ክፍል ሦስት
ጤና ይስጥልን ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች? የኢፌዴሪ 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ባለፈው ረቡዕ ማካሄዱ ይታወሳል:: በወቅቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እኛም የዚህኑ ማብራሪያ ሁለት ክፍሎች በተከታታይ ማቅረባችን ይታወሳል:: በዛሬው ዕትማችን በአማራ ልዩ ኃይል፣ በሐሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ ፣ በዲያስፖራ እና ሽምቅ ውጊያን በሚመለከት የሰጡትን ማብራሪያ የያዘውን የመጨረሻውን ክፍል ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ
የአማራ ልዩ ኃይልን በተመለከተ
ከአማራ ልዩ ሃይም ጋር ተያይዞ ሰፋፊ ጉዳዮች ይነሳሉ:: የአማራ ልዩ ሃይል አሁን ኦፐሬሽን ከጀመርን በኋላ ከትግራይ ጋር ልክ የአማራ ልዩ ሃይል መሬቴን ላስመልስ ብሎ ተደራጅቶ ውጊያ እንደገጠመ ለማስመሰል የሚፈልጉ በጣም በርካታ ሃይሎች አሉ:: ስህተት ነው::
ይሄ ሪፎርም የሚባል ነገር ሳይፈጠር የወልቃት ኮሚቴ እንደነበር እናንተ አታውቁም ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አያውቅም ፣ ወልቃይት ኮሚቴ የሚባል የዛሬ አምስት አስርም ዓመት ሲጨቃጨቅ እንደነበረ የማያውቅ ሰው አለ እዚህ ውስጥ ? ይሄ የወልቃይት ኮሚቴ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ሊያቀርብ ሲመጣ ሱልልታ ላይ መታሰሩን አታውቁም? ሰው አያውቅም ይሄን ? ለምንድን ነው ታዲያ የድንበር ኮሚሽን ብለን ያቋቋምነው ? ምን ፍለጋ ነው ? ኮሚሽን እኮ የተቋቋመው ጥያቄ ስላለ ነው ፣ ችግር ስላለ ነው። ኮሚሽኑን ጁንታው አልቀበልም ያለው ሥራውን ስለሚያውቅ ነው::
አዲስ አሁን እዚህ ግጭት ውስጥ ስለገባን የአማራ ሚሊሻ በተለየ ያደረገው አድረጎ የሚቀርበው ነገር ትክክል አይደለም:: በኢህአዴግ መድረክ ውስጥ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ባለፉት አስር ዓመታት የወልቃይት እና ራያ ጉዳይ ሳይነሳ ቀርቶ አያውቅም:: ፓርላማ ተነስቷል ፤ በፓርቲ ይነሳል ፤ በህዝብ ይነሳል፤ በሚዲያ ይነሳል::
ልክ አሁን ከኦፕሬሽን ጋር እንደተፈጠረ አድርጎ አንዳንዶችማ የአማራ ልዩ ሃይል ይውጣ ይላሉ ፤ ይህ በጣም የሚያስቅ ነው:: የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ ወታደር በየትኛው ስቴት እንደሚቀመጥ የመናገር መብት የለውም:: የኮሎራዶው አሪዞና ቢሄድ የአሪዞናው ካሊፎርኒያ ቢሄድ ይህ አሜሪካ መንግሥት ስልጣን ነው:: ማን የት ማስፈር እንዳለብን ለእኛ መተው ያስፈልጋል::
ሶሮቃ እና ቅረቅር ላይ ውጊያ የጀመረው የአማራ ልዩ ሃይልነው? አናውቅም የአማራ ልዩ ሃይል ባህርዳር እና ጎንደር ተቀምጦ ውጊያ እንደተከፈተበት? ባህርዳር እና ጎንደር ላይ ሮኬት የተተኮሰበት አማራ ልዩ ሃይል መቀሌ ላይ ሮኬት ስለተተኮሰ ነው? መልስ የሰጠ ነበር ? ይህ ስህተት ነው :: የአማራ ልዩ ሃይል በዚህ ኦፕሬሽን ውስጥ ተጋግዞ የተደረገው ጥረትም የፌዴራል መንግሥት እስከወሰነበት ጊዜ ድረስ አልገባም::
እኛ ነኝ የመወሰን ስልጣን ስላለን ነው:: በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስልጣን ስላለን የአማራ ልዩ ሃይል እዚህ ላይ ሸፍንልን፣ የአፋር ልዩ ሃይል እዚህ ላይ ሸፍንልን ፤ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ደግሞ እያወጣን ስለሆነ ወታደሩን ይሄን ቀጣና ሸፍን ብለናል:: በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሁሉም በአንድ ኮማንድ ውስጥ ስለሚሆኑ ማለት ነው:: እንችላለን::
ምን ማለት ነው የአማራ ልዩ ሃይል ማለት ? ነገ ጠዋት እኮ የፌዴራል መንግሥት ከፈለገ መላውን የአማራ ልዩ ሃይል የመከላከያ ሃይል ነው ሊል ይችላል:: ይሄ ልክ ከሌላ አገር አንደመጣ አስመስሎ የሚቀርበው ስዕል ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ነገር ግን የአማራ ልዩ ሃይል ተልኮ ተሰጥቶት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገብቶ የበደለው በደል ካለ ለኢትዮጵያ ወታደር ፣ ለኤርትራ ጦር እንዳነሳሁት ይጠየቃል:: ላጠፋው ጥፋት ይጠየቃል:: ተልኮ ተሰጥቶት እየሞተ ያለን ሃይል ፣ ዋጋ እየከፈለ ያለን ሃይል እንደዘራፊ እና ጨቋኝ አድረጎ መሳል ግን ስህተት ነው::
የአማራ ልዩ ሃይል እየሞተ ያለው በመንግሥት የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ነው ፤ መስዋዕት እየከፈለ ያለው:: የአማራ ልዩ ሃይል እስከመጨረሻው መንግሥት ከፈለገ እና ከአቅሙ በላይ ከሆነ ጅግጅጋ ጫፍ ሊያሰማራው ይችላል:: ኢትጵያዊ ነው ያስታጠቅነው የሰለጠነው ኢትጵያን እንዲከላከል ነው:: ሌላ ምንም ምክንያት የለውም::
ይሄን በተዛባ መንገድ የሚያነሱ ሃይሎች ቆጠብ ብለው ቢያዩት:: ነገር ግን የአማራ ልዩ ሃይል ሊሆን ይችላል የኤርትራ ወታደር ሊሆን ይችላል፣የኢትዮጵያ ወታደር ከጁንታው በተለየ መንገድ ህዝባችን ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ደግሞ ካለ በህግ ይጠየቃል። የሚቀላቀል ነገር ስላለ እንዳይቀላቀል ማድረግ ያስፈልጋል። መሬት በሚመለከት የድንበር ኮሚሽን አቋቁመናል:: የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አለ በህግ ይታያል:: እሱን ህዝብ አሳትፈን በህግ የምንመልሰው ነው::
በህግ የሚመለሰውን ነገር ለማድበስበስ የሚደረጉ ሙከራዎች እና ይግባ ይውጣ ፤ ልክ እንደ ጠላት ጦር የሚደረገው ግን ትክክል አይደለም:: አካባቢውን የፌዴራል መንግሥት በቅርበት የአማራ ልዩ ሃይልን ጨምሮ አሰማርቶ እያሠራ ነው ያለው። ጥፋት የሚጠፋ ካላ ሃላፊነት የሚወሰድ ይሆናል ማለት ነው።
የሚቀላቀሉ ጉዳዮች ከመሬት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ቦታ ቢበጅላቸው:: መሬትን በሚመለከት ቅድምም ተነስቷል እንኳን በአማራ እና በትግራ፣ እንኳን በሱማሌ እና በአፋር ፤ በሱማሌ እና በኦሮሚያ፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ይቅርና ከጎረቤት ሃገራት ጋር ድንበር እኮ አካለን አልጨረስንም::
አላለቀም:: ምክንቱም ፌዴራል ስርዓት የሚባል የተፈጠረው አሁን ነው::
ከጎንደር ክፍል ሃገር ቆንጥሮ ፣ ከወሎ ቆንጥሮ፤ ከጎጃም ቆንጥሮ አማራ ክልል ፤ ከወለጋ ቆንጥሮ ከምናም ቆንጥሮ ኦሮሚያ ክልል አሁን ነው:: አልነበረም ይሄ:: እና ጎንደር እያነሳ ያለው ከተከዜ ወደዚህ ያለው ቦታ ለዘመናት የጎንደር ክፍለ ሃገር አካል ነው:: ከወንድም ህዝብ ጋር ነጥላችሁናል:: ወንድሞቼ እዚያ ቀርተዋል ነው እያለ ያለው።
እውነት ነው ውሸት በህግ ይታያል። የአማራ ልዩ ሃይልን ግን ሌላ ወራሪ አድረጎ ለማቅረብ መሞከር ትክልል አይደለም። እና የአማራ ልዩ ሃይል ለጊዜው ኦሮሚያ ችግር የለብንም ፣ ጋምቤላ ችግር የለብንም እዚያ አሰማርተነዋል:: ችግር ካለብን ግን ነገ ሶማሌም እናሰማራዋለን:: የሃገር ሉአላዊት ላይ ጥፋት ከደረሰ የሚሰማራ ሃይል መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል::
ሀሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ
“ሁለተኛ ግፌ ጫንቃዬን ተገርፌ ልብሴን መገፈፌ” ይላል የአገሬ ሰው ፤ ሁለተኛው ግፍ አሱ ነው። ይህ ሁሉ በደል ደርሶብን የአገር ኢኮኖሚ የሚያናጋ አገር የሚያዋርድ ሥራ ተሠርቶብን ተነጥቀን ተዘርፈን ተገድለን ተክደን ስናበቃ መልሰው እኛኑ ወንጀለኛ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል:: ይህ አሳዛኝ ነገር ነው::
የኝ እምነት ጦርነቱን እውነት አሸንፎታል ፕሮፓጋንዳውን እውነት ያሸንፏል ችግር የለውም የጊዜ ጉዳይ ነው አካሄዱ ግን ቲ ፒ እል አፍ በየተቋማት አምነስቴ በሉት ዩ ኤን በሉት ምናምን በሉት ኤጀንሲ ላይ ያለው ኢትዮጵያዊ አብዛኛው የቲፒኤል ኤፍ ካድሬ ቤተሰብ አካል ነው:: ላለፉት 30 ዓመታት ሰግስጓል:: የአሜሪካን መንግሥትን በመረጃ እያወናበደ ያለው የዚህ ኤጀንት ካድሬ ቤተሰብ ነው:: ጓደኞች አሏቸው 20 እና 30 ዓመት ጓደኛ የሆኑባቸው ሰዎች አሉ። ገንዘብም አላቸው ጓደኞች ናቸው ከስድስት ወር በፊት ሎቢ ቀጥረዋል፤ ሎቢስቶች የሚባሉ አሉ ያው ኮራብሽን ነው ግን ቀጥረዋል:: ለምን የተዘረፈ ሀብት አላቸው ለምን ኢትዮጵያ እንደዛ ሀብት የላትም ተዘርፋ ገና ለማስመለስ ጥረት የምታደርግ ናት:: እነሱ ገና ብዙ ብር ስላላቸው በየሀገሩ ሎቢስት ቀጥረዋል:: ሚዲያ ገዝተዋል የፓርላማ አባላት ቀጥረዋል ይጮሁላቸዋል::
መተከል ብትሄዱ ግን ጉሙዝ ሎቢስት መግዛት አይችልም ብቻ ሳይሆን የት እንደሚገዛም ስለማያውቅ ማንም አይጮህለትም:: የአማራ አርሶ አደር ፣ የአገው አርሶ አደር ከመተከል ተፈናቅሎ በየመንደር ውስጥ ያለው ማንም አይጮህለትም:: ድምጽ ለሌላቸው ሳይሆን ገንዘብ ላላቸው ስለሚጮህ ማለት ነው:: እኔ ቲ ፒ ኤል ኤፍን የማስበው ለኢትዮጵያ የሙቀጫ ልጅ ነው የሆነባት:: የሙቀጫ ልጅ እናቱን ካልወቀጠ ካልረገጠ ሥራውን አይሠራም:: ልክ እንደ ሙቀጫ ልጅ ኢትዮጵያን በማዋረድ ኢትዮጵያን በመዝረፍ ኢትዮጵያን በመከፋፈል ኢትዮጵያን በማደህየት ሥራዬን እሠራለሁ ብሎ የሚያስብ ሃይል መሆኑ በጣም ያሳዝናል::
አሁን እየሆነ ያለው እሱ ነው እዛ ሲያልቅ ሌላም ቦታ ባለተራ ፋይናንሱ ገንዘቡን የሚበተነው በዚያው መንገድ ነው:: ሁሉም ግን ይደርቃል:: በቀጣይነት የሚቀጥል አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብ ጽናት ካለው እነዚህን ጉዳዮች አድርቀን ሰላማችንን አረጋግጠን ብልጽግናችንን የምናመጣባቸው ጊዜያቶች ሩቅ አይደሉም:: ይደርቃል ዋናው አደገኛው ችግር የጁንታው ሀሳብና ህልም ሳይሆን እዚህ ያለው ሃይል ነው::
ጁንታው ለምሳሌ የከሚሴን ብቻ ብንወስድ ሁለት ሃይሎች አሉት እዛ የሚቀመጡ ቅልብተኞች አንደኛው ሃይል ኦሮሞ አለቀ ኦሮሞ አለቀ ኦሮሞ ተነስ ይላል:: አንደኛው ሃይል አማራ አለቀ አማራ አለቀ አማራ ተነስ ይላል:: ደሞ አይነሳም እኮ እሱ እዛው ነው ያለው:: ሁለቱም ግባቸው ህዝቡን በማባለት የጁንታውን ህልም ማሳካት ነው::
የኢትዮጵያ ህዝብ ንቃ ተነስ ከተባለ ካለህ ይህ የኢትዮጵያ ባህል አይደለም ብለህ እምቢ በል:: ታረቅ ተስማማ ሰከን ረጋ በል አንወያይ ወንድምህ ነው ካለህ እሱ ዘመድ ነው:: ተነስ ተነስ የሚለው ሃይል ሊያጫርሰን መሆኑን ጥንቃቄ ማድረግና አንድ መሆኑን ሶርሱን ማወቅ አለብን:: ሶርሱ አንድ ነው ሁለቱንም የሚቀልበው አንድ ሃይል ነው ይሄንን ጥንቃቄ ማድረግ ከኛ ይጠበቃል::
ዲያስፖራን በሚመለከት
ዲያስፖራው ብዙ ጥረት እያደረጉ ነው፤ ኢትዮጵያን የሚወዱ ዲያስፖራዊች ሰፊ ሥራ እየሠሩ ነው ነገር ግን ዲያስፖራዎች ሳይሰቃዩ በጁንታው መንገድ አንድ እንድ ዶላር ወይም ሁለት ሁለት ዶላር መቶ ሺ ሰው ቢያዋጣ ሁለት መቶ ሺ ደላር ነው፤ በዚህ ሎቢስት መቅጠር ይችላሉ::
ምናልባት ሁለት ዶላር ተጭበርብሬ ተሰርቄ እንዳይሆን እንኳን እንዳይል ቢሰረቅም ለሀገር ስለሆነ ብዙ አይጎዳውም:: ብዙ ብር አይደለም ሁለት ብር መቶ ሺ ሰው ቢያዋጣ ሁለት መቶ ሺ ብር ሎቢስት ቀጥሮ አሁን ያለውን ጩኸት ሊያረጋጋ ይችላል::
እኔ በተደጋጋሚ ግብዣ ቀርቦልኛል ሎቢስት ቅጠሩ ክፈሉ የሚል እኔ ለነሱ ለሀብታሞች ከምከፈል እዚሁ ትግራይ የተራበውን አበላለሁ አልከፍለም ገንዘብ የለኝም ብዬ ነው እምቢ ያልኩት:: እንደሚጮሁ እንደሚሳደቡ አውቃለሁ ግን ለዛ ገንዘብ የለኝም ለጊዜው::
ዲያስፖራዎች በዛ መንገድ በአገራቸው ላይ የሚፈጠረውን በውሸት ላይ የተመሰረተ ውንጀላ ለመከላከል ቢሠሩ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ:: እየሠሩ ነው ያለው ቢጠናከር የውጭ አገር ሰዎችን በሚመለከት ንጽጽራቸው ሶሪያ ሊቢያ የመን ይላሉ እና ለውጭ ሀገር ሰዎች የምላቸው አሁን እዚህ የምደግመው የፓፓያ ዛፍና የፓልም ዛፍ አይቀላቀልባችሁ ነው፤ ይመሳሰላሉ እንጂ አንድ አይደለም:: ኢትዮጵያና ሶሪያን የሚያገናኛቸው ነገር የለም ኢትዮጵያ የመንን የሚያገናኝ ነገር የለም ኢትዮጵያ የራሷ መልክ የራሷ ቅርጽ የራሷ ማንነት ያላት ናት፤ የሚያጋጥማትንም ፈተና የምትወጣው መንገድ በዛው ላይ የተመሰረተ ነው::
እኛ የሞራል ልዕልና ያለን ሰዎች ነን፤ የእውነት የሞራል የፍትህ ለዕልና ስላለን ነው ጦርነቱንም ያሸነፍነው፤ ወደፊትም የምናሸንፈው፡፡
ኢትዮጵያ ማለት እኮ እንኳን ደመወዝ ተከፍሎ እንትን ክፍለ ጦር ተብሎ በክተት አዋጅ አርሶ አደር ሰብስባ ወራሪ ማሸነፍ የቻለች አገር ናት:: ፔሮል የሌለው ስም የሌለው ድረስ ተብሎ ማለት ነው አሁን ያለው ሰራዊት ታንክ አለው መድፍ አለው:: አይኑረው በክተት አዋጅ ኢትዮጵያ ክብሯን ጠብቃለች ትጠብቃለች ኢትዮጵያ በደነብ ሳይገነዘቡ ከሌላው አገር ሥዕል እየወሰዱ ማየት ስህተት ነው::
ሦስት አይነት የውጭ ሰዎች አጋጥመውኛል አንዳንዶች ከጠበኩት በላይ ወዳጅ አገራት የኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ክብር የኢትዮጵያ ህዝብ የወደፊት ተስፋ የገባቸውና ከወዳጅ አገራት ጋር በወዳጅነትና በአውነት መቆም የፈለጉ የሞከሩ የሠሩ የደገፉ አገራት አሉ፤ በደንብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚነገርላቸው ወደፊትም በሚያጋጥማቸው ፈተና እኛም ጎናቸው የምንቆምላቸው ሀገራት አይተንበታል ይህ ጨለማ ወዳጅ እና ጠላቶቻችንን እንድንለይ አድርጎናል::
በልለ መንገድ ደግሞ በሌላ በኩል ደግሞ እጃቸውን አንደዚህ አድርገን እንጠምዝዝ የሚሉ ሃይሎችም አይተናል፤ እኔ ከየትኛውም አገር ጋር ግጭት አልፈልግም ከየትኛውም አገር ጋር አተካራ አልፈልግም በሰላም የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጥበትን መስራት ብቻነው የምፈልገው እንድትረዱት የምፈልገው የሌሎች ሃይሎች በኢትዮጵያ ጥቅምና ክብር ላይ ከመጣችሁ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይደረግም:: እሱ በመጠምዘዝ የሚሆን ነገር የለም ተላላኪ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጠርም:: ጥቅም አለን ጥቅም አላችሁ ያንን እያስታረቅን ተከባብረን አብረን እንኖራለን:: ሁለተኛው ሀይል እሱ ነው::
ሦስተኛው ሃይል ግን አሁን ነው ጊዜው፤ ኢትዮጵያን እናጥፋት ብሎ ገንዘቡን ጊዜውን በደንብ አድርጎ አደራጅቶ አልጥኖ የሚሠራ አለ:: ጠላት አለ፤ መጠምዘዝ የሚፈልግ አለ፤ ወዳጅ አለ:: ለሁሉም መንገር የምፈልገው ኢትዮጵያ ማለት በሦስት ሳምንት ውስጥ የተደራጀና ከእኔ ወዲያ የጦርነት ጨዋታ አያውቅም፣ በአፍሪካ እኔ ነኝ የሚል ሃይል በሦስት ሳምንት መደምሰስ የቻለ፤ ይህንን የትኛው አገር ማድረግ አንደሚችል ባለፈውም አይተናል ወደፊትም እናየዋለን፤ ችግር የለውም::
ጀግኖች አገራቸውን የሚወዱ በአገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ ቆራጥ ልጆች ያሏት አገር ፤ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ህዝብ በሁለት ሦስት ወር መቀለብ የቻለ፣ ምን ማለት ነው ይኼ፤ በአፍሪካ አንዳንድ አገራት መቶ በመቶ መቀለብ የቻለ መንግሥት ማለት ነው:: ቁጥሩ እንዲህ የተለጠጠው ኢትዮጵያ ስለሆነ ነው አንጂ 4 ሚሊየን ከባድ ህዝብ ነው፤ ብዙ ቦታ አገር ስለሆነ:: ፈተናን፣ ያልተገባ ጫናን፣ ጥቃትን፣ መድሎን፣ ክህደትን በዘመናት መካከል የተሻገረች አገር መሆኗንም ይዘነጋሉ:: አዲስ አይደለም ለኛ ይኼ:: አበቃላት ወደቀች ተበተነች ስትባል የማትወድቅ ሃገር መሆኗን በተደጋጋሚ አሳይታለች::
አሁን የአብዴ ኢሌ ጦር፤ የኦነግ ሸኔ ጦር፣ የህወሓት ጦር ኢትዮጵያን እንደዚህ ይዞ የመበተንና የማፍረስ ህልሙን ሳንጠናከርና ሳንደራጅ አፍርሰነዋል ፤ዛሬ ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚል ስጋት 0 ነጥብ 1 በመቶ እኔ የለኝም:: ስጋቶች በሙሉ ተንደዋል፤ በመከራ ውስጥ መናድ የቻለች ከሁሉ በላይ እስላምም ቢሆን ክርስቲያን ወደሰማይ የሚያንጋጥጥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከፈጣ ጋር ትስስር ያለው የፈጣሪ ምህረት አለ ብሎ የሚያስብ ህዝብ እና ከፈጣሪ የራሱ የሆነ ኪዳን ያለው ህዝብ ነው፤ አይጥለውም እግዚአብሄርም ይህንን አገር አይጥለውም:: እነሱ ብዙ ቢያስቡም ማለት ነው:: ይህንን መገንዘብ አለባቸው::
ከድህነትት ፈጥነን ለመውጣት ሰላም
ያስፈልገናል፤ ፈጥነን ለመውጣት ትብብር ያስፈልገናል:: ፈጥነን ለመውጣ ደጋፊ ያስፈልገናል:: ፈጥነን ለመውጣት ግን ክብራችንን መሸጥ አይጠበቅብንም:: ከነከብራችን ባለንበት አንቀጥላለን እንጂ:: ይህንን በደምብ መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል ዓለም አቀፍ ነገሩ ላይ:: በዲፕሎማሲው በኩል ሰፊ ሥራ እየተሠራ ያለው::
ብዙ ጥረት ነው የሚደረገው:: የሚገርመኝ ሲመጡ ያደንቃሉ፤ ያመሰግናሉ እዚህ መጥቶ ሳያመሰግን የሄደ ሰው አይቼ አላውቅም:: እዛ ሲሄዱ ምን እንደሚደርስባቸው አላውቅም:: የመጣ እስከአሁን ያገኘሁት ሰው /በቀን አራት ሰው፣ ሦስት ሰው ነው የምትሰሙትንም፣ የማትሰሙትንም ሳወራ የምውለው/ የማያደንቅ ሰው የለም:: ሲሄድ ግን ፍላጎቱ ሌላ ነው:: እሱን እንግዲህ ወደፊት እያየን እንሄዳለን:: ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ከሁሉም ህዝቦች ጋር በሰላም በትብብር በዓለም አቀፍ ህግጋት ራሷን መለወጥ የምትፈልግ አገር መሆኗን፣ ከዚያ ውጪ ግን በጠላትነት መንፈስ ብዙ ማስደንገጥና ማስፈራራት የማይሠራ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ይሆናል::
የሽምቅ ውጊያን በሚመለከት
የጁንታው ሃይሎች ከዚህ ቀደም ነግሬያችሁ ነበር እረስታችሁት ነው መሰለኝ፤ የጭንቅላት ድርቀት ያጋጠመው ሃይል ነው ብያችሁ ነበር:: ያ ድርቀት ነው አሁንም ስለ ሽምቅ የሚያሳስበው እንጂ አሁን እኮ ዘመኑ ለሽምቅ አይሆንም:: ጭራሽ፤ ዓለም ተቀይሯል ያኔ የነበረው የፖለቲካ ከባቢያዊ ሁኔታ ዛሬ የለም፤አያዋጣም:: ለትግራይ የሚያስፈልገው አዲስ ፣ ወጣት የተማረ፣አሁን ያለውን ነገር የሚገነዘብ፣ ትግራይን በራሳቸው ልጆች ከኢትዮጵያ ጋ ባለው ህግ መሰረት ተግባብቶ እና ተዋህዶ አብሮ ማደግ ብቻ ነው::
ከዚያ ውጪ ያለው ሰው ሊገድል ይችላል ፣ሊያደክም ይችላል፤ ግን የትም አያደርስም:: ትርጉም የለውም:: ይህ የስልት ስህተት መጀመርያ ከለውጡ በኋላ ሸሽተው መቀሌ ሲገቡ ትልቅ ስህተት ተሳሳቱ ቀጥሎ ብልፅግና ቢለምናቸው ከብልጽግና ጋ አልቀጥልም ቢሉ ሌላ ስህተት ተሳሳቱ፤ቀጥለው ደግሞ የማይነካውን ቀይ መስመር አልፈው ሰሜን እዝን ሲመቱ ሦስተኛ ስህተት፤ሦስት ጊዜም ሳይነቁ አሁን ደግሞ ሽምቅ አራተኛ ስህተት ማለት ነው::
አንዴ የስህተት መንገድ ከጀመርክ ማቆሚያ የለውም:: አያዋጣምና ህዝቡ በፍጥነት ከዚህ ስህተት መውጣት አለበት:: እየተጎዳ ያለው የትግራይ ህዝብ ነው:: የእነሱ የተሳሳተ እሳቤና ስልት ምንድነው የነበረው ፣ ውጊያውን ጎንደር እናደርገዋለን ምናምን የሚል ነው፣ ጎንደርስ ቢካሄድ ሰው ነው የሚጠፋው:: ውጊያ በኢትዮጵያ እስካለ ድረስ የሚያጠፋው ኢትዮጵያዊያንን ነው:: ስለሆነም አይጠቅምምና በፍጥነት ተረባርበን የትግራይን ክልል እንድናደራጅና ህዝባችንን ካለበት መከራና ችግር እንድናወጣ ያስፈልጋል።
እኛ የምንፈልገው ከአሥር እና ከአስራ አምስት ሰው አይበልጥም:: ለአስራ አምስት ሰው ተብሎ ክልል መታመስ የለበትም:: እነሱን ለህግ በማቅረብ ለተቀረው ሚሊሺያ ምናምን ምህረት ይደረግለታል። ወደ አገሩ ገብቶ ሥራውን መሥራትና በፍጥነት ክልሉን ማደራጀት ነው የሚያስፈልገው። እኛ ሁሉንም ሰው የማሰርም ሆነ የመጠየቅ ፍላጎት የለንም:: የትግራይ ህዝብ ይህን ተገንዝቦ በፍጥነት ወደ ሰላሙ እና ክልል ወደ ማደራጀት እንድንገባ ድጋፍ ቢያደርግ መልካም ነው። በየቦታው ያላችሁ የትግራይ ሰዎች ግዴታ የለባችሁምና እኛን አትውደዱን ግን ትግራይን እንድናደራጅ ተባባሪ ብትሆኑ በጣም ጥሩ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013