የቫይታሚን ‹‹ዲ›› እጥረት- ቀጣዩ የጤና ስጋት

ግራ ገብቶታል፣ በዚህ እድሜው እንዲህ አይነት ህመም ይገጥመኛል ብሎ አላሰበም። ጡንቻው ይዝልበታል። ድካም ይሰማዋል። አልፎ አልፎ ደግሞ በእግሮቹ አጥንት ላይ ህመም ይሰማዋል። ህመሙ እለት በእለት እየጨመረ ሲመጣ ነው መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅ ወደ ህክምና ተቋም ያመራው። ወደ ህክምና ተቋም አምርቶ አስፈላጊው መርመራ ከተደረገለት በኋላ የተነገረውን ውጤት ሲሰማ ግን ማመን አልቻለም። እንዲህ አይነቱ ህመም ይገጥመኛል ብሎም አላሰበም።

የተነገረው የህክምና ውጤት የቫይታሚን ዲ እጥረት ነበር። እርሱ ያገኘውን ምግብ ሁሉ እንደሚመገብ ቢረዳም ለዚህ ህመም ያበቃው በሚመገበው ምግብ ውስጥ በቂ የቫይታሚን ዲ ንጥረ ነገር አለመኖሩ ነው በሐኪም የተነገረው። አዘውትሮ ሲመገበው የነበረው የታሸገ ጣፍጭ ምግብ ይህን ህመም እንዳስከተለበት የተረዳውም ከህክምና ምርመራ በኋላ ነው:: ይህ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሙ የተቀየረው ወጣት ቢኒያም ተክሉ ታሪክ ነው።

አሁን አሁን ልክ እንደ ወጣት ቢኒያም ሁሉ አንዳንድ ሰዎች በህክምና ምርመራ የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባቸው እየተነገረ ነው:: ከዚህ ቀደም በአብዛኛው የቫይታሚን ዲ እጥረት በሕፃናት ላይ ብቻ እንደሚታይ የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ግን በወጣቶች፣ በጎልማሶች ብሎም በእድሜ በገፉ ሰዎች ላይም ጭምር እየተከሰተ እንደሆነና ቀጣዩ የጤና ስጋት እየሆነ እንደመጣ መረጃዎች እያሳዩ ነው::

አቶ ቢራራ መለሰ የሥነ ምግብ ባለሙያ ናቸው:: ከዚህ ቀደም በጤና ሚንስቴር የሥርዓተ ምግብ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል:: አሁን ደግሞ በዚሁ ሙያቸው በአንድ ተቋም ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ:: እርሳቸው እንደሚሉት፣ ሁለት ዓይነት ንጥረ ምግቦች ያሉ ሲሆን ሰውነት በብዛት የሚፈልጋቸው የንጥረ ምግብ ዓይነቶች ማክሮ ኒውትረንት ይሰኛሉ:: እነዚህም ኃይልና ሙቀት ሰጪዎች፣ ፕሮቲኖች፣ ጤናማ ስብና ውሃ ናቸው:: በትንሽ መጠን ሰውነታችን የሚፈልጋቸው የንጥረ ምግቦች ዓይነቶች ደግሞ ማይክሮ ኒውትነትን ሲባል ይህም ሚኒራሎችንና ቫይታሚኖችን ያጠቃልላል:: ማዕድናት ሲባሉ ለምሳሌ የደም ማነስ ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ አይረን፣ ዚንክ፣ ካልሺየምን ያካትታሉ:: ቫይታሚኖች ደግሞ ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚገኙትን ቫይታሚን ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ፣ ኬ እየተባሉ የሚጠሩትን ያጠቃልላሉ::

እነዚህ ቫይታሚኖች በውስጣቸው ሌላ ብዙ ዓይነት ቫይታሚኖችን አቅፈው የያዙ ናቸው:: ለአብነትም ቫይታሚን ቢ-1፣ ቢ-2 እና ቢ-3 የሚባሉ የቫይታሚን ዓይነቶች አሉ::

እያንዳንዳቸው የማይክሮ ንጥረ ምግቦች ሚኒራሎችና ቫይታሚኖች በሰውነት ውስጥ የተለያዩ ጥቅም አላቸው:: ቫይታሚን ዲ ደግሞ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ነው:: ለአብነት ካልሲየም ከወተትና ከተለያዩ የእህል አይነቶች የሚገኝ ማዕድን ሲሆን ለአጥንት ጥንካሬ፣ ለጥርስና አጠቃላይ በሰውነት ውስጥ ለሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችና ለምግብ ልመት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው:: ቫይታሚን ዲ በአጥንት ጥንካሬ ላይና ከምግብ ልመት ጋር በተያያዘ እንደ ግብዓት ብቻ ሳይሆን እንደ ሞተር ሆኖም ያገለግላል:: ለምሳሌ ካርቦሃይድሬት እንዲፈጭ የዚንክ፣ ካልሲየምና ቫይታሚ ዲ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው::

ከምግብ ብቻ የሚገኙ ቫይታሚን ዲዎች እንዳሉ ሆነው ቫይታሚን ዲን ልዩ የሚያደርገው ከፀሐይ ብርሃን ጋር የሚገናኝ መሆኑ ነው:: አገልግሎት የማይሰጥ የቫይታሚን ዲ ዓይነት በሰውነት ውስጥ ሲኖር ፀሐይ በሚገኝበት ሰዓት ምላሽ ፈጥሮ ወደሚያገለግል የቫይታሚን ዲ ዓይነት ይቀየራል:: ይህ ሲሆን በሰውነት ውስጥ የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳይኖር ያደርጋል:: ከቫይታሚን ዲ እጥረት ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎችን ይከላከላል:: ሕፃናት ገላቸውን ከታጠቡ በኋላ የጠዋት ፀሐይ እንዲሞቁ የሚደረገውም ቫይታሚን ዲ ከፀሐይ ብርሃን እንዲያገኙ ነው:: ይህ የሚሆነው በቆዳቸው ላይ ፀሐይ በሚያርፍበት ጊዜ ምላሽ ይፈጠርና አገልግሎት የማይሰጠው የቫይታሚን ዲ ወደ ጠቃሚ ቫይታሚን ዲ ይቀየራል:: ይህ ታዲያ በሕፃናት ላይ ብቻ ሳይሆን በአዋቂዎች ላይም ይሰራል::

አቶ ቢራራ እንደሚያስረዱት የቫይታሚን ዲ እጥረት መንስኤ አንደኛው ለምሳሌ ሕፃናት በአግባቡ የፀሐይ ብርሃን አለማግኘት ሲሆን፣ በአዋቂዎች በኩል ደግሞ ለረጅም ጊዜ ከቢሮ ሳይወጡ ማሳለፍ ፣ የፀሐይ ብርሃን በበቂ ሁኔታ በማይደርስባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ አፓርትመንትና ሌሎች ተደራራቢ ቤቶች ውስጥ መኖር ናቸው:: ሁለተኛው የቫይታሚን ዲ እጥረት መንስኤ ደግሞ የተመጣጠኑ ምግቦችን በተለይ በቫይታሚን ዲ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በበቂ ሁኔታ አለመመገብ ነው::

የቫይታሚን ዲ እጥረት በአብዛኛው በሕፃናት ላይ የሚከሰት ቢሆንም በአዋቂዎች ላይም ይታያል:: ሕፃናት ፈጣን እድገት ስለሚያሳዩ፣ ፈጣን የምግብ መፈጨት ሂደት ስላላቸውና በሽታ የመከላከል አቅማቸውም ገና ስለማይጠነክር የቫይታሚን ዲ እጥረት በብዛት ይገጥማቸዋል:: ነገር ግን የቫይታሚን ዲ እጥረት በወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች ላይም ሊከሰት ይችላል:: በተለይ ደግሞ አሁን አሁን በወጣቶች ላይ የቫይታሚን ዲ እጥረት በብዛት ይታያል:: ለዚህም አንዱ መንስኤ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት አለመከተል ነው::

ወጣቶች የፀሐይ ብርሃን በበቂ ሁኔታ ሊያገኙ ይችላሉ:: ነገር ግን በቂ ንጥረ ነገሮች ያሏቸው ምግቦችን ማለትም አትክልትና ፍራፍሬዎችን ስለማይመገቡና ከዚህ ይልቅ ጣፋጭና የታሸጉ ምግቦችን መመገብ ስለሚያዘውትሩ ለቫይታሚን ዲ እጥረት ይጋለጣሉ:: የጣፋጭነት ይዘት ያላቸው ምግቦችን መመገብ ለጊዜው ኃይልና ሙቀት ቢሰጡም የምግብ ፍላጎትን ስለሚዘጉ ቫይታሚኖችንና ሚኒራሎችን ይከለክላሉ:: ስለዚህ በወጣቶች በኩል የተዛባ የአመጋገብ ልምድ ስላለ ለቫይታሚን ዲ እጥረት አስተዋጽኦ አለው:: ከቫይታሚን ዲ እጥረት ጋር በተያያዘ የካልሺየም፣ ዚንክና አይረን እጥረትም በወጣቶች ላይ የደም ማነስ ችግር ሲያስከትል እየተስተዋለ ነው::

በተመሳሳይ በትምህርት ቤቶች አካባቢም ለተማሪዎች የሚቀርበው ምግብ የተመጣጠነ አይደለም:: በብዛት ለተማሪዎች በሽያጭ የሚቀርቡት ጣፋጭና ጥቅም አልባ ምግቦች ናቸው:: ከአመጋገብ ሥርዓት መጓደል ጋር በተያያዘና የተመጣጠኑ ምግቦችን አለመመገብ ለቫይታሚን ዲ እጥረት መከሰት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው::

አቶ ቢራራ እንደሚያስረዱት፣ አንድ ሰው የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለበት በተለያዩ መንገዶች ሊያውቅ ይችላል:: ይሁንና ይህን ለማወቅ እንደ ቫይታሚኑ ዓይነት ይለያያል:: ለምሳሌ የደም ማነስ ምልክቶች በሰውነት አካል ላይ ይታያሉ:: ነገር ግን የቫይታሚን ዲ እጥረት ምልክቶች በሰውነት ላይ ላይታዩ ይችላሉ:: ለዛም ነው የህክምና ባለሙያዎች የቫይታሚን ዲ እጥረት ምን ዓይነት ምልክቶች እንዳሏቸው በአካላዊ ምርመራ የሚለዩት:: ከዚህ ውጭ በሰውነት ውስጥ መኖር ያለባቸው የንጥረ ምግብ መጠኖችን ለማወቅ የደም ናሙና ተወስዶ በላብራቶሪ ይታያል:: መጠኑ በእድሜ ደረጃ ተለክቶ ተፈላጊው የምግብ ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ ካለ እጥረት የለም ከሌለ ደግሞ የቫይታሚን እጥረት አለ ማለት ነው::

ከዚህ በመነሳት እያንዳንዱ የቫይታሚን እጥረት ምን አይነት ምልክት እንዳለው ለማወቅ ይቻላል:: ይሁንና አብዛኛዎቹ የቫይታሚን እጥረት ምልክቶች ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው:: ይህም ሊሆን የቻለው አንደኛው ቫይታሚን ከሌላው ቫይታሚን ጋር ተያያዥነትና ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ነው:: ስለዚህ እያንዳንዱ የቫይታሚን እጥረት የሚያሳየው የራሱ ምልክት አለው:: ለምሳሌ መገርጣት፣ የሰውነት መድረቅ፣ ድካም ሊሆን ይችላል:: በተመሳሳይ ከቫይታሚን ዲ እጥረት ጋር በተያያዘ ሊታዩ የሚችሉ የተለመዱ ምልክቶች የጡንቻ መድከም፣ ጭንቀት፣ ድካምና የአጥንት ህመም ናቸው::

የቫይታሚን እጥረት እንዳለ ከተረጋገጠ የተለያዩ ህክምናዎች ይኖራሉ:: እጥረቱ እንዳይባባስ መከላከልም ይቻላል:: የመጀመሪያው የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል ነው:: በቫይታሚን ዲ የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ ይመከራል:: ሁለተኛ እጥረቱ ሕፃናት ላይ የሚታይ ከሆነ በቂ የፀሐይ ብርሃን በተለይ የጠዋት ፀሐይ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል:: ሦስተኛ ያለውን የቫይታሚን ዲ እጥረት በቶሎ ለመፍታት ተጨማሪ ምግቦችን መመገብ ነው::

በሌላ በኩል የቫይታሚን እጥረቱ በወጣቶችና አዋቂዎች ላይ የተከሰተ ከሆነ የአመጋገብ ሥርዓት መስተካከል ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል:: የምግብ ስብጥርና ምድቦችን አውቆ መመገብ ያስፈልጋል:: ከጣፋጭና ጥቅም አልባ ምግቦች ራስን ማራቅ ይገባል:: በነዚህ ምትክ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በብዛት መመገብ ይመከራል:: የእንስሳት ተዋፅኦም በጣም ጠቃሚ ነው:: ወተት፣ እንቁላል፣ ቀይ ስጋ ወዘተ መመገብ ያስፈልጋል:: አመጋገብን ማስተካከልና በቂ የፀሐይ ብርሃን ማግኘት ከተቻለ የቫይታሚን ዲ እጥረትን ማስተካከል ይቻላል::

አቶ ቢራራ እንደሚሉት፣ የቫይታሚ ዲ እጥረት የአጥንት ህመም እንዲከሰት ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል:: አጥንት እንዲጠነክርና እንዲዳብር ብሎም በጣም የተጎዳ ከሆነ እንዲያገግም በንጥረ ምግብ ውስጥ የሚገኙ ቫይታሚኖች ያስፈልጋሉ:: ስለዚህ የቫይታሚን ዲ እና ካልሺየም ሚኒራል እጥረት ካለ አጥንት ጥንካሬ አይኖረውም:: ስለዚህ ከቫይታሚን ዲ የሚገኙ የምግብ ንጥረ ነገሮች ለአጥንት ጤናና ጥንካሬ ወሳኝ በመሆናቸው በነዚህ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ ያስፈልጋል::

በኢትዮጵያ በብዛት የታወቁት ቫይታሚን ኤ፣ የአይረን፣ የዚንክ፣ ካልሺየም እጥረቶች ናቸው:: የቫይታሚን ዲ እጥረት ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ችግሩ ጎልቶ እየወጣ የመጣው:: ይህ ሲባል ቫይታሚን ዲ እጥረት ችግር ሳይሆን ቀርቶ አይደለም:: የቫይታሚን ዲ እጥረት አሁን ላይ እየመጣ ያለና የጤና ስጋት እየሆነ ነው:: በተለይ አሁን ላይ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤው እየተለወጠ መምጣት ለቫይታሚን ዲ እጥረት ስጋት መጨመር አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል:: ቫይታሚን ዲ ደግሞ ከሌሎቹ የሚለየው በሰውነት ውስጥ አገልግሎት የማይሰጥ መስሎ ተቀምጦ የፀሐይ ብርሃን ማግኘት ሲጀምር ነው ምላሽ የሚሰጠውና ወደ ጠቃሚ ቫይታሚን የሚቀየረው::

ከዚህ አኳያ የፀሐይ ብርሃን አለማግኘት እንደ ቀላል ጉዳይ የሚታይ አይደለም:: ሰዎች በተለይ የጠዋት ፀሐይ ለተወሰኑ ደቂቃዎች መሞቅ አለባቸው:: ረጅም ሰዓት በሥራ ቦታና በመኖሪያ ቤት ውስጥ ማሳለፍም ተገቢ እንዳልሆነ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ:: ሁሌም እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል:: ከዚህ ባለፈ እንደው የቫይታሚን ዲ እጥረትን ለማስተካከል ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ የምግብ ንጥረ ነገሮች በሰውነት ውስጥ እንዲኖሩና ጤናማ ለመሆን ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ ከእንስሳት ተዋፅኦ፣ ከእህል ዘሮች፣ ከጥራጥሬ፣ ከሰብል የተመጣጠኑ ምግቦችን መመገብ ያስፈልጋል:: በዚህ መልኩ ከቫይታሚን እጥረት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You