አስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ የማእድን ዘርፉ ገና ብዙ እንዳልተሰራበትና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደማይገኝ በተለያዩ ጊዚያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ማእድንና ነዳጅ ሚንስቴር መረጃ እ.ኤ.አ በ2014 አገሪቱ ከማዕድን የወጪ ንግድ 541 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያገኘች ቢሆንም እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ከዘርፉ የወጪ ንግድ የሚሰበሰበው ገቢና አመታዊ የተጣራ አገራዊ ምርት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2013/14 የሴክተሩ ዓመታዊ እድገት 3 ነጥብ 2 ከመቶ እንደነበርና እ.ኤ.አ በ2014/15 ወደ 25 ነጥብ 6 በመቶ እንደተሻገረ እንደገና ደግሞ እ.ኤ.አ በ2015/16 ወደ 3 ነጥብ 3 በመቶም ማሽቆልቆሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2016/17 ይህ አሃዝ ወደ ኔጋቲቭ 29 ነጥብ 8 ከመቶ እንደወረደና እ.ኤ.አ በ2017/18 ደግሞ ወደ ኔጋቲቭ 20 ነጥብ 8 በመቶ መውረዱን መረጃው ያመላከተ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2018 የማዕድን ዘርፉ ለአመታዊ የተጠራ ሀገራዊ ምርት ያለው አስተዋፅኦ እ.ኤ.አ በ2013 ከነበረው 9 ነጥብ 1 ከመቶ ወደ 1 ከመቶ ማሽቆልቆሉን ጠቅሷል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ በማዕድን ዘርፉ ልዩ ልዩ የሪፎርም ስራዎች በመሰራታቸው ከዘርፉ የወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በዚህ መነሻነት በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወር ከማዕድን ወጪ ንግድ በተለይ ደግሞ ከወርቅ ማዕድን ከፍተኛ ገቢ ስለመገኘቱ ከነዳጅና ማዕድን ሚንስቴር የተገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
በዚሁ መሰረትም በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር ውስጥ ከአጠቃላይ የማዕድን የወጪ ንግድ 339 ነጥብ 5 የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወርቅ ብቻውን 335 ነጥብ 54 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አስገኝቷል፡፡ በዚህም የወርቅ ማዕድን ለብቻው ከፍተኛውን የወጪ ንግድ ገቢ አስገኝቷል፡፡ ኤመራልድ፣ ሳፋየርና ኦፓል ከተሰኙ የከበሩ ማዕድናት የወጪ ንግድ ደግሞ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፡፡
ካለፈው ዓመት የወርቅ ማዕድን ወጪ ንግድ ጋር ሲነፃፀር የአሁኑ የስድስት ወር አፈፃፀም በጣም ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ፤ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና የትግራይ ክልል ወርቅን በዋናነት ወደ ብሄራዊ ባንክ በማቅረብ ለወጪ ንግዱ አፈፃፀም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
የባለፈው ዓመት የአንድ ዓመቱ የወጪ ንግድ አፈፃፀም 207 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አካባቢ እንደነበርም በመረጃው የተመላከተ ሲሆን በዘንድሮው በጀት አመት ከወርቅ ማዕድን የወጪ ንግድ ብቻ 335 ነጥብ 54 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘት በመቻሉ አፈፃፀሙ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህም በስድስት ወር ብቻ የ140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ልዩነት እንዳለው ያሳያል፡፡
ከማዕድን የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው ከፍ ሊል የቻለውም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የወርቅ ዋጋን በማሻሻሉ ሲሆን የዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ መጨመርም ለወጪ ንግድ ገቢ ከፍተኛነት አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲቀንስ የተሰሩ ስራዎችም ለገቢው ማደግ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በሰዎች እጅ ያሉ ወርቆች በተለይ በድምበር አካባቢዎች በአብዛኛው ወደ ብሄራዊ ባንክ መምጣት መቻላቸውን አስረድተዋል ፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ከዘርፉ ከ340 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንም በቅርቡ ከሚንስቴሩ የወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን በ2013 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የማዕድን ዘርፍ ከዕቅድ በላይ 198 በመቶ ማስመዝገቡም ተጠቁሟል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰሞኑ ባካሄደው ስድስተኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የወጪና ገቢ ንግድን በሚመለከት ከአባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ ባለፈው አመት የወጪ ንግዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሩ አፈፃፀም ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ደግሞ የ21 በመቶ ማሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ሀገሪቱ የኮሮና ወረርሽኝ፣ አንበጣና ግጭት ባስተናገደችበት በዚህ ወቅት የወጪ ንግድ መሻሻል ማሳየቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ ወርቅን በሚመለከት ከሪፎርም በፊት አንዳንድ ቦታዎች ከኢንቨስትመንት የተዘጉና ስራ ያቆሙ የወርቅ ማምረቻ እንደነበሩ አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ ከኩባንያዎች፣ ከድርጅቶችና ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመነጋገር አዳዲስ አመራሮች እንዲገቡ፣ ስራ ያቆሙም እንዲጀምሩ በማድረግ የወርቅ የወጪ ንግድ በብዙ እጥፍ እንዲያድግ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች አዳዲሶቹ ወደምርት ሲገቡ ቁጥሩ እንደሚጨምርም ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ የወርቅ ወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም ሚንስቴር መስሪያቤቱ በቀጣይ የተለያዩ ስራዎችን እንደሚሰራ ነው የተናገሩት ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2013