ግርማ መንግሥቴ
የዲሞክራሲ ምድርና ሰማይ ከተላቀቁ ጀምሮ “ፓርላማ” ወይም “የተወካዮች ምክር ቤት”፣ “ምርጫ”፣ “ተሳትፎ” ወዘተ የሚባሉት ጽንሰ-ሐሳቦች እንደ ዘወትር ፀሎት ከ”ምእመን” ወይም ከፖለቲከኞች ምላስና ከንፈር ላይ አይጠፉም። ሁሌም መፅናኛ፣ መፎከሪያ፣ መደለያና መደላደያ ናቸው። ይህ እንግዲህ ከዛሬ 200 ዓመት በፊት ጀምሮ መሆኑ ነው። እያለ እያለ ወደ አሁኑ ዘመን ሲመጣ ደግሞ ጉዳዩ የእኛን ጨምሮ የበርካታ አገራት ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን።
ጉዳዩ በጉዳይነት ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ወደ ተግባርም ተሸጋግሮ ብዙዎችን ሲያነጋግር ነው የኖረው፤ ወደፊትም ስለመቀጠሉ አጠራጣሪ አይሆንም። በመሆኑም መወዛገብ፣ መነዛነዝ፣ መጨቃጨቅ ወዘተ በፓርላማ አዲስ አይደለም፤ አዲስ አይሆንም፤ አዲስ ሊሆንም አይገባም – ለህዝብና ለአገር ጥቅም ብቻ እስከሆነ ድረስ፤ በጥብቅ ፓርቲ ዲሲፕሊን እስከተመራ፣ በውስጠ ዲሞክራሲ እስከተዳደረ ድረስ።
ይህ መንደርደሪያ ወደ ሰሞኑ የአገራችን ፓርላማ ውሎ ለመምጣት ያገለግል ዘንድ ታስቦ ስለመሆኑ በራሱ ይናገራል። መጋቢት 14 ቀን የነበረው የፓርላማ ውሎና የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ምላሽ (ማብራሪያ) ም እንደዚሁ ከዚሁ ጋር አንድና ተያያዥ ነውና ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።
ለነገሩ ወትሮም ቢሆን ፓርላማ ከሚዲያ መንጋጋ ወጥቶ አያውቅም፤ ሚዲውም እንደዛው። በመሆኑም ሁለቱ ስለሁሉቱም ዝምብለው አያውቅም።
ቅድመ ለውጥ ሚዲያውን ሲያናግሩት የነበሩት ከ”የፓርላማው ዝምታ” እስከ “ፓርላማው ጥርስ አወጣ” ድረስ ያሉት ተቃራኒ አተያዮች ነበሩ። ከለውጡ ወዲህ ደግሞ ብዙም እዚህ ግባ ያልተባለ፤ ሕጎችን፣ አዋጆችን ወዘተ ከማሻሻል ያላለፈ፤ ስለ ጁንታው ይግባ/ይውጣ፣ ይመለስ/ይሂድ ወዘተ አይነት ተግባራት ካልሆኑ በስተቀር ጥርስ ስለ ማውጣቱ የተባለ ነገር አልተሰማም።
አገር ስትናጥ ስለመክረሟ ፓርላማው በደንብ ያውቃል፤ አንዱ በአንዱ ላይ ስለመነሳቱና እዚህም እዚያም ወከባ በወከባ ስለመሆኑና ንፁሐን ስለመሰቃየታቸው ፓርላማው ከማወቅም ባለፈ አባላቱ እያለቀሱ እስከመናገር ድረስ የሄዱበት ርቀት ሁሉ ነበርና የፓርላማው እውቀት ጥግ ድረስ ነው “ብሎ ማለት የሚቻልበት ሁኔታ ነው ያለው።”
የአሁኑን፤ የሰሞኑን የፓርላማ ውሎ ከወትሮዎቹ አቻዎቹ ለየት የሚያደርገው አንድ አቢይ ጉዳይ ቢኖር ከቁመናው ይልቅ የመልኩ ጉዳይ ሲሆን፤ እሱም ማንን የመምሰሉ፤ የፊነኛነቱ ጉዳይ ነው።
በዓለም ታሪክም ሆነ በጽንሰ ሐሳቡ ፍልስፍና መሰረት ከሄድን ፓርላማ ወይም የተወካዮች ምክር ቤት በመልኩ መምሰል ያለበት የወከለውን ህዝብ ነው፤ በቃ። ከዛ ውጭ ሌላ ሊመስል አይችልም። ከመሰለም ድብን ያለ ስህተት ሲሆን፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ወይ ወካይ ወይ ተወካይ ተሳስተዋልና ጉዳዩ ያነጋግራል፤ ያወያያል ማለት ነውና እኛም ልክ ነን።
በሰሞኑ የፓርላማችን ውሎ በርካታ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን የአብዛኛዎቹ ሐሳቦች መነሻ ፓርላማው ያነሳቸው ሳይሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ያነሷቸው ሐሳቦች ናቸው። ከዶክተር አቢይ ማብራሪያ ብዙ ነገር ሰምተናል፤ ብዙ ነገር ታዝበናል፤ ብዙም ነገር አድንቀናል። በፓርላማው ከተነሱት ግን ብዙም ነገር አላደነቅንም፤ ብዙም ነገር አላወቅንም፤ ብዙም ነገር አልሰማንም። የሰማነው አንድ ጮክ ያለ ነገር ቢኖር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚለው ወደ አካባቢና መንደር ወረድ በማለት የውይይቱን ጠርዝና ደርዝ እዛው አካባቢ ለማድረግ የተሞከረበት ሁኔታ የነበረ መሆኑን ሲሆን፤ ይህም አባላት እንደ አጠቃላይ፤ በድምሩ አገራዊ መልክና ቁመና ከመያዝ ይልቅ የምኔን ብተው . . . እንደተባለው፤ ተመልሰው እዛው መሆናቸውን ያሳዩበት ሁኔታ መኖሩን ነው ያየነውና ያነጋግራል ስንል ዝም ብለን አይደለም።
እዚህ ላይ መነጋገር ያስፈለገባቸው አንኳር እውነቶች ብዙ ቢሆኑም ዋናው ጉዳይ ግን አንድ ነው። በፓርላማው የሚነሱ ጉዳዮች፣ ቤቱ የ”ተወካዮች” እስከሆነ ድረስ፤ በመልክ ከአንድ መመሳሰል ካለባቸው አካል ጋር መመሳሰል ያለባቸው መሆኑ። ወይ የወከላቸውን ህዝብ፣ ወይም የሚቆጣጠሩትን መንግሥት፤ አሊያም ያልወከላቸውንና የማይቆጣጠሩትን አካል። ለጊዜው ሌላ መልክ እውቅና አላገኘምና በእነዚሁ ላይ እንነጋገር።
በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር በቅድሚያ በፓርላማው አባላት ከተነሱት፤ ፊነኛነትን ያመላከቱ ሀሳቦች ከመጀመር ይልቅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ውስጥ ከተነሱት መጀመሩ ባይቀልም አይከብድምና ከእሱው እንጀምር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከሰጡት ዘለግ ያለ ማብራሪያ በአብዛኛው ስሜታቸውን የኮሰኮሰው ከብሔር ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የተነሳው ሀሳብ ነው ብሎ “አቅጣጫ ማስቀመጥ” ይቻላል።
ይህ በእሳቸው አንደበት “ካንሰር” ተብሎ የተገለፀው የብሔር ፖለቲካ ለማንምና ለምንም “የማይጠቅም ሲሆን ከዚህ አይነቱ ካንሰር በሽታ ካልተላቀቅን ለችግሮችቻችን ምንም አይነት መፍትሄ ይዘን ልንመጣ አንችልም።” ይህ እኛ ከመምጣታችን በፊት ጀምሮ “አብሮ ተዋልዶና ተዋዶ የኖረን ህዝብ ዛሬ አንተ አማራ ነህ፤ አንተ ኦሮሞ ነህ” … ብንለው ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም። የሚሻለው ከዚህ ወጥተን በአንድ ላይ ይህችን አገር ካለችበት ችግር ማውጣትና ወደ ብልጽግና ማድረስ ነው።
እዚህ ላይ ነገሩን በገደምዳሜው ይህን ያህል ካነሳነው በቂ ነውና ወደ “የፓርላማው መልኮች” እንመለስ።
ቀደም ሲል በመግቢያችን እንዳነሳነው “የፓርላማው መልኮች” መምሰል ያለባቸውና መምሰል የሌለባቸው መልኮች እንዳሉት ተመልክተናል። መምሰል ካለባቸው አንድም የወከላቸውን ህዝብ፤ አልያም የሚቆጣጠሩትን መንግሥት። ሁለቱንም ካልመሰሉ ደግሞ ሁለቱንም አይደሉምና ጉዳዩ ሌላ መልክ ከመያዝ ወደ ኋላ አይልም።
በዚህ፣ ቀደም ሲል በጠቀስነው የፓርላማ ውሎ የተወሰኑ አባላት በመልክ ሁለቱንም ሲመስሉ አላየናቸውም። መንግሥትን ይመስላሉ እንዳንል መንግሥትን እንደማይመስሉና ከዚህ አይነቱ ካንሰር መላቀቅ እንዳለባቸው ተነግሯል፤ ህዝብን ይመስላሉ እንዳንል ህዝቡ የሕግ የበላይነትን ሻተ እንጂ በብሔርና ዘር ሸንሽናችሁኝ ተነጋገሩብኝ አላለም። ስለዚህ የፓርላማው መልክ የማንን ይመስላል? ብንባል የማንን ልንል ነው ማለት ነው።?
ከጥንት ጀምሮ ስናየው እንደኖርነው የሌላው አገር ፓርላማ መልኩ ቁርጥ አገሩን፤ ህዝቡን ነው። ለምሳሌ የእንግሊዝ ፓርለማ ቁርጥ እንግሊዝንና እንግሊዞችን ነው። ከወግ ጠባቂነት እስከ ወግ አጥባቂነቱ ድረስ ያለው መልኩ ቁርጥ እነዛኑ ወግ ጠባቂና ወግ አጥባቂዎቹን እንጂ ሌላ አይደለም። “ምሰለን” ብሎ የሚማፀነው ቢኖር እንኳ የእንግሊዙ ፓርላማ ለመምሰል ፍቃደኛ አይደለም። ከፈለጉ እሱን ይምሰሉ እንጂ እሱ እነሱን ለመምሰል አልተፈጠረምና አያደርገውም።
መቸም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከዚህ ካንሰር ተላቀቁ”፣ “ከዚህ አይነቱ የመንደር ፖለቲካ ውጡ” … ሲሉ ተማፅነዋልና፤ ሲማፀኑም ሰምተናልና የፓርላማው መልኩ እሳቸውን ስላለመምሰሉ ከአዚህ ሌላ ማስረጃ የለም። የኢትዮጵያ ህዝብም እባካችሁ በዘርና ዘር ማንዘር አታጫርሱኝ ሲል እንጂ የሚሰማው በተቃራኒው አይደለምና ከፓርላማው መልክ ጋር አይገጥምም። ታዲያ የፓርላማው መልክ ከወዴት የመጣ ነው ብሎ ማለት ይቻላል?? ነው ወይስ እንደ ውሃ “መልክ የለሽ” (ከለርለስ) ነው? አይደለም።
መቸም ዓለም እንደሚያውቀው በአንድ አገር የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ወዘተ ህይወት ውስጥ ፓርላማ ትልቁን ቦታ የሚይዝ ተቋም ነው። በመሆኑም ግዙፍ ተግባርና ሃላፊነቶችን ተሸክሟል።
ይሁን እንጂ አንዳንዴ ከሚጠበቀው በላይ እንደሚገኝ ሁሉ፤ አንዳንዴ ከሚጠበቀው በታችም የሚገኝበት አጋጣሚ አለ። ሁለቱም የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከቀጣዩ ቀዳሚው ይመረጣልና ሁለተኛው ብዙም አይደገፍም። ይሁን ቢባል እንኳን ደርዝ አለውና ከደርዙ እንዲጠብ አይፈለግም።
ሚዲያውን፤ በተለይም ድሮም ጠብ ያለሽ በዳቦ የሆነውን ማህበራዊ ሚዲያ ለዚህ ሁሉ የሰሞኑ ውዝግብና እሰጥ አገባ ይዳረግ ዘንድ አጀንዳ ያቀበለው፤ የሳምንቱ መጨረሻና መሸጋገሪያ ቀናት ጋዜጦች ልዩ ትኩረታቸውን ወደ እዚሁ ወቅታዊና በማንም ያልተጠበቀ ጉዳይ ብቻ እንዲያዞሩ ሁኔታዎችን “ያመቻቸው”ን የመጋቢት 14 ቀን 2013 አ.ም የፓርላማ ውሎ እዚህ አንስተን ስንነጋገር አላማችን ግልፅ ሲሆን፤ እሱም የፓርላማ ተግባርና ሃላፊነት በሚመጥነው መልኩና ልኩ እንዲከናወን፤ የሚጠበቅበትን አገራዊ ሃላፊነት እንዲወጣ ለማንቃት ሲሆን እግረ መንገዳችንንም ለወደፊቱ ከከፋ ስህተት እንዲቆጠብ ለማስታወስ ነው።
ሰሞኑን በሰሜን ሸዋና ከሚሴ አካባቢ የተስተዋለውን የሰላምና ደህንነት መናጋት፤ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት መቀጠፍና ንብረት መውደምን ተከትሎ ጉዳዩ በፓርላማ ተነስቶ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ተደረገ። ምንም እንኳ አገሪቷ ከገጠሟት በርካታ ፈተናዎች አኳያ እዚህ ግባ የሚባሉ ሀሳቦች ተነስተዋል ባይባልም፤ የሰሜን ሸዋው ቀውስ ግን የመነሳት እድል ገጥሞት ነበር።
በሰሜን ሸዋና ከሚሴ አካባቢ ተከስቶ ለነበረው ቀውስ እንደ አገር ችግሩን የጋራ አድርጎ በመውሰድ መፍትሄው ላይ መረባረብን የሚጠይቅ ሀሳብ ይነሳል፤ ለአንድ አላማና ተግባር ይሰለፋል ተብሎ ከሚጠበቀው ገዥ ፓርቲ፤ በፓርቲው ውስጥ ለሚንሸራሸረው ሀሳብ ፍልስፍናዊ ወጋኝነት ይስተዋልበታል ተብሎ ከሚጠበቅ አካል በተንሸራተተ መልኩ ጉዳዩን የሁለት ብሔሮች አድርጎ በማቅረብ የፓርላማው መልክ እንዲጠይም፤ የአባላቱም አቋምና ተጠሪነት “ለህሊናቸው፣ ለሕገ- መንግሥቱ እና ለመረጣቸው ህዝብ” መሆኑ እንዲሰል አድርጎት አልፏል።
የነበረው ሁኔታ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገው ሀሳቡን የማምከን ሙከራ እንዳለ ሆኖ፣ ከአገራዊ፣ ህዝባዊና ሕገ-መንግሥታዊነት ይልቅ ለራስ ብሔር የመቆም ዝንባሌን የመሰለ አቋምን የሚያንፀባርቅ (በማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ቋንቋ “አንጃ” (ፋክሽን) የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ – ተፈጥሮ ካልሆነ ማለት ነው) ነበር። “አቋም” (ስታንድ) በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ ከንባብ ልምዳችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ በአንድ ፓርቲ ውስጥ (ለምሳሌ በብልጽግና)፣ ችግሮችን በውስጥ ተነጋግሮ፣ ተጨቃጭቆና ተፋጭቶ በመፍታት፣ የጋራ አቋም ላይ የመድረስ (ቢያንስ ዝንባሌው) ከሌለ፤ የጋራ አላማን ከግብ ለማድረስ ይቻል ዘንድ የጋራ ተግባር ከሌለ፤ ፓርቲው ለሚያራምደው ፍልስፍና (ለምሳሌ “መደመር”) ውገና ካልታየ፤ የተከበረው መድረክ የዘውጌነት ማቀንቀኛ፣ የብሔር ማጠንጠኛ፣ የቡድን ፍላጎት መወሰኛ ከሆነ፤ የሚነሱ ሀሳቦች፣ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መድረኩንም ሆነ ውክልናውን የማይመጥኑ ከሆነ ወዘተ አይደለም የፓርላማ የሰው ልጅ መልክም ሊለዋወጥ ይችላልና ጉዳዩ ሳይደርቅ በእርጥቡ፣ ሳይርቅ በቅርቡ – – – ያሰኛል።
ተግባሩን በተመለከተ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎችና ተቆርቋሪ ወገኖች እንደሚሉት የተፈፀመው ስህተት ከሕግም፣ ከፖለቲካም፣ ከሞራልና ሥነምግባር አኳያ ሲመዘን “አሳፋሪና ምክር ቤቱን የማይመጥን ነው።” በመሆኑም ይህንን ድርጊት የፈፀሙ አካላትም ሆኑ “ምክር ቤቱ ህዝብንና መንግሥትን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ” ይገባቸዋል።
እንደ አንዳንድ ጥናቶች ከሆነ ይህ አይነቱ ስህተት ምንጩ የምክር ቤቱ አባላት ሳይሆኑ የእራሱ የገዥው ፓርቲ ተፈጥሮ ነው።
የካቲት 12 እና 13/2013 ዓ.ም የፓርላማውን የሥራ ሃላፊነትና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚኖረውን ድርሻ በተመለከተ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ በርካታ ጥናቶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን አንዱም በአምቦ ዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህሩ አቶ ሰለሞን ተፈራ የቀረበው ጥናት ነው።
እንደ አቶ ሰለሞን ጥናት “የገዥው ፓርቲ ተፈጥሮ የፓርቲ ሥነምግባር በፓርላማው ሥራ ላይ ጫና” ያሳድራል።
“በሕገ መንግሥቱ መሰረት አንድ የፓርላማ አባል ተጠሪነቱ ለሕገ-መንግሥቱ፣ ለህዝቡና ለህሊናው ቢሆንም የፓርቲ አባል በመሆኑ ብቻ የፓርቲውን አላማ ለማስፈፀም ይገደዳል።” የሚለው የአቶ ሰለሞን ጥናት ሳይውል ሳያድር በተግባር ሊታይ የቻለ መሆኑን ማወቅ ተችሏልና መሻሻል ያለበት አሰራር፣ አካሄድ፣ አተያይ ካለ አሁኑኑ ሊሻሻል ይገባዋል። በጥናቱ የተደረሰበት ድምዳሜን በተመለከተም ከመጋቢት 14ቱ የፓርላማ ውሎ በላይ ማረጋገጫ የለምና ልብ ያለው ልብ ሊለው ይገባል።
እዚህ ላይ በአንድ ገዥ ፓርቲም ሆነ በፓርቲው ውስጣዊ አሰራር ውስጥ ጠንካራ የፓርቲ ዲሲፕሊን ሊኖር እንደሚገባ፤ አባላት የውስጥ ችግሮቻቸውን እዛው ተነጋግረው እንዲፈቱ ወዘተ የሚያሳስቡ አስተያየቶች በየዘመናቱ ይደመጣሉ። ብልህ ይጠቀምባቸዋል፤ ያልገባው ደግሞ ሁሌም ሲጎዳባቸው ይስተዋላል። አንዱን እንጥቀስ።
በ1957 የሶሻሊስት አገራት ፓርቲዎች ተሰብስበው ባወጡት የጋራ መግለጫ ውስጥ ከሰፈሩት ሀሳቦች መካከል አንዱ “ማርክሲስት የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳዮችን በሚመረምርበት ጊዜ በዲያሌክቲክስ እና በማቴሪያሊዝም ላይ ካልተመሰረተ የሚኖረው ውጤት ትክክል ያልሆነ እና በስሜታዊነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያደርጋል፤ የሰዎች አስተሳሰብ ሳይዳብር እዚያው እነበረበት ቦታ ላይ እንዲዳክር፤ ነገሮችንና እና ክስተቶችን በሚገባ የመተንተን ችሎታ እንዳይኖር፤ የበራዥነት እና የቀኖናዊነት ስህተቶች፤ የፖሊሲ ስህተቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ተግባራዊ የሆኑ ሥራዎች በሚከናወኑበት ጊዜ እንደዚሁም ለፓርቲው ካድሬዎች እና ለሰፊውም ህዝብ በማርክሲዝም-ሌኒኒዝም መንፈስ ላይ በመመስረት ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ ዲያሌክቲካዊ ማቴሪያሊዝምን በሥራ ላይ ማዋል ለኮሚኒስቶች እና ለሠራተኛ ፓርቲዎች ዋና-ዋና ከሆኑ ተግባሮቻቸው መካከል አንዱ ነው።” የሚል ይገኝበታል። ይህ ብቻም አይደለም መግለጫው ይህንን ሀሳቡን ሲያጠናክርም፤
“የማርክሲስት ፍልስፍና የዓለምን ምንነት ለመገንዘብ እና ተገንዝቦም ለመለወጥ የሚያስችል ፍልስፍና ነው። ይሁን እንጂ አጠቃቀሙን በሚገባ ማወቅ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ድንጋጌዎቹ እና መመሪያዎቹም በትክክል በሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉበት ተጨባጭ የሆኑ ታሪካዊ ሁኔታዎችን በሚገባ ጠንቅቆ ማወቅ ማለት፤ መነሻዎቹን እና መደምደሚያዎቹን በቃል ጥናት ማነብነብ ማለት ሳይሆን የሀሳቡን ፍሬ-ነገር ለመገንዘብ መቻል፤ እንደዚሁም ሰላምን፤ ዲሞክራሲን፤ ብሔራዊ ነፃነትን እና ሶሻሊዝምን ለመመስረት በሚካሄዱት ሬቮሉሽናዊ ትግሎች ላይ ተጨባጭ የሆኑ ተግባሮችን ማከናወኛ እንዲሆን ለማድረግ መቻል ማለት ነው።” ይላል።
ይህን የፓርቲዎቹን መግለጫ ለኢትዮጵያ የ1960ዎቹ እልቂት ጋር አስተሳስሮ ለተመለከተውም ሆነ ከአሁኖቹ ሁኔታዎቻችን ጋር ላገናዘበው ምን ያህል ትክክል እንደሆነና ምንም ሳይገባን የሌሎችን (አገራት) ስህተቶች ሁሉ እንደ ትክክክለኛ አሰራር በመውሰድ (ከእነሱ እንደ መማር ፈንታ) መልሰን እንደምንደግም ያመለክተናል።
የኢትዮጵያ ዕዳ የ”ጠንቅቆ አለማወቅ” ችግር መሆኑን ሳስብ፤ “በዲያሌክቲክስ እና በማቴሪያሊዝም ላይ” ካለመመስረት የመጣ መሆኑን ሳገናዝብ፤ “አስተሳሰብ ሳይዳብር” በእንጭጭነት የተገባበት መሆኑ ትዝ ሲለኝ፤ በባዶ ሜዳ “ኮሚኒስቶች” መውጪያ መግቢያ ማጣቷን በዓይነ ህሊናዬ ስመለከት፤ ፕሮፍ “አንዳቸውም አልገባቸውም፤ ሁሉም ለስልጣን ጥም ሲሉ ነው እርስ በእርስ የተጨራረሱት” ያሉትን ሳስታውስ … ጮሌነት መሆኑን ስረዳ፤ ውስጤ “ለካ አገሬ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ስትከፍል የኖረችው፤ ምናልባትም ወደ ፊትም ልትከፍል የምትችለው በእንደነዚህ አይነቶቹ እጅ እግር በሌላቸው ችግሮች ምክንያት ነው።” ሲል ያጉተመትምብኛል።
(“የፓርላማ አባል ተጠሪነቱ ለሕገ-መንግሥቱ፣ ለህዝቡና ለህሊናው” ሲሆን የፓርላማው መልክም በእነዚሁ ልክ የሚወሰን ይሆናል። የሚለው የዕለቱ መልዕክታችን ነው!!!)
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013