ለምለም መንግሥቱ
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በኢትዮጵያ በነበረው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ብዙ ሥራ በሳንካዎች የተሞላና ሀገሪቱንም በሚፈለገው የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ላይ እንዳላደረሳት በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።እየተንከባለለ የመጣው ችግርም ሀገራዊ ለውጡ ላይ ጫና ማሳደሩ ይታወቃል።ያለፉት የኢኮኖሚ ችግሮች በሀገራዊ ለውጡ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ፣ባለፉት ሶስት የለውጥ አመታት በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ በምክትል ሚኒስትር ማዕረግ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ከዶክተር ነመራ ገበየሁ ጋር ቃለምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡– ዶክተር ነመራ፤በቅድሚያ እን ዲያብራሩልን የምንፈልገው አንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች የሚባለው ምን ምን ሁኔታዎችን አሟልታ ስትገኝ ነው?
ዶክተር ነመራ፡– የመጀመሪያው ነገር ዕድገትን ማረጋገጥ ወይንም ማስቀጠል መቻል ነው።እድገት ብዙ ጊዜ ቁጥር ላይ ያተኩራል።ይሄ ማለት በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ምርት በአንድ አመት ውስጥ በምን ያህል አደገ የሚባለው ሲሆን፣በሌላ አነጋገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሀገር ገቢ እንደማለት ነው።ይሁን እንጂ እነዚህ ዕድገቶች በራሳቸው በቂ አይደሉም።በመቶኛ ወይንም በቁጥር ብቻ መግለጽ ኢኮኖሚ አደገ ለማለት አያስችልም።ዕድገቱ ወደ ልማት ምን ያህል ተቀይሯል የሚለው ነው መታየት ያለበት።የአንድን ሀገር የዕድገት ስኬት የሚያረጋግጠው ይሄ ነው።ይሄንን በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል።
አንዳንድ ድህነት ውስጥ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አካባቢ ድህነትን በፍጥነት መቀነስ የሚችል መሆን መቻል አለበት።በሥራ ዕድል ፈጠራም ይሁን በተለያየ መንገድ ድህነትን መቀነስ የሚቻልበትን ሥራ መሥራት ይጠበቃል።በተሰራው ሥራ ዕድገት እያመጣን ነው ወይንስ እያመጣን አይደለም የሚለው መታየት አለበት።የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠይቃል።ስለአንድ ኢኮኖሚ ሲወራ ድህነትን መቀነስ ብቻ አይደለም።የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት በጤና፣በትምህርት፣በመንገድና በሌሎችም የመሠረተ ልማት ሥራዎች በማስገኘት አረጋግጦልናል የሚለው ወሳኝ ነው።የመጣው የኢኮኖሚ ዕድገት ሰው የሚፈልገውን የሥራ ዕድል ፈጥሮለታል የሚለው እንዳለ ሆኖ የዜጎችን የተለያየ ፍላጎት ማሟላት የቻለ መሆን ይኖርበታል።የአንድ ሰው ገቢ ወሳኝ ቢሆንም ግን ዋና መለኪያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
በሁለንተናዊ መልኩ ሲታይ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ወደ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቱ መቀየር ወይንም ትራንስሌት መሆኑ ሲረጋገጥ ነው የአንድን ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት በሙሉ ዕይታ መለካት የሚቻለው።ዕድገት ቁጥር ነው።በዚህ ብቻ ማረጋገጥ አይቻልም ስለዚህ የአንድ ሀገር ገቢ ከአመት አመት ያለው ምርት ዕድገት በገበያ ዋጋ ሲለካ ያለው ለውጥ መታየት አለበት።
አዲስዘመን፡– የኢኮኖሚ ዕድገቱ በዚህ መልኩ የሚገለጽ ከሆነ ከለውጡ በፊት በነበረው ተከታታይ አመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመስፈርቱ ሲመዘን በምን አይነት ሁኔታ ላይ ነበር ለማለት ይቻላል ? ዕድገቱ በዜጎች የኑሮ ደረጃ ላይ ለውጥ ያመጣ ነበር ?
ዶክተር ነመራ፡– ከለውጡ በፊት በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ መልካም የሚባሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንጻር ስትታይ ትልቅ የሚባል ዕድገት በኢኮኖሚው ስታስመዘግብ ቆይታለች።ይሄ መካድ የለበትም።ዕድገቱን ለማስቀጠል ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል።ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ዕድገት በአሀዝ ብቻ መለካት የለበትም።በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሚባል ክፍተት ነበር።ለዕድገቱ ምንጭ የሆኑት መሠረተ ልማት ሥራዎች በስፋት ተከናውነዋል።ዕድገትም ነበር።ነገር ግን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አልነበረም።ይሄ ክፍተት ነው።ምርትና ምርታማነት አድጎ የዜጋውን ኑሮ በሚያሻሽል መልኩ፣ለሁሉም ዜጎች የሥራ ዕድልን በሚፈጥር፣ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ፣የሚታየውን የዋጋ ንረት በሚቀርፍ ሁኔታ የመጣ የኢኮኖሚ ዕድገት አልነበረም።ጥራት የጎደለው ዕድገት ነው የነበረው።ዕድገቱን ማስቀጠል አለብን።ግን እንዲቀጥል የሚፈለገው ዕድገት ጥራት ያለው መሆን አለበት።የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በተለይም በኑሮአቸው ላይ የሚታይ ለውጥ የሚያመጣ መሆን መቻል አለበት በሚል ነው የአስር አመቱ ዕቅድ የተዘጋጀው ።
አዲስ ዘመን ፡– ያለፈው የኢኮኖሚ ዕድገት ክፍተቶች ከነበሩበት፤ በዜጎች የኑሮ መሻሻል ላይ ለውጥ ካላመጣ እንደሀገር በሁለት አሀዝ ዕድገት እየተመዘገበ ነበር እየተባለ ሲነገር ከነበረው ጋር እንዴት ይጣጣማል?
ዶክተር ነመራ፡– ዕድገት ከሌሎች ልማት ቀጥሎ አይመጣም።በሌላ አነጋገር አንድ ሀገር ገቢው ካላደገ ዕድገት የለም።ገቢውን ወደ ኢንቨስትመንት የሚቀይረው።የኢኮኖሚ ዕድገት ማለት ይሄ ነው።ከአመት አመት በሚለካው አመታዊ የተጣራ ሀገራዊ ምርት (ጂዲፒ) በኢትዮጵያ እውነቱን ለመናገር የኢኮኖሚ ዕድገት ነበር።ያንን ዕድገት ወደ ልማት መቀየር የሚለው ነው ክፍተቱ።መሠረተልማት እንደተዘረጋው ሁሉ በግብርናው፣በኢንደስትሪ፣ማዕድንና ቱሪዝም ዘርፎች ላይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቂ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ አልቆየም ማለት ነው።የሥራ ዕድል ፈጠራ፣የዋጋ ማረጋጋት ከመሰረተ ልማት መዘርጋት ጋር አይያያዝም።
የኢኮኖሚ ዕድገቱ በቀጥታ የሚያያዘው ምር ትና ምርታማነትን ከማሳደግ ጋር ነው።አንዱ ትልቁ ክፍተት የኢኮኖሚ ዕድገቱ በመንግሥትም፣ በፖሊሲም፣በስትራቴጂም ትኩረት ተሰጥቶት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ አልተሰራም።አሁን የሚታየው የኑሮ ውድነት፣የዋጋ ንረትና የሥራ አጥነት ክፍተት የዚህ ነጸብራቅ ነው።ተከታታይነት ያለው ዕድገት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማረጋገጥ መቻል አለብን።ያ ካልሆነ የምንፈልገውን ሁለንተናዊ ልማት ማምጣት አንችልም።ይሄን መረዳት ያስፈልጋል።የአስር አመቱ የልማት ዕቅድም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢ–ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ከሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ያሳደረው ተጽዕኖ በተለይም ከ2005ዓ.ም በኋላ እስከ 2010ዓ.ም ድረስ ሰፊ የህዝብ አመጽን በማስከተሉ በርካታ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶች መውደማቸው ይታወሳል።ይሄ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ጫና እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ነመራ፡– እውነት ነው።የኢኮኖሚ ዕድገት ጥራትን ማረጋገጥ ሲባል አንዱና ትልቁ ክፍተት የነበረው ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በተመለከተ ነው።በመሠረተ ልማት ዝርጋታም ሆነ በሥራ ዕድል ፈጠራ ሁሉም ማህበረሰብና አካባቢ እኩል ተጠቃሚ አልነበረም።እነዚህ ድምር ውጤቶች ናቸው በወቅቱ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ውጥረት እንዲፈጠር ያደረጉት።የኢትዮጵያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጥ ባያገኝ ኖሮ ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ ሁኔታ የምትሄድበት አጋጣሚ ይፈጠር ነበር።በዚያን ጊዜ ትልቁ በኢኮኖሚው ውስጥ ያጋጠመው ችግር በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኢንቨስትመንት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ነበር።ፖለቲካው ከኢኮኖሚ ችግር ጋር ተያይዞ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይሄድ ነበር።ሀገሪቱ ችግሩን በፖለቲካ ለመፍታት ጥረት ባታደርግ ኖሮ ችግሩ የከፋ ይሆን ነበር።ሀገራዊ ለውጡ እንደመጣም እነዚህን ችግሮች ለማቃለል፣የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣የዴሞክራሲ ተቋማትንም ሪፎርም ለማድረግ፣የፀጥታና ደህንነት ተቋማትንም ለማረጋገጥ፣በፖለቲካውም ያጋጠሙ ችግሮ ችን ለመፍታት ትልቅ ስራ ሲሰራ ነበር።በኢኮኖሚው በኩልም ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መነሻ አድርጎ የተነሳው፤ከለውጡ በፊት ባለፉት 27 አመታት ያጋጠሙት ችግሮችን በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚ ሲታዩ የነበሩ ክፍተቶች መቀረፍ እንዳለባቸው እምነት ተይዞ ትልቅ የሪፎርም አጀንዳ የነበረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው።በዚሁ መሠረት ሀገር በቀል ሪፎርሙ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት አስችሏል።
አዲስ ዘመን፡– ከሀገራዊ ለውጡ ማግሥት በኢኮኖሚው ዘርፍ የነበረውን ችግር ተረድቶ በቀጣይም ምላሽ ለመስጠት የተወሰደው እርምጃ ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር ነመራ፡– በአስር አመት የልማት ዕቅዱ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ መቻል ነው።ዕድገቱ በጣም ጥራት ያለው መሆን መቻል አለበት።በመሰረተ ልማት ዘርፍ የሚከናወኑት ተግባራት እንዲሁም ምርትና ምርታማነት የሚያድግበት፣አቅርቦት የሚሳለጥበት ሰፋፊ ሥራዎች የሚሰሩት ኢኮኖሚውን ባረጋገጠ ሁኔታ መሆን ይኖርባቸዋል።
ሰፋፊ የሚባሉ እርምጃዎች ተወስደዋል።ሀገር በቀል ሪፎርሙ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ሶስት ነገሮችን ይዟል።የመጀመሪያው የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደርን በተመለከተ የገንዘብ፣የታክስ፣ ፊሲካል ፖሊሲ የሚባለው አጠቃላይ በፋይናንስ ዘርፉ ክፍተቶች ነበሩ።በዚህ ረገድ የመንግሥት ወጪና ገቢ ላይ ከፍተኛ ብክነት ነበር።መንግሥት በሙሉ አቅሙ በሀገር ውስጥ ገቢ ሲሰበስብ አልነበረም።ያለፉትን ሶስት አመታት የመንግሥት የገቢ አሰባሰብ አቅም የቃኘን እንደሆነ በገንዘብ ሚኒስቴር፣በጉምሩክ፣በፖሊሲ ደረጃ የተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎች ውጤት አምጥተዋል።የሀገሪቱ ገቢ አድጓል። ገቢ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣በምን ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባትና የፋይናንስ አስተዳደሩ እንዴት መመራት እንዳለበትም ሪፎርሙ አካትቷል።በፋይናንስ ዘርፉ ከፍተኛ ብክነት የነበረው በመንግሥት ወጪዎች ላይ በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሰርቷል።በመንግሥት ሥር ይተዳደሩ የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል እንዲዞሩ ወይም እንዲሸጡ በማድረግ ረገድም እንዲሁ ተሰርቷል።ሌላው ብድርን ይመለከታል።የውጭ ብድር በኢኮኖሚው ላይ ጫና ፈጥሮ ነበር።በሪፎርሙ ዕዳ ጫናውን ለመቀነስ አግዟል።ክፍተቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ተቃሏል ለማለት አያስደፍርም።ሆኖም ግን በመጠኑም ቢሆን ጥሩ የሚባል ሥራ ተሰርቷል።
ከተሰሩት ሥራዎችም የብድር መመለሻ ጊዜን ማራዘም፣የወለድ ምጣኔያቸው ላይ ድርድር ወይንም ስምምነት ማድረግ ይጠቀሳሉ።በነዚህ ሥራዎች ሀገሪቱ እፎይታ አግኝታለች።በፋይናንስ ዘርፉ የነበሩ የፖሊሲ ማነቆዎች በመቅረፍ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ የግሉ ዘርፍ ብድር እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተችሏል።የግሉን ዘርፍ ማበረታታት ካልተቻለ ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ያለውን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ስለማይቻል እርምጃው ወሳኝ ሆኖ ተገኝቷል። ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ኢንቨስትመንት ለመጀመር ብዙ ማነቆዎች ነበሩ።ችግሮቹ ከገንዘብና መሠረተ ልማት አቅርቦት፣ ከአስተዳደር ጀምሮ ይገለጻል።የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተዘጋጅተው አቅርቦቶች ባለመኖራቸው ውጤታማ መሆን አልተቻለም።ከዚህ በመነሳት ነው ሆንግሮን የኢኮኖሚ ሪፎርም መዋቅር ውስጥ የተገባው።ሪፎርሙ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውና አቅርቦቱ፣የትራንስፖርት አገልግሎቱ ምን መምሰል እንዳለበት፣የሀገር ውስጥና ውጪ ንግድ ማሳለጥን ይመለከታል።አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ ኢንቨስትመንቱ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ካለበት መሻሻል ስላለበት ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሶስተኛው ዘርፎችን የተመለከተ ነው።ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት በሁለት ዘርፎች ላይ ብቻ ነው ትኩረት አድርጋ ስትሰራ የነበረው።ግብርናና ኢንደስትሪ ላይ።በእርግጥ በነዚህ ዘርፎች እንቅስቃሴው ጥሩ ቢሆንም የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም።ማነቆዎች ነበሩበት።መንግሥት ግብርናውን በማገዝ በኩል፣የመስኖ ኢንቨስትመንቱ እንዲሁም ለግብርና ዘርፍ የሚሰጥ የገንዘብ ብድር ዝቅተኛ ነበር።በነዚህ ዙሪያ ባለፉት ሶስት አመታት ችግሮቹ ተለይተው ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።ትኩረት ያልተሰጣቸው ዘርፎች ናቸው ትኩረት የተሰጠው።ለአብነትም የማእድን ዘርፉን ለማልማት የሚያስችል የፖሊሲ ስትራቴጂ አልነበረም።አሁን ግን በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ(በሆንግሮን ኢኮኖሚ ሪፎርም) ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብትና አቅም ባገናዘበ አምስት ዘርፎች ተለይተዋል።እነርሱም ግብርና፣ኢንደስትሪ፣ማእድን፣ቱሪዝምና አይስቲ ዘርፎች ናቸው።በእያንዳንዱ ዘርፍ ሪፎርም የአስር አመት ዕቅድ ተዘጋጅቷል።
አዲስ ዘመን፡– የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲው እና የገንዘብ ኖት ለውጦች በኢኮኖሚው ዘርፍ የነበረውን ጫና በማቃለልና ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱ ይታወሳል።በዚህ ረገድ አንድ ሁለት ተብለው ተዘርዝረው የሚነገሩ ተጨባጭ ለውጦችን ቢገልጹልን።
ዶክተር ነመራ፡– ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በሆንግሮን ኢኮኖሚ ሪፎርም ብዙ ሥራ ተሰርቷል። በሪፎርሙ ገቢን ማሳደግ ነበር።ገቢያችንን ማሳደግ ጀምረናል።ለምሳሌ ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ የዓለም ኢኮኖሚን ባናጋበት ማግሥት ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም በጀት አመት ስድስት ነጥብ አንድ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው ያስመዘገበችው።ውጤቱ ከተያዘው ዕቅድ ዝቅ ያለ ቢሆንም ተጋርጦ ከነበረው ችግር አኳያ ትልቅ የሚባል ነው።አንዳንድ ኢንደስትሪዎች እንዳይጎዱ መንግሥት ቀጥታ ድጋፍ ማድረጉ እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፉ በወሰዳቸው እርምጃዎች ጭምር የመጣ ለውጥ ነው።ከሪፎርሙ በፊት የነበረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት አንድ ላይ ቢመጣ ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ ችግር ይወስዳት ነበር።ሀገሪቱ ውስጥ በሆንግሮን ኢኮኖሚ ሪፎርምም ሆነ በፖለቲካው የተወሰዱ እርምጃዎች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በጥሩ መስመር ላይ ማስያዝ ተችሏል።የዕዳ ጫናውንም መቆጣጠር የተቻለበት ሁኔታ አለ።በተለይም የግሉን አግልሎ ለመንግሥት ተቋማት ብቻ ይሰጥ የነበረው የብድር አገልግሎት በማስቀረት በፋይናንስ ዘርፉ የነበረውን ክፍተት በማስተካከል ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ ለግሉ ዘርፍ ባልተለመደ ሁኔታ ብድር ተመቻችቷል።
የገንዘብ ኖት ቅያሪውም የሆንግሮን ኢኮኖሚ ሪፎርም አንዱ አካል ነው። የሀገር ውስጥ ቁጠባ አነስተኛ ነበር።የዚህም አንዱ ትልቁ ችግር ገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነበር።ባንክ ውስጥና ከባንክ ውጭ የሚፈሰው ብር ወይንም ገንዘብ ቁጥሩ አይገናኝም ነበር።በዚህ ረገድ ባንኮች የሚተዳደሩበትና ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉ ሰፋፊ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።የብር ኖት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ባንክ ውስጥ የሚፈሰው ብር ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ነው የተቀየረው።ባንክ ውስጥ የተቀመጠው ብር ደግሞ ወደ ብድር ይቀየራል።ብድር ደግሞ ለኢንቨስትመንት ይውላል።በዚያው ልክ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመግታት ያግዛል።በወርቅ ንግድ ላይም የታየው ትልቅ ለውጥ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።ለዚህም ነው እንደሀገርም እንደመንግሥትም የአስር አመት መሪ ዕቅድ እንደአቅጣጫ የተቀመጠው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ከ10 አመት በኃላ ከአፍሪካ ከ30 አመት በኃላ ደግሞ ከዓለም የዕድገት ምሳሌ የሆኑ ሀገራት አንዷ የማድረግ ግብ ተቀምጧል።እንደ ሀገር ይህን ለማሳካት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል?
ዶክተር ነመራ፡– በአስር አመቱ መሪ ዕቅድ የተያዘው፤ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ በልማት ስኬት በተምሳሌትነት የምትታይ ሀገር ማድረግ ነው።በ30 አመቱ ዕቅድ ደግሞ በዓለም ደረጃ በሁለንተናዊ ልማት ስኬት የለውጥ ተምሳሌት ተብላ የምትታይ ሀገር መሆን አለባት የሚል ራዕይ ነው የተያዘው።ምን አቅም አለ ለሚለው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የነጻነት ተምሳሌት ተብላ የምትታይ ሀገር ናት።በዚያው ልክ መሬት የሰው ኃይልና ሌሎችም ዕምቅ ሀብቶች አሏት።በመሬት በኩልም ብዙ አልለማም።በሙሉ አቅም መጠቀም ከቻልን ኢትጵያን ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።በማእድንና በቱሪዝም ዘርፍም ትልቅ አቅም አላት።ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ በማእድን ዘርፉ ሲከናወን የነበረው ልማት ወርቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።ነገር ግን በዘርፉ ያላት ዕምቅ ሀብት ከወርቅም በላይ ነው።የሀገሪቱን ኢንደስትሪ ሊመግብና ሊቀይር የሚችል እንዲሁም ለውጭ ገበያም ማዋል የሚቻልበት ዕድል አለ።ይህን ሀብት አሁን በተያዘው የኢኮኖሚ ሪፎርም መቀጠል ከተቻለ ወደ ልማት መቀየር ይቻላል።
በቱሪዝም ዘርፍም እንዲሁ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ካሁን በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በመንግሥት ደረጃ በቁርጠኝነት የቱሪስት መዳረሻዎች በመሰራት ላይ ናቸው።ገቢ በማስገኘትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ቱሪዝም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል።በዘርፉ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመሰራት ላይ ይገኛል።መረሳት የሌለበት ነገር ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ እየገነባን ያለነው የኢኮኖሚ ተቋማት በኢትዮጵያ ታሪክ ሊጠቀስ የሚችል ነው።ሀገሪቱ ይህንን መሸከም የሚችል አቅም እንዳላት በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ማረጋገጥ ተችሏል።ኢኮኖሚውን ክፍት ማድረግ አለብን።ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የኢኮኖሚ ተቋማት መገንባት መቻል አለብን።የአንድ ፓርቲ ወይንም ለአምስት አመት ተመርጦ የሚገዛ መንግሥት ብቻ መሆን የለበትም።ኢኮኖሚው ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል።ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የ10 አመትና የ30 አመት ዕቅድ አቅዶ መንቀሳቀስ አልተለመደም።ኢትዮጵያ ያላት የሰው ኃይልም ሀብት በመሆኑ መልክኣ ምድሯም ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሚያገናኝ ፣በነጻነት ትግሉም በተምሳሌትነት የምትጠቀስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትልቅ ቦታ ያላት በልማት ስኬትም የማትታይበት ሁኔታ የለም።
አዲስ ዘመን፡– አንድ ሀገር የኢኮኖሚ አቅሙ ሲጎለብትና ሲበለጽግ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑ አይቀርም።ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ምን አይነት ተግባራት መከናወን አለባቸው?
ዶክተር ነመራ፡– ኢትዮጵያ ያሏትን ዕምቅ አቅሞች ወደ ልማትና ዕድገት መቀየር መቻል አለብን።የ10 አመት የልማት ዕቅዱም ይህንኑ ነው የያዘው።ግብርናችን አሁን ካለበት ማደግ ይኖርበታል።አሁን የተያዘው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ፕሮግራም፣ከውጭ የሚገባውን ግብርና ውጤት በሀገር ውስጥ መተካት የሚለውን ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ትራንስፎርሜሽን ማምጣት ይኖርብናል።ከአሁን በፊት ያለሙና ትኩረት ያላገኙ ዘርፎች ላይ ለመስራት ከፖሊሲ ጀምሮ የማሻሻያ እርምጃዎች ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ሲሰሩ ቆይተዋል።ጠንካራ የሆኑ ተቋማትን የመገንባት አቅም እስክንፈጥር ድረስ መስራት ይኖርብናል።የሀገሪቱን የኢኮኖሚና የልማት እንቅስቃሴ ጥያቄ ውስጥ መክተት የለበትም።በፖለቲካል ኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ እያደረግነው ያለው በተለይም በሀገር ደረጃ ያሉ መሪዎችን ቁርጠኝነት ማስቀጠል መቻል አለብን። የተቋማት ግንባታ በሁለትና ሶስት አመት ብቻ ተገንብቶ የሚያልቅ አይደለም።ከኢኮኖሚና የፖለቲካ ሽግግሩ ጎን ለጎን ሆኖ ሀገሪቱን ወደ ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሸጋግራት መሆን አለበት በሚል ዕሳቤ እንዲሁም በዴሞክራሲ፣በአስተዳደር እና በሌሎችም ጠንካራ የህዝብ ተቋማትን ለመገንባት አቅጣጫ ተይዞ እንደ መንግሥት እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ያጋጠመ መሆኑ ቢታወቅም፤ ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ ግን እየተባባሰ መሄዱ በስፋት ይነሳል።እዚህ ላይ ያለዎትን ሀሳብና የወደፊቱ አቅጣጫ ላይ ያለውን ሁኔታ ቢነግሩን?
ዶክተር ነመራ፡– በግሌ ከለውጡ በኃላ ችግሩ ተባብሷል በሚለው ሀሳብ አልስማማም።ስለ ዋጋ ንረት ስናነሳ ሁለት ነገሮችን መገንዘብ መቻል አለብን።ችግሮችን በተመለከተ ስትራክቸራል የሚባል ነገር አለ።ሌላው ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ መዋዠቅ የሚያሳየው ነው።አሁን የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የመጀመሪያው ሀሳብ ነው።አንዴ ሰማይ የተሰቀለ ዋጋ ነው ያለን።ይሄ ከኢኮኖሚ ጥራት አለመኖር ጋር ይያያዛል።የዜጎች የኑሮ ደረጃ ማሻሻልን ታሳቢ ያደረገ አልነበረም።በዚያው ልክም የዜጎች ገቢ አላደገም።በአጠቃላይ በኢኮኖሚ ደረጃ ካየን ደግሞ ትልቁ ሥራ የነበረው በኢኮኖሚክስ ቋንቋ ‹‹ዲማንድ ሳይድ››ላይ ወይንም መሠረተ ልማት መዘርጋት ላይ ነው።ኢኮኖሚን በሚያሳደግ መልኩ የልማት ሥራው አለመከናወኑም ሌላው ተግዳሮት ነው።ይሄ እኩል የሆነ ሚዛን እንዳይኖር አድርጎታል።ገበያው ውስጥ ያለው የዋጋ ንረት ከዚህ ጋር ይያያዛል።ከለውጡ በፊት ስንከተለው የነበረው ኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ዋጋውን ወደ ላይ የሚገፋ ነበር።እዚህ ላይ ምሳሌ ለመስጠት ቋሚ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ገቢያቸው ላለፉት 27 አመታት በዋጋው ልክ አላደገም።የኢኮኖሚ ዕድገቱ የጥራት ጉድለት አለበት የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው።የነበሩት ህገወጥ አሰራሮችና የንግድ እንቅስቃሴዎች፣የተመረተውን ምርት በአግባቡ ወደ ሚፈለገው ገበያ አለማድረስ በመካከል ላይ ያሉ ደላሎች ይፈጥሩት የነበረው ተደማምሮ የዋጋ አለመረጋጋቱን የከፋ አድርጎታል።ችግሩ መንግሥት ለመቆጣጠር እንኳን ያልቻለበት ሁኔታ ነበር።ከባንክ ውጭ የሚፈሰው ገንዘብ ጥቁር ገበያውን እንዴት እንዳሳበጠውም ማየት ይቻላል።ይህ ሁሉ ችግር ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ብቻ የታየ ሳይሆን ቀደም ሲል ከነበረው ብልሹ አሰራርና መዋቅራዊ አሰራር የመነጨ ነው።በሁለንተናዊ አቅጣጫ የተያዘው የሪፎርም ሥራ ከተጠናከረ የዋጋ መረጋጋት በሂደት ይመጣል።
አዲስዘመን፡– የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሲነሳ የኢኮኖሚ አሻጥር እና ሳቦታጅ የሚሉ ቃላቶች ተያይዘው ይከተላሉ።የነፍስ ወከፍ ገቢም እንዲሁ ይነሳል።እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ምን ማለት ናቸው?
ዶክተር ነመራ፡– የነፍስ ወከፍ ገቢን በተመለከተ አንዳንድ ጊዜ የሚያሳስት አሀዝ ነው።የምንጠቀመው የማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ዓለምአቀፍ መለኪያ ነው።አጠቃላይ የኢኮኖሚውን ጤናማነትና ዕድገት አመላካች የሆነ መለኪያ ነው።ከዚህ አንጻር የነፍስ ወከፍ ገቢ መገለጫ ላይሆን ይችላል።ይሄ ምን ማለት ነው አጠቃላይ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ወይም ደግሞ ያለውን የኢኮኖሚ ዋጋ ለአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማካፈል ማለት ነው።አንድ ቤተሰብ ውስጥ ጥሩ ደመወዝ የሚያገኝ ሰው አለ ብንልና ይህ ሰው አምስት የቤተሰብ አባላት ካለው ለአራቱ እኩል ይካፈላል።በዚህ መልኩ መረዳት ይቻላል።ከዚህ አንጻር ነው ብቻውን ጥሩ መለኪያ ተደርጎ የማይወሰደው።
በዜጎች ወይንም በግለሰብ ደረጃ ወርደን ስናየው ሊያሳስት ይችላል ከሚል እንጂ ጥቅሙን በዚያው ልክ ማሳነስም የለብንም።በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ገቢው የማይቀየርና ምንም ገቢ የሌለው ማህበረሰብ በስፋት ባለበት ሀገር የነፍስ ወከፍ ገቢን እንደ አንድ ጉዳይ ማንሳት እንዳያሳስት ነው።
አሻጥርና ኑሮ ውድነት ጋር የተያያዘው ደግሞ ከባንክ ውጭ የሚፈሰው ገንዘብ ብዙ ነበር።ህገወጥነቱም እንዲሁ።በዚህ ረገድም የሚቀሩ ሥራዎች ቢኖሩም የበለጠ መሥራት ይጠበቃል።የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ አጠቃላይ ህዝቡን ሊመግብ የሚችል ምርት ማምረት ይጠበቃል።በፖሊሲ በኩል ያለውንም እያስተካከሉ መሄድ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡– ለውጡ በብዙ ፈተናዎች ያለፈ መሆኑ ይታወቃል።ከነዚህ ፈተናዎች ተሻግሮ ከ10 አመት ወይንም ከ30 አመት በኃላ የተቀመጠውን የዕድገት ግብ ከማሳካት ባለፈ ዕድገቱ በሁሉም ዜጋ ላይ የሚታይ እንዲሆን ምን አቅጣጫ ተቀምጧል?
ዶክተር ነመራ፡– አሁን ያስቀመጥነው አቅጣጫ በ10 አመት የልማት ዕቅዱ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕቅድ ማረጋገጥ ነው።የኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት አቅርቦትን ማሳለጥ በተመለከተ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራት አለባቸው።የኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት አሁን ባለው ሁኔታ አፍሪካ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።ያለሙ ዘርፎችንም በማልማት ልማቱን በፍጥነት ማሳደግ አለብን።የልማት ዕድገቱ ሁለተናዊ ስኬት ማምጣት ይኖርበታል።የሚዘረጋው ሥርአት ሁሉንም ዜጎች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግና ሁሉንም አካባቢ በእኩል የሚያለማ መሆን ይኖርበታል።በዚህ ረገድ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት የተሰሩት ሥራዎች ይህንን ተስፋ የሚያመላክቱ ናቸው።ይህንን ደግሞ መሬት ላይ አውርደን ሥራ መሥራት አለብን።ቀደም ሲል የነበረው ክፍተት በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ እኩል ተጠቃሚ አልነበረም ።ሴቶችም እንዲሁ ተጠቃሚ አልነበሩም፤የሥራ አጥነት ችግር ከወጣቶቹ ሴቶቹን ነው የሚጎዳው።በዚህ ረገድ የልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ከተማና ገጠርን ማዕከል ያደረገ ልማት አለማከናወን ትልቅ ክፍተት ነበረበት።የልማት ዕቅዱ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በሚፈታ መልኩ ነው የተቃኘው።በእንስሳት ዘርፉም እንዲሁ የማልማት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል።ጥራት ያለው ኢኮኖሚን በማረጋገጥ የጋራ ብልጽግናን እውን ማድረግ መቻል አለብን።እነዚህ ሁለት አቅጣጫዎች የተያዙ ናቸው።በመንግሥት በኩልም ትልቅ ቁርጠኝነት ተይዞ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ዶክተር ነመራ ስለሰጡን ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ነመራ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013