ታምራት ተስፋዬ
ሰመሃል ግዑሽ ትባላለች። በትምህርት ሙያ እና የስኬት መዳረሻ የስነ ህዋ ምሁር/አስትሮፊዚስት መሆን ፍላጎት ነበራት።ምክንያቱ ደግሞ በእነዚህ መስኮች የሴቶች ተሳትፎ አለ ከሚባል የለም ለማለት የቀለለ መሆኑን በመታዘቧ ነው።
ይሁንና አዲስ እና ውብ ነገር የመፍጠር ፍላጎት የነበራት ሰመሃል፣አርክቴክቸር የመሆን ምራጫዋ አሸናፊ ሆነ።የመጀመሪያ ዲግሪዋን እየተማረች የተወሰኑ የቆዳ ምርቶችን በመምረጥ ዲዛይን ማድረግ ጀመረች።የትምህርት ዘርፍ ያገኘችውን እውቀትና ክህሎት በቆዳ ኢንዱስትሪው ውስጥ አዳዲስ የፋሽን ዲዛይኖችን በመፍጠር በኩል ትልቅ እገዛ አደረገላት።
በተመረቀችበት ሙያ ሥራ ብትጀምርም ምንድነው የምፈልገው? የቱ ነው የሚያስደስተኝ? የሚል ጥያቄዋ ግን መልስ አላገኘም ነበር።በመጨረሻ ግን በቆዳ ኢንዱስትሪው ውስጥ በመሳተፍ አዳዲስ የፋሽን ዲዛይኖችን መፍጠር ቀዳሚ ፍላጎቷ እና የጥያቄዋ መልስ መሆኑን አረጋገጠች።
አማራጮቿ በርካታ ቢሆኑ እንኳን አብልጣ የምትወደው ላይ ትኩረት በማድረግ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ገባት።ሙያውም ሙሉ ትኩረቷን ወሰደው።ፍላጎቷ ወደ ቢዝነስ ተለውጦ በጠባብ ክፍል የተጀመረው በሴቶች የእጅ ጥበብ የሚቀመሩት የቆዳ ምርቶቿ በተለያዩ አውደ ራእዮች ላይ ተመራጭ ወደ መሆን ተሸጋገሩ።
ምጣዱ ከሰማ እንጀራውን መጋገር ቀላል ነው እንደሚባለው፣ሰመሃል በአሁኑ ወቅት ጥራት ያላቸውን የእጅ ሥራ የሆኑ የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርት ‹‹ቀበና ሌዘር›› በመባል የሚጠራ ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ለመሆን በቅታለች።በኢትዮጵያ ካሉ ውጤታማ የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅቶች መካከል አንዷ ለመሆን ችላለች።
አሁን ላይ የተለያዩ ምርቶች ለገበያ ታቀርባለች።የሥራ፣ የስፖርት የኪስ እና የሥራ ቦርሳዎችን እንዲሁም የኮሮና ወረርሽን ከመተላለፍ የሚገቱ የፊት ጭንብሎችን ታመርታለች። እኤአ ከ 2017 ወዲህም ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ ዘልቃለች ።፡በአሁኑ ወቅትም ምርቶቿን በደቡብ አፍሪካ እና በሩዋንዳ እንዲሁም በዩናይትድ እስቴትስ፣በአውሮፓ ገበያ ይሸጣሉ።፡
ሰመሃል ሰራተኞቿ ልዩ ትርጉም አላቸው።ከሁሉም በላይ ለሰራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እና መጠነ ሰፊ መዋእለ ነዋይ ፈሰስ ታደርጋለች።በዚህም እሳቤ እና ተግባርም የሰራተኞች ቅሬታ አሊያም የሥራ መልቀቅ አጋጥሟት አያውቅም።ከሰራተኞቿ መካከልም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
ሴቶችን ለማብቃት የምትተጋው ጉዞም ረጅም ነው።በትርፍ ጊዜዋ በተለይም በጎዳና ላይ ኑሮአቸውን ላደረጉ ወጣት ሴቶች ስልጠና ትሰጣለች።ለበርካቶችም በድርጅቷ የሥራ እድል ብሎም የራሳቸውን ንግድ እንዲጀምሩ አመቻችታለች።ወጣቷ ‹‹ከፌስ ቱ ፌስ አፍሪካ›› ጋር በነበራት ቆይታም፣ ስልጠና የሰጠቻቸው ሆነ ሰራተኞቿ አቅም ፈጥረው የራሳቸውን ቢዝነስ ሲጀምሩ እንደመመልከት እጅግ የሚያስደስት ነገር እንደሌለ ነው የገለፀችው።
ሰመሃል 92 በመቶ የሚሆነውን ግብአት የምታገኘው ከአገር ውስጥ ነው።ቀሪውን ደግሞ ከውጭ አገራት ታስገባለች።በስራዋ ላይ የምትጋፈጠው ትልቁ ፈተናዋም ይህ ነው።ጥራት ያለው ቆዳ ምርት እና ግብአት ማግኘት ከባድ ፈተና ነው ትላለች። ከዚህ ባሻገር ስራዋን ይበልጥ ለማጎልበት የካፒታል አቅምም ጨምድዶ ይዟታል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም ቢሆን ቀላል የማይባል ጫናን ፈጥሮባታል።ትእዛዞች ተሰርዘውባታል። ይሁን እና ሠራተኞቿን ላለመበተን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን ጨምሮ ሌሎች አማራጭ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ፈተናውን ለመሻገር በመትጋት ላይ ትገኛለች።
ለዚህ በአላማ ፅናት ለዚህ ስኬታ ለመብቃቷም የተለያዩ ምክንያቶችን ትዘረዝራለች።ከሁሉ በላይ ግን ቤተሰቧ በተለይም አባቷን በቅድሚያ ታነሳለች።‹‹ካለ ምንም ገደብ ያሰብሽውን ማሳካት ትችያለሽ ››እያሉ የመክሯት እና ሞራል የሆኗትንም ማበረታቻ ታስታውሳለች።
በኢትዮጵያ አብዛኛው ቤት ውስጥ የወንድ የበላይነት እንዳለ እና አብዛኞቹ ቤተሰቦችም ከሴት ይልቅ ለወንዶች ብዙ እድሎችን እንደሚሰጡ የምታስረዳው ሰመሃል፣‹‹በእኛ ቤት ግን ይህ አይሰራም፣በተለይ በገጠራም አካባቢ ብወለድ እና ቤተሰቦቼ የማይደግፉኝ ቢሆን በ12 ዓመቴ ትምህርቴን አቋርጬ ለትዳር እታጭ ነበር›› ትላለች።ይህ አለመሆኑም በሥራዋ ውጤታማ እንድትሆን እና የስኬቷን መንገድ እንድትራመድ እንዳገዛት ትጠቁማለች።
ሰመሃል፣ከቀናት በፊትም ተስፋ ያላቸው አህጉራዊ ሥራ ፈጣሪዎች በሚል ‹‹ጄት ኤጅ ኔሽን ቢውልደር›› በተባለ በመላው አፍሪካ የሚገኙ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን የሚያበረታታና የድጋፍ ሥራ የሚሰራ ድርጅት ሽልማት ካበረከተላቸው ወጣቶች መካከል አንዷ ሆናለች።ሽልማቱን በአዲስ አበባ በተካሄደ ስነ ስርዓት ላይ ተበርክቶላታል።
ከዚህ ሽልማት በተጨማሪ ሰመሃል በርካታ ሽልማቶችን ያገኘች ሲሆን ሌሎች ማህበራዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣች ነው።ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች በተለይም ለሴቶችም ትልቅ አርዓያ መሆን የምትችል ስኬታማ ወጣት መሆናን በርካቶች እየመሰከሩላት ይገኛል።
የዲዛይነር፣ አርክቴክት፣ እና ሥራ ፈጣሪዋ እንስት ትልቁ ግብ የቆዳ ኢንዱስትሪው ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠርበትና ለአገሪቱም ሰፊ የገቢ ማስገኛ ዘርፍ ይሆን ዘንድ የበኩሏን አስተዋጽኦ የማድረግ ህልሟን ማሳካት ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013