ኢራንና ሩሲያ በህንድ ውቅያኖስ ላይ ወታደራዊ ልምምድ አካሄዱ

ኢራንና ሩሲያ በህንድ ውቅያኖስ ላይ ወታደራዊ ልምምድ አካሄዱ።

ሩሲያ እና ኦማንን ያሳተፈ በኢራን የተዘጋጀው የባህር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ በትናንትናው እለት መጀመሩን ሮይተርስ የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ ዘግቧል።

እንደዘገባው ከሆነ በልምምዱ ላይ ዘጠኝ ሀገራት በታዛቢነት ተጋብዘዋል።

“አይኤምኢኤክስ 2024” የተሰኘው የዚህ ልምምድ አላማ በቀጣናው የጋራ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና የማሪታይም ደህንነትን ለመጠበቅ ወዳጅነትን ለማሳየት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

የልምምዱ ተሳታፊዎች የዓለም አቀፍ የንግድ ደህንነት በማስከበር፣ የባህር መስመሮችን በመከላከል፣ የሰብአዊ ሥራዎችን በማጠናከር እና በነፍስ አድን እና የእርዳታ አቅርቦትን በማጠናከር ዙሪያ ልምምድ ያደርጋሉ።

ልምምዱ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለው እርምጃ ማየልን እና በኢራን የሚደገፈው የየመኑ ሀውቲ ታጣቂ በመርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የአጸፋ ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ ከተፈጠረው ቀጣናዊ ውጥረት ጋር ተገጣጥሟል።

ኢራን በቀጣናው ከአሜሪካ ጋር ለገባችበት ውጥረት ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ወታደራዊ ትብብር በማድረግ ምላሽ እየሰጠች ነው።

ባለፈው ሚያዝያ ወር ኢራን፣ ቻይና እና ሩሲያ አምስተኛ የጋራ የባህር ኃይል ልምምዳቸውን በኦማን ባህረሰላጤ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

ሳኡዲ አረቢያን፣ ኳታር፣ ህንድ፣ ባንግላዴሽ እና ታይላንድን ጨምሮ ሀገራት የአሁኑን ወታደራዊ ልምምድ እየተመለከቱ ናቸው።

ኢራን የሊባኖስን ወረራ እና የሄዝቦላህ መሪ ነስረላህ ግድያን ለመበቀል በእስራኤል ላይ የሚሳይል ናዳ ማዝነቧ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You