አስመረት ብስራት
የኢትዮጵያ ጽኑ ሴቶች ማኅበር (ኤውብ) እጅግ ብዙ ሴቶች የቋንቋ፣ የንግድ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት እንዲሁም የተለያዩ ስልጠናዎች የሚያገኙበት፣ ትስስር የሚያደርጉበት፣ በስራቸውም የላቁና የበቁ ሴቶች እውቅና እና ድጋፍ የሚያገኙበት፤ ከበቁም በኋላ እራሳቸውን ከፊት ረድፍ ላይ የሚያሰልፉ ሴቶችን የፈጠረ ተቋም ነው።
የኤውብን መስራች ወይዘሮ ናሁሰናይ ግርማን ለማነጋገር ወደ ፅህፈት ቤታቸው ጎራ ባልኩበት ወቅት ለስልጠና ከመጡት ወይዘሮ ፍፁም አጥናፍወርቅ ኪዳነማሪያም ጋር ተገናኝተን ስንጨዋወት በቅርቡ የሚመረቅ መፅሃፏን አበርክታልኝ በሌላ ጊዜ ለመገናኘት ተቀጣጥረን ተለያየን። ቀኑ ደርሶ በቅርቡ ተገናኘንና ስለአጠቃላይ የህይወት ተሞክሮዋ ያጫወተችኝን በዚህ መልኩ አቅርቤዋለሁ፤ መልካም ንባብ።
ፍፁም አጥናፍወርቅ ኪዳነማርያም ትባላለች። ̋የእኔነቴን መሰረት ያፀናችው፣ ሰው ለመሆኔ ዋጋ የከፈለችው እናቴን ለማስታወስ በእናቴ ስም አጠራለሁ” የምትለን ወይዘሮ ፍፁም ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ፣ ልደታ ክ/ከተማ፣ ጦር ሀይሎች ጀርባ፣ ኳስ ሜዳ አከባቢ ነው። በስልሳዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር ፍፁም የምድራችን በረከት ሆና የመጣችው።
̋አባቴ በልጅነቴ በሞት ሲለየን እናቴ ያሳደገችኝ ብቻዋን ነው። አባቴ በዘመኑ ጥሩ የኑሮ ደረጃ እና የገንዘብ አቅም የነበረው ስለነበር የእሱ ቤተሰቦች እኛን ልጆቹን በገንዘብም ይሁን በማንኛውም ነገር አልደገፉንም ነበር። አሁን ላይ አልወቅሳቸውም። ምክንያቱም የእናቴ በብቸኝነትና በጥንካሬ ማሳደግ ባለእዳነት እንዲሰማኝ ስላደረገችኝ ቃሏን አክብሬ ጥሩ ተማሪ፣ ጠንካራ ሠራተኛ፣ ሌሎችን የማግዝ እና ለራሴም ለሌሎችም የተሻለ ሕይወት ለመስጠት እንድታትር አድርጎኛል። ዛሬ ላይ እነሱንም በይቅርታ እና በፍቅር ተቀላቅዬ ጥሩ ቤተሰብ አድርጌኣቸዋለሁ።” ትላለች።
ወይዘሮ ፍፁም የህይወት ጉዞዋን ስትተርክ እንደነገረችኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ማለትም እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ብርሃን ለእናንተ የተባለ ትምህርት ቤት ነው የተማረችው። በወቅቱ እንደ ማንኛውም ልጅ ጫወታ የሚያታልላት በስፖርቱም በሁሉም የምትሳተፍ ልጅ እንደነበረች ታስታውሳለች።
ከፍ እያለች ስትሄድ የትምህርት ጥቅም እየገባት በመሄዱ በወቅቱ የሚሰጠውን የስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ከትምህርት ቤቱ ከፍተኛውን ውጤት ካመጡት ሁለት ተማሪዎቸ አንዷ በመሆን ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ በማምጣት ወደ ሰባተኛ ክፍል ገባች።
በተስፋ ኮኮብ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ለት/ቤቱ ኮኮብ ተማሪ ሆና መማርዋን ታስታውሳለች። በሁሉም ነገር ላይ እንደምትሳተፍና ደስተኛ እንዲሁም ተጫዋች እንደነበረች ባጠቃላይ ታስታውሳለች። ከስምንተኛ ክፍል ወደ ዘጠነኛ ክፈል የተዛወረችውም 99 ነጥብ በማምጣት ነበር።
ዘጠነኛ ክፍል አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ከተማረች በኋላ አስራ አንደኛ ክፍል ስትደርስ እስፔሻል ክፍል በመከፈቱ ከሀያ በላይ ከሆኑ ክፍሎች የደረጃ ተማሪዎች አንድ ላይ በመሆን መማር ሲጀምሩ ከአንደኛ ደረጃ በመተው ቢያንስ እሰከ አስር ያለውን ደረጃን ለመያዝ ጥረት ማድረግ ጀመረች።
ያኔ አራት ሴት ተማሪዎች ብቻ አብረው የነበሩበት ክፍል ውስጥ ሴቶቹ ብቻቸውን ሲያጠኑ ወንዶቹ በቡድን በማጥናታቸው ተወዳዳሪነታቸው ላይ ከባድ ፈተና ጋርጦባት እንደነበረ ትናገራለች። የልጅነት ህልሟ የነበረው የህክምና ትምህርት ቤት መግባት ስለነበር ያንን ለማግኘት ሁልጊዜም ጥረት ማድረግ ጀመረች።
እንዳሰበችው ሳይሆን ቀርቶ 2 ነጥብ 8 በወቅቱ ዲፕሎማ ለመማር የሚያስችል ውጤት በማግኘቷ ምርጫ በማጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይብረሪ ሳይንስ ለመማር ተገደደች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማረችም ህልሟን ለማሳካት ደከመኝ ሰለቸኝ የማትለው ይህች ሴት የማትሪክ ውጤትን ለማሻሻል ተፈተነች። ውጤቱም ጥሩ በመሆኑ የዲፕሎማ ትምህርቷን ጨርሳ ማኔጅመንት ዲግሪ በማታ ለሰባት አመታት ተማረች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስራ የጀመረችው ይህች ሴት የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በነበረችበት መስሪያ ቤት እድገት በማግኘት የሀገር ውስጥ እቃ ግዥ ሀላፊ በመሆን ተመደበች። ከዛም ጥረት በማድረግ ስታገለግል ከቆየች በኋላ በአስተዳደር ሰራተኛ በመሆን የዩኒቨርሲቲው አንድ አካል የሆነ ተቋም ውስጥ መስራት ጀመረች።
ማስተርሷን ለመማር በነበራት ፍላጎት ለዩኒቨርሲቲ ያቀረበችው ጥያቄ ለሰራተኞች ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ የትምህርት እድል አይሰጥም በተባለው ምክንያት በፕሮጀክት ማኔጅመንት ለመማር አምስት ጊዜ ተፈትና እድሉን ሳታገኝ ትቀራለች። ከዛም በግል ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተልእኮ ከወሰደች በኋላ በዚሁ ትምህርት በሀገር ውስጥ የማስትሬት ዲግሪዋን ለማግኘት ቻለች።
በተለያዩ ስራዎች እራሷን እየጠመደች ልምድ ካካበተች በኋላ የተለያዩ ጥናቶችን በመምራት የምትሰራው ፍፁም የማይደፈሩ የተባሉ ቦታዎች ድረስ መሄድ ያስደስታት ነበር። በወቅቱ ጅግጅጋ በጣም የሰላም ስጋት የነበረበት አከባቢ በመሆኑ ብዙ ሰው እዛ ለመሄድ ፍላጎት ሲያጣ እኔ እሄዳለሁ በማለቷ በርካታ ሰዎች ተቋውሞ ቢያሳዩም እሷ ግን አቅሟን ለማሳየት የሚያስችላት በመሆኑ ለመሄድ ቆርጣ ተነሳች።
በሄደችበት ወቅት በሀረር በኩል በትራንስፖርት ተጉዛ ስራዋን በአግባቡ ሰርታ በመምጣቷ ብዙዎች ከመደነቃቸው ባሻገር የራሷን አቅም በአግባቡ ያየችበት እንደነበር ትናገራለች።
ከዛም በኋላ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትርፍ ጊዜዋ የተለያዩ ጥናቶችን መስራት የጀመረችው ፍፁም በመንግስት ተቋም ለአስር አመታት ከሰራች በኋላ ደግሞ የግል ተቋማት ላይ ማመልከቻ ማስገባት ጀመረች። በስራዋ ከሀገር በቀል ድርጅቶች እስከ ተባበሩት መንግስታት (UN) ድረስ በተለያዩ የስራ ደረጃዎች ላይ ሰርታለች።
ሁልጊዜም የተለየ ስራ ለመስራት በመሞከር ራሷን በመፈተን ስትሰራ ከቆየች በኋላ ነበር በኤውብ ባገኘችው ስልጠና አቅሟን በማጎልበት በግሏ መስራት ስለምትችለው ነገር ማሰብ የጀመረችው። በወቅቱ ራስን መሆን፣ በራስ መተማመን ላይ ከፍተኛ አቅም ስላገኘች የተለያዩ ስልጠናዎችን በማግኘት አቅሟን አዳብራለች።
ሴትነት ያጎናፀፋትን አቅም ለማወቅ የተለያዩ ልምዶች ካገኘች በኋላ በራሷ ወደፊት ለመሄድ ቆርጣ ለመስራት ተነሳች። የምወደውን ስራ ለመስራት በማሰብ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ወይም መርሃግብር አመቻችነት ስራ ላይ መስራት ከጀመረች ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሳይሳካላት በመቅረቱ ያንን ታቆምና ሌላ ስራም ጀምራ ነበር። በመሀል ትዳር መመስረት፣ ልጅ መው ለድ የሚባሉትን የህይወት ሀላፊነቶችን እየተወጣች ወደፊት ተጉዛለች።
̋የትዳር ሕይወቴን በተመለከተ ዘንድሮ (ባለፈው ህዳር ወር) 15ኛ ዓመታችንን አክብረናል። ባለቤቴ አቶ ታፈሰ ሣህሌ በጣም መልካም የሆነ ባል ነው። ከአብራካችን የተወለደ አንድ የ11 ዓመት በፍቅር ታፈሰ የሚባል ወንድ ልጅ አለን። ልጃችንን የምናሳድገው ጥሩ ዜጋ ይሆን ዘንድ እኛ የምንሰራቸውን የበጎ ፍቃደኝነት ሥራዎች በተግባር እያሳየነው እና ሲያድግም እኛ ለእሱ የተሻለ ትምህርት ስለሰጠነው የተሻለ ዜጋ ሆኖ ያንን እድል ያላገኙትን ልጆች የእሱ ኃላፊነት መሆናቸውን እንዲያውቅ ከወዲሁ እያዘጋጀነው ነው።”
ወይዘሮ ፍፁም አንዲት ሴት ልጅ ከገጠር አምጥታ እያስተማረች የዜግነት ግዴታዋን እየተወጣች መሆኑን ትናገራለች። ይህች ልጅ አሁን 3ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በደረጃም ከ1 እስከ 3ኛ በመውጣት አጋሮቿን እያኮራች ትገኛለች።
ሴት በመሆን በሂደት የተለያዩ ተግዳሮቶችን ማለትም ፆታዊ ትንኮሳዎችን፤ አለቅነትን ያልተቀበሉ የበታች ሰራተኞች፤ ሌሎች በሙሉ ቢኖሩም ራስ ላይ ሁልጊዜ ሳይበገሩ መስራት፤ መውለድ ማግባት የያዙት የትምህርት ደረጃዎች ወደ ኋላ ሳያስቀራት ወደ ፊት መሄዷን ነው የምትናገረው።
ራስን ለማሳደግ ከሀምሳ የሚበልጡ የተለያዩ ዘርፎች አጫጭር ስልጠናዎችን እየወሰደች እንደሆነ የምትናገረው ፍፁም በተለያየ መልክ ራሷን ከማሳደጓ በላይ እያንዳንዱ የያዘችው ነገር ላይ ትኩረት አድርጋ በመስራት ያገኘችውን ማንኛውም አይነት እድል ከጀመረች ሳታቋርጥ እስከ መጨረሻው ድረስ በመድረስ ቁርጠኝነትን በመለማመድ ደስታን ለራሷና ለሌሎች ደግሞ ተምሳሌት መሆኗ አኩርቷታል።
በልጅነቷ እናቷ እንደመከሯት መማር በህይወት ውስጥ ማግኘት የምትፈልገውን ደረጃ ለመድረስ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን እንዲሁም በውይይት የምታመን፣ ሁሌም ሰርታ መታየት የምትችል ጠንካራ ሴት ለመሆን በቅታለች።
ሴቶች በጊዜያዊ በብልጭልጭ ነገሮች ከመወዳደር ይልቅ በእውቀት መወዳደርን ምርጫቸው ቢያደርጉ፤ ለገንዘባቸውና ጊዜያቸውን በሚያንፃቸው ቦታ ቢያውሉ ያኔ የተሻለ አለም መስራት ይችላሉ። ሴቶች በጓደኞቻቸው ተፅእኖ ስር መውደቅ በቡድን የማሰብ አዝማሚያዎችን አቁመው ማድረግ የሚፈልጉትን በራስ መተማመን ማድረግ ይኖርባቸዋል።
̋ሀገራችንን እንወዳለን እያልን ሀገራችንን ባለማወቃችን እገረማለሁ። በህይወቴ ካደረግኳቸው ነገሮች ኩራት የሰጠኝ እናቴ በልጅነታችን ሀገር ቤት ስትወስደን ያለው ጠረን የሚናፈቅበት አይነት ስለሆነ ያንን በስፋት ለማየት በተለያዩ ጊዜያቶች ማለትም በሃይማኖታዊ ጉዞዎች በተቻለኝ መጠን በአመት አንዴ ሀገር መጎብኘቴ ነው።”
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰረት በጎ አድራጎት፤ የአረጋውያኑ ድርጅት እንረዳዳ አረጋውያን ድርጅት 10 አረጋውያንን በመርዳት ተጀምሮ ዛሬ 824 አረጋውያንን ከመርዳት አልፎ ለልጅ ልጆቻቸው ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ይሰጣል፤ ለትምህርታቸው ደግሞ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቻቸው አማካይነት የጥናት እገዛ ይሰጣቸዋል። እሷም እዚህ ድርጅት ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ በጎ ፈቃደኞች አንዷ መሆኗን ነው የምትናገረው።
̋መጽሐፌ የታተመው ከጓደኞቼ እቁብ ሰብስቤ ነው። ለእነሱ ድንገተኛና ከእቅድ ውጪ የሆነ ነው፤ በኋላ ቢያገኙትም። በዚያ ላይ በእቁብ መጽሐፍ ማሳተም እንደሚቻል ማሳየታችን ጽፈው ወጪው ለከበዳቸው ጥሩ ምሳሌነት ይሆናል። ከሦስት ጓደኞቼ ውጭ ሁሉም የኤውብ ጓደኞቼ ሲሆኑ ከዚያ ውስጥ ከአንድ የኤውብ አጋራችን (ወንድ) በስተቀር ሁሉም ሴቶች ናቸው። ለሁሉም እቁብተኞቼ ክብርና ምስጋና ይድረስልኝ” ስትል በሰጠቸው የምስጋና መልዕክት ውይይታችንን ጨርሰን ተሰነባበትን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም