
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ አበባ ፡- መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ ያለምንም መሸማቀቅ በነጻነት የሚመርጡበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንና ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ገለጹ። ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የጸጥታ አካላት ከላይ እስከ ታች ተናበው በመስራት ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው አዲስ ወግ ውይይት ላይ ትናንት ተገኝተው እንደገለጹት፤መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ ያለመሸማቀቅ በነጻነት የሚመርጡበትን፣ ፓርቲዎች በነጻነት የምርጫ ቅስቀሳ የሚያካሂዱበትና ምርጫ ቦርድ ስራውን በተገቢው መልኩ የሚያከናውንበትን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ምርጫ እንዲካሄድ የጸጥታ አካላት ተግባራዊ ሥራ ጀምረዋል።
ሰላማዊ ፣ፍትሐዊና በህብረተሰቡ ዘንድ አመኔታን ያገኘ ምርጫ ለማካሄድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ መራጮች ያለማንም ተጽዕኖ በነጻነት የሚመርጡበትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበትና ደጋፊዎቻቸውን በፈለጉት መንገድ አግኝተው የሚያወያዩበትን፣ ያለምንም ተጽዕኖ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉበትን እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ አካላትም ሕግ የሰጣቸውን ተልዕኮ መፈጸም የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠርና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የጸጥታ አካላት ዝግጅት አድርገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አመልክተዋል። የመራጩን፣የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የምርጫ አስፈጻሚዎች ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የምርጫ ቦርድ አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁሶች በወቅቱ የሚፈለጉበት የምርጫ ጣቢያና ክልል እንዲደርሱ አስፈላጊው እጀባና ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኘ ገልጸው፤ የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ከፌዴራል ፖሊስ ፤ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከብሔራዊ ደህንነት አገልግሎትና ከመከላከያ ሚኒስቴር የተወጣጡ አመራሮች ያሉበት አገር አቀፍ የምርጫ ኮሚቴ ተቋቁሞ የጸጥታ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ እየተሰሩ እንደሚገኙና አበረታች ውጤቶችም እየታዩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እስካሁንም ባለው የምርጫ ሂደት ከላይ እስከ ታች ድረስ የተደራጀ እንቅስቃሴ ቢኖርም ችግሮች አላጋጠሙም ማለት አይቻልም ያሉት አቶ ገዱ፤ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች እጩዎችን በወንጀል ይፈለጋሉ ብሎ የማሰር፣የማሸማቀቅ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ለማድረግ በሚፈልጉበት ጊዜ ያንን ለማደናቀፍ መሞከር፣ እጩ የማስመዝገብ ሁኔታዎችን አልፎ አልፎ የማደናቀፍ ክስተቶች መታየታቸውን አመልክተዋል፡፡
መንግስት ሰላማዊ፣ ነጻና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ገዱ፤ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከምርጫ ቦርድ ጋር በመገናኘት በውይይት የሚፈቱበትን መንገድና በህግ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ደግሞ ተጠያቂ የሚሆኑበትን የአሰራር ሥርዓት እየተበጀ ነው ብለዋል፡፡
ምርጫው ሰላማዊ፣ ተአማኒ፣ፍትሐዊ እንዲሆን የጸጥታ አካላት ከላይ እስከ ታች ተናበው መስራት መጀመራቸውን ያመለከቱት አማካሪው፣ ይህ ጅምር በሂደት እየተጠናከረ ይሄዳል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ገዱ ገለጻ፤ መገናኛ ብዙኃን መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ ያለምንም መሸማቀቅ የሚመርጡበትን፤ ፓርቲዎችም ሀሳባቸውን በነጻነት የሚያቀርቡበት ሁኔታ በማስተማርና በማንቃት ሕዝቡን ወደ ትክክለኛ መንገድ የመምራት ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
በዓለም አቀፍ ተቋም የመረጃ ማጣሪያ ባለሙያ ኤደን ብርሀኔ እና የመገናኛ ብዙኃን ተኮር የሕግ ባለሙያ ሰለሞን ጎሹ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዲስ ወግ ውይይት ላይ፣ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች በምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ይህን ተጽዕኖ ለመከላከልና ለማክሸፍም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የዜና ምንጮችን ማጣራት፣የመረጃውን ትክክለኝነት ከማጋራት በፊት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ፣ለዚህም የመረጃዎችን እውነትነት የሚያረጋግጡ ተቋማትን ማቋቋም እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም