እፀገነት አክሊሉ
በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በአካባቢያቸውም ላይ ሆነው ለችግር የተጋለጡ ስለመኖራቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ለእነዚህ ወገኖች አስፈላጊው የሰብዓዊ ድጋፍ ይቀርብላቸው ዘንድም በርካታ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው። በተለይም መንግስት 70 በመቶ ያህሉን ድርሻ በመያዝ ከፍተኛ የሆነ ህይወት የማዳን ስራ ሰርቷል፤ በመስራት ላይም ይገኛል።
እኛም በተለይም በትግራይ ክልል ባጋጠመው የሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ዜጎችን ለመደገፍ ምን ተከናወነ ስንል በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ለሆኑት ለአቶ ደበበ ዘውዴ ጥያቄዎችን አቅርበናል።
አዲስ ዘመን ፦ በአገራችን በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ምን ያህል ናቸው? ከክልል አንጻር ሲቃኝስ ምን መልክ አለው?
አቶ ደበበ ፦ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና ሌሎች ችግሮች ምክንያት በርካታ ወገኖች ለችግር ፣ ለመፈናቀል ተዳርገዋል። እነዚህ ወገኖች ደግሞ ሰብዓዊ ድጋፍን የሚፈልጉ በመሆናቸው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከሴክተሮችና ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። በተለይም የረጂ ድርጅቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነም ይገልጻል።
ከክልል አንጻር እንግዲህ ከዚህ ቀደም በጉጂም በመተከል በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሰዎች በእርስ በእርስ ግጭቶች ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ለችግር ተጋልጠው ነበር። አሁን ደግሞ ህወሓት መራሹ ቡድን በፈጠረው ችግርና መንግስት ህግን ለማስከበር በወሰደው እርምጃ ምክንያት በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ያሉ ዜጎች ለመፈናቀልና ለችግር ተዳርገዋል።
በትግራይ ክልል ብቻ ለነዚህ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ለመድረስ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን ጨምሮ የፌደራል ተቋማት አጋር አካላት የሚሳተፉበት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ምላሽ ማዕከል በማቋቋም ወደ ተግባር ተገብቶ እየተሰራ ይገኛል ።
ማዕከሉ በዋናነት በክልሉ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ለጉዳት የተዳረጉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹትን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን በመንግስትና በተለያዩ አካላት የመጡትን በማስተባበር ያከፋፍላል። ከዚህም ባሻገር በጤና፣በንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲሁም በጸጥታ በኩል ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል በሚለው ዙሪያ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ።
አዲስ ዘመን፦ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት የእርዳታ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር ምን ያህል ነበር?
አቶ ደበበ ፦ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በትግራይ ክልል አንድ ሚሊዮን ዜጎች በሴፍቲኔት ይረዱ ነበር፤ 110 ሺ ተፈናቃዮችም ነበሩ። የእለት እርዳታ ፈላጊው ደግሞ 680 ሺ ነበሩ፤ ይህ በጠቅላላው ሲደመር 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ይሆናል።
አሁን ከግጭቱ በኋላ የተፈናቃዮች ቁጥር ከሰባት መቶ ሺ በላይ የደረሰ ሲሆን ከቀደመው ጋር ሲደመር የእርዳታ ጠባቂውን ቁጥር ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አድርሶታል። አሁን ላይ እየረዳን ያለነው ደግሞ ለ 4ነጥብ 1 ሚሊዮን ሕዝብ ነው። ይህ እርዳታ ደግሞ እየቀረበ ያለው በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በትግራይ እየተካሄደ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ምን ደረጃ ላይ ነው? በመንግስት በኩል ያለው የድጋፍ አቅርቦት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ደበበ፦ በክልሉ ደቡብ ትግራይ ማለትም ራያ፣ አላማጣ ፣ራያ ጨርጨር፣ ዛታ ፣አፍላ ኮረም ወረዳዎች ለሁለተኛ ዙር እርዳታ የሚውል ከ 7 ሺ 200 ኩንታል በላይ ምግብ ተመድቦ የስርጭቱ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። እንዲሁም በምዕራቡ በኩል አዲረመጽ፣ ባዕከር፣ ሁመራ፣ ዳንሻና ማይካድራ ወረዳዎች ለሚኖሩ ሰዎች በኮሚሽኑ ከ 30 ሺ ኩንታል በላይ የምግብ ድጋፍ ተደርጓል ።
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስት የራሱን 70 በመቶ ድርሻ እየተወጣ እንዳለ ይታወቃል፤ ግን ደግሞ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች እያደረጉት ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ምን መልክ አለው?
አቶ ደበበ ፦ አዎ መንግስት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው። እዚህ ላይ ረጂ ድርጅቶች ሲባል በአደጋ ጊዜ ደራሽ (ኢመርጀንሲ ኦፕሬሽን) የሚባሉ አሉ፤ በእነዛ ስር ደግሞ ዋና ዋናዎቹ እንደ ሲአር ኤስ ፣ ዎርልድ ቪዥንና ሌሎችም አሉ። እነዚህ ረጂ ድርጅቶች የሚያመጡት እርዳታ ደግሞ በትግራይ ልማት ማህበር በኩል ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ሆኗል። በትግራይ ክልል እስከ አሁን ባለው ሂደት ለ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ተረጂዎች ስምንት መቶ 41 ሺ 250 ኩንታል የምግብ እህል ተሰጥቷል ። ይህ ደግሞ በገንዘብ ሲተመን አንድ ነጥብ 94 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ይገመታል።
ለእነዚህ ወገኖች እየተከፋፈለ ያለው የምግብ እርዳታ አብዛኛውን እየተሸፈነ ያለው በመንግስት ነው። 30 በመቶውን ደግሞ አጋር አካላት እያቀረቡ ነው ያሉት። ነገር ግን እነዚህ ረጂ ድርጅቶች አሁን ባለው ሁኔታ አቅርቦታቸውን መጨመር ስለሚገባቸው በዚህ ላይ ተግባቦት እየፈጸምን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን ፦ በክልሉ እየተሰጠ ያለው ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ አይደለም እየተባለ በአንዳንድ አካላት የሚናፈስ ወሬ አለና እንደው የክልሉ እርዳታ አሰጣጥ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል ? ምክንያቱም እርስዎም በቦታው ተገኝተው እርዳታውን ሲያደርጉ ስለነበር ብዬ ነው፤
አቶ ደበበ፦ እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር የክልሉ ሕዝብ በገጠርም በከተማም ያለው ቁጥሩ ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፤ ቀደም ሲል ያለው የተረጂዎችና ተፈናቃዮች ቁጥር 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ነበር ብለን አሁን የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች እየተረዱ ነው ካልን ታዲያ ሕዝቡ ከዚህ በልጦ ነው እርዳታ አልደረሰውም የሚባለው? ስለዚህ መንግሥት ለእነዚህ ሁሉ ወገኖች አስፈላጊውን ሁሉ እርዳታ እያቀረበ ነው ። እሱ ብቻ አይደለም ረጂ ድርጅቶች ክልሎች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እየሰጡ ድጋፍ እያደረጉ ነው። ስለዚህ በተለያየ መልኩ የግል ጥቅማቸውን ለማካበት ፍላጎታቸውን ለማርካት አልያም በኢትዮጵያ ላይ ሌላ ጫና ለማሳደርና ገጽታዋን ለማበላሸት የሚፈልጉ አካላት እያወሩ ያሉት ነገር ፍጹም ከእውነት የራቀ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
አሁን ላይ እንደውም የረጂ ድርጅቶች ቁጥር ከፍ እያለና የመርዳት ፍላጎታቸውም እየጨመረ በመሆኑ መንግስት ድርሻቸውን ከፍ ለማድረግ እየሰራ ነው ። ነገር ግን እነዚህ አካላት ገብተው በትክክል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነወይ? የሚለውን ጥያቄ በቦታው ሄዶ ማየት ደግሞ የእናንተ የጋዜጠኞቹ ኃላፊነት ነው ። ከዛ ውጪ ግን እውነት ለመናገር በክልሉ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀልበስ መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
በሌላ በኩልም ከምግብና ምግብ ነክ እርዳታዎች በተጨማሪ የንጽህና ጉዳይ፣ የመጠጥ ውሃ፣ ጤናን በተመለከተ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። በትምህርት ቤት የተጠለሉት ቦታ መቀየር ስላለባቸው መንግስትና አይ ኦ ኤም (IOM) ቦታዎችን ለይተው አስፈላጊውን ነገር አቅርበው መጠለያ ለመስራት እየተዘጋጁ ነው። ይህም የሚሆነው በቀጣይ እነዚህ ወገኖች በተረጋጋ ሁኔታ መኖር ስላለባቸውና መንግስትም ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ስለሚገባው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ረጂ ድርጅቶች በገቡባቸው ወቅቶች እየሰሩ ነው፤ ነገር ግን የሚፈለገውን ያህል ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ወይ ካልን አሁንም ችግር አለ፤ መንግስትም ቃል የሚገቡትን ያህል እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ እያነጋገራቸው ነው። ነገር ግን በመንግስት በኩል 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህዝብ ተረዳ ማለት በጣም ብዙ ነው።
በመሆኑም እነዚህ አካላት አቅማቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግሥት ደግሞ አስካሁን ሲያደርግ የነበረው እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ ሚናውን ቀነስ ለማድረግም የተሞካከሩ ስራዎች አሉ።
አዲስ ዘመን ፦ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እያደረጉ ያለው ጥረት ምን ይመስላል ?
አቶ ደበበ ፦ ይሳተፋሉ እየተሳተፉም ነው፤ እያደረጉ ያለውን ድጋፍም በተለያየ መገናኛ ብዙኃን እየሰማን ነው። እዚህ ላይ ግን እነዚህ አካላት ምን አደረጉ፣ ምን ያህል ደገፉ የሚለውን ለመመለስ እቸገራለሁ፤ ምክንያቱም አንዳንዱ ድጋፍ በእኛ በኩል ላይሄድና በሰላም ሚኒስቴር ወይም በሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች በኩል ሊገባ ይችላል። ለምሳሌ በቅርቡ የደቡብ ክልል ወደ ትግራይ 21 መኪና እርዳታ ይዞ ሲሄድ ለኮሚሽኑ ያሳወቀው ነገር የለም፤ ምንአልባት እዛ ከደረሰ በኋላ በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከሉ በኩል ሊከፋፈል ይችላል ። በመሆኑም ሁሉም በየበኩሉ ቢጠየቅና መልስ ቢሰጥ ጥሩ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ እነዚህ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ምግብ ብቻ ሳይሆን መጠለያም፣ ማብሰያም ይፈልጋሉና ኮሚሽኑ የምግብ እርዳታን ከማቅረብ ባሻገር በዚህስ በኩል እየተወጣ ያለው ሚና ምን ይመስላል?
አቶ ደበበ፦ መጠለያና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በተመለከተ 26 ሺ 12 ገደማ ልዩ ልዩ የመመገቢያ ቁሳቁሶች ቀርበዋል። 32 የመጠለያ ሸራ ማለትም ከድንኳን በላይ የሆነ ገብቷል፤ እንግዲህ በገንዘብ ሲተመን 246 ነጥብ 6 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ሲሆን ይህ በጠቅላላው 128ሺ 5 መቶ 35 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በዚህ ረገድ በልዩ ልዩ ቁሳቁሶች አቅርቦት ረገድ አሁንም በርካታ ጥረቶችን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም የሚጠይቁት ሀብት በጣም በርካታ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት አሁንም የአቅሙን እያደረገ ይገኛል ። በቀጣይም ከ 90 ሺ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ በአጋር አካላት በኩል እንዲሸፈን ለማድረግ በእቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ፦ ከላይ ስንነሳ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከኮሚሽኑ ጋር አብረው እየሰሩ መሆኑን ነግረውኛልና እንደው ሚናቸው በምን መልኩ ነው የሚገለጸው?
አቶ ደበበ፦ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ብሔራዊ አደጋ ስጋት ኮሚሽን ብቻ አይደለም ጤና፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ መከላከያና ሌሎችንም ያቀፈ ነው ። ከክልል መስተዳድሮች ጋር ተቀናጅቶ ነው የሚሰራው፤ ኮሚሽኑ ደግሞ ለእነዚህ አካላት ድጋፍ ነው የሚያደርገው፤ ሴክተሮች ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ምክንያቱም ድጋፍ ፈላጊዎች ባሉበት አካባቢ ሊሰጥ የሚገባው ነገር ምግብና ምግብ ነክ ጉዳዮች ብቻ አይደሉም፡፡ ከዛ ይልቅ ውሃ ትምህርት ጤና የግብርና ዘርፍ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መጠገን ሁሉ አለ ፤ በመሆኑም እነዚህን ስራዎች ለመስራት የሚመለከታቸው አካላት አብረው እየሰሩ ነው።
አስር ሴክተር መስሪያ ቤቶች አብረውን ይሰራሉ ፤ እነዚህ መስሪያ ቤቶች ሁልጊዜ ዝግጁ ናቸው። ለምሳሌ 3 ሺ ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ላይ ጤና፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ የትምህርት አገልግሎት ካልተገኘ ከባድ ነው፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከቤት ንብረታቸው ሳይፈናቀሉ ለችግር የተጋለጡም አሉ፤ እነሱም ለግብርና ስራቸው እንዲዘጋጁ ግብርና አብሯቸው መስራት አለበት፤በመሆኑም እነዚህ መስሪያ ቤቶች ወሳኝ ስራን እየሰሩ ነው።
ሌላው የትምህርት ሴክተር መስሪያ ቤቶች በክልሉ አሁን ላይ ትምህርት መጀመር ስላለበት አብረውን እየሰሩ ነው፤ በዚህም ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞችን ማስወጣት የግድ ነው ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት መስራት አለበት ።
በጠቅላላው አደጋን በአንድ መስሪያ ቤት ስራ ብቻ መወጣት የሚቻል ባለመሆኑ ሁሉም የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው፤ እየተወጡም ነው።
የሴክተር መስሪያ ቤቶች ድጋፍ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚያደርግ ደግሞ በጌዲኦ አይተናል ። ለምሳሌ እዛ አካባቢ ተፈናቅለው የነበሩት 860ሺ 56 ወገኖች ሲሆኑ እነዚሕን ወደቀያቸው ለመመለስ ችግር አልሆነም፤ ምክንያቱ ደግሞ ተባባሪ የሆኑ የክልል መስተዳድር አካላት ነበሩ ፡፡ ሌላው ደግሞ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በሚገርም ቅንጅት መስራታቸውና የተራድኦ ድርጅቶችም ስላገዙን ሰዎቹን ሙሉ በሙሉ ወደቀያቸው መልሰን ሕዝቡም ወደልማቱ ገብቷል።
ልክ እንደዚሁ በትግራይና በሌሎች አካባቢዎች ላይ ያለውንም ሁኔታ ለመመለስ በጋራ እንሰራለን ። እዚህ ላይ ግን ሁኔታዎች ከባድ እንደሚሆኑም እናስባለን ፡፡ ምክንያቱም በትግራይ ብቻ እንኳን የተፈናቃዩ ቁጥር ከ 746ሺ በላይ ነው ። እነዚህን ቢያንስ ዘላቂ ሕይወታቸውን ሊመሩ የሚችሉበት መንገድ እስኪመቻች እንኳን በአንድ ማዕከል ተሰባስበው መሰረታዊ የሆኑ የጤና፣ የትምህርት፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ሊያገኙበት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ። የሚሰሩ ስራዎችም በጋራ ቅንጅት ነው።
እዚህ ላይ ግን ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከእኛ ጋር ስለሰሩ ብቻ ችግሩን እናልፈዋለን ማለት ሳይሆን አጋር አካላት፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በአገር ወስጥ ያሉ ባለሀብቶችና ክልሎች እያደረጉ ያሉት ድጋፍም ቀላል አይደለም፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ በመተከልና በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ መፈናቀሎች ደርሰው ብዙዎች ተፈናቅለው ለችግር የተጋለጡ፤ እርዳታን የሚጠብቁ ወገኖች አሉና በዚህስ በኩል እየተሰራ ያለው ስራ ምን ይመስላል ?
አቶ ደበበ ፦ በመተከል ዞን በተፈጠረ ግጭት 1 መቶ 4ሺ 960 ዜጎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ነው የነበሩት፤ እነዚህ ተፈናቃዮችም በወንበርታ፣ ማንዱራ፣ ዳንጉር፣ ጉባ፣ ድባጤ፣ ቡለን ነው። ከነዚህ ውስጥ 4ሺ 981 ወገኖች ነፍሰጡርና አጥቢ እናቶች ሲሆኑ 23ሺ 718 ደግሞ ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ናቸው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው 75ሺ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ዞን በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
እስከ አሁን ባለው ሁኔታም ለእነዚህ ወገኖች 51ሺ 408 ኩንታል አልሚ ምግብ ፣ስንዴ፣ዘይትና የበቆሎ ዱቄት ተጓጉዞላቸዋል ። በተጨማሪ ለመጠለያ፤ ለመመገቢያ እንዲሁም አልባሳት የሚሆኑ 2 መቶ 81 ሺ 480 ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ተልኳል። ቀሪዎችም ጭነቶች በመጓጓዝ ላይ ይገኛሉ።
የእርዳታ አቅርቦቱም ከፌደራል፣ ከዞን፣ ከክልልና ከወረዳ የተውጣጡ ባለሙያዎች በመተከል ዞን ተሰማርተው ልክ እንደ ትግራይ ሁሉ አስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ፦ እንግዲህ ከትግራይና ከመተከል በተጨማሪ በአማራ ክልልም በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የእርዳታ እጃቸውን የሚዘረጉ ወገኖች አሉና ለእነሱስ ምን ዓይነት ምላሽ እየተሰጠስ ነው?
አቶ ደበበ፦ አዎ በአማራ ክልል በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች አሉ፤ በተለይም በዳንግላ፣ ፋግታ፣ እንጅባራ፣ ጓጉሳ፣ አንክሻ፣ ዚገም፣ ጃዊ፣ ጓንጓ፣ ቻግኒ የሚባሉ ቦታዎች ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች አሉ። ለምሳሌ አዊ ዞን በ11 ወረዳዎች ላይ 97ሺ 229 መሆናቸውን ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ፤ ለእነዚህም ለ67 ሺ ሰዎች ሊያገለግል የሚችል 11ሺ ኩንታል በላይ ምግብ ተሰራጭቷል ። ለሁለተኛው ዙር የሚሆን 3ሺ 662 ኩንታል ስንዴ ፣ 3 ሺ 266 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ፣ 210 ኩንታል የምግብ ዘይት ለ 48 ሺ 960 ሰዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ታሳቢ ተደርጎ ተጓጉዟል ። ቀሪውም ይጓጓዛል።
በዚሁ አካባቢ በተለይም ከትግራይ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ሰዎች በመኖራቸው ለእነዚህም 73ሺ 847 የህብረተሰብ ክፍሎች 12ሺ 185 ኩንታል ተመድቦ እስከ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓም ድረስ እንዲደርሳቸው ሆኗል።
አዲስ ዘመን ፦ ኮሚሽኑ በተለይም የእርዳታ አቅርቦቱን በተፈለገው ልክ ለማዳረስ የሚያስችል ክምችት አለው ዝግጁነቱስ ምን ያህል ነው?
አቶ ደበበ፦ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ባለው የክምችት አቅም እርዳታውን በመቅረብ ላይ ነው። አሁን ደግሞ ገንዘቡ የኢትዮጵያ ሆኖ በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል 3 መቶ ሺ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ አገር ለመግዛት በተወሰነው መሰረት የመጀመሪያው ዙር 40 ሺ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ወደብ ደርሷል ። የቀረውም እየተጓጓዘ ሲሆን ይህ ስንዴ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ተቀምጦ እንደ አስፈላጊነቱ ለህብረተሰቡ የሚከፋፈል ይሆናል ።
ይህ ሁኔታ እንግዲህ መንግሥት በተለይም ግጭቱ እስኪቆምና ህብረተሰቡ ወደመደበኛ የኑሮ ሁኔታው እስኪመለስ ድረስ ለችግር እንዳይጋለጡ ለማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራም መሆኑን ያሳያል ።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ ሰብዓዊ ድጋፉን በማቅረብ በኩል እያጋጠመ ያለው ችግር ምንድን ነው?
አቶ ደበበ፦ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጸጥታው ሁኔታ እርዳታው በሚፈለገው ልክ እንዳይሄድ እያደረገ ነው። በተለይም ስድስት ቦታዎች ላይ እስከ አሁን መድረስ አልተቻለም። ሌላው በተለይም መጠለያና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ማቅረብ ላይ ከፍተኛ የሆነ እጥረት መታዩቱ ነው።
እነዚህ እጥረቶች ደግሞ የመንግሥት ድርሻ እንዳለ ሆነ አጋር አካላት የሚያሟሏቸው በመሆናቸው እንዲያቀርቡ ቢጠየቁም ምላሻቸው የዘገየ ነው። ከዚህ አንጻር ሁሉንም ነገር በራሳችን መወጣት ብንችል የተሻለ ይሆናል።
ሌላው የሰብዓዊ ድጋፉን በማስተባበር በኩል ሰፊ ስራዎችን እየሰራን ቢሆንም አንዳንድ ችግሮች ደግሞ አሉ። በተለይም ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቀውና ለነፍሰ ጡሮች ለህጻናትና ለአጥቢዎች የሚቀርቡ አልሚ ምግቦች በጣም ውድ ከመሆናቸው የተነሳ እጥረት አለብን ።ይህንንም አጋር አካላት እንዲያሟሉትም ስራዎች እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከምግብ እርዳታው ከሌሎችም ሰብዓዊ ድጋፎች ሁሉ በቀጣይ ክልሉን ወደነበረበት መመለሱ ከባድ ስራ ይመስለኛልና በዚህስ በኩል እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን መልክ አለው?
አቶ ደበበ፦ መልሶ ማቋቋም ከፍተኛ የሆነ ወጪን የሚጠይቅ ነው፤ ይህንን ደግሞ ለመወጣት በጋራ መቆም ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ግን ህብረተሰቡ አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ ብዥታ ውስጥ ያለ በመሆኑ ትልልቅ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀትና ስለእውነታው ማስረዳት ያስፈልጋል። ከዛ በኋላ ሁኔታው ከባድ ቢሆንም እንኳን ራሱ ህብረተሰቡ ስለሚሳተፍበት ማቅለል ይችላል።
በጠቅላላው ግን መንግሥት ለዜጎቹ በመልካም ሁኔታ መኖር ይጥራል አንድም ቀን አልተኛም። ግን ደግሞ አገራችን ያለችበት ሁኔታ መንግስት በሚያደርገው ጥረት ብቻ የምንወጣው ባለመሆኑ መረዳዳት የግድ ያስፈልጋል።
ከዚህ ቀደም አገሪቱ በድርቅ፣ በጦርነት በተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ውስጥ አልፋለች፤ብዙዎችም የተፈናቀሉበት ሁኔታ ስላለ ከዚህ ሁሉ ለመውጣት አንደኛ አእምሯችንን ለጥሩ ነገር መጠቀም፤ በሌላ ጎን ደግሞ አብሮን የኖረውን የመረዳዳት አብሮ የመሥራት ባህል የማስቀጠል ኃላፊነቱ የእኛ ነው። ይህንን ማድረግ ከቻልን ደግሞ የተሻለች አገር እንገነባለን።
አሁን የተለያዩ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች እንኳን ሕዝቡ ያለፈውን ሁሉ ትቶ “እኛነታችን ይበልጣል፤ ፖለቲከኞች ያልፋሉ” የሚለውን ቆም ብሎ በማሰብ አገሪቱንም ክልሉንም ወደሰላም ለማምጣት መስራት ያስፈልጋል፤ ማድረግም ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ደበበ ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013