ዳንኤል ዘነበ
ምች(cold sore) በተለምዶ ከሚከሰቱ የቆዳ ኢንፌክሽኖች መካከል ዋነኛው ሲሆን በተለይም የላይኛው ወይም የታችኛው የከንፈር ጠርዝ ከፊታችን ቆዳ ጋር በሚገናኝበት አካባቢ ላይ በሚወጡ ውሃ የቋጠሩ ጥቃቅን ቁስለቶች ይታወቃል። በተለምዶ የምች በሽታ የምንለው (Cold sores) የሚከሰተው የኸርፒስ (Herpes) ቫይረስ 1 በሚባሉ በሽታ አምጭ ተዋህስያን ነው። የኸርፒስ (Herpes) ቫይረስ ቤተሰብ በውስጡ ከ100 በላይ የቫይረስ ዝርያዎች ሲኖሩ 8ቱ በሰው ልጅ ላይ በሽታ ያስከትላሉ። ከነዚህም መካከል የምች አምጪ ተህዋስያን ኤች.ኤስ.ቪ-1 (HSV-1) ይገኙበታል።
የኸርፒስ (Herpes) ቫይረስ ቤተሰቦች ቆዳን ጨምሮ በዓይን፣ በመራቢያ አካላት እንዲሁም የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ኢንፌክሽኖች ያስከስታሉ። የምች አምጪ ተህዋስያን ኤች.ኤስ.ቪ- 1 (HSV-1) እንዲሁም ኤች.ኤስ.ቪ -2 (HSV-2) ከጨቅላ ሕፃናት እስከ የዕድሜ ባለፅጋ የዕድሜ ክልል ኢንፌክሽን መፍጠር የሚችሉ ሲሆን ኤች .ኤስ.ቪ- 1 (HSV-1) በምች አምጪ ባህሪው ይታወቃል።
ኤች.ኤስ.ቪ -1(HSV-1) ከሰው ወደ ሰው በቆዳ-ቆዳ እና በቆዳ -የሚውከስ ሽፋን (የአፍ ውስጥ ለስላሳ ሸፍን መሰል) ንክኪ የሚተላለፍ ሲሆን ኤች.ኤስ.ቪ-2 (HSV-2) ደግሞ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት እንዲሁም ከመራቢያ አካላት-ፊት በሚደረግ ንክኪ ይተላለፋል። የኸርፒስ (Herpes) ቫይረስ ዝርያዎች በነጭ የደም ሴሎቻችን ተጠግተው ከሰውታችን ሙሉ በሙሉ በመወገድ ፈንታ በሰውነታችን የነርቭ አካላት ውስጥ በመሸሸግ የሰውነታችን ውስጣዊ ሁኔታዎች ምቹ እስኪሆኑ በመጠባበቅ ከተሽሽጉበት በመውጣት በድጋሜ የምች በሽታን ያስከትላሉ።
የምች በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የምች በሽታ ተህዋስያን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰውነታችን ኢንፌክሽን ሲያስከስቱ በአብዛኛው ምንም ምልክት አይኖራቸውም፤ ነገር ግን በሚከተሉት ጊዜያት ሲከሰቱ የሚከተሉትን የመሳሰሉ ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። የላይኛውን ወይም የታችኛውን የከንፈር ጠርዝ በቀኝ ወይም በግራ በኩል ከፊት ቆዳ ጋር የሚያገናኘው ቦታ አካባቢ የመለብለብ፣ የማሳከክ ወይም ጨምድዶ የመያዝ ስሜት ሊሰማዎት ይችላል። ከዚያም ከ24 ሰዓታት በኋላ ከሥራቸው ቀልተው ውሃ የቋጥሩ ጥቃቅን የቁስለቶች ስብስብ ይፈጠራል። በምች የሚመጡ ቁስለቶች ከተፈጠሩ በኋላ በቀላሉ በመፈንዳት ፈሳሽ ሊያፈልቁ ይችላሉ። ከዚያም ወዲያው በመድረቅ በቅርፊት ይሸፈናሉ።
ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች በተጓዳኝ የራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ የድካም ስሜት እንዲሁም በአንገት ወይም በብብት ውስጥ የሚገኙ ሊምፍ ኖድ የሚባሉ ዕጢዎች እብጠት ሊያስከትል ይችላል። ቁስለቶቹም በተለምዶ ከ2-4 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ያለ ጠባሳ ይድናሉ።
የምች በሽታን በተደጋጋሚ የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች
ለሰውነት በሽታ መከላከል አቅም የመውረድ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች (የኤች.አይ.ቪ፣ የካንሰር ህመሞች) በወር አበባ ጊዜ የሚከሰቱ ሆርሞናዊ ለውጦች በተለምዶ በቫይረስ በሚመጡ እንደ ጉንፋን ባሉ ኢንፌክሽኖች መጠቃት ጭንቀት እና የአእምሮ ውጥረት ወዘተ ይጠቀሳሉ።
በምች ለሚመጡ ቁስለቶች በቤታችን ምን ማድረግ እንችላለን?
የህመም ማስታገሻ በምች በሽታ የሚመጡ ቁስለቶች በተያያዘ የሚሰማዎትን ህመም ለመቀነስ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ በፋርማሲ የምናገኛቸውን አይቡፐሮፈን (Ibuprofen) እና አሴታሚኖፈን (Paracetamol) በፋርማሲ ባለሙያው ትዕዛዝ መሰረት መጠቀም ይቻላል።
ቅዝቃዜ
ከምች በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን በቁስለቶቹ ዙሪያ የሚከሰት የቆዳ መቅላት እና መቆጣትን ለመቀነስ በቀዝቃዛ ውሃ በተነከረ ጨርቅ ወይም በበረዶ ቁራጭ በቀን ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት ከ5-10 ደቂቃ በቦታው ላይ መያዝ እንደሚረዳ የቆዳ ሐኪሞች ይናገራሉ።
እራስን ከጭንቀት ነፃ ማድረግ
የአዕምሮ ውጥረትን መቀነስ የሰውነትን በሽታ መከላከል አቅም እንደሚጨምር በተደረጉ ጥናቶች ተረጋግጠዋል። ስለዚህም የሚያዝናኑን ነገሮችን በመፈለግ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ከዚህም በዘለለ የባለሙያ ምክር በማግኘት ልንከላከለው ይገባል።
ለምች በሽታ የባህል ህክምናን መጠቀም ተገቢ ነው?
የባህል ህክምና የአንድ አካባቢ ተወላጆች ለዘመናት ያካበቷቸው እንስሳን እና እጸዋት ነክ እውቀቶችን እንዲሁም ማህበረሰባዊ አስተሳሰቦችን መሠረት ያደረገ የህክምና ዘርፍ ነው። ጆርናል ኦፍ እስያ-ፓሲፊክ ባዮዲቨርሲቲ (Journal of Asia-Pacific Biodiversity) በወጣው ጥናት መሠረት የዓለማችን 64% የሚሆነው ማህበረሰብ ለሚገጥሙት የጤና እክሎች የባህል ህክምናን እንደ መጀመሪያ አማራጩ ይጠቀማል። በአገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ከ80% በላይ የሚሆነው ማህበረሰብ የባህል ህክምና ተጠቃሚ እንደሆነ የተለያዩ አገር በቀል ጥናቶች ያመለክታሉ።
የምዕራባውያን ባህል ህክምና በምች ለሚመጡ ቁስለቶች በቫይታሚን ሲ የበለጸጉ እንደ ሎሚ፣ ብርቱካን፣ ኪዊ እና ፓፓያ ያሉ ምግቦችን እንድንጠቀም ይመክራል። የአገራችን የባህል ህክምና ደግሞ ዳማከሴ (Ocimum Lamiifolium) የተባለው አገር በቀል ተክል ቅጠሎች ጭማቂ በመጠጣት ወይም ቅጠሎቹን አንድ ላይ በመጨፍለቅ ቁስለቶቹ ላይ በማድረግ እንድንጠቀም ይመክራል። በዳማከሴ (Ocimum Lamiifolium) ጠቅላላ አጠቃቀም እንዲሁም ስለጸረ-ምች አምጪ ተህዋስያን ባህሪያቱ የተደረጉ ጥናቶች ባይኖሩም ስለ አጠቃላይ ጸረ-ህዋስ እና ጸረ-የሰውነት መቆጣት (Anti-inflammatory) ባህሪያቱ የሚያወሱ አንዳንድ የአገር በቀል ጥናቶች ብቅ ብቅ ብለዋል።
ለምች በሽታ ሐኪም ማማከር ተገቢ ነው?
በምች በሽታ የሚመጡ ቁስለቶች በአብዛኛው ጊዜ በራሳቸው የሚድኑ በመሆናቸው የሐኪም ምክር መሻት ላያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን ከታች የተዘረዘሩት ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ጊዜ የሐኪም ምክር ማግኘት የግድ ይላል። የኤች.አይ.ቪ ወይም የካንሰር ተጠቂ ከሆንን፣ የምች በሽታ ቁስለቶች ዓይናችን አካባቢ ከተከሰቱ፣ ከ2 ሳምንታት በላይ ሳይድኑ የሚቆዩ ቁስለቶች፣ የአቶፒክ ደርማታይቲስ (Atopic dermatitis) ታማሚ ከሆንን እና በተደጋጋሚ ቁስለቶቹ የሚያጋጥሙ ከሆነ ሐኪም ማማከር ግድ ይላል።
በህክምና ምን ሊረዱ ይችላሉ?
ሐኪምዎ ቁስለቶቹን አጢኖ ከተመለከተ/ች በኋላ አሳይክሎቪር (Acyclovir) እና ቫልሳይክሎቪር (Valcyclovir) የመሳሰሉ ጸረ-ምች አምጪ ተህዋስ መድኃኒቶችን እንዲሁም የተለያዩ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን ሊያዝልዎ ይችላል። ጸረ-ምች አምጪ ተህዋስ መድኃኒቶቹ በቆዳ ላይ የሚቀቡ ወይም በአፍ የሚዋጡ ሊሆኑ ይችላሉ።
ማሳሰቢያ፦ የምች አምጪ ተህዋሲያን እጅግ ተላላፊ በመሆናቸው የምች በሽታ በሚከሰትብን ጊዜ የፊታችንን እና የእጃችንን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅ ያስፈልገናል። ቁስለቶቹ ባጋጠሙን ጊዜ የምንጠቀምባቸውን የከንፈር ቀለሞች እና ቅባቶች ሌሎች ሰዎች እንዳይጠቀሙ በአግባቡ ማስወገድ ወይም ለይቶ ማስቀመጥ ተገቢ ነው።
ምንጭ፦ ከዶክተር ኦንላይን ገጽ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013