በመላኩ ኤሮሴ
በቅርቡ በነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ በማድረግ አዲስ የነዳጅ ሽያጭ ዋጋም ይፋ መደረጉ ይታወቃል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር በቅርቡ የነዳጅ ዋጋ መሸጫ በአማካይ 20 በመቶ ጭማሪ እንደተደረገበት ነው ይፋ ያደረገው። በአዲሱ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ እንደየአካባቢው የሚለያይ ነው። የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ማስተካከያ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በገበያ ውስጥ የአንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ መጀመሩ ጉዳዩን የብዙዎች መነጋገሪያ አድርጎታል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ሰሞኑን በፓርላማ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ጭማሪን አስመልክቶ ከህዝብ እንደራሴዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያና ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገው የነዳጃ ዋጋ ጭማሪ የተጋነነ አይደለም። በተለይም ከጎረቤት አገራት አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ አሁንም ዝቅተኛ ነው።
የሁሉም የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ከኢትዮጵያ እንደሚበልጥ ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት አንደኛዋ አገር ነዳጅ በሌትር 67 ብር ነው ፤ ሌላኛዋ ጋር 79 ብር መሆኑን አብራርተዋል። ዝቅተኛ የሚባለው ኬንያ ሲሆን፣ 38 ብር ነው። ኢትዮጵያ ግን በሌትር 25 ነጥብ 6 ብር ነው። የትኛውም ጎረቤት አገር ኢትዮጵያ ያላት የሊትር ዋጋ የለውም ሲሉ ነው ያስረዱት ።
“የኢትዮጵያ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ዝቅተኛ የሆነው ከተለየ ጉድጓድ ስለምትቀዳ ሳይሆን መንግስት ስለሚደጉም ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ብቻ 30 ቢሊዬን ብር መደጎሙን አንስተዋል። በዚህ ወር ብቻ ከነዳጅ ድጎማ ጋር ተያይዞ መንግስት ሦስት ቢሊዬን ብር እዳ መሸከሙን ገልጸዋል።
የዓለም የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ሲሄድ ኢትዮጵያ ደግሞ የነዳጅ ዋጋን ዝም ብላ ከለቀቀችው ኢንፍሌሽንን ስለሚያባብስ ለኢንፍሌሽን ተብሎ መንግስት ብዙ ነገር ይሸከማል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ከነዳጅ ድጎማ ጋር ተያይዞ ሊሰራ የሚገባው ነገር ግን ያልቻልነው ነገር አለ ይላሉ። መንግስት ነዳጅ የሚደጉመው ለሀብታም ነው። መኪና ላለው ሀብታም ጭምር እንጂ ለባስና ለታክሲ ብቻ አይደለም ይላሉ።
እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ፤ መንግስት የሚፈልገው ባስና ታክሲን አግዞ እነዚህ የትራንስፖርት አማራጮች በተሳፋሪዎች ላይ ዋጋ እንዳይጨምሩ ነው። ነገር ግን የነዳጅ ዋጋ ለሁሉም ስለሆነ ሀብታሙም መኪና ያለው ሁሉ በረከሰ ዋጋ ነዳጅ ይገዛል። መንግስት እንዴት አድርጎ ነው ሀብታሙን ትቶ ድሀውን ብቻ ማገዝ የሚችለው የሚለው አልሰራም። ያስቸግራል ግን እንዴት ለይቶ ማስጠቀም እንደሚቻል ለማወቅ ግን ስራ ይፈልጋል።
ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ መኪናዎች ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ በመፍጠር ሀብታሞች ራሳቸውን ችለው እንዲገዙ ካልተደረገ በሌሎች ጎረቤት አገራት የሚገኝ ሀብታም የማያገኘውን እድል የኢትዮጵያ ሀብታም የሚያገኝበት ሁኔታ ሊኖር ስለማይችል ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል። ገንዘብ እያወጣን ያለነው ለሀብታሞች ነውና። እንዴት ይለይ የሚለው ጥናት የሚፈልግ በመሆኑ ተለይቶ ይሰራበታል ብለዋል።
አንዳንድ የዘርፉ ልሂቃን፤ አዲሱ የነዳጅ የዋጋ ጭማሪ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችልና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበለጠ እየተባባሰ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ በመንግስት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል ስጋት እያስተጋቡ ቢሆንም አንዳንድ ምሁራን በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪው ተገቢ ነው የሚል እምነት አላቸው።
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉት፤ መንግስት የወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው። መንግስት ለነዳጅ ይደጉም የነበረው ከሌላ ዘርፍ ወስዶ ነው። አሁን መንግስት የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ ለነዳጅ ድጎማ ያውል የነበረውን ገንዘብ ለሌሎች ነገሮች ማዋል ይችላል።
መንግስት በየጊዜው ለነዳጅ የሚያርገው ድጎማ ሆስፒታል ወይም ትምህርት ቤት ይሰራ ቢባል በርካታ ሊያሰራ እንደሚችል ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ በማድረግ መንግስት ላይ ያለውን ጫና መቀነስ ተገቢ እርምጃ ነው ሲሉ ይናገራሉ ።
ህብረተሰቡ ድጎማ ስለሚፈልግ መንግስት እጁን በመክተት ዘርፉን እየደገፈው መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ሞላ፤ የመንግስት ድጋፍም ህብረተሰቡ አቅሙን እስኪያሳድግ መሆኑን ያነሳሉ። ህብረተሰቡ አቅም ቢኖረው መንግስት ከዘርፉ እጁን የማስወጣት ፍላጎት አለው። በቀጣይ መንግስት እጁን የሚያስወጣበትን ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት ይላሉ።
ዋጋ ጭማሪው የመንግስትን ጫና ከመቀነስ ባሻገር ህብረተሰቡ የነዳጅ አጠቃቀም የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ያብራሩት ምሁሩ፤ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል የሚለውን የአንዳንድ አካላት ሀሳብ ሞግተዋል። መንግስት ከካዝና አውጥቶ ለነዳጅ ዘርፍ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ የሚቀጥል ከሆነ የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ካለው በላይ የመጨመር እድል ስለሚኖረው የዋጋ ንረቱን እንደሚያባብሰው በመጠቆም፤ ድጎማ መቀነሱ የዋጋ ንረቱን ከማባባስ ይልቅ እንዲቀንስ እገዛ ይኖረዋል ይላሉ።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዥ የምታወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ2003 ዓ.ም. አገሪቱ ለነዳጅ ዋጋ ያወጣችው የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ የምንዛሪ ዋጋ መሰረት 22.8 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ አሃዝ እያደገ መጥቶ በ2011 ዓ.ም. 70 ቢሊየን ብር ለነዳጅ ግዥ ወጪ ሆኗል። ይህም ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዥ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ የተባለውን ወጪ ያወጣችበት ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2013