የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች ወንዶች እጅ ኳስ ቻምፒዮና ከጥቅምት 23 እስከ 27/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በወጣቶች ስፖርት አካዳሚና አራት ኪሎ ትምህርትና ስልጠና ማዕከላት ጅምናዝየሞች ይካሄዳል። በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከየዞኑ የተወከሉ 12 ሀገራት ለዓለም እጅ ኳስ ዋንጫ ለማለፍ የሚፋለሙ ሲሆን የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድንም ከወዲሁ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡
የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከአፍሪካና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር በትብብር የሚያዘጋጁት የ2024 የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች ወንዶች እጅ ኳስ ቻምፒዮና ለአንድ ሳምንት ይካሄዳል። ኢትዮጵያ ከወራት በፊት በዞን ደረጃ የተካሄደውን ከ18 እና 20 ዓመት በታች ወጣትና ታዳጊዎች እጅ ኳስ ቻምፒዮናን ማስተናገዷ የሚታወስ ሲሆን፣ አህጉር አቀፉንም ውድድር በስኬት ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። ውድድሩን ከማስተናገድ ባሻገር ከ18 ዓመት በታች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ ተሳታፊ በመሆኑ ኢትዮጵያ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆና ለመቅረብ የሚያስችላትን ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች።
በአፍሪካ እጅ ኳስ ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ አሰልጣኝ እና የቡድን መሪ ተመድቦለት ዝግጅት እያደረገ ነው። በዋና አሰልጣኝነት ኢንስፔክተር ተስፋዬ ሙለታ እንዲሁም በምክትል አሰልጣኝነት ጃቢር ሸምሱ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፋቸው የሚታወቅ ሲሆን በአህጉር አቀፉ መድረክም ውጤታማ ለመሆን ቡድኑን እያዘጋጁት ይገኛሉ። የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰጠኸኝ አዲሱ ደግሞ የቡድኑ መሪ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከአምስት ወራት በፊት ከዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር ባዘጋጀችውና 11 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት የዞን 5 ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች እጅ ኳስ ቻምፒዮናን በስኬት ከማስተናገዱ በተጨማሪ ብሔራዊ ቡድኗም ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ችሎ ነበር። በወቅቱ ብሔራዊ ቡድኖቹ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው ዝግጅታቸውን ቢያደርጉም፣ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ከ18 ዓመት በታች ቡድኑ ደግሞ ዋንጫው ማንሳት ችሏል።
ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን ለዚህ ስኬት ያበቁት አሰልጣኞች አሁንም በአፍሪካ ቻምፒዮና ውጤታማ ለመሆን ጥቅምት ከ8/2017 ዓ.ም ጀምሮ ቡድኑን አሰባስበው ዝግጅት የጀመሩ ሲሆን፣ የተመረጡና በክለብ ውድድር ምክንያት ውጪ ሀገር የሄዱ ስድስት ተጫዋቾችን በማካተት ጠንካራ ዝግጅት እንሚያደርጉ ዋና አሰልጣኙ ኢንስፔክተር ተስፋዬ ሙለታ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ለዝግጅቱ 18 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ጥሪ ተደርጎላቸው ዝግጅት ሲጀምሩ በሂደት አራት ተጫዋቾች እንደሚቀነሱም ታውቋል፡፡
አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከእረፍት እንደመመለሳቸው ለስድስት ቀናት ጠዋት እና ማታ የአካል ብቃትን መሠረት ያደረግ ዝግጅት እንደሚደረግ አሰልጣኙ ጠቁመዋል። ከ18 ዓመት በታች ከሚገኘው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሦስት ተጫዋቾች ተቀንሰው እድሜያቸው ገና የሆኑ ሦስት ተጫዋቾች ደግሞ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ መካተታቸውንም ተናግረዋል። ለአንድ ሳምንት ያህል የአካል ብቃትንና ትንፋሽን መሠረት ያደረገው ልምምድ ከተጠናቀቀ በኋላም የቡድን ቅንጅት ላይ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።
ውድድሩ ኢትዮጵያ እንደ መካሄዱ ዋንጫ ለማንሳት ጠንካራ ዝግጅት እንደሚደረግ የገለፁት አሰልጣኙ፣ ቡድኑ በቂ ዝግጅት በማድረግ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ አስፈላጊው ድጋፍና ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በስድስቱ አፍሪካ ዞን ውድድሮችን አድርገው አሸናፊ የሆኑ ከ18 እና 20 ዓመት በታች ሁለት ቡድኖች በአጠቃላይ አሥራ ሁለት ቡድኖች በአህጉር አቀፉ ቻምፒዮና የሚፋለሙ ይሆናል። በታዳጊዎች ኢትዮጵያ፣ ካሜሩን፣ ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ እና ዚምባብዌ የሚሳተፉ ሲሆን፣ በወጣቶች ኮንጎ ጋና፣ ጊኒ፣ ርዋንዳ እና ዚምባብዌ ተሳታፊ ሀገራት ናቸው። በሁለቱም የእድሜ እርከኖች የሚያሸንፉ ሀገራት አፍሪካን ወክለው በዓለም እጅ ኳስ ቻምፒዮና ላይ ይሳተፋሉ፡፡
ኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትሕ ወልደሰንብት በፌዴሬሽኖች ጥረት ውድድሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቢሆንም ብዙ ትኩረት ይሰጥ እንዳልነበረ አስታውሰው፣ አሁን ግን በመንግሥት ልዩ ትኩረት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ውድደሩን ኢትዮጵያ ለማዘጋጀት የተፈለገችውም የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለመገንባት እና ሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ለማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል። የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በመኖሩ ታዳጊዎችን ለማነሳሳትና ብሔራዊ ቡድን የመጫወትና የውድድር እድልን ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለውም አክለዋል። ለውድድሩ ከ350 በላይ ልዑካኖች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሲሆን በመድረኩ የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ላይ አካዳሚ የመክፍት እቅዱን እንዲቀጥልበት ለማሳመን ይሰራልም ተብሏል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም