ኢያሱ መሰለ
ቀን ቀን እየሠሩ እራስን መለወጥ የሚችሉበትን አጋጣሚ እንደዋዛ የሚያባክኑ ወጣቶች ባሉበት ሀገር ሌትና ቀን እየሠሩ ኑሯቸውን ለማሸነፍ የሚጥሩ እንስት የእድሜ ባለጸጋን መመልከት ያስገርማል። ታታሪዋ እናት 24 ዓመታትን በምግብ አብሳይነት ሰው ቤት ተቀጥረው ሰርተዋል።
ከአስራ አምስት ዓመት በላይ የራሳቸውን ምግብ ቤት ከፍተው ቀንም ሌሊትም እየሰሩ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጥረዋል። አሁንም በስልሳ ሰባት ዓመታቸው ያለእንቅልፍ እያደሩ ኑሯቸውን ለማሸነፍ ይጥራሉ። በሰው ፍቅርና ክብር ታጅበው እዚህ የደረሱት ታታሪዋ እናት በተለያዩ ወቅቶች መጥፎ አጋጣሚዎችን ማስተናገዳቸውንም ያስታውሳሉ።
ሌሊት ሥራ ቦታ ላይ እንዳሉ ለአፍታ ወንበራቸው ላይ ቁጭ ብለው ሸለብ ሲያደርጉ የራሳቸው አስተናጋጆች በአደራ የተቀመጠውን የሰው ገንዘብ ሰርቀዋቸው ሊሰወሩ ሞክረዋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ አቅሉን በሳተ ተስተናጋጅ የመፈንከት አደጋ ደርሶባቸዋል። ፒያሳ ሰራተኛ ሰፈር የምትገኘው እናት ጓዳ ምግብ ቤት ኑሮን ለማሸነፍ፣ ልጆችን ለማሳደግ ቀንና ሌሊት ደፋ ቀና ከሚሉት እናት ጋር አሁንም የሰፈሩ ድምቀት እንደሆነች ቀጥላለች። የባለታሪኳ የሥራ ተነሳሽነትና ተሞክሮ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው የዚህ ዓምድ እንግዳ ልናደርጋቸው ወደናል።
ወይዘሮ ታደለች አበጋዝ ይባላሉ። እርሳቸው እንደነገሩን እድሜያቸው 67 ዓመት አካባቢ ይጠጋል። የትውልድ አካባቢያቸው ጉራጌ ዞን ጉንችሬ ወረዳ ነው። በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የ14 ዓመት ልጅ እያሉ ትዳር መስርተው ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። ኑሯቸውን በፒያሳ አርሾ አካባቢ አድርገው ከባለቤታቸው ጋር መኖር ይጀምራሉ። ያኔ የአዲስ አበባ ኑሮ እንደ አሁኑ ፈታኝ ባይሆንም ብርቱዋ ሴት ግን የቤት እመቤት ሆኖ ከመቀመጥ ይልቅ ሥራ እየሰሩ ባለቤታቸውን ማገዝና ኑሯቸውን መደጎም ይፈልጋሉ። አንድ ቀን እህታቸው ቤት እንግድነት ሄደው የተፈጠረው አጋጣሚ ለዛሬው ስራቸው መነሻ እንደሆናቸው ይናገራሉ።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ወይዘሮ ታደለች በእህታቸው ምግብ ቤት /ክቧ ግሮሰሪ/ እንግድነት ይሄዳሉ፤ አንድ ሰው እዚሁ ግሮሰሪ ክትፎ አዘው ከተመገቡ በኋላ ምግቡ እንደተመቻቸውና እንዲህ አይነት ሙያ ያለው ሰውን ቢያገኙ በድርጅታቸው የመቅጠር ፍላጎት እንዳላቸው ለወይዘሮ ታደለች እህት ነግረዋቸው ይወጣሉ። ጆሯቸውን ሰጥተው ሲያዳምጡ የነበሩት ወይዘሮ ታደለች የጫጉላ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ የሥራ እድሉን መጠቀም እንደሚፈልጉ ለእህታቸው ይገልጻሉ። እህታቸው ግን ‹‹የለም ገና ሙሽርነትሽን አልጨረሽም፤ ባለቤትሽም አይፈቅድልሽም›› ይሏቸዋል። ከሥራ ወዳዱ የጉራጌ ማህበረሰብ የመጡት እናት ባለቤታቸው ስራን አትስሪ እንደማይሏቸው በመተማመን እቤት ገብተው ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ለባለቤታቸው ይነግሯቸዋል። እርሳቸውም ደስተኛ ይሆናሉ።
ወይዘሮ ታደለች ፒያሳ ወደብ ሆቴል በምግብ አዘጋጅነት ተቀጥረው መስራት ይጀምራሉ። ቀስ እያሉም በወደብ ሆቴል የምግብ ዝግጅት ውስጥ ትልቁን ሚና መጫወት ይጀምራሉ፤ በይበልጥም ክትፎ የመስራት ሙያቸው ለየት ያለ በመሆኑ ሆቴሉ እውቅናው እያደገ የተጠቃሚዎችም ቁጥር እየጨመረ ይመጣል። ወደብ ሆቴል የትልልቅ ሰዎች መናኸሪያ ይሆናል። ታዋቂ ሰዎች ፣ ዲያስፖራዎች፣ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ የሆቴሉ ተጠቃሚ መሆን ይጀምራሉ።
ወይዘሮ ታደለች ከማይረሱት ክስተት አንዱ በአንድ ወቅት አቶ ሰውነት ቢሻው የሰጧቸው የምስክር ወረቀት ነው። አቶ ሰውነት ቢሻው የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ይዘው እየመጡ ወደብ ሆቴል ያስመግቡ እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ ታደለች ድርጅቱ ላደረገላቸው መልካም መስተንግዶ በይበልጥም ወይዘሮ ታደለች በግላቸው ላሳዩት የሙያ ብቃት የምስክር ወረቀት እንደሰጧቸው ይናገራሉ። የወደብ ሆቴል ባለቤት አቶ ክብረት ይግለጡ ሰራተኞችን የሚያከብሩ፣ የሚግባቡና ዘመናዊ አሠራርን የሚከተሉ መሆናቸው ለሆቴሉ እድገትና ለሰራተኞችም ምቹ እንደነበር ወይዘሮ ታደለች ያስታውሳሉ።
በዚህ የተነሳ በወደብ ሆቴል 24 ዓመታት እንደሠሩ ይገልጻሉ። አንድም ቀን ከአሰሪዎቻቸው ጋር ክፉ ነገር ተነጋግረው እንደማያውቁም፤ ቀረቤታቸው የአሰሪና የሰራተኛ መሆኑ ቀርቶ ቤተሰባዊ እንደሆነና አቶ ክብረት የአምስት ልጆቻቸው የክርስትና አባት በመሆን አበልጃሞች እስከ መሆን መድረሳቸውን ወይዘሮዋ ይናገራሉ።
በኋላ ግን የልጆቻቸው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የወር ደመወዝ ከመጠበቅ ይልቅ እራሳቸውን ችለው ቢሰሩ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ በማሰብ ከአሰሪያቸው አቶ ክብረት ጋር ይማከራሉ። አቶ ክብረትም በሀሳባቸው ደስተኛ ይሆናሉ። እንደውም ‹‹እኔ ተመቸኝ ብዬ ሁልጊዜ ሳትለወጪ ኑሪ አልልሽም፤ እደግፍሻለሁ›› ይሏቸዋል።
ወይዘሮ ታደለች እዚያው ፒያሳ አንዲት አነስተኛ ቤት ተከራይተው ‹‹እናት ምግብ ቤትን ይከፍታሉ›› እናት ምግብ ቤት በተጠቃሚው ሰው አጠራር ማዘር ቤት ትባላላች። ፒያሳ ውስጥ ከምትታወቅበት መለያዋ አንዱ የ24 ሰዓት አገልግሎት የምትሰጥ እና ጣት የሚያስቆረጥም ምግብ መገኛ መሆኗ ነው።
የቤቷ ስፋት አምስት ሜትር በአምስት ሜትር ነው። በአንድ በኩል ጣሪያዋ ተሸንቁሮ የምግብ ማብሰያ ቆጥ ተሰርቶላታል። ወደ ቆጡ የሚወስደው መወጣጫ ደረጃ የተወሰነውን ቦታ ይዟል፤ ቀሪውም ቦታ አነስተኛ ባንኮኒና መደርደሪያ ተቀምጦበታል። በዚህ የተነሳ ቤቷ የምታስተናግደው ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነው። ቀላል የማይባሉ ሰዎች ግን ስራ ቦታቸው ድረስ እያስላኩ እንደሚመገቡ ወይዘሮ ታደለች ይናገራሉ።
እናት ጓዳ ለምግብ ማወራረጃ ብቻ የሚሆን አንድ፣ ቢበዛ ደግሞ ሁለት ቢራ ካልሆነ በስተቀር መጠጥ አይሸጥባትም፤ ለዚያውም ጠጥተው ያልመጡ ከሆነ ነው። የሙዚቃ ድምጽ ከፍ ተደርጎ አይከፈትባትም፤ ሲጋራ አይጨስባትም፤ ከምግብ አገልግሎት ውጭ ሌላ አትሰጥም። ለረዢም ጊዜ ምግብ አብሷይዋም አስተናጋጇም ወይዘሮ ታደለች ናቸው። በተለይም ባለቤታቸው ከመቱባቸው ጊዜ ጀምሮ የቤተሰቡ ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ በእርሳቸው ትከሻ ላይ ወድቋል።
ወይዘሮ ታደለች ቀንም ሌሊትም ምግብ እያበሰሉ ይሸጣሉ። ስምንት ልጆችን አስተምረው ለቁም ነገር ያበቁት ታታሪዋ እናት ልጆቻቸው በዚህች ቤት ውስጥ እንዲሰሩ አይፈቅዱላቸውም። ምክንያታቸው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በተለይም ሌሊት ሌሊት ለመመገብ የሚመጡት ሰዎች ሊጠጡ ስለሚችሉ እራሳቸው እንደጸባያቸው ማስተናገድን ስለሚመርጡ ነው።
ደንበኞች ለእርሳቸውና ለልጆቻቸው የሚኖራቸው ክብር የተለያየ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮዋ አብዛኛዎቹ የሌሊት ደንበኞቻቸው ወጣቶች እንደመሆናቸው ወጣት ከወጣት ጋር በትእግስት ላይነጋገር ይችላል በሚል ልጆቻቸውን ለአደጋ ላለማጋለጥ ሲሉ እራሳቸው ይሠራሉ። ለእንቅልፍ እምብዛም ቦታ የማይሰጡት እናት ቀን ቀን እቤታቸው እየሄዱ ትንሽ ሰዓት ያሸልባሉ፣ አንዳንዴም ሌሊት ሌሊት እዚያው የሚሰሩበት ቦታ ትንሽ ፋታ ሲያገኙ ወንበር ላይ ተቀምጠው ያሸልባሉ።
አብዛኛው የሌሊት ደንበኛ እንደ እናቱ ቤት ተስተናግዶ የሚሄድባት ቤቱ ስለሆነች ወይዘሮ ታደለችን ማዘር ብሎ አክብሮ ይስተናገዳል። በአካባቢው በስራም ይሁን በመዝናናት ላይ ያለ ማንኛውም ሰው እናት ጓዳ ገብቶ ይመገባል። ከሩቅ ቦታ ድረስ እየመጡ የሚበሉም መኖራቸውን ይናገራሉ። ቤቷ እንደትንሽነቷ አይደለችም የሚሉት ታታሪዋ እናት ስሟ እስከ አሜሪካን ድረስ የናኘ መሆኑን ይገልጻሉ። አሜሪካን ሀገር ኖረው የመጡ ዲያስፖራዎችና የውጭ ሃገር ዜጎች የምሽት መዝናኛቸው ፒያሳ አካባቢ ከሆነ የእናት ጓዳን ሳይረግጡ አያድሩም።
ወይዘሮ ታደለች ኑሯቸውን ለማሸነፍና ልጆቻቸውን ለቁም ነገር ለማድረስ ሲሉ አስቸጋሪ ህይወትን መርተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የከፈሏቸውን ዋጋዎችም አይረሷቸውም። ታትረው ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ መልካም ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ መጥፎ ሁኔታዎችም ገጥሟቸዋል።
በአንድ ወቅት የገጠማቸውን መጥፎ ሁኔታ እንዲህ ይገልጻሉ። ልጃቸው ማታ ስራ ቦታቸው መጥቶ 49 ሺህ ብር እንዲያስቀምጡለት አደራ ይሰጣቸውና ወደ ቤቱ ይሄዳል። እርሳቸውም ብሩን በክብር ያስቀምጣሉ። ወይዘሮ ታደለች ሲሰሩና ሲያስተናግዱ አምሽተው ከሌሊቱ አሥር ሰዓት አካባቢ እንቅልፍ ይጫጫናቸውና በተቀመጡበት ወንበር ላይ ሸለብ ያደርጋቸዋል።
በዚህ መኃል አስተናጋጆቹ የታዘዙትን ምግብ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው ባንኮኒ በመስበር የተቀመጠውን 49 ሺ ብር ይዘው ይጠፋሉ። ተመጋቢዎች መጥተው ሲጣሩ ወይዘሮ ታደለች ካሸለቡበት ይነቃሉ። አስተናጋጆቹን ሲጠሯቸው በቤት ውስጥ የሉም። ምን ችግር ገጠማቸው ብለው በመደናገጥ ወደ ውጭ ይወጣሉ፤ ልጆቹ ተያይዘው ቁልቁል እንደወረዱ ይነግሯቸዋል። ወዲያው ወደ ቤት ተመልሰው ያስቀመጡትን የአደራ ብር ሲመከለቱ ባንኮኒው ተሰብሮ ብሩ ተወስዷል። ለልጆቻቸውና ለሰፈሩ ልጆች ስልክ አስደውለው እግር በእግር እንዲከታተሏቸው ያስደርጋሉ።
በአጋጣሚ ወደ ላም በረት ሲሄዱ የነበሩ ፈላጊዎች ልጆቹን ያገኟቸውና በፖሊስ አስይዘዋቸው ብራቸውን ምንም ሳያጠፉት ይያዛሉ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ልጆቻቸው የሌሊት ሥራ እንዳይሰሩ ቢቆጧቸውም ያለ ሥራ መኖር የማይችሉት ብርቱዋ ሴት ግን ዛሬም ውሎና አዳራቸውን በትንሷ ቤት አድርገዋል።
ታታሪዋ እናት ሌላም መጥፎ ገጠመኝ እንደተከሰተባቸው ያስታውሳሉ። አንድ ቀን ማታ ከሚኖሩበት ቤት ወደ ሥራ ቦታቸው ይመጣሉ። ልክ ምግብ ቤቷ በር ላይ ሲደርሱ መንገድ ላይ የተቀመጠ አንድ ክብደት ማንሻ ብረት ያዩና ሰው ያደናቅፋል በማለት ጥግ ለማስያዝ አስበው ዝቅ ይላሉ። ከበረንዳው ላይ አንድ ሰው ጀርባውን ወደ ውጭ ሰጥቶ እራት እየበላ ነው። ሰውየው ከተወሰነ ደቂቃ በፊት አንዲት እብድ በተቀመጠበት ቦታ መጥታ አስደንግጣው ስለሄደች በስጋት ውስጥ ሆኖ እየበላ ነው። በዚህ መሃል ድንገት ከጀርባው መጥተው ዝቅ ብለው እቃ የሚያነሱትን ባልቴት ዞር ብሎ ሲመለከታቸው፤ እብዷ ልትመታው ምናምን ያነሳችበት መስሎት አጠገቡ የነበረውን ጠርሙስ ማዘር ላይ ይወረውረውና ቅንድባቸው አጠገብ ይፈነክታቸዋል።
ሁኔታዎች ወደ ሌላ ነገር ተለወጡ፤ የአካባቢው ሰዎችና ደንበኞች ልጁን አንጠልጥለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት፤ ልጁ በድንጋጤ የፈጸመው ድርጊት ቢሆንም ሞቅታ እንዳለበት የተመለከቱ የጸጥታ አስከባሪዎች ሊለቁት ስላልፈለጉ አስር ቤት አሳደሩት። ምንም እንኳን በጥፋቱ መሰረት መቀጣቱ አግባብ ቢሆንም ወይዘሮ ታደለች ግን ከሚወርድበት ዱላ ሊታደጉት ተማጽነዋል፤ እነዚህ ሁለት ገጠመኞች በስራ ዘመናቸው የገጠሟቸው መጥፎ ክስተቶች መሆናቸውን ሁልጊዜ ያስታውሳሉ። ከዚህ በተረፈ ግን አዛውንቷ ሰዎች የሚሰጧቸውን ክብርና ፍቅር ተናግረው እንደማይጨርሱት ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ታደለች ዛሬም ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት አላቸው፤ እድሜቸው ገፍቷል፤ ልጆቻቸውም እራሳቸውን ችለውላቸዋል። እንደ አብራካቸው ክፋይ የሚመለከቷቸው ስድስት የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች አሏቸው። አንዱን እቤታቸው አስገብተው እርሳቸውን እያገዘ እንዲኖር የሥራ እድል ፈጥረውለታል። ሰፊ የሥራ ቦታ ቢያገኙ ሌሎች አምስትና ስድስት የሚሆኑ የጎዳና ልጆችን የመርዳት ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ። ለዚህም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የቦታ ትብብር እንዲያደርጉላቸው ይፈልጋሉ። ወይዘሮ ታደለች ከሁሉ በላይ ሰርቶ መኖር የሚቻለው የሀገር ሰላም ሲጠበቅ እንደሆነ ያምናሉ። እንደ እርሳቸው አባባል ሰዎች ሰርቶ መኖር፤ ወጥቶ መግባት የሚችሉት ሰላም ሲኖር ነው። እርስ በእርስ መተዛዘንና መተጋገዝ ከችግር ያወጣል የሚሉት አዛውንቷ፣ ሰው ለፍቅርና ለሰላም ትልቅ ዋጋ መስጠት እንዳለበት ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013