አንተነህ ቸሬ
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ) ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹ግንባሩ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጅ ቡድን አይደለም›› ያሉ ብዙ ወገኖች ተቃውሟቸውን ሲገልፁና ትግል ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ቡድኑ ያሳካቸው በጎ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ‹‹እፈጽማቸዋለሁ›› ብሎ ለሕዝብ ቃል የገባቸውን ጉዳዮች ወደ ጎን ትቶ በግልና በቡድን ጥቅም ታውሮ በአገር ላይ ያደረሳቸው ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ኪሳራዎች ተቆጥረው አያልቁም። በተለይም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በቡድኑ ላይ ሲካሄዱ የነበሩ ተቃውሞዎች ጠንክረው የ2010 ዓ.ም ለውጥ እውን ሆነ። በዚህ የትግልና የለውጥ ሂደት አበርክቶ ከነበራቸው በርካታ አካላት መካከል ሰላማዊና የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ይጠቀሳሉ።
‹‹ዶክተር›› በተባለ የትግል ስሙ የሚታወቀው ክፈተው አሰፋ ተወልዶ ባደገበት አርማጭሆ አካባቢ የነበረው አፈናና ጭቆና ገና በ17 ዓመቱ፣ በ1993 ዓ.ም፣ ለትጥቅ ትግል ብረት እንዲያነሳ አስገደደውና ወደ በረሃ ገባ።
‹‹ … በተለይ አርማጭሆ አካባቢ ወታደራዊ አገዛዝ ነው የነበረው። አርማጭሆና አካባቢው ወያኔ ኢላማው ውስጥ ካስገባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ስለነበር ታዋቂ የነበሩ የአካባቢውን ሰዎች ቀድሞ መንጥሯቸዋል። ሴቶችንም ይደፍሩ ነበር። ከአንድ ቤት እስከሰባት የቤተሰብ አባላት በግፍ ተገድለዋል። የንብ መንጋ ከሰፈረበት ዛፍ ላይ ሰዎችን አስረው ሰዎቹ በንብ ተነድፈው እንዲሞቱ አድርገዋል። በእኛ ቤተሰብ ላይም የተፈፀመው መከራ ቀላል የማይባል ነበር። አምስት የቤተሰባችን አባላት ያለጥፋታቸው ታስረው ተሰቃይተዋል።
ይህን ሁሉ ግፍ እየተመለከትኩ መኖርን አሜን ብዬ መቀበል ባለመቻሌ ለትጥቅ ትግል ወደ በረሃ ወረድኩ። እኛ በረሃ ከገባን በኋላ ወላጆቻችን ‹‹የባንዳ ቤተሰብ›› እየተባሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው እንዳይሳለሙ እንኳ ተደርገዋል። ስራም መስራት አልቻሉም። ከስራቸው ተፈናቀሉ፤ ሀብታቸውም ተወረሰባቸው። ብዙ ሰቆቃዎችን አሳልፈናል›› በማለት ወደ ትግል እንዲገባ ስላስገደደው ሁኔታ ያስታውሳል።
ወደ ትግል ከገባ በኋላ በቤተሰቦቹና ዘመዶቹ ላይ ይደርስ ከነበረው ስቃይ በተጨማሪ ትግል ነውና እርሱም ብዙ መከራዎችን ዐይቷል። ‹‹በትግሉ ወቅት አራት ቦታዎች ላይ ቆስያለሁ። እግሮቼና እጆቼ ብዙ ስብራቶች ደርሰውባቸዋል። አጎቴ እና ታላቅ ወንድሜ በትግሉ ላይ ተሰውተዋል። ብዙ መከራና በደል ደርሶብናል›› ይላል።
መከራውና በደሉ ከትግል ሜዳ የተሻገሩ ተራዛሚ ተፅዕኖዎችንም አስከትሏል። በትግሉ ላይ የተሰዉ የታጋይ ልጆች ጥሩ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የሚያደርግ ጠንካራ ቤተሰብ አለመኖሩ፣ የታጋይ ቤተሰቦችና ዘመዶች በሥርዓቱ ምክንያት ከስራቸው መፈናቀላቸው እንዲሁም በትግሉ ወቅት ልጆቻቸውን ያጡ አዛውንቶች ጧሪ ቀባሪ ማጣታቸው የዚህ ማሳያዎች ናቸው።
ከአርማጭሆ ተነስቶ ወደ ኤርትራ በረሃዎች የዘለቀው የክፈተውና ጓዶቹ ትግል የሚመራው ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር›› በተባለው ድርጅት በኩል ነበር። ክፈተው እንደሚለው፤ ወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግሥት በመሆኑና በሁለቱም ወገኖች በኩል የነበረው ስሜት ጥሩ ስላልነበረ ወደ ኤርትራ ሄዶ መታገል ቀላል አልነበረም። የሆነው ሆኖ እነክፈተው ትግሉን የጀመሩት ‹‹ይሳካል›› በሚል እምነት ነው።
‹‹የትግል መነሻችን አምባገነኑ የወያኔ ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ ሊወገድ እንደማይችል ማመናችን ነበር። የትግላችን ግብ ወያኔን ማስወገድ ወይም ማስገደድ ነበር። ማስገደድ ሲባል ሕገ መንግሥቱን ማስቀየርን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎች እንዲወሰዱ ግፊት ማድረግ ሲሆን ማስወገድ ደግሞ ሥርዓቱን አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈንና ሕዝቡ የሥርዓቱ ባለቤት የሚሆንበትን እድል መፍጠር ማለት ነው›› ይላል።
የክፈተውና ጓዶቹ ትግል ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎና ከሌሎች የትግል አማራጮች ጋር ተቀናጅቶ የ2010 ዓ.ም ለውጥ እውን ሆነ። ለውጡ ግን ለእነክፈተው የማስገደድም ሆነ የማስወገድ አማራጭን እውን አላደረገም። ‹‹አጨራረሱ ግን በማስገደድም በማስወገድም አልተጠናቀቀም። በመደራደር ነው ወደ አገራችን የገባነው›› ይላል።
አምደማርያም እዝራ በሰላማዊ እና በትጥቅ ትግል አማራጮች ለብዙ ዓመታት ከታገሉ ታጋዮች መካከል አንዱ ነው። ከ2010 ዓ.ም ለውጥ በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ‹‹የህ.ወ.ሓ.ት አፓርታይድ ሥርዓት ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ጨፍልቆና ቀጥቅጦ እንደፈለገ የሚያደርግበት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች የማይከበሩበት፣ ፍትሕና እኩልነት የማይታወቁበት፣ የፍትሕና የእኩልነት ጥያቄን ያነሱ ግለሰቦች የሚሰቃዩበትና ደብዛቸው የሚጠፋበት በአጠቃላይ አስፈሪ ድባብ የነበረበት ሥርዓት›› በማለት ይገልጸዋል።
በትግሉ ሂደት ስለነበረው ተሳትፎና ስለተቀበላቸው መከራዎች ሲያስረዳም ‹‹ወደ ትጥቅ ትግል ከመግባቴ በፊት በሰላማዊ መንገድ ስታገል ቆይቻለሁ። የ‹‹ጃኖ›› መጽሔት የሰሜን ቀጣና አምደኛ ሆኜ ስለፍትሕና እኩልነት የሚጠይቁ ጽሑፎችን እጽፍ ነበር። ከምርጫ 97 በኋላ ‹‹አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ›› ፓርቲ ሲመሰረት የፓርቲው አባል ሆንኩ። ፓርቲው በጎንደርና አካባቢው እንቅስቃሴ ሲያደርግ እሳተፍ ነበር። በወቅቱ መምህር ነበርኩ፤ በፖለቲካ አመለካከቴ ምክንያት ከስራዬ ተባረርኩ። የጸጉር ሙያ ስለነበረኝ ጸጉር ቤት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ። ትግሉ ወደ ጸጉር ቤት የሚመጡ ደንበኞችን ማንቃትንም ያጠቃልላል ብዬ በማመን በሳምንት አራት መጽሔቶችንና ጋዜጦችን በራሴ ወጪ እየገዛሁ ደንበኞች ወደ ጸጉር ቤቱ ሲመጡ እንዲያነቡና ስለአገሪቱ ሁኔታ እንዲገነዘቡ ለማድረግ እጥር ነበር። በወቅቱ እኔ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ክትትል ውስጥ ስለነበርኩ የጸጉር ቤቱ ባለቤት እኔን ከስራ እንዲያሰናብት ታዘዘ። ከዚያም ተባረርኩ። ከእነርሱ ጋር እንድሰራም ጠየቁኝ፤ ፈቃደኛ ካልሆንኩ ግን እንደሚያስሩኝና እንደሚገድሉኝ አስጠነቀቁኝ። ‹‹ባሳደገህ ማኅበረሰብ ፊት አስከሬንህ ይጎተታል›› አሉኝ። እኔ ግን ህሊናዬን ሸጬ ለመኖር ፈቃደኛ ስላልነበርኩና እኔ ሞቼ ሀገሬን ለማኖር ስለወሰንኩ ጥያቄያቸውን ሳልቀበል ቀረሁ። በየጊዜው ብዙ ድብደባዎች ተፈጽመውብኛል፤ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታስሬም ነበር።
በመጨረሻም በሰላማዊ ትግሉ ለውጥ ማምጣት እንደማይሳካ በመገንዘቤና ገዢዎቹ ወደ ስልጣን በመጡበት ቋንቋ በማናገር ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ማውረድ ይቻላል ብዬ ስላመንኩ መስከረም 4 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ ትጥቅ ትግል ገባሁ።
ወደ ትግል ስገባ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምኜ ነው። ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በአርማጭሆ፣ በመተማ፣ በቋራና በሌሎች አካባቢዎች የተለያዩ የተቃውሞ ትግሎች ሲደረጉ ነበር። ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር›› ተመስርቶ ትግል ጀመረ። ታጋዮቹ ብዙ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ይደመጥ ስለነበርና ከጊዜ በኋላም ‹‹ግንቦት ሰባት›› ስለተባለው ድርጅት እሰማ ስለነበር ይህን ድርጅት ተቀላቅዬ ለውጥ ማምጣት አለብኝ ብዬ ወስኜ ወደ ኤርትራ ሄድኩ። እኔ በትግሉ ላይ እያለሁ ልሞት እችላለሁ፤ በእኛ መስዋዕትነት አገራችን ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕና አንድነት ታገኛለች የሚል ሙሉ እምነት ነበረኝ›› ይላል።
ትግላቸው በተለያየ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ ከሰላማዊ ትግሉና በተለያዩ አካባቢዎች ከተደረጉ ትግሎች ጋር በመቀናጀቱ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ የሚገልጸው አምደማርያም፤ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የታዩት ‹‹የኦሮሞ ደም የእኔም ደም ነው›› የሚለውንና ሌሎች የትብብር መልዕክቶችን በማሳያነት ይጠቅሳል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊና ከ2006 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በእስራት ላይ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባለፈው ዓመት ባሳተሙት ‹‹የታፋኙ ማስታወሻ›› መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፤ ማንም በማያውቃቸው የተለያዩ የአፈና ቤቶች ውስጥ ከአንድ ዓመት ከሦስት ወራት በላይ ታስረዋል። መንጋትና መምሸቱን መለየት የማይቻልባቸው የአፈና ቤቶች ውስጥ ብዙ መከራ አይተዋል። እጅግ ግራ የሚያጋባና የሚያሳዝን የምርመራ ሥርዓት ስለመኖሩም በመጽሐፋቸው አትተዋል። በእርሳቸው መታሰር ምክንያት ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ክፉኛ ሲጨነቁ ከርመዋል። ገዢው ቡድን በጥብቅ ሲፈልጋቸው ከነበሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ስለነበሩ የቤተሰቡ ጭንቀት እጥፍ ድርብ ነበር።
ከለውጡ በኋላ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ከእስራት የተፈቱት አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ቤት በወጡ ማግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ይህ ለእርሳቸው እንደተአምር የሚቆጠር አጋጣሚ ነበር። ከእስር መፈታታቸው ሳያንስ የአገሪቱ መሪ ቢሮ ድረስ ሄደው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መገናኘታቸው የፈጠረባቸው ደስታና ተስፋ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር በመጽሐፋቸውም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ባደረጓቸው ንግግሮቻቸው ገልጸዋል።
ክፈተው ትግላቸው ውጤት እንዳስገኘ ባይክድም ገና ያልተመለሰ ጥያቄ እንዳለ ግን በአፅንዖት ይናገራል። ‹‹ወያኔን ከማስወገድ አንፃር ትግላችን ተሳክቷል። የሥርዓት ለውጥ ከማምጣት አኳያ ግን የሥርዓት ለውጥ አለ ብዬ አላምንም። መንግሥት ቃል ገብቶ የነበረው መዋቅራዊ ለውጥም ሆነ ‹የሕዝቡን የልብ ትርታ እናዳምጣለን፤ ከሕዝባችን ጋር ሆነን ችግሮችን እንፈታለን› የተባለው ነገር አልተፈጸመም። በኋላ ምን እንደሚመጣ ባናውቅም እስካሁን ያለው ነገር የታገልንበት መንገድ የተሳሳተ ነው ብዬ እንዳምንም እያደረገኝ ነው። ተጠቃሚ የሆነው ትግሉን የታገለው ኃይል ሳይሆን ‹የለውጡ ባለቤት ነኝ› ብሎ ከቀድሞው ሥርዓት የቀጠለው ኃይል ነው። ዋናው ነገር ወያኔ ከተወገደ በኋላ ምን ዓይነት ሥርዓት ነው የሚተካው የሚለው ጉዳይ ነበር። አገሪቱ ያለችበት የፖለቲካ ሥርዓት ከብሔር ፖለቲካ ሊላቀቅ አልቻለም፤ የብሔር ፖለቲካ አመለካከት ሊሰበር አልቻለም›› ይላል።
‹‹ስልጣን የሕዝብ ነው ብለን ስለምናምን ስንታገል ስልጣን መያዝ ግባችን አልነበረም። የትግሉ መሪዎች የነበሩት ሰዎች ግን ዋጋ የከፈለውን ታጋይ ሁሉ እንደሸንኮራ አገዳ መጠው ጥለው ለራሳቸው ስልጣንና ጥቅም ማሳኪያ አድርገውታል። ምንም እንኳ ‹‹የለውጡ ባለቤቶች እኛ ነን›› ባሉ አካላት ትግላችንን የተቀማን ቢሆንም ለውጡ ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበታል›› የሚለው ክፈተው፤ ታጋዮቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ እነርሱን ለማቋቋም ቃል የተገባላቸው ሁሉ እንዳል ተፈፀመ በምሬት ይናገራል።
‹‹አሁን ያለነው ከሰው እየለመንና እየተጉላላን ነው። መጠለያ እንኳ ማግኘት አልቻልንም። የስራ እድል አልተፈጠረልንም። ለብዙ ዓመታት ትግል ላይ የነበረ ሰው ሲመለስ ሕይወቱን የሚጀምረው እንደ አዲስ መሆኑ እየታወቀ ብድር እንኳ አልተመቻቸልንም›› ይላል።
አገሪቱ ስላለችበት ወቅታዊ ቀውስና መፍትሄዎችን በተመለከተም ‹‹የአሁኑ አገራዊ ቀውስ በጣም ከባድ ነው። በየቀኑ ሰው ሳይሞት አይውልም/አያድርም። የብሔር ፖለቲካ በጣም አስቸጋሪና አደገኛ ነው። ወያኔ ጥሎልን የሄደው የቤት ስራ ቀላል አይደለም። የብሔር ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጀርባ ላይ እንዲወርድ ለማድረግ ሰፊ የሆነ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ትብብር ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ መንግሥት በዋናነት ጠንካራ የፀጥታና የደህንነት መዋቅር ፈጥሮ ንፁሃንን እቀጠፈ ያለውን መዋቅራዊ ሥርዓት ማስወገድ መቻል አለበት። ጠንካራ የፀጥታና የደህንነት መዋቅር ከሌለ ሁኔታው ከዚህም የባሰ አስጊ ይሆናል። የኢትዮጵያን ሰላም የማይመኙ የውስጥና የውጭ ጠላቶች አሉ። አገሪቱ ጠንካራ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ካልገነባች ቀን ቀን የመንግሥት፤ ሌሊት ደግሞ የአሸባሪና የጽንፈኛ ቡድኖች አባልና ዓላማ አስፈፃሚ መሆናቸው አይቀርም። መንግሥት ውስጡን ማጥራት አለበት›› በማለት ይመክራል።
‹‹ትግላችን የታገልንበትን ዓላማ አሳክቷልም፣ አላሳካምም ብዬ ነው የማምነው›› የሚለው አምደማርያም፤ ‹‹በአፍሪካ ግዙፍ ጦር አለኝ›› የሚለውንና ‹የደህንነት፣ የመከላከያ፣ የፋይናንስ፣ የፍትሕና የዲፕሎማሲ ተቋማትን በሙሉ ተቆጣጥረን መቼውንም ቢሆን ከስልጣን አንነቃነቅም፤ ኢትዮጵያን እንደፈለግን አድርገን እንገዛታለን› ብለው የነበሩ አፋኞች ከስልጣን ተወግደውና አንዳንዶቹም ታስረው ስንመለከት ትግላችን ፍሬ አፍርቷል ብለን እንድናስብና እንድንደሰት ያደርገናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ‹እኛ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን› ብለው መናገራቸውና ኢትዮጵያዊነት በመሪ ደረጃ እንዲህ ሲወደስ መስማቴ ትልቅ ነገር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ‹ወልቃይት፣ ጠገዴና ራያ በታሪክም በሕግም የአማራ አፅመ ርስቶች ናቸው፤ ወደ ቀደመ ማንነታቸው ይመለሱ› ብለን እናምን ስለነበርና እነዚህ ግዛቶች ወደ ማንነታቸው ተመልሰው ማየታችንም ከትግላችን ስኬቶች አንዱ ነው›› ይላል።
በአንፃሩ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ፣ የሚፈፀሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶች (ግድያዎችና ማፈናቀሎች) ለውጡን ጥያቄ ውስጥ ያስገቡና እንዲያውም ‹‹ለውጥ የለም›› ወደሚል ድምዳሜ እንዲገፋው ምክንያት ስለመሆኑ ያስረዳል።
በ2010 ዓ.ም ታጋዮች ከኤርትራ በረሃ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ለታጋዮቹ የተገባው ቃል አለመፈፀሙ እጅግ እንደሚያሳዝናቸው ይናገራል። ‹‹በትግሉ ብዙ ታጋዮች ተሰውተዋል። ከ15 ዓመታት በላይ በትግል ላይ የቆዩ ብዙ ታጋዮች አሉ። ስለቤተሰቦቻቸው መረጃ የሌላቸው፣ ሕይወትን እንደ አዲስ መጀመር ያለባቸው … ብዙ ታጋዮች ነበሩ። ‹እነዚህ ታጋዮች ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉት እንዴት ነው?› የሚል ጉዳይ ተነስቶ ውይይት ተደርጎ ነበር። የድርጅቱ መሪዎች ‹ይህ ድርጅት ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ይቀየራል። ነገር ግን ድርጅቱ ዋጋ የከፈለውን ታጋይ ሳያቋቁም ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት መቀየር አይችልም፤ አይቀየርምም። ከመንግሥት ጋር ተነጋግረናል፤ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባን የመጀመሪያው ስራችን ታጋዮቹን ማቋቋም ነው። ይህን ለማድረግ ሦስት ወራት በቂ ነው› አሉን። ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ገባን። ያረፍነው ወረታ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ነበር። በወቅቱ እስከምትቋቋሙ ድረስ እዚህ መቆየት ወይም ወደ ቤተሰብ መሄድ ትችላላችሁ ተብሎ ስለነበር የተወሰነው ታጋይ ለመጓጓዣ የተሰጠችውን መጠነኛ ገንዘብ ይዞ ወደየትውልድ አካባቢው ሲመለስ ጥቂቶቹ ደግሞ በዚያው ቆዩ። ሦስት ወር የተባለው ከሦስት ዓመታት በኋላም መፍትሄ ሊያገኝ ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት ታጋዮቹ በሚያሳዝን ሁኔታ በየጎዳናው ወድቀው፣ ወደ ሱዳን ተደሰው፣ በወረታ ግብርና ኮሌጅ ውስጥ ይገኛሉ። በሕክምና እጦት ምክንያት የሞቱም አሉ። ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ድረስ ምንም መፍትሄ ሊገኝ አልቻለም›› በማለት ይናገራል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013