግስት ኢትዮጵያ ከምዕራብውያን ጋር ያለኝን ችግር ለማቃለል ታግዘኛለች የሚል አቋም ነበረው። አሁን ያለው መንግስት ደግሞ ከምዕራባውያን ጋር ያለውን ችግር ለማቃለል የምታግዘን ግብፅ ናት ብለው አምነዋል። ስለዚህ ከግብጽ ጋር ለመወዳጀት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነታቸውን አሻክረው ከግብጽ ጋር ወግነዋል።
ከአሜሪካ ጋርም ይያዛል። ለረጅም ዓመታት በሱዳን ማዕቀብ ጥላለች። በድርድሩ ወቅትም የአሜሪካን አቋም የመደገፍ ፍላጎት አለ። ሱዳን ይህ ማዕቀብ እንዲነሳላት በግብፅ በኩል መሄዳቸውም ነው። በዚህ ውለታ ደግሞ ግብፅ የጀመረችው ሴራ ሱዳንን ከኢትዮጵያ የመነጠል ሁኔታ ነው የጀመሩት። እ.ኤ.አ 2015 ላይ የአሜሪካ መንግስት ጊዜያዊ ሥምምነት ይፈጠር ሲል መጀመሪያ ተቃውማ የነበረችው ሱዳን ነበረች። ቀደም ሲል ከሱዳን ጋር በብዙ ነገሮች ላይ አብረን እንሰራ ነበር። ሁለንተናዊ ግንኙነቶች ነበሩን። ግድቡ ላይ ሰለማዊ ድርድር እንዲኖርም ሱዳን የራሱ በጎ ሚና ነበራት። አሁን ያኔ የነበረው ተቀዛቅዞ ከሆነ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ድርድር በሠላማዊ እና የኢትዮጵያን ጥቅም ባስጠበቀ መንገድ እንዲጠናቀቅ ምን መደረግ አለበት?
አቶ ፈቅአህመድ፡- ድርድር ውስጥ ገብቶ በአሸናፊነት መውጣት የሚለው በአሁኑ ጊዜ እየተዳከመ የመጣ አስተሳሰብ ነው። ድርድር ውስጥ ሁሉም አካል አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት መንገድ ነው የሚታሰበው። ቀደም ሲል የነበረው ማንኛውንም ስልት ተጠቅሞ አሸናፊ መሆን ነበር። ይህ ግን የተደረሰበትን ውጤት ዘላቂ ስለማያደርግ በተቻለ መጠን ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ የድርድር መርህ መከተል ይገባል።
በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተደረገው ድርድር አለ። ያንን ቆም ብሎ ማየት አለብን። ቆም ብሎ መገምገም ያለበት ይመስለኛል። ድርድሩ የተጠበቀውን ያክል ርቀት ሄዶ ውጤት ሊያመጣ የቻለ አይመስለኝም። ለዚህ በአብዛኛው ተጠያቂው የታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት ናቸው። እኛም የመጣንበት መንገድ ቆም ብለን ገምግመን አዲስ የድርድር ስልት መቀየስ አለብን ብዬ አስባለሁ። አዲስ የድርድር ስልት ማለት ቀደም ሲል የያዝናቸውን አቋሞች ማየት አለብን። መሰረታዊ ፍላጎታችን፣ የድርድር ታክቲኮቻችን፣ እቅዶቻችን፣ የተደራዳሪ ቡድኖችን ከገመገምን በኋላ አዲስ ስልት፣ አቋም፣ አዲስ መሰረታዊ ፍላጎታችን፣ እቅድ እና ቡድን ይዘን የተለያዩ አማራጮችን ይዘን ወደ ድርድሩ መግባት አለብን።
ይህን ለማድረግ ደግሞ የድርድሩን ተሳትፎ ማስፋት፣ በተቻለ መጠን ሁሉንም ማካተት፣ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎችን እና በሂደት የሚማሩ ተደራዳሪዎችን ማደራጀት እና ሌሎች በርካታ መደራደሪያ ስልቶችና አሰራሮችን መከተል ይገባል። እነርሱ የሚሄዱበትን አካሄድ ቀድሞ መተንበይና መዘጋጀት፣ ትኩረት ውስጥ የከተቱ ስልቶችን በየጊዜው እየቀያየሩ መዘጋጀት አስፈላጊ ነው። መዘናጋት አያስፈልግም። በጉዳዩ ላይ ሁሉንም ያካተተ ድርድር መካሄድ አለበት። ሌላው ቀርቶ ግድቡን የሚቃወሙም አካላት ካሉ እነርሱን ያካተተ ውይይት በማካሄድ በግድቡ ዙሪያ አንድነትን መፍጠርና ህዝብን ማሰባሰብ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አቶ ፈቅአህመድ ለሰጡኝ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ።
አቶ ፈቅአህመድ፡- እኔም አመስግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም