
በአሜሪካ፣ ቴክሳስ ግዛት አርብ ዕለት ባጋጠመ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 24 ሰዎች ሲሞቱ በካምፕ ውስጥ የነበሩ ወደ 25 የሚጠጉ ሴት ታዳጊዎች መጥፋታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በነጻነት ቀን ያጋጠመውን ይህንን የጎርፍ አደጋ “አስደንጋጭ” እና “አስከፊ ” ብለውታል። የፌዴራል ባለሥልጣናትም ርዳታ እያደረጉ እንደሆነ የቴክሳስ ገዥ ግሬግ አቦት ተናግረዋል።
ምንም እንኳን የግዛቷ ባለሥልጣናት በጎርፉ ምክንያት የገቡበት ያልታወቁ ሰዎችን ቁጥር ባያረጋግጡም ፍለጋው እና የነፍስ አድን ጥረቱ ሌሊቱን መቀጠሉን የግዛቷ ገዥ ገልጸዋል። የጎርፍ አደጋው መንስዔ ግዛቷ በበርካታ ወራት የምታገኘው የዝናብ መጠን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ መዝነቡ እንደሆነ ተገልጿል። ጎርፉ ድልድዮችን ጠራርጎ ሲወስድ እና በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዝ ጎርፍ መንገዶችን ሲያጥለቀልቅ በማህበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች አሳይተዋል።
የቴክሳስ ምክትል አስተዳዳሪ ዳን ፓትሪክ “ጎርፉ ከመከሰቱ በፊት የወንዙ የውሃ ከፍታ ጨምሮ ነበር። በ45 ደቂቃ ውስጥ፣ ጉዳሉፕ ወንዝ 26 ጫማ ከፍታ ጨምሯል። አውዳሚ ጎርፍ ነው፤ ሕይወትን እና ንብረትን አጥፍቷል።” ብለዋል።
ፓትሪክ ጨምረውም ” ሕጻናቱ የገቡበት አልታወቀም ማለት ሞተዋል ማለት አይደለም፤ ከግንኙነት መስመር ወጥተው ሊሆን ይችላል” ሲሉ ቤተሰቦችን አጽናንተዋል። ነዋሪዎች ለነፍስ አድኑ ጥረት የግል ሄሊኮፕተራቸውንና ድሮናቸውን በመስጠታቸው ምስጋናቸውን ያቀረቡት ፓትሪክ፣ ነገር ግን ሌላ ተጨማሪ መሣሪያ እንደማያስፈልጋቸው ተናግረዋል። የነፍስ አድን ተቋሙ 14 ሄሊኮፕተሮች ፣ 12 ድሮኖች ፣ ዘጠኝ የነፍስ አድን ቡድን እና በሥፍራው በአጠቃላይ ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ዋናተኞች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የቴክሳስ ሜጀር ጀነራል ቶማስ ሱልዘር እንዳሉት ዋናተኞችን የያዙ አምስት ሄሊኮፕተሮች እንዲሁም በውሃ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችሉ ከፍተኛ የጦር ተሽከርካሪዎች በሥፍራው ተሰማርተዋል። በዚህም 237 የሚሆኑ ሰዎችን መታደግ ተችሏል ብለዋል። የቴክሳስ ፓርክ እና የዱር እንስሳት መሥሪያ ቤት ተቆጣጣሪዎችም ባለሥልጣናት ከ20 በላይ ታዳጊ ሴቶች ጠፍተውበታል በተባለው ሚይስቲክ ካምፕ ደርሰዋል።
ሆኖም በአካባቢው የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው በሰመር ካምፑ ውስጥ የነበሩትን ጨምሮ በግዛቷ ያሉትን ሰዎች ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ከባድ አድርጎታል። ቤታቸው በጎርፉ የተወሰደባቸው አንድ እናት ልጇንና የልጇን ባል ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። በቴክሳስ ኦስቲን ነዋሪ የሆኑ ሌላ ሴትም በጉዋዳሉፕ ወንዝ አቅራቢያ ከሚኖሩ አያቶቿ ምንም ዓይነት መልዕክት እንዳላገኘች በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርታለች። በክር ካውንቲ የሕግ አስፈፃሚ (የሸሪፍ) መሥሪያ ቤትም በርካታ የጎርፍ አደጋዎች መከሰታቸውን ገልጾ፣ በዚህም በርካታ ሰዎች መጥፋታቸውን እና ሕይወት መጥፋቱን አረጋግጧል።
የክር ካውንቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ዳኛ ሮብ ክሊይ አርብ ዕለት ከሰዓት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በካምፑ ውስጥ የነበሩ ልጆችን አስቀድሞ ማውጣት ያልተቻለው ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። “ይህ ጎርፍ እንደሚከሰት አናውቅም ነበር። ማንም ሰው ይህ ጎርፍ እንደሚከሰት አያውቅም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በአካባቢው የጎርፍ አደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትም እንደሌለም ባለሥልጣኑ ገልጸዋል።
አርብ ዕለት የተከሰተው ጎርፍ በአውሮፓውያኑ በ1987 በደቡባዊ ክር ካውንቲ በምትገኘው ኮምፎርት ከተማ አጠገብ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ካምፕ አስር ታዳጊዎችን ከገደለው ጎርፍ የከፋ እንደሆነም ተናግረዋል። አደጋው ከተከሰተ አንስቶ የነፍስ አድን እና ከአካባቢው ሰዎችን የማስወጣት ሥራ እንደቀጠለ ሲሆን በግዛቷ ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው። በማዕከላዊ እና ምዕራብ ቴክሳስ በሚገኙት ሂል ካውንቲይ እና ኮንቾ ቫሊ ክልሎች የአደጋ ጊዜ ታውጇል።
ነዋሪዎችም ንቁ ሆነው እንዲጠብቁ እና በጎርፍ በተጥለቀለቁት መንገዶች እንዳያሽከረክሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። የክር ካውንቲ ሸሪፍ ቢሮ በወንዝ ዳርቻዎች የሚኖሩና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ከፍ ወዳለ ቦታ እንዲሄዱ አሳስቧል። በሌላ በኩል የኒው ጀርሲ ባለሥልጣናት ሐሙስ ዕለት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ እና መብረቅ ምክንያት ቢያንስ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል። ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ የ79 እና የ25 ዓመት ወንዶች ሲሆኑ ሕይወታቸው ያለፈው በነበሩት መኪና ላይ ዛፍ ከወደቀ በኋላ ነው። ሌላኛዋ የ44 ዓመት ሴትም በሰሜን ፕሌንፊልድ መኪናዋ ላይ ዛፍ ከወደቀባት በኋላ ሕይወቷ አልፏል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም