ፍሬህይወት አወቀ
የኢትዮጵያዊነት መለያ የሆነው የሀገር ባህል አልባሳት ወይም ሐበሻ ልብስ ድሮ ድሮ በባህላት ቀን እና በእምነት ቦታዎች ብቻ ይዘወተር እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና ዛሬ ዛሬ ለፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎች ምስጋና ይግባቸውና ከበዓላትና ከእምነት ቦታዎች ውጭ ባሉ ማንኛውም ቦታና በተለያዩ መድረኮች ላይ መለበስ መቻሉ የዘርፉን ዕድገት ያሳያል። ይህ በስብሰባዎች ጭምር መለበስ የተጀመረው የሀገር ባህል ልብስ ጥቂት በማይባሉ ዲዛይነሮች ሸሚዝ፣ ቀሚስ፣ ሻርፕ፣ ሱሪ፣ መጋረጃ፣ አልጋ ልብስና ጋቢ… ሆነው ሲመረቱ ይታያል።
እኛም በዘርፉ ሰልጥነው የተለያዩ የሀገር ባህል አልባሳትን በተለያዩ የፋሽን ዲዛይን በመሥራት 29 ዓመታትን ያስቆጠሩት የፓራዳይዝ ፋሽን መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ገነት ከበደ ለዛሬ የስኬት እንግዳ አድርገን አቅርበናቸዋል። ወ/ሮ ገነት በዘርፉ በቆዩባቸው ዓመታት እንዴት ስኬታማ መሆን እንደቻሉና በቀጣይም ስላለቸው ራዕይ እንዲሁም ዘርፉን በማሳደግ ሀገሪቱ መጠቀም የሚገባት ያህል እንድትጠቀምና ምርቶቹን ለውጭው ዓለም በማስተዋወቅ ሐበሻ ልብስ የኢትዮጵያዊነት መለያ መሆኑን ማጉላት እንደሚገባ አጫውተውናል።
ወሎ ሰፈር አካባቢ ከሚገኘው ፓራዳይዝ ፋሽን የደረስነው ገና በጥዋቱ ነበር። ቦታው የሀገር ባህል ማምረቻና መሸጫ ነው። አራት የሚደርሱ አነስተኛ ክፍሎች አሉት። ክፍሎቹ በሙሉ በተለያዩ ፋሽን በዲዛይን በተዋቡ አልባሳት ተሞልተዋል። በቀዳሚነት ከሚገኘውና ሰፋ ካለው ክፍል ውስጥ ስድስት የሚደርሱ የመስፊያ ማሽኖች አሉ። ከዚህ ሰፋ ካለው ክፍል ውጭ ባሉት ሶስት ክፍሎች ግድግዳ ላይ ደግሞ ዓይን ያዝ የሚያደርጉ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችና ሽልማቶች ተኮልኩለዋል። በሥራቸው ያገኙት ዕውቅና ለመሆኑ ጥርጣሬ ባይኖረንም ጠየቅናቸው። እርሳቸውም በተለያየ ጊዜ በሚደረግ ውድድር አሸናፊ በመሆን ያገኟቸው ከ50 በላይ የሆኑ ሽልማቶችና የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ስለመሆናቸው አስረድተው አብዝኛው ዕውቅና ያገኙት ከውጭ አገራት መሆኑን አስረዱን ።
ትውልድና ዕድገታቸው አዲስ አበባ ከተማ የሆኑት ወይዘሮ ገነት፤ ትምህርታቸውን በናዝሬት ትምህርት ቤት የአርት ወይም የስዕል፣ የግብረገብ፣ የቋንቋ እና የልብስ ቅድ ዲዛይን ትምህርት ይማሩ እንደነበር በማስታወስ ትምህርት ቤቱ ዛሬ ላይ ለያዙት የፋሽን ዲዛይን ሙያ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያነሳሉ። በወቅቱም ትኩረታቸው የአልባሳት ቅድ ላይ በማድረግ የእጅ ሥራ ትምህርትን አብልጠው ይወዱ ነበር። ይሁንና በባሕል ልብስ ፋሽን ይበልጥ የተሳቡት ግን ሲዳሩ በተዘጋጀላቸው የሀገር ባህል የመልስ ልብሳቸው ነው። ከልብሱ ውበት በበለጠ በወቅቱ አንቱ የተባሉ የሀገር ባህል ልብስ በፋሽን ዲዛይን የሰሩላቸው እማማ ጽጌ ያደርጉት የነበረውን ጥንቃቄ ዛሬም ድረስ ያስታውሱታል።
የመልስ ልብሳቸውን የሰሩላቸው የወቅቱ የፋሽን ዲዛይነር እማማ ጽጌ በሰሩላቸው ልብስ ወደ ዘርፉ ይበልጥ ተስበዋልና ልብሱን ለመሥራት የተጠቀሙትን ዘዴ፣ ልኬትና እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ዛሬም ድረስ በህሊናቸው የሚታያቸው መሆኑን ያነሳሉ። በወቅቱ የተዘጋጀላቸው የመልስ ልብስም በሕይወታቸው ትልቅ ቦታ እንደነበረውና ከዛን ጊዜ ጀምሮ በፋሽን ዲዛይን ሥራ ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ ጉጉት ያደረባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
በትዳር ምክንያት ከሀገራቸው ውጭ በሄዱበት አጋጣሚ የፋሽን ዲዛን ትምህርታቸውን አርጀንቲና እና ጣልያን ሀገር በመማር ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በዘርፉ የመሥራት ዕቅድ ወጠኑ። የተማሩትን ትምህርት በተግባር ለማሳየት ከፍተኛ ጉጉት አደረባቸው። በመልስ ልብሳቸው ውስጣቸው የቀረውን የሀገር ባህል ዲዛይን ለማውጣት የፋሽን ዲዛይን ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የተመረቁበትን ቀን ተጠቅመውበታል። ትምህርታቸውን ባጠናቀቁበት ወቅት በነበራቸው የሐበሻ ጨርቅም ለምርቃታቸው ቀሚስ ሠርተው መልበስ ችለዋል።
በወቅቱ የነበራቸውን የሐበሻ ጨርቅ ተጠቅመው በሰሩት ዲዛይን በዙሪያቸው የነበሩ ሁሉ ወደዱላቸው። ይህን የተረዱት ወይዘሮ ገነትም ወደ ሀገሬ ሄጄ መሥራት አለብኝ ብለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ቅጽበትም ዘርፉን ተቀላቅለው ሥራቸውን ጀመሩ። ለሥራው ያስፈልጋቸው የነበረው መነሻ ካፒታል ጥቂት የነበረና ዘርፉን በቀላሉ መቀላቀል ይቻል እንደነበር ያስታውሳሉ። ሸማኔው የተጠበበትን የሀገር ባህል ልብስ በተለያዩ ዲዛይን መሥራት በጀመሩበት ወቅት ከውጭ የመጡ ሰዎች ኤግዚብሽኖችን ያሳዩ ስለነበር ሥራቸውን የማሳየት ዕድል አግኝተዋል።
ያገኙትን ዕድል በመጠቀም የሚሰሩት ፋሽን ልብስ ባሳዩበት አጋጣሚ ሁሉ ፍላጎቱ እጨመረ መጣ። የሰዎችን ጥሩ አቀባበል የተመለከቱት ወይዘሮ ገነት ሥራውን ይበልጥ በፍቅርና በትጋት መሥራት ጀመሩ። በመኖሪያ ቤታቸው ሲሰሩ የነበረው ሥራ ፍላጎቱ እየጨመረ በመምጣቱ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ መቀየር ያለባቸው መሆኑን በመረዳት ቤት ተከራይተው ሠራተኞች ቀጥረው ሊሰሩ ግድ ሆነ። የዛሬ 29 ዓመት ወደ ዘርፉ ስገባ የነበረው ተቀባይነትም ሆነ ሀገርን የማስተዋወቅ ዕድሉ ከፍተኛ ነበር። ይሁንና የሀገር ባህል ልብስ በተለያዩ የፋሽን ዲዛይን ተደርገው በባለሙያዎች ቢሰሩም ዘርፉ በሚፈለገው መጠን አለማደጉን ይናገራሉ።
የሀገር ባህል ወይም ሐበሻ ማለት የኢትዮጵያውያን ብቻ የሆነና መለያ እንደመሆኑ ሀገር የሚያስጠራ ዘርፍ ነው። ይሁንና አሁን ያለው ነገር ግን ሽመናን በሚገባ በማስተዋወቅ ልንጠቀምበት አልተቻለንም። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ የሆነውን ሽመናን አጉልቶ በማውጣት ሀገሪቱ ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም። ለዚህም ሽመናን በዘመናዊ መልክ መያዝ ባለመቻሉ ነው፤ ይህ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ሽመና በሚገባ ማሳደግ ከተቻለ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይቻላል። በተለይም አልባሳቱ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ማሳደግ ይቻላል ይላሉ።
ኢትዮጵያዊ በሆነው የሽመና ጥበብ ተጠቅመው የተለያዩ የዲዛን በመሥራት በማንኛውም ጊዜና ቦታ መለበስ እንዲችል አድርገው የሚሰሩት ወይዘሮ ገነት ለአራት ዓመታት ያህል ለአየር መንገድ የአስተናጋጅ ሠራተኞች ሠርተው ያቀርቡም ነበር። በሥራቸው እጅግ ደስተኛ እንደሆኑት ሁሉ ሰዎችም አልባሳቱን በደስታ ያሰራ እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን በአሁን ወቅት ለባህል አልባሳቱ ግብአት የሚሆነው ዋናው ክር በሚፈለገው መጠንና ጥራት ባለመገኘቱ ምክንያት የአልባሳቱ ዋጋ እጅግ ተወድዶ ደንበኞች እየሸሹ ነው። ከዚህም በላይ የባህል አልባሳቶቻችን በቻይና ሻማ እየተለጠፉ በመምጣታቸው ኢትዮጵያዊ የሆነው ሐበሻ ባህሉን መልቀቁ የሚያሳዝናቸውና የሚያስቆቻቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህ የሆነበት ምክንያትም ዘርፉን መንግሥት የረሳው በመሆኑ ነው። መንግሥት ኢትዮጵያዊ ብቻ የሆነውን ሽመና በዘመናዊ መንገድ እንዲመራ ጥረት ማድረግ አለበት። ባለሙያው ብቻውን ቢለፋ ውጤት የለውም በማለት ከዘርፉ ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆን ያስፈልጋል። አሁን ላይ የፋሽን ዲዛይን ሥራውን ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ ባለሙያዎች በተቻላቸው አቅም እየሰሩ ቢሆንም ዋጋው እጅግ ከመናሩ የተነሳ ፈላጊውን እየገፋው እንደሆነ ያነሳሉ። ይሁንና መንግሥት በግብአቱ ላይ ያሉትን ችግሮች መፍታት ከቻለ ሀገራዊ የሆነው የሀገር ባህል አልባሳት በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ ይችላል። ለበርካታ ዜጎችም ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ረጅም ሰንሰለት ያለው ዘርፍ መሆኑን ወይዘሮ ገነት ያስረዳሉ።
በአሁን ወቅትም ጉለሌ አካባቢ በመንግሥት የተደራጁ ሸማኔዎች በሽመና ሥራ ላይ ተሰማርተዋለ። ለሚያመርቱት አልባሳት ሸማውን ከእነዚሁ ሴቶች ይገዛሉ። የገዙትን ሸማም ደንበኞቻቸው በሚፈልጉት የፋሽን ዲዛይን ሠርተው ያቀርባሉ። እንዲህ አይነት የገበያ ሰንሰለት ቢኖር ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻልም አንስተዋል። የሸማ ሥራ በርካታ ባለሙያዎችን የሚጠይቅና ሰፊ የገበያ ሰንሰለት ያለው ሲሆን ፓራዳይዝ ፋሽንም ከ20 በላይ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ የነበረና በአሁን ወቅት ግን ከገበያው መቀዛቀዝ እንዲሁም ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለ13 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ እየሠራ ይገኛል።
በአሁን ወቅት ያለው የሀገር ባህል አልባሳት የዋጋ ንረት በዋነኛነት ከግብዓት አቅርቦት እጥረት የመጣ መሆኑን የሚያነሱት ወ/ሮ ገነት፤ ካለፈው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ግን ሸማኔው ተጠቃሚ እየሆነ መሆኑንና ማንኛውንም ሥራ ሲቀበሉ በቅድሚያ ሸማኔውን በማነጋገር ሸማኔው በሚሰጠው ዋጋ ላይ ተመስርተው መሆኑንና የአንድ ልብስ 80 በመቶ የሚሆነው ዋጋ የሸማኔው ነው። ይሁንና አንድ ልብስ ተሰርቶ እስኪቀርብ ድረስ ያለውን ሂደት ደንበኞች የሚያውቁበት አሰራር ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ በአብዛኛው ለዋጋው መወደድ ዲዛይነሮች ምክንያት እንደሆኑ የሚነገር መሆኑንና ይህም ትክክል እንዳልሆነ ያነሳሉ።
ሽመና በቴክኖሎጂ አልተደገፈም፤ መንግሥትም ዘርፉን አልተመለከተውም የሚሉት ወ/ሮ ገነት፤ ዘርፉ በሚገባ ከተሰራበት በከፍተኛ ወጪ አልባሳትን ዛሬም ድረስ ከውጭ ከማስገባት መዳን እንደሚቻልና ወደ ውጭ በመላክም የውጭ ምንዛሪ ለመሳብ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው ። ለአብነትም ህንድ በሽመና እየሰሩ ዛሬ በዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በሽመናው ላይ ጠንካራ መሰረት መጣል ከተቻለ ዘርፉ ሊያድግ የሚችል ዘርፍ ነው። ነገር ግን አልተሰራበትም በዘርፉ ያሉት ባለሙያዎችም ሞያውን ስለሚወዱት ብቻ የሚሰሩት እንደሆነ አስረድተዋል። በተለይም ባለስልጣኖች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የአካባቢውን ባህል የሚያንፀባርቁ የሀገር ባህል አልባሳት በዘመናዊ መልክ ተዘጋጅቶ ይለብሳሉ። ነገር ግን ከመልበስ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው በማሰብ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመድ ማድረግ ቢችሉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሚና ይኖረዋል።
ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማሳደግ ሲቻልም ዛሬ ከየተቋሙ ተመርቀው ለሚወጡ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል። በተለይም ሀገርን የሚሳድግና የሚያኮራውን ዘርፍ አጥብቀን በመያዝ ልንጠቀምበት ይገባል። ይህም ሲባል ዛሬም ድረስ ሽመና በእንጨትና በብረት ይሠራል። የሽመና ጨርቅ ጥራትንም በሚመለከት የክር ፋብሪካዎች ምን እየሠሩ እንደሆነ ማየት ተገቢ ነው። ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ›› እንደሚባለው መንግሥት ከባለሀብቱ ጋር በጋራ ቢሰራ ዘረፉን ማሳደግና መለወጥ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ያስረዳሉ ።
በሽመና ውስጥ ከሚስተዋለው የግብዓት ችግር በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ የጎዳው ቢሆንም አንዳንድ ችግሮች የሥራ አማራጭ ሲሆኑ ይታያል። ፓራዳይዝ ፋሽንም የኮሮና ቫይረስ መከላከያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሲያመርት ነበር። በወቅቱ ከ30 እስከ 40 ሺህ የሚደርስ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማምረት ለበርካታ ደንበኞች አቅርበዋል። አሁንም በሸማ ጨርቅ ቀለል ያሉና የማይሞቁ ጭምብሎችን እየሰሩ ወደ ውጭ ለመላክ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
በቀጣይም የሀገር ባህል አልባሳቱን ለውጭው ዓለም ምቹ በሆኑ ዲዛይኖች እያመረቱ ለመላክ ዕቅድ ያላቸውና ሥራውን የጀመሩት እንደሆነ የጠቆሙት ወይዘሮ ገነት ይህም ሀገርን በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ድርሻ ያለው ነው ይላሉ። ፓራዳይዝ ፋሽን በ29 ዓመት የሥራ እንቅስቃሴው በአነስተኛ ካፒታል ተነስቶ በአሁን ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠር ሐሴት ማፍራት ችሏል።
በፓራዳይዝ ፋሽን በሸማ ጨርቅ የማይሰራ ነገር የለም የሚሉት ወ/ሮ ገነት፤ የተለያዩ የሀገር ባህል አልባሳትን በዘመናዊ መልክ እያመረቱ ለሀገር ውስትና በመጠኑም ወደ ውጭ ይልካሉ። በዚህም መሰረት አንድ የአንገት ልብስ ወይም ሻርፕ ከ350 ብር ጀምሮ የሚገኝ ሲሆን፤ የሠርግ ልብስ ከ10 እስከ 15 ሺህ ብር፣ መጋረጃ አንዱ ነጠላ ከ500 እስከ አንድ ሺህ ብር እንዲሁም ጋቢ እስከ 2,000 ብር ይሸጣል።
የሀገር ባህል አልባሳት የኢትዮጵያ ትኩረት ይስጡት፤ ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ምርቶቻችንን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ እናግኝ በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት መቋጫ አደርገን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013