የሞተር ሳይክሎቹ ነገር…

ከቢሮዬ ብዙም በማይርቁ ህንፃዎች፣ በየፎቁ ማረፊያ ላይ ዘወትር የሚታየው የቡና አቀራረብ ይማርካል። እሱን ተከትሎ በወጉ ከሚቆላው ቡና ለአፍንጫ የሚደርሰው ልዩ መዓዛ ፣ የሻይ ቅመም ሽታ … ብቻ ምን አለፋችሁ ቦታውን አልፎ ለመሄድ በእጅጉ ይፈትናል።

በተለይማ ‹‹ሱስ›› አለብኝ ለሚል ቡና አዘውታሪ የሚያየውን አልፎት ሊሄድ ይቸግረዋል። ከቀናት በአንዱ አብረውኝ ከነበሩት መካከል አንደኛዋ “ኧረ ይሄንን ቡና ማለፍ …” ትንሽ የሆነ ቃላት ወረወረች። ሁላችንም ተያይተን ፈገግ አልን። ምክንያቱም ቀሪዎቻችን የማኪያቶ እንጂ የቡና አፍቃሪዎች አይደለንም። ያም ሆኖ ቡና ፉት አንልም ማለት አይደለም። ስለዚህ የምንጠጣውን ቁጭ ብለን ለመወሰን ግብዣውን መቀበል ግድ ነውና ተስማማን።

ረፋድ ላይ የቡና ሰዓት ነው ልበል? ከዚህም ከዛም በሚመጡ እንግዶች ወንበሮቹ ተይዘዋል። በወጉ ተደረደሩ አነስ አነስ ያሉ ወንበሮችን ሳብ አድርገን ተቀመጥን። በጋራ ቡና ለመጠጣት የተቀመጡት የየራሳቸውን ጨዋታ ይዘዋል። ከወንዱም፣ ከሴቱም ተደበላልቀው፣ በርከት ብለው አጠገባችን የተቀመጡ ወጣቶች ይታያሉ። ጀርባቸውን ሰጥተውናል። ጨዋታቸው ጆሮ ገብ ነውና ልቤን እየሰረቀው ነው።

እንደው ለወጉ ከጓደኞቼ ጋር በአካል ተቀመጥኩ እንጂ በጨዋታ ማዳመጡ ተሳታፊ የነበርኩት ከወደኋላዬ ነው። በአካል እዚህ፣ በጨዋታ ደግሞ እዛ። ቀልቤን የሳበው ጭውውታቸው አሁን አሁን የከተማውን ነዋሪ እያስፈራ ያለው በሞተር ሳይክል የሚደረግ ዝርፊያ ነው። እኔ አሁንም ጆሮዬን ጥያለሁ፡፡

“ሰማሽ እንዴ…›› አንዷ ጨዋታዋን ቀጠለች። “ምኑን… ?›› አጠገቧ ያለችው እንደኔ ጆሮዋን ጣለች”

“እዛ ኮንዶሚኒየሙ ጋር የሚመላለሰው ሞተር ሳይክል እኮ ሥራው… “ ስትል አዳማጭዋ ብዙ አላስኬደቻትም። እሷም በተደጋጋሚ የሰማችው ወሬ መሆኑን አከለችበት። ‹‹እንደውም እኮ! ለፖሊስ ወንጀሉ ሲጠቆም ‹‹በማስረጃ አስደግፋችሁ አምጡ እጅ ከፍንጅ ካልሆነ ተብለው ነዋሪዎቹ ‹‹ኩም›› ተደረጉ አሉ›› ወሬውን ቀጠለች። … ጨዋታው ደርቷል። ሁሉም የሰማውን ሁሉ ያብራራ ጀመር። የአንዳንዱ ጨዋታ ከ “አሉ “ አለፍ ያለ ነው። በተጨባጭ የተያዙትና በፖሊስ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ያዩ፣ የሰሙትን አክለው ነው የሚያወሩት።

‹‹ኧረ ! የሌባ ነገር በጣም አስፈሪ ሆኗል። በሞተር ሳይከል እያለፉ አንገቱ ላይ ወርቅ አድርጎ ያዩትን ወጣት መሀል ከተማ ላይ መንትፈውት ማምለጣቸውን ፤ ከጆሮ ላይ ሞባይል፣ ከሴቶች ትከሻ ቦርሳ እየተመነተፈ መሆኑ በማብራሪያ ተገለጸ። አስፈሪና አሳዛኝ በሆነ መልክ በከተማችን እየሆኑ ያሉ ችግሮችን የሚገለጽ ስጋት አዘል ወሬ ከዚህም ከዛም ይዋጣል።

እኔም በአንድ ወቅት በሞተር ሳይክል ታጅቦ የተደረገ አንድ የዝርፊያ ሙከራ ትውስ አለኝ። “አይደፈሬ” በሚባል ቤተክርስቲያን ላይ የተሞከረ ነበር። በጊዜው በመሳሪያ ታግዘው ዝርፊያ ሊፈጽሙ የነበሩ ሶስት ታርጋ የሌላቸው ሞተር ሳይክሎች በዓይነ ህሊናዬ ግጥም አሉ። በቤተክርስቲያኑ ሠራተኞችና አስተዳደሪዎች በተሰበሰቡበት ቢሮ ውስጥ ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ድርጊት የገለጹትም “ወዴት እየሄድን ነው” ሲሉ ነበር ። የአሁኑ የሰዎች ጭውውትም ወደ እዛው እውነታ ወሰደኝ። “ወደየት እየሄድን ነው?”››

በሞተር ሳይክል የሚደረገው ውንብድና በዚህ ብቻ የሚያቆም እንዳልሆነ ደግሞ አንድ ባልደረባዬ ነግሮኝ ነበር። ምነው ፖሊሶቻችን የት ናቸው? ምንስ እየሰሩ ነው? ለማለት አስደፈረኝ። ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ በወጣትነት ዕድሜ ክልል ላይ ያለ ሞተረኛ ደጋግሞ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ይመላለሳል። እንዲህ የሚያደርገው ታዲያ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በጥቁር ገበያ በመመንዘሩ ነው። እግር የማብዛቱ ሽፋን ደግሞ በብዙዎች የተለመደው ጫት ነበር።

ይህ ሰው ሁሌም “ጫት ይዘህ ና” ይባላል። የጫቱ ስያሜ በጥቁር ገበያ የሚመነዘረውን የገንዘብ ዓይነት የሚያሳውቅ ኮድ አለው። የአወዳይ ፣ የባህር ዳር ፣ የገለምሶ ፤ ፓውንድ ፣ ዶላር ፣ ዩሮ… እንደ ማለት ነው። በዚህ ኮድ የተደወለለት ቦታ ላይ ገንዘብ ይዞ ይመጣል፣ ሥራውን ይፈጽማል።

በዚህ ተግባር ተጠምዶ ሲመላለስ ታዲያ አንድ ፖሊስ ቢጠራጠር አስቁሞ ይፈትሸዋል ። ሞተር ሳይክሉን ብጥር አድርጎ ጫማውን ሳይቀር ይበረብርና ምንም ስላለገኘበት ይለቀዋል። አጅሬ ግን የመነዘረውን የውጭ ገንዘብ የከተተው የደህንነት መጠበቂያ (ሄልሜቱ) ውስጥ ኖሯል። “ዛሬ ገብቼለት ነበር፤ ግን አፈዘዝኩት” “ እያለ ያመለጠበትን መንገድ እንደ ጀብዱ ያወራዋል።

‹‹ዛሬ ተሳከቶልህ ይሆናል ነገ ግን መያዝህ አይቀርም››አልኩ። በልቤ። ባለ ሞተር ሳይክሎች ከሚሰሩት ሕገ ወጥ ተግባር ባልተናነሰም ለነፍስ አድን ሥራዎችም የሚፈጥኑ ጥቂቶች አይደሉም። ሁሉም ወንጀለኞች ናቸው ባይባልም ጥሩ የሚሰሩትን ማመስገን ደግሞ ያስፈልጋል። መድኃኒት አለበት ከተባለ ቦታ ለህመምተኛ ፈጥነው ያደርሳሉ። በየመንገዱ የሚቆሙ መኪናዎችን የሚጠግን የጋራዥ ሠራተኛ በፍጥነት አምጥተውም መኪናውን ያሰራሉ። ለላቦራቶሪ ምርመራ የሚሄድ ናሙና በፍጥነት ሲያደርሱና ውጤት ሲያቀብሉ ለተመለከታቸው አንጀት አርስ ብሎ ያመሰግናቸዋል።

የኦን ላይ ገበያ ምርቶችን ለገዢው በማስረከብም ሚናቸው ከፍ ያለ ነው። እነሱን ታዲያ ኑሮ አቅላይ፣ ፈጥኖ ደራሸ ‹‹ከተፎ›› ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ሕጋዊ የሆኑትን ብቻ አይቶ መዘናጋት ደግሞ አያስፈልግም። ተገቢው ክትትል ተገቢው ቁጥጥር ያስፈልጋል።

በመንገድ ላይ በእጅ ስልክ የሚያወሩትም ከአስፋልት ዳር ራቅ ብለው ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ቢጠቀሙ ንብረታቸውን ከመንታፊዎች ያድናሉ። አሁን አሁን እየበረታ ያለው የሞባይል መንታፊ በእግረኛም፣ በሞተረኛም መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። እኔ ደግሞ አይቼና ሰምቼ ከታዘብኩት ለመረጃም፣ ለትምህርትም ይሆን ዘንድ ይህን አልኩ ። ቸር እንሰንብት !

አልማዝ አያሌው

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You