ፋሽን የሚለው ቃል በየጊዜው የሚቀያየር፣ በአንድ ወቅት ተለብሶ ተፈላጊነቱ የሚያበቃ እና ገበያ ተኮር እንደሆነ ዲዛይነር ኤርሚያስ ልዑልሰገድ ይገልጻል። ዲዛይነር ኤርሚያስ የታሪዮ ፋሽን መስራች ነው። እሱ እንደሚለው የፋሽን ሃሳብ የጊዜ ወሰን የሌለው እና የራሱን እሳቤ የያዘ ነው።
ኤርሚያስ የፋሽን ዲዛይን ሃሳብ ይዞ ብቅ ያለው ገና የ12ተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ሲሆን፤ መነሻው የራሱ ባህሪ እና ለፋሽን ያለው መረዳት ነው። የሚፈልገውን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ያመነበትን ሃሳብ ለመናገር በፍጹም የማይፈራ፣ ወጣ ያለ ባህሪ እንዳለው ጠቅሶ፣ አንዳንዶች ይህን ባህሪውን እንደ ትዕቢት እንደሚቆጥሩትም ይገልጻል። እነዚህ ባህሪያት የኤርሚያስ መገለጫዎች ናቸው ይላል።
ኤርሚያስ በተማሪነቱ ወቅት ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ የመማር ፍላጎት ነበረው፤ ዲዛይነር የመሆን ፍላጎትን ያዳበረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚያጠናቅቅበት ወቅት ነበር። ካይኒ ዌስት የተባለ ዘፋኝ በአንድ ወቅት ባወጣው አልበም ተስቦ የድምጻዊውን ማንነት በሚያጣራበት ወቅት ድምጻዊው የራሱ የጫማ ፋሽን ብራንድ እንዳለው ይገነዘባል።
12ተኛ ክፍል እያለን በትምህርት ቤታችን ራሳችንን የሚገልጽ ልብስ ለመሥራት ስንዘጋጅ ምን ዓይነት ልብስ ይሁን በሚለው ኤርሚያስ ያቀረበው ዲዛይን እና አንድ ጓደኛው ያቀረበው የዲዛይን ሃሳብ በጋራ በማጣመር አዲስ ዲዛይን ተሰራ። ከዚያም ልብስ ዲዛይን ወደ ማድረግ ሃሳብ መምጣቱን ተናግሯል።
እሱነቱን ይገልጻሉ የሚላቸው አለባበሶች እንደልብ አለማግኘቱ ኤርሚያስ ፋሽን ዲዛይንን ለመማር እንዲወስን አደረገው። ይህን ተከትሎም ‹‹ታሪዮ›› የሚለው እሳቤ ተመሠረተ ሲል ይገልጻል።
እሱ እንዳብራራው፤ ‹‹ ታሪዮ ›› የሚለው ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ነው፤ ትርጉሙም ራስን በማወቅ የሚመጣ በራስ መተማመን አልያም ጎልቶ መታየት የሚል ነው። የሰዎችን እይታ መፈለግ፣ በሌሎች እይታ ውስጥ መግባት፣ በፋሽን ኢንዱስትሪው ጎልተው የሚወጡ ደማቅ የሆኑ ቀለማት የሚሉትን እሳቤዎች ኤርሚያስ አይስማማባቸውም።
‹‹አንድ ሰው በራሱ ለመተማመን ራሱን በደንብ ማወቅ አለበት፤ ፋሽን ሰዎች ራሳቸውን የሚገልጹበት አንዱ መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ። አንድ ሰው ራሱን በፋሽን ውስጥ ለመግለጽ ከማሰቡ አስቀድሞ ግን ራሱን በደንብ ማወቅ፣ ታሪኩን ማወቅ ይኖርበታል፤ እንደዚያ ካልሆነ ግን የሆነን ሰው መንገድ መከተል ይሆናል ›› ሲል ያብራራል።
የታሪዮ ፋሽን ዋና መገለጫ ‹‹ ፍርሀት የለም ›› የሚል ሃሳብን የያዘ መሆኑን ተናግሮ፣ ሰዎች ምንም የሚያስፈራቸው ሁኔታ ባይኖር ራሳቸውን በትክክል መግለጽ፣ አቅማቸውን አውጥተው ማሳየት ይችላሉ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ሲል አመልክቷል።
‹‹ እኔ የማምነው አንድ ሰው ራሱን ይበልጥ እያወቀ እና እየተረዳ በመጣ ቁጥር የማንም ሰው ይሁንታ እና ማረጋገጫ አይፈልግም፤ በጣም እየተረጋጋ የሚመጣ እና የራሱን ትክክለኛ ባህሪ የሚገነባ በመሆኑ ባለው እይታ ራሱን የሚገልጽበት መንገድ ጎልቶ እንዲወጣ ያደርገዋል ›› ሲል ያብራራል፡፡
የ12ተኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ ለፈተና በሚዘጋጅበት ወቅት የዲዛይን ትምህርት መማር ጀመረ። ታሪዮ የሚለው የፋሽን ዲዛይን ሃሳብም እውን ወደ መሆን መጣ። በሰባት ወር የትምህርት ጊዜው ታሪዮ የሚለውን ብራንድ እንዴት መገንባት ይቻላል የሚለውን እና ቴክኒካል እውቀትን ቀሰመ።
የፋሽን ዲዛይን ተማሪዎች ተምረው ሲጨርሱ የራሳቸውን የፈጠራ ሥራዎች በምረቃ ቀናቸው ያቀርባሉ። ኤርሚያስም በዚህ ቀን ያቀረበው የዲዛይን ሥራ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አተረፈለት። ‹‹በወረቀት ላይ ዲዛይን አድርጌ ለሰዎች ሳሳይ ብዙዎች አልወደዱትም ነበር፤ ተሰርቶ ሲያልቅ ግን ተቀበሉት›› ሲል ይገልጻል።
የታሪዮ ፋሽን በገበያ ላይ ተቀባይነት ያገኙ አልያም ገበያን መሠረት ተደርገው የሚሰሩ ልብሶችን በማውጣት ላይ አያተኩርም። ‹‹የምሰራቸው ልብሶች በሰዎች ዲዛይን ውስጥ ቶሎ የሚታዩ አይደሉም፤ ሰዎች በፈለጉበት ጊዜ የሚለብሷቸው፣ እንደፈለጉ ዲዛይን እንዲያደርጓቸውና በየእለቱ እንዲጠቀሙባቸው እፈልጋለሁ›› የሚለው ኤርሚያስ፣ በጊዜ የማይገደቡ የፋሽን ዲዛይኖችን ወደ ገበያው ይዞ መቅረቡን ተናግሯል። ‹‹እንደ ታሪዮ ኮሌክሽን ሳይሆን ሥራዎቻችንን ምዕራፍ ብለን ነው የምንገልጻቸው። በእያንዳንዱ ሥራዎቻችን ላይ ማስተላለፍ ከምንፈልገው ታሪክ ጋር ነው የምናጋራው። ››
ለመጀመሪያ ጊዜ ሰርቶ ያስተዋወቀው የፋሽን ዲዛይን ስብስብ በእርሱ አጠራር ምዕራፍ ‹‹አልኬቡላን›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው። ‹‹አልኬቡላን አውሮፓውያን ወደ አፍሪካ አህጉር ከመምጣታቸው በፊት አህጉሪቱ ትጠራበት የነበረው ስም ነው። ትርጉሙ የሰው ዘር መገኛ ማለት ነው። በዚህም የመጣንበትን መንገድ እንወቅ የሚል መልእክት አስተላልፏል። ለእዚህም ለአፍሪካ ትልቅ ዋጋ የከፈሉ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ያሉ የነፃነት ታጋዮችን እንደ ምሳሌ ተጠቅመናል ›› ሲል ገልጿል።
የፋሽን ዲዛይን ሥራዎች በአብዛኛው የሚተዋወቁት በሴቶች ነው። ኤርሚያስ ግን ሃሳቡን በልብስ ዲዛይኖች ላይ ማሳረፍ የጀመረው በወንዶች ነው። ‹‹ታሪዮ ፋሽን ገበያውን የተከተለ አይደለም፤ አዲስ ነገር ሰርቶ ለዛ የሚሆን ገበያን መፍጠር እፈልጋለሁ፡፡›› ይላል።
ኤርሚያስ ሥራዎቹን ለማስተዋወቅ ታዋቂ ሰዎችን አልያም የፋሽን ዲዛይን ሞዴሎችን አይጠቀመም። ሃሳቡ ሰዎች ታዋቂ ሰው ስለለበሰው አይተው እንዲለብሱት አይደለም። ራሳቸውን አውቀው ስታይላቸውን ፈልገው ማንነታቸውን እንዲለብሱት ነው።
የታሪዮ ፋሽን ሃሳብ ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ያህል እድሜ አስቆጥሯል። ዲዛይን የሚያደርግበት መንገድ ታሪዮ የሚለውን ሃሳብ ሊገልጹ ይችላሉ የሚላቸውን አለባበሶች ከገበያ የማይወጡ አልያም በዚህ ጊዜ ያበቃሉ የማይባሉ ዲዛይኖች እና ሰዎች በማንኛውም ወቅት እና ጊዜ ሊለብሷቸው የሚችሏቸውን ልብሶች ነው።
ታሪዮ ራሱን የቻለ የአኗኗር ዘይቤ እንዲሆን እንደሚፈልግ ጠቅሶ፣ ሰዎች በየእለቱ የሚገለገሉባቸውን እንደ የሸክላ፣ የእንጨት ሥራዎች ያሉትን የእደ ጥበብ ውጤቶች በቤት ማስዋብ ላይ ማሳረፍ እንደሚፈልግም ይናገራል።
ዲዛይን ስሜት ላይ ተጽእኖ የማሳደር ውሳኔን የማሳደር ትልቅ አቅም እንዳለው ተናግሮ፣ ትልቁ አላማዬ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያውቁ በራሳቸው እንዲተማመኑ ማድረግ ነው፤ በመሆኑም ተመሳሳይ የሆነ ውበት እና መልዕክት ያላቸውን ሃሳቦች እቃዎችና ቤቶች ላይ ዲዛይን ማድረግ እፈልጋለሁ ብሏል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም