ክፍል ሁለት
ጤና ይስጥልን ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ የኢፌዴሪ 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ከትላንት በስቲያ ማካሄዱ ይታወሳል። በወቅቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን እኛም የዚህኑ ማብራሪያ ክፍል አንድ በትላንትናው የወቅታዊ ገፅ እትማችን በተለይ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ ይዘን መቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው እትማችን ደግሞ ሁለተኛውና በፖለቲካዊ እና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
ሰፈርተኝነት
ትልቁ የኢትዮጵያ ካንሰር በሽታ ከሰፈራችን የዘለለ ነገር አለማሰብ ነው ። ማንም በሰፈሩ አስቦ ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይችልም። ይህ ደግሞ ዛሬም ተረጋግጧል ፣ነገም የምታዩት ነው። በሰፈር ሃሳብ ኢትዮጵያን ማሳነስ እንጂ ማሳደግ አይቻልም። እባካችሁን ቢያንስ የምክር ቤት አባላት ከዚህ ውጡ።
አሁን ሰው ያለው ሰፈር ይደመጣል፤ ለትግራይ ህዝብስ ማነው የሚጮኸው ? የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው ተደፍረውና ተገድለው ስቃይ ላይ ናቸው ። የተገደሉ ብዙ ናቸው ትግራይ ላይ ብትሄዱ ከእኛ ውጪ የተበደለ የተገፋ የለም ይላሉ ። ምንበደልን የምንገፋ እኛ ነን ይላሉ። ቤንሻንጉል ብትሄዱ መተከል ብቻ ብትሄዱ የጉሙዝ ተወላጆች በስጋት ወደ ጫካ ገብተዋል አንድም ሚዲያ አይናገርላቸውም።
ምናልባት በቁጥር ብዙ ሊሆኑ ቢችሉም ይሄ አገር እኮ የኦሮሞና የአማራ አይደለም። ሌሎች ብዙ ብሄሮች አሉ። ሰከን ብላችሁ የሚበጅ ነገር ብትሰሩ ጥሩ ነው። ሁልጊዜ የኛ ነገር ውድ የሌላው የረከሰ ከሆነ አይሆንም። ሁሉም ዜጋ መከበር አለበት። ወጥቶ የሚገባበት ሁኔታ መኖር አለበት። ያንተ ወድ ህይወት የሌላው ርካሽ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም።በዚህ መንገድ የምትነግዱ የፖለቲካ ነጋዴዎች እባካችሁ ይህንን ችግር አስቡበት ።
ኦሮሞና አማራ ሲገዳደሉ የምታጯጩሁ አክትቪስቶችና ሚዲያዎች ኦሮሞና አማራ ከተገዳደለ አገር አትኖርም። ምን ልታስተዳድሩ ነው፣ የሚባላ ህዝብስ ምን ይሰራላችኋል። እንኳን የሚባላ ህዝብ የቆሙት ፕሮጀክቶች ጭንቅላታችንን አዙረውናል። አገር እያፈረሱ እመራለሁ ማለት አይቻልም።
ይህ በሁሉም ቦታ አለና እባካችሁ ከዚህ እንውጣ። መባላላታችን ለኦሮሞ፣ለአማራ ወይም ለጉራጌ አይጠቅምም። በቃ ሰው ይሞታል እናለቅሳለን ፤ እንቀብራለን። የሰው ቤተሰብ እናፈርሳለን ከዛ ደግሞ ህይወት ይቀጥላል። ይህ ጭንቅላት የሚያዞር፣ ለመኖርና ለመስራት የማይመች በመሆኑ እባካችሁ ሰከን ብለን ብናስብና ለጠላቶቻችን ሲሳይ ባንሆን መልካም ነው።
ኦሮሞና አማራን ለማባላት ገንዘብና ጊዜያቸውን ሰውተው የሚሰቃዩ ኃይሎች እንዳሉ እያወቃችሁ በተቀደደ ቦይ የምትገቡ አመራሮች ትገርሙኛላችሁ። በራሳችሁ ጊዜ ብትባሉ መልካም ፤ ነገር ግን እዚህ አገር ላይ የምንፈልገውን አናሳካም ለሚሉ ኃይሎች ዕድል መስጠት ጥሩ አይደለም፡፡
ማስተዋል መልካም ነው፤ ኦሮሞ ፣አማራ ወይም ጉራጌ ቢሞት ጉዳቱ እንደ አገር ነው። የዜጎች መበደል፣መዘረፍ መሞት እኩል ካላሳዘነን የጋራ አገር አንገነባም። ይህ ፖለቲከኞችን የሚመለከት ጉዳይ ነው።ይህ አገር የ80 ብሔሮች አገር እንደሆነ ፣ ሁሉም ከኖረ ብቻ ኢትዮጵያ እንደምታድግ በመረዳት ለጋራ ነገር ልናስብ ይገባናል።
የህግ ማስከበር ዘመቻ
ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ጦርነት ሰላምን ለማምጣት ይካሄዳል ይላሉ። ፍትህን ለማምጣትና የአገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅም ይካሄዳል የሚሉ አሉ። ለጦርነት የተለያየ ስያሜ እየሰጡ የተካሄደውም ለሰላምና ለፍትህ ነው የሚል ነገር ያነሳሉ፤ ይሁን እንጂ በማንኛውም መመዘኛ ጦርነት ሲታሰብም ፣ ሲሰራም ፣ ሲጠናቀቅም ኪሳራ እንጂ ጥቅም የለውም። የጦርነት ጥቅሙ የሚታየው ጦርነትን ካለመጀመር ብቻ ነው።
ጦርነት ከተጀመረ ውርደትና ሞት ነው። ጦርነት ከባህሪው ፍቺን፣ ጥላቻን፣መገፋትን የሚፈልግ ነገር ነው። ጦርነት ጥቁር ጥላ ነው። ታስታውሱ እንደሆን ለዘመን መለወጫ ለትግራይ ህዝብ የጥይት ድምፅ አያስፈልገውም በቃው ያልነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በአደባባይም በሚስጥርም የህወሓት አመራሮችን ለማነጋገር ሞክሬያለሁ።
ሽምግልናም ልከናል። ጥይት ካለ ዘረፋ፣ መደፈርና ሌሎች ነገሮችን መከላከል አይቻልም። ዋናው መፍትሄ ወደ ውጊያ አለመግባት ነው። ወደ ውጊያ ከተገባ ሁሉም የራሱን ማስፋትና ማጥቃት ላይ ስለሚያተኩር መደበኛ የሆኑ የህዝቦች መብቶች ይገፈፋሉ።
ህወሓት 27 ዓመት ቢዘርፍ ቢገድል ቢያጠፋ ለዚሁ ምክር ቤት እነሱን ወክዬ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቄያለሁ ። ህዝቡም ይቅርታውን ተቀብሎ ነገሩም ቀርቶ ነበር ። ግን በእጅ ደም ሲኖር አያስቀምጥም፤ እንጂ በድለናል ይቅርታ አድርጉልን አሁን ወደ ልማት እንሂድ በሚለው ተስማምተን ነበር። ችግሩ የነበረው በዳዩ ላይ ነው።
እኔ የህወሓት አመራሮችን፣ ሥራ አስፈጻሚዎችን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በግል ለምኛለው። እሱም አልሆን ሲል አዲስ አበባ ወስጥ ዋና ዋና ሀብታሞችና ታዋቂ ሰዎችን በሚስጥር ጠርቼ ሽምግልና ልኬያለሁ ። እነዚህን ሰዎች ለምኗቸው የሚሂዱበት መንገድ ጥፋት ነው። በዚህ መንገድ ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም፤ በተመሳሳይ ወደ ውጊያ የሚገቡ ከሆነ እናሸንፋቸዋለን እኛ የሚሊሺያ ውጊያ አንዋጋም የሚለውን ጭምር ነግሬ ከውጊያው በፊት ሽምግልና ልኬያለሁ።
የሄደው ሁሉ ደርሶ ሲመለስ ያዝንልኝ ነበር። እዛ ያለው እንደፈለገ ማድረግ የሚችል እዚህ ያለው ደግሞ ምንም ማድረግ የማይችል አድርጎ ሁሉም ያስብ ነበር። እንደው ጥንቃቄ ብታደርግ ትንሽ ብታስብበት የሚል እንጂ በዛ ጎን ጥፋት ሊመጣ ይችላል ብሎ የሚያስብ አልነበረም።
ሁሉም ቀርቶ አንድ አምባሳደር ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ወደ መቀሌ ሄዶ ከዶክተር ደብረፅዮን ጋር አውርቶ ግጭቱ ይቅር ሲለው አትቸገር እኛ ሁለት ሳምንት አይፈጅብንም ካሸነፍናቸው በኋላ ድርድር እናደርጋለን የሚል ምላሽ ነበር የሰጠው። እብሪት ውድቀትን ታስቀድማለችና ህወሓት ብቻ ሳይሆን አሁን ያለን ፖለቲከኞች ከዚህ መጠበቅ አለብን።
ህወሓት ስልፉና ሁሉ ነገሩ ጦርነት ነበር። ተው ቢባሉ ቢለመኑ እንቢ አሉ። እንደውም ጦርነት ጨዋታችን ድራማችን ነው አስከ ማለት ደረሱ። ጦርነት ለማንም ድራማ ሆኖ አያውቅም፤ ጦርነት ብፍስ ነው የሚበላው። የአንድ ሰው መሞት ብዙዎችን ይጎዳል። በዚህ ምክንያት ነበር እናንተም ይህ መንግሥት ልምምጥ አበዛ እርምጃ አይወስድም እያላችሁ የነበረው።
እርምጃ መውሰድ ሰውና ሀብት ነው የበላው። በዚህ ግጭት ምን ያክል ውድቀት እንደደረሰ እኛ እናውቃለን። የህወሓት የጦርነት ፍላጎት አሳዛኝ የሚሆነው ላለፉት ሃያ ዓመታት በስልጣን እያለም ከትግራይ ህዝብ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮኑን በሴፍቲኔት እየተረዳ መሆኑ ነው። ከሚሰጠው ኮታም ላይ ይቀነስበትም ነበር። በዚህ ላይ ኮሮናና አንበጣ ባለበትና ገበሬው የዘራውን ሳይሰበስብ ጦርነት አይጀመርም። የፈለገ ክፋት አንኳን ቢኖር ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ይህንን አያደርግም፤ ጊዜ መምረጥ ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ የክልሉ አመራር ግጭት ሰባኪና ጨማቂ እንዲሁም የጦርነት ተንታኝ ሆኖ ነበር። ጦርነቱን ደግሞ በአካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን እንትና ከፈለገ አምስት አሥር ጊዜ ይምጣ ከማለታቸው ባሻገር እኛ ከተነካን ምስራቅ አፍሪካ ትጠፋለች የሚለውን እነሱ አምነው ፈረንጆቹን ሁሉ አሳምነው ነበር።
ምስራቅ አፍሪካ የምትታመሰው መጀመሪያ የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ ከተጎዳ ብቻ ነው። ውስጥ ያለው ሳይጎዳ ሌላው የሚታመስበት እድል አይኖርም። ይህ በዚህ አላበቃም በአገሪቱ በታሪክ የሰማነው አንበሳ ገዳይ ተብሎ ሲፎከር ነው። አሁን ገበሬ ገዳይ ነው እየተፈጠረ ያለው። የሚያርስ ገበሬ እየገደለ ልክ እንደ ጀግና የሚፎክር።
የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ላለፉት ሀያ ዓመታት የት ነበር። ለምን አሁን ያለውን ቀደም ብሎ አላደረገውም? ስልጠናና መሳሪያ ከየት ነበር የሚያገኘው የሚለው ነገር ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ መሆን አለበት።
በህግ ማስከበር ዘመቻው ሦስት መቶ የኦነግ ሸኔ አባላት ትግራይ ላይ እየሰለጠኑ አግኝተን ይዘናል። ነገር ግን የኦነግ ሸኔ ሽፍታ አማራ ብቻ ገደለ የሚለው አደገኛ ነገር ነው። የኦነግ ሸኔ ከአማራ በላይ ያዋረደው ኦሮሞን ነው። ኦሮሞን ከነነብሱ አቃጥሏል፣ አሥር አስራ አምስቱን ምሽግ ወስጥ ጥሏል።
በምዕራብ ወለጋ ሦስትና አራት ወር ስንዋጋ ስልክ አልነበረም ነገር ግን አንድም የውጭ አካል ያቀረበው አቤቱታ አልነበረም። በትግራይ ግን ሲጠፋ ችግር ሆነ። ኦነግ ሸኔ የኢትዮጵያ ጠላት ነው። ለኦሮሞ አይበጅም፣ ለአማራ አይበጅም ለማንም አይበጅም። ምክንያቱም በሰላም መጥተህ ተወዳድረህ አሸንፍ ሲባል የጁንታ ቡችላ ሆኖ ገበሬ እየገደለ የሚፎክር ነውና።
ኦነግ ሸኔ ለሁሉም ጥፋት ነው፤ ጥቅም የለውም። ለራሱም ጥቅም የለውም።የወለጋ ህዝብ መንገድና ልማት እንዳይሰራለት ሆኖ ስቃይ ውስጥ ነበር። አንድም ሰው አልተናገረም ፣ በራሱ ነው ይህን ኃይል የገፋው። ወለጋ ውስጥ የሞቱ የአማራ አርሶ አደሮች አማራ አደሉም የኦሮሞ አካሎች ናቸው።
ኦሮሞን አምነውና ወደው የሚኖሩ ናቸው። እነሱን መግደል ኦሮሞን መግደል ነው። ማንም ሰው ሲወድ ነው ወደ አንድ አካባቢ የሚሄደው። እንኳን ለኑሮ ለመዝናናት ቦታ ይመረጣል ፤ በኦሮሚያ ወስጥ ማንም ሰው ሲሞት በዋናነት ኦሮሞ ነው የሞተው።
እነዚህ ኃይሎች የሁላችንም ጠላቶች ናቸው። የእነዚህን ኃይሎች ሥራ የአማራና የኦሮሞ ጉዳይ ካደረግነው የጠላት ምኞት ማሳካት ነው። ነገር ግን ኦነግ ሸኔ ለአማራም፣ ለኦሮሞም ፣ ለጉራጌም ፣ ለወላይታውም ጠላት ነው ብለን በጋራ የምንቆም ከሆነ እናጠፋዋለን፡፡ ስለሆነም ሽፍታው ቡድን ለማንም የሚጠቅም አይደለም ብሎ በጋራ ማውገዝ ያስፈልጋል።
ትግራይ የተፈጠረው ችግር እነዚህ አይነት ቡችሎች በየቦታው ፈጥሮ ገበሬ ይገደላል። አሁን ትግራይ ውስጥ ሰው ይታፈናል። ሰው ይገደላል። አንዳንድ ነገር የሚረሳ ይመስለኛል። ሁለት መቶ ሺህ ወታደር አለኝ እያለ ትግራይ የነበረው ኃይል ሲፎክር ነበር እኛ ሁለት መቶ ሺ አልገደልንም ። ያ ኃይል ተበትኗል። አሁን ከየቤቱ
እየወጣ እየገደለ ነው። ሌላው ቀርቶ በአካባቢው እርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ይታፈናሉ። እርዳታ እንዳይሰጡ ይገደላሉ። ከዚህ ቀደም ካደረጉት ጥፋት በላይ አሁን ትግራይ ላይ ነገሮች ተረጋግተው ሥራ እንዳይሰራ እያደረገ ነው። ይህ ትግራይ ላይ ብቻ ሳይሆን ቅማንትም ላይ ይስተዋላል። ግን ከአጥፊዎቹ በላይ ያንን የጥፋት ሀሳብ ተሸክሞ የሚያቀነቅነው ያሳምማል።
ቅድም ስለ ከሚሴ ሲነሳ እዚ ያለው የወሎ ክፍለ አገር ህዝብ ነው። የፌዴራል ስርዓት ሲመጣ ነው አማራ ክልል ልዩ ዞን የተባለው እንጂ የወሎ ክፍለ አገር ህዝብ ነው። በወሎ ውስጥ የተዋለደ የተጋባ ከማንም በላይ የሚተዋወቅ ህዝብ ነው። እኛ ነን በዞን ከፋፍለን የያዝነው። ሰከን ብለን ብናይ ጥሩ ነው ፤ አያዋጣም ። የሰው ደም እንደፈለገ ማፍሰስ ይቁም። በርሃብ የሚሰቃየው አንሶ በእኛ የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት ሰው መሞቱ ይቁም።
ወደ ትግራይ ስንመለስ ብዙዎች የደረሰብንን በደል እያወቁም ሊክዱ ይፈልጋሉ። በአንድ ቀን ሁለት መቶ ቦታ ነበር በሠራዊቱ ላይ ጥቃት የተፈፀመው። በጣም በተጠና መንገድ ነው የተከናወነው።
ከሰባት ሺ በላይ ቤታቸው የነበሩ የጦር አመራሮች ተይዘዋል። መቀሌን ስንይዝ ከአንድ ሺህ ሶስት መቶ በላይ ኦፊሰሮች ታግተው ነበር። ጉዳዩ በዚህ አላበቃም ጦርነቱ አገራዊ እንዲሆን አማራ ክልል ላይ ጦርነት ተከፍቷል። በአገር ብቻ እንዳይቀርም ወደ ኤርትራ ሮኬት ተተኩሷል።
አሁን ስለ መሠረተ ልማት ሲወራ የባህርዳርና የጎንደር አየር ማረፊያዎች በሮኬት ማጥቃት በምን ሳይንስ ይተነተናል ፤ እኛ ትግራይ ላይ እየተዋጋን አክሡምና መቀሌ አየር ጣቢያ እንዲጠቁ አላደረግንም። ሮኬት እያለን አልተጠቀምንም። ሮኬት የተተኮሰው መቀሌን ለቀው ተከዜ በርሃ ሲገቡ ነው። መሠረተ ልማቶች ጥቅም እንዳይሰጡ ተደርገው ነው የተበላሹት ።
መቀሌ ብቻ ከአሥር ሺህ በላይ እስረኛ ተፈቷል። በነገራችን ላይ በድፍን ትግራይ ከ30ሺ በላይ እስረኞች ተፈተዋል እኛ ሰው እንደዚህ እንደሚታጎርም አናውቅም ነበር ። መቀሌ ብቻ አሥር ሺ እስረኛ ፈተዋል። እስረኛው ይዘርፋል፣ የነሱ ርዝራዥ ይዘርፋል፣ መከላከያም የሚያበላሸው ነገር አለ፣ ሌሎች ኃይሎችም ተጨማምሮ አገራችን ጉዳት ላይ ነች።
የዚህ ሁሉ ጉዳት መነሻ ኃላፊነት የጎደለው የህወሓት ሀይል ቢሆንም ጉዳቱን እየቀመሰ ያለው ምስኪኑ ህዝብ ነው። በሴፍቲኔት የሚኖር 1.8 ሚሊዮን ህዝብ ተጨማሪ እዳ አይገባውም ነበር። ለትግራይ ህዝብ ጦርነት፣ ግጭት አይገባውም። የተሸከመው የጁንታ ሀይል በእጁ የነበረው ደምና ሃጢዓት አስክሮት ተጨማሪ እዳ አምጥቶባቸዋል። ይሄ ያስከተለው መዘዝ በጣም ብዙ ነው።
የኛ የህግ ማስከበር ዘመቻ በግልፅ ዓላማ ላይ የተመሰረተና ሶስት የተለያዩ ዓላማዎች ያሉት ነው። አንደኛው ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ከሀያ ዓመት በላይ በማያውቀው፣ በማያገባው፣ በዘሩ ምክንያት ብቻ ያሰሩት፣ የጨፈጨፉት፣ በየቦታው አስከሬኑን የጣሉትን ወንጀለኞች የፈፀሙትን ወንጀል በኢትዮጵያ ህግ ስለሚያስጠይቅ ስለሆነ እጃችሁን ለመንግሥት ፣ ለህግ ስጡ ነው ያልነው።
ለህግ የሰጡ ሰዎች እኮ እንደምታውቁት አልብሰን ፣ አብልተን፣ አሁን አበባ ይመስላሉ። እጃችሁም ለህግ ስጡና ህግ ይዳኛችሁ፣ ህግ የፈለገውን ያድርግ ብለናል፣ ስለያዝን እንግደል አላልንም።
ሁለተኛው ታጋቾችን ማስፈታት ነው። ኢትዮጵያን አምነው ለኢትዮጵያ ክብር ከቀያቸው ተፈናቅለው፣ ሀያ ዓመት ምሽግ ላይ ያሉ ሰዎች፣ ባልጠበቁት መንገድ ከጀርባቸው ተመትተው በሺህ የሚቆጠሩ ኦፊሰሮች ታፍነውብናል፣ የትኛው አገር ነው የራሱን ዜጋ ለማስለቀቅ ጥረት የማያደርገው።
አሁን እንደሚፎከረው እኮ አይደለም፣ ማንም ሰው የራሱ ኦፊሰር ቢያዘበት ታጋቹን ነፃ ለማውጣት ብዙ ኦፕሬሽን ያካሄዳል። ይህን በእስራኤል አይተናል፣ በተለያዩ አገራት ይሰራል። እኛ ግን ኦፊሰር ጄነራሎች ጨምሮ ከአንድ ሺ በላይ መኮንኖች ታግተውብናል።
ሦስተኛው ዓላማ የትግራይ ህዝብ ህዝባችን ስለሆነ ይሄ ክልል የሽግግር አስተዳደር ኖሮት፣ መሠረታዊ አገልግሎት እየሰጡ፣ መንግሥት ሆኖ፣ ወደ ምርጫ ሄዶ እራሱ የሚፈልገውን ኃይል በምርጫ መምረጥ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
እንደምታውቁት በመጀመሪያው ዓላማ ላይ በርካታ ወንጀለኞች ይዘናል። የቀሩ ወንጀለኞች አሉ። የቀሩ ወንጀለኞችን ከአጠቃላይ ኦፕሬሽን ጋር ለማያያዝ የሚሞክር ኃይል አለ፣ይህ ስህተት ነው።
የአሜሪካ ጦር አፍጋኒስታን ላይ አልቃይዳን ቢደመስስም ፣ ቢንላደንን ለመያዝ ግን ዓመታት ወስዶበታል። አፍጋኒስታን ላይ ጦር ማፍረስና ቢላደን መያዝ ለየብቻ ነው። እኛ የህወሓትን ተቋማዊ መዋቅር አጥፍተነዋል። ግለሰቦች ይፈለጋሉ፤ ሲገኙ ደግሞ ለህግ ይቀርባሉ።
ታጋች ማስፈታት መቶ በመቶ ተሳክቶልናል፣ ኦፊሰሮቻችንን አስፈትተናል። አዋርደው ገድለው የጣሏቸውን ቀብረናል። የተዘረፍነው መሳሪያ ቁጥር ስፍር የለውም ፣ ባለፈው አንስቼላችኋለሁ። አስመልሰናል።
ሦስተኛው የትግራይ አስተዳደር በሁሉም ወረዳዎች በሚባል ደረጃ ተዋቅሮ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ ነው። ይሄ አስተዳደር መታገዝ አለበት። ህዝቡ ማገዝ አለበት፣ ፌዴራል መንግሥት ማገዝ አለበት፣ ክልሎች ማገዝ አለባቸው። የምናግዘው ለህዝባችን ስንል ነው። ህዝቡን ካላገዝነው ይጎሳቆላል። መሠረታዊ አገልግሎት አያገኝም። ይሄ አስተዳደር ግን የሁልጊዜ አይደለም። ምርጫ እስከሚካሄድ የሚቆይ ነው።
የተከበረው ም/ቤት እንዲገነዘበው የምፈልገው ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተዋቀረው በትግራይ ክልል ካሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነው፣ አንድ አማራ፣ አንድ ኦሮሞ ፣ አንድ ጉራጌ የተቀላቀለ የለም። ውጊያ ላይ እያለን እንኳን የትግራይ ህዝብ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በሚጠብቅ መንገድ ነው የተንቀሳቀስነው፣ ያረጋገጥነውም ይሄንን ነው። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉት የራሱ ልጆች ናቸው፣ ካልፈለጋቸው በምርጫ ይጣላቸው፣ የፈለገውን ይምረጥ፣ መብቱ ነው።
ህግ የማስከበር ዘመቻ የተካሄደው ሦስቱን ግቦች ለማሳካት ነው። በሂደቱ ንፁኃን ሰዎች እንዳይጎዱ ባለፈውም አንስቼዋለሁ፣ አሁን አልዘረዝረውም። መቀሌ እንዳንዋጋ፣ አክሡም እንዳንዋጋ ፣ ሽሬ እንዳንዋጋ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። አክሡምን ከያዝን በኋላ ታስታውሱ ከሆነ ህዳር ጽዮን ማሪያም ተከብሯል። ከተሞች ላይ ችግር እንዳይመጣ፣ ወታደሮቻችን በቦቴ ውሃ ነዋሪዎችን እንዲያጠጡ፣ ሙከራ ተደርጓል።
እዚህ ጋር ያለው ችግር ምንድን ነው፣ የተበተነው ርዝራዡ ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊት ከገባ ውሃም፣ ቀለብም ከሰጠ በኋላ እየቆዩ አንድ ሁለት ሰው ሲያገኙ ሲተኩሱ፣ ሲገድሉ፣ ድርጊቱ በመከላከያ ላይ ቁጣ በመፍጠሩ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች አሉ ።
መከላከያን ለሁለተኛ ጊዜ ለግጭት እየጎነታተሉት ነው። በዘመቻው ወቅት ከባድ መሣሪያዎች ከተሞች ላይ አልተኮስንም፣ ሮኬቶችን ጨምሮ እነሱ እየተኮሱ እኛ አልተኮስንም። ሚሳኤሎች እንዳይሰሩ የማምከን ስራ ነው የሰራነው። ሮኬት ስላለን ብለን አልተኮስንም። ይህም የሆነው ህዝቡ የኛ ህዝብ ስለሆነና የሚደርስበትም ጣጣ የእኛው እዳ ስለሆነ ነው።
ኢራቅ ላይ ዘመናዊ ጦሮች ፣ ዘመናዊ ኃይሎች ባደረጉት ውጊያ ከስልሳ ፕርሰንት በላይ ያጠቃው ንጹኃንን ነው። አፍጋኒስታን ላይ 25 ፐርሰንት በላይ ያጠቃው ንጹኃንን ነው። የመን የሰማችሁት ነው። ሶሪያም እየሰማችሁ ነው። በከፍተኛ ደረጃ ንጹኃን ይጠቃሉ፣ በእንደዚህ አይነት ጦርነቶች ሊከሰቱ የሚችሉ ጥፋቶችን ለማስቆም ትልቁ መፍትሄ ውጊያ አለመጀመር ነው።
ከጀመርክ ዘመናዊ ሁን ፣ ድሃ ፣ ሀብታም ፣ውጊያ ከፍ ያለ ውድመት ማድረሱ የማይቀር ነው ። ውጊያ ጀምረህ ስታበቃ ፊት በጥፊ አይመታም ምናምን አትልም። እሱ በቦክስ ውድድር ውስጥ ያለ ህግ ነው ፋውል የሚባለው። አንዴ ከተገባ ውጊያ በጣም አስቀያሚ ነገር ነው ።
ህወሓት በከተሞች ላይ ከባድ መሳሪያ ያከማቸው፣ የሀይማኖት ተቋማት አካባቢን እንደ ምሽግ የተጠቀመውና ሮኬት የተኮሰበት ዋና ምክንያት በጣም ክፍተኛ የሆነ የንጽሃን እልቂት እንዲፈጠር በማሰብ ነው። ይህ ፍላጎቱ እንዳይሳካ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። አሁን ለትግራይ ህዝብ ፣ ለትግራይ ወዳጆች፣ ለተከበረው ም/ቤት መግለፅ የምፈልገው፣ ህወሓት ማለት በንፋስ ላይ እንደተበተነ ዱቄት ነው። ከእንግዲህ በኋላ ሰብስበን ዱቄት ልናደርገው አንችልም።
እሱን ትተን አዲስ ኃይል፣ አዲስ የተማረ፣ አሁን ያለውን ዘመን በሚዋጅ አስተሳሰብ መምራት የሚችሉ ሰዎች መፍጠር ነው ፣ ይህ ደግሞ ይቻላል። ትግራይ ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፣ ብዙ ምሁራን አሉ። አብረን መላላጥና መጋጋጥ ጠቀሜታ የለውም።
እንበልና የተከበረው ም/ቤት ፈቅዶ መንግሥትን እረፍ ብላችሁ፣ እዚያ የተሸሸጉ አንዳንድ ሰዎች መጥተው መንግሥት ይሁኑ ቢባል እና መቀሌ ቢመለሱ፣ በምን ዓይናቸው ነው ከሰው ፊት ቀርበው እንደትላንትና መናገር የሚችሉት። መልካቸው ስለተበላሸ ብቻ አይደለም። ሞራልም ደቅቋል እኮ በየት በኩል? ማንስ ነው የሚሰማቸው? ማንስ ነው የሚያምናቸው? ይሄ ታሪክ ነው በፍፁም ብንዋጋም ባንዋጋም አይደገምም።
እኔ የሚያስታውሰኝ 83፣ 84 አካባቢ ወደ ምዕራብ ስለነበርኩኝ፣ የሆነ ወሬ ነበር ሁልጊዜ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ስፔሻል ስፓርታና አየር ወለድ ጦር ይዘው ጋምቤላ ገቡ ይባላል። በቃ ሠራዊት ውስጥ ወሬ ብቻ ነው።
ሆን ብሎ እሳቸው ጋምቤላ ገቡ ይባላል፣ እራሳቸው የሉም። የዚህ አይነት ፕሮፓጋንዳ ለኢትዮጵያም ለትግራይም አይጠቅምም። ንፁሁ ህዝባችን እየተጎዳ ስለሆነ አሁን የሚያስፈልገው ጠንካራውን ይዞ ክልሉን አረጋግቶ ወደ ሰላም መውሰድ ነው።
ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ
ውጊያ ጥፋት ነው፤ ብዙዎችን ይጎዳል። ጥያቄ የለውም። የሚጋነነውን ፕሮፓጋንዳውን ትታችሁ፣ ሴት በመድፈር፣ ንብረት በመዝረፍ፣ ጥፋቶች እንደተካሄዱ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ሳምንት የወሰደ ግምገማ አድርገናል። ገና ትናንት እሁድ ነው የጨረስነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ፣ በትግራይ እህቶቻችን ላይ መድፈርን፣ መዝረፍን የፈጸመ ማንኛውም ወታደር
በህግ ይጠየቃል። እኛ ጁንታን ምታ እንጂ ንጹኃንን አጎሳቁል አላልንም። ይህን ያደረገ በህግ ይጠየቃል። ጁንታውን ስንጠላ ህዝቡን መለየት አለብን። ጁንታውን ስንጠላ በወታደራዊ ስነ ምግባር ግዳጆችን መምራት ይጠበቅብናል። ካልሆነ ውጤቱ አደገኛ ነገር ነው።
የተከበረው ምክር ቤት እንዲያስብ የምፈልገው አሁን ኦሮሞ፣ አማራ፣ ወላይታ ብለን፣ የምንባላው ነገር የእንደዚህ አይነት ኦፕሬሽን/ግዳጅ / ብልሹ አሰራር ውጤት ነው። የዛሬ መቶ ዓመት የሆነ አካባቢ የሆነ ኦፕሬሽን እንደ ህዝብ አማራ የሚባል ህዝብ የሄደበት አይደለም።
አንድ የአማራ ጄኔራል ወይንም አንድ የአማራ ደጃዝማች ሊሆን ይችላል፤ አሰልፎ የሄደው ፣ ጦር ከጦርነት በኋላ መዝረፍ፣ መድፈር፣ መግደል ውስጥ ሲገባ እስከዛሬ ድረስ አማራና ኦሮሞ፣ ወላይታ ምናምን ይባላል። ህዝብና ህዝብ ተጋጭቶ ሳይሆን ለዘመቻ የሄደው ኃይል በፈፀመው ጥፋት ሁለቱንም ሲያባላ ይኖራል።
ከጦርነት በኋላ መግደል መዝረፍ ውስጥ ሲገባ እስከዛሬ ድረስ አማራ ኦሮሞ ወላይታና ምናምን ይባላል። ህዝብና ህዝብ ተጋጭተው ሳይሆን ለዘመቻ የሄደው ኃይል ከድል በኋላ የሚያስከትለው ጥፋት አደገኛ ቁስል ነው። ይኸው እየተሰቃየንበት ነው። እንጂ አሁን ያለው አማራማ ምን የሚያውቀው ታሪክ አለ፤ ምን የሚያገናኘው ነገር አለ።
ወታደር ካሸነፈ በኋላ በከፍተኛ ስነ ምግባር ካልተያዘ ለዘመናት የሚቆይ ቁርሾ ሊጥል ይችላል። ለዛም ነው ጠንከር ብለን በኛ ሠራዊት ላይ እርምጃ መውሰድ የምንፈልገው። ጀግኖችን እንሾማለን፤እንሸልማለን ጥፋተኛን ደግሞ በህግ እንጠይቃለን።
ጥፋትን በሚመለከት ከፍተኛ ግነትና ፕሮፓጋንዳ አለ፤ እሱ ነባራዊ ነው። አንድም ጥፋት ካለች ግን ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል። በእኛ በኩል ከምናደርገው ውጭ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠንካራ ጥናቶች ሲያደርግ ቆይቷል። በቅርቡ ሪፖርት ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። ሰብዓዊ መብት በሚያቀርበውና በኛ ሪፖርት መካከል፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያቀርበውና በጁንታው ርዝራዦች በሚያቀርቡት መካከል የቁጥር እና የድርጊት ልዩነት ሊኖር ይችላል።
ይህንን በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል። የተከበረው ምክርቤትም በአንክሮ ማየት ያለበት የጁንታውን ብቻ ሳይሆን ህዝቡ እየደረሰበት ያለው መከራ የሚስተካከልበት ሁኔታ የናንተም ስጋት መሆን አለበት። የሚፈናቀልና የሚራብ ሰው ስላለ።
አንዳንዶች እውነት ያዛባሉ፤ እውነትን በትክክል ማየት አይችሉም። አንድ ሰው በግራ ዓይኑ የሆነ ነገር እያየ በቀኝ ዓይኑ ሌላ ነገር ማየት አይችልም። ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚሰቃዩ ፣ ትግራይ ስላለው ችግር የሚሰቃዩ ሰዎች የሰሜን እዝ ጥቃት በሚመለከት ምንም አያነሱም። ሰሜን እዝ እኮ አልተጠቃም ተዋረደ። ሴቶች እኮ በወንድ ነው የተደፈሩት የኛ ወታደሮች ግን በሳንጃ ተደፍረዋል።
ስለነሱ የሚያነሳ ሰው የለም። በየከተማው ተጨፍጭፈው በመኪና ሲረገጡ ማንም ስለነሱ ያነሳ የለም። እንዴት ነው በአንድ ዓይንህ ስለ ሰው ልጅ የምታየው በሌላ ዓይንህ ግን ደንታ የሌለህ? አላውቅም። የማይካድራ ጭፍጨፋ የተደራጀ ኃይል በገዛ አገራቸው ሸቅለው የሚኖሩ ዜጎች ጨፍጭፎ ማንም ሰው ደንታው አይደለም።
የማይካድራው ሰው አይደለም? ማይካድራ ላይ የተጨፈጨፈው ጭፍጨፋ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የትም ቦታ ላይ አልተደረገም። አሁን ባለው ኦፕሬሽን ግን ተረስቷል፤ ማይካድራ ትዝም አይላቸው። ጁንታው በእኛው ሮኬት ያፈረሰው የጎንደርና የባህርዳር ኤርፖርት አሁንም በቢልዮኖች እየጠየቀ ነው፤ ማንም ሰው ደንታው አይደለም።
ባህርዳር ላይ ሰው ሞቷል፤ ጎንደር ሮኬት ሲተኮስ የአንድ ቤተሰብ አባላት ደባርቅ ላይ አልቀዋል። አርሶ አደሮችም። ማንም ሰው አያነሳም። የትግራዩ ይቅር ቤንሻንጉል ላይ መተከል ዞን ስላለው ጭፍጨፋ መፈናቀል ማንም ሰው አያነሳም። ለምን እነሱ ጥቁሮች ናቸው፣ አርሶአደሮች ናቸው፣ ምንም ገንዘብ የላቸውም፣ ፌስቡክ የላቸውም ፣ ሎቢ አይቀጥሩ።
ጩኸት ሁሉ በአንድ ቦታ መሆን የዓይን መንሸዋረርን እንጂ የበደል ልክን አያሳይም። ይሄ ትክክል አይደለም። ለእኛ ቤንሻንጉል ያለውም ፣ ትግራይ ያለውም ሆነ ፣ አማራ ያለው ዜጋችን ሁሉም እኩል ነው። ደሀም ቢሆን ሀብታም አርሶ የሚበላም ቢሆን አርብቶ የሚያድር ቢሆን ስለ ሁሉም መብት በእኩል የምንጮህ እንጂ ሰው ስላለ የሚጮህለት ከሆነ በጣም አደገኛ ነገር ነው።
ሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተ
እርዳታን በሚመለከት ላነሳችሁት ጥያቄ ከዚህ ኦፕሬሽን በኋላ 4.2 ሚልየን ህዝብ መግበናል። እቅዳችን 3 ሚሊዮን ነበር። 4.2 ሚልየን ህዝብ ስንመግብ ከ92 በላይ የእርዳታ ማከፋፈያ ቦታዎች ከፍተን ነው ። አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ህዝብ መመገብ ከተቻለ ምን አይነት አቅም እንዳለ ያሳያል። አንድም አገር አንድ ኪሎ ስንዴ ልኮ የተመለሰበት የለም።
የትግራይ ህዝብ በቲውተር የተለጠፈውን ጹሁፍ አይበላም – ስንዴ እንጂ። ያልተገደበ ሁኔታ ካልተከፈተ ተብሎ ተጮኸ እሺ ከተባለ በኋላ እንደሚታየው ነው። ከኦፕሬሽን በኋላ ከአርባ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥተናል። በዶላር ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። ጁንታው ለቆረጠው፣ መብራት፣ ለቴሌ፤ ለኤርፖርት፣ ለውሃ፣ ለትምህርትና ለጤና ተቋማት መጠገኛ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል፡
ይህ ባያጋጥም የሚገጥመንን የዋጋ ግሽበት ማረጋጋት ይቻል ነበር። ‹‹አልማጭ ከመዶሻው ይጋጭ›› እንደሚባለው ከጠፋው ጥፋት በላይ አሁንም እንደልባችን ተንቀሳቅሰን ህዝባችን እንዳንረዳ የጁንታው ርዝራዥ በከፍተኛ ደረጃ እንቅፋት እየፈጠረ ነው።
ክልሎች የትግራይን ህዝብ ለማገዝ ላደረጉት ጥረት ከፍተኛ ምስጋና የሚገባው ነው። እያንዳንዱ ክልል ለማገዝ ጥረት አድርጓል፤ አሁንም ማገዝ ይጠበቅብናል። የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቦታቸው መመለስ አለብን። የጥፋት ኃይሉ ስለጀመረው ብለን የምንተወው ጉዳይ አይደለም። ባለሃብቱና ህዝቡ ለዚህ መተባበር መቻል አለበት። ዲያስፖራው እያዋጣ ለጥፋት ከሚያውለው ገንዘብ ለልማት ቢያዋጣ ያተርፋል።
ስደተኞችን በሚመለከት ከ27 ሀገራት የመጡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች በሀገራችን አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከሁለት መቶ ሺ በላይ የሆኑትን እንደ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እናስተምራለን። በአዲስ አበባ ያሉ የሶሪያ ስደተኞች ህገ ወጥ ናችሁና ውጡ አላልናቸውም። ስደተኛ መቀበል ግን ቀላል ነገር አይደለም። ደን ያጠፋል ለምሳሌ ጋምቤላ ያለው ደን እየጠፋ ነው። ሀገራት ረዳን የሚሉት ገንዘብ እየጠፋ ካለው ጋር ሲነፃፀር ውስን ነው።
ከኤርትራን ብቻ ሁለት መቶ ሺ ገደማ ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራሉ። ከዚህ ውስጥ 90 ሺህ የሚሆኑት ትግራይ ውስጥ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ካምፕ ውስጥ አይኖሩም። 50 ሺ የሚሆኑት በአፋር ክልል የሚኖሩ ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች 70 ሺህ ገደማ ይኖራሉ።
የኤርትራ ስደተኞች ትግራይ ውስጥ ይኖራሉ ተብሎ ለሚነሳው ጉዳይ ትግራይ ውስጥ አራት ካምፕ ይገኛል። ሁለቱ ካምፖች በኢትዮጰያና ኤርትራ ደንበር በ20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው። ከዓለም የስደተኞች ተቋም መስፈርት ውጪ የተሰሩ ናቸው። የስደተኛ ካምፕ መሰራት ያለበት ከድንበር አካባቢ ከሃምሳ ኪሎሜትር በላይ ርቆ ነው። እነዚህ ካምፖች መስፈርቱን የጠበቁ እንዲሆኑ የዛሬ ዓመት ገደማ፣ ከጦርነቱ በፊት ፣ ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ካምፑ ይነሳና ምቹ ወደሆነ አካባቢ ይሁን የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር።
ለዚህ ምክንያቱም ሁለት ጉዳይ ነበር ። አንደኛው በካምፑ ውስጥ የኤርትራ ተቃዋሚ እየተባለ የሚሰራ ስራ ስላለ የኤርትራ መንግሥት እኛ ተቃዋሚዎችን መልሰን ስናበቃ እናንተ ታደራጃላችሁ የሚል ጥያቄ በማቅረቡ ለቁጥጥር ስላልተመቸን ካምፑ ይነሳ አልን። በርግጥ ይህን ሲያደርግ የነበረው ጁንታው እንጂ እኛ አልነበርንም።
ሁለተኛው ምክንያት በኤርትራ ስደተኞች ስም በርካታ የትግራይ ወጣቶች ኤርትራዊ ናቸው እየተባለ እንደስደተኛ ወደ ውጪ ሀገር እንዲሄዱ መደረጉ ነው። ችግሩን ለመቅረፍ ድርጅቱ ካምፑን እንዲያስጠጋ ተጠይቆ ነበር። ነገር ግን ሳይፈታ ቆይቷል። ችግሩ በተከሰተበት ወቅት በካምፑ የሚገኙ ስደተኞች ወደ የከተማው ተበትነዋል። ስለሆነም ከሰባት ሺህ ስደተኞች በላይ በመሰብሰብ ምቹ ወደሆኑ ካምፖች እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
ድርጅቱን አንድ ሺህ ሰው ሽሬ አካባቢ አግኝተናል የትራንስፖርት ወጪ አግዙን ብለን ስንጠይቅ በጀት የለንም አሉ። እኛ ለስደተኛ ትራንስፖርት ሸፍነንና ለተፈናቀለ አብልተን ስጋት አለኝ ብሎ መጻፍ ትርጉም የለውም። ስደተኛ ከኤርትራም ይሁን ከየትኛው ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ባለን አቅም አስተምረን ተንከባክበን መያዝ እንጂ የመጉዳት ፍላጎት የለንም።
የተወካዮች ምክር ቤቱ ከለውጡ በኋላ ያወጣው አዋጅ በየትም ዓለም ላይ የሌለ ተራማጅ አዋጅ ነው። በዚህ ሊወቅሱን የሚፈልጉ አካላት ድጋሜ ማሰብ ይኖርባቸዋል። ተሰዶ የሚመጣውን ሰው የምንንከባከበው ከልባችን ነው። ምክንያቱም የእኛም ወንድም እና እህቶች ተሰደው ስለሚኖሩ።
የኤርትራ ሠራዊትን በተመለከተ
የኤርትራ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ ገብቷል ተብሎ የሚነሳው ወሬ በመጀመሪያ ወዳጅም ጠላትም ማወቅ ያለበት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በገዛ ወገኑ ክህደት ተፈፅሞበት ጥፋት ሲካሄድበት የኤርትራ ህዝብና መንግሥት ወደ ኤርትራ የሄዱትን ወታደሮች የተቀበለበትና የያዘበት መንገድ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ውለታ ነው።
የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ማንም አክቲቪስት በሚጽፈው የሚበላሽ ግንኙነት አይደለም። በችግር ቀን ሰው አብሮህ አይቆምም፤ እንኳን ሰው የራስህ ጥላ ጨለማ ሲሆን ይከዳል። ጥላህን የምታየው ብርሃን ሲኖር ነው።
ስለዚህ ወታደሮቻችን ከሞት ሸሽተው ሂደው በችግር ጊዜ የተደረገላቸው እንክብካቤ የኢትዮጰያ ታሪክ አይረሳውም። ይህን እንድንክድ፣ እንድንረሳ፣ እንድንሳደብ የሚፈልጉ ሃይሎች ሞኞች ናቸው፤ አናደርገውም ። የኤርትራን ህዝብና መንግሥት ስላደረገው እንክብካቤ የኢትዮጵያ መንግሥት አመስግኗል።
ከዚያ በኋላ የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው የሚለው ውሸት ነው። እነሱም አያስቡም፣ እኛም በህዝባችን ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴ አንቀበልም። ዘመቻው በግልፅ ከተለዩ ጠላቶቻችን ጋር እንጂ ከህዝባችን ጋር አይደለም።
የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እንቅስቃሴ እያደረገ በእኛ ህዝብ ላይ በማንኛውም መንገድ የሚያደርጋቸውን ጥፋቶች አንቀበልም ። የማንቀበለው የኤርትራ ስለሆነ አይደለም የእኛ ወታደርንም አንቀበልም።
ዘመቻው በግልጽ ከተለዩ ጠላቶቻችን ጋር እንጂ ከህዝባችን ጋር አይደለም። ይህንን በሚመለከት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በተደጋጋሚ ከከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ስንነጋገር ቆይተናል።
የኤርትራ ወታደር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ያለባቸውን አካባቢዎች በሚመለከት የኤርትራ መንግሥት የሚያነሳው መከራከሪያ አለ። ላለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያ ወታደር በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር መካከል የነበረበትን ምሽግ ለቃችሁ ሄዳችኋል፣ የጁንታው ኃይል ላለፉት 20 ዓመታት ከፈጸመብን በተጨማሪ አሁን እንኳን ወደውጊያው እንድንገባ ሮኬት ተኩሶ ጋብዞናል ፣ አሁን ደግሞ እናንተ ይህን ምሽግ ለቃችሁ ወደ መካከለኛው ትግራይ ጠላት ፍለጋ እየሄዳችሁ ስለሆነ እዚያ ስታጠቁት ተገልብጦ ወደ እኛ ሊመጣ ይችላል። የሃገር ደህንነት ስጋት አለብን፤ ለዚህ ብለን ድንበር አካባቢ ያሉትን ቦታዎች ይዘናል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ወታደር ስራውን ጨርሶ ምሽጎቹን የሚቆጣጠር ከሆነ በማግስቱ እኛ እንለቃለን፤ መቆየት አንፈልግም ብለዋል።
ሌላኛው በኤርትራ ወታደሮች የሚፈጸም በደል አለ፣ በዘረፋ ይታማል የሚለውን ጥያቄ ለኤርትራ መንግሥት አቅርበናል፣ ይህንን የኤርትራ መንግሥት በከፍተኛ መንገድ ነው የኮነነው፤ ማንም የእኔ ወታደር በዚህ ጉዳይ የሚሳተፍ ካለ እርምጃ እወስዳለሁም ብሏል።
ህግ የማስከበሩን ስራ ጨርሰን ድንበሮቻችንን መከላከል ወደምንችልበት ደረጃ ስንደርስ ይኸ ጉዳይ ይቋጫል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ከኤርትራ መንግሥት ጋር የምንነጋገርበት መድረክ እያመቻቸን ነውና እንወያይበታለን። መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች በፍጥነት ማስተካከል ያስፈልጋል። ግን ለደህንነቴ ስጋት አለብኝና መንግሥት ዋስትና ይስጠኝ ባሉት ጉዳይ ላይ ዛሬ ልንሰጥ አልቻልንም፣ ለምን ከኋላ የሚወጋን ሃይል ስላለ። ከኋላ የሚወጋንን ሃይል ካስተካከልን በኋላ የቀረውን ስራ እንሰራለን።
ብዙ የወደመ ነገር ስላለ ወታደሩ በነበረው ቁመናና ሲሰራ በነበረው ሁኔታ አሁን እንዲሰራ ለማድረግ ተጨማሪ የዓመታት ስራዎች ያስፈልጋሉ። ይኸን የትግራይ ህዝብ መደገፍና መገንዘብ ይገባዋል። የኤርትራ መንግሥት በግልጽ የተናገረው የእኔ የወደፊት እጣ ፈንታ ከኢትዮጵያና ከትግራይ ህዝብ ጋር የተሳሰረ ነው ፤ አላስፈላጊ ቁርሾ መፍጠር አልፈልግም ፤የሚፈጥሩ ግለሰቦች ካሉ አጥንቼ እርምጃ እወስዳለሁ ባለው መሰረት በኤርትራ በኩል የሚጠፋውን ጥፋት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተነጋግረን ማስተካከያ እንዲደረግ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ የሚጠፋውን የኢትዮጵያ መከላከያ ማስተካከያ እንዲያደርግ እናደርጋለን። ይህም የምናደርገው በህዝባችን ላይ ጥፋት እንዲፈጸም ስለማንፈልግ ነው። ያሉት ችግሮች በቁንጽል የሚታዩ ከሆነ ግን መፍትሄ አይመጣም።
የአማራ ልዩ ሀይልን በተመለከተ
ከአማራ ልዩ ሃይል ጋር ተያይዞ ሰፋፊ ጉዳዮች ይነሳሉ ። የአማራ ልዩ ሃይል በትግራይ የህግ ማስከበሩ ስራ ከተጀመረ በኋላ መሬቴን ላስመልስ ብሎ ተደራጅቶ ውጊያ እንደገጠመ ለማስመሰል የሚፈልጉ በርካታ ኃይሎች አሉ፣ ይህ ስህተት ነው። የአማራ ልዩ ኃይል በህግ ማስከበሩ ዘመቻ የተሳተፈው በፈዴራል መንግሥት በተደረገለት ግብዣ ነው። የአማራ ልዩ ሃይል ያጠፋው ጥፋት ካለ ታይቶ በህግ ይዳኛል፤ ለጊዜው ግን ልክ ከሌላ ሀገር እንደመጣ ማየት ተገቢ አይደለም። ኢትዮጵያን ማገልገል ግዴታው ስለሆነ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ማገልገል ግዴታው ነው።
አሁን ያለውን ዓለም ለሚገነዘብ በትግራይ ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር፣ ትግራይን በራሷ ልጆች ማስተዳደር፣ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ህግ መሠረት ተግባብቶና ተዋዶ አብሮ ማደግ ብቻ ነው። ከዛ ውጭ ሰው ሊገደል ይችላል፣ ጉዳዩ ሊያደክም ይችላል ግን የትም አያደርስም። ትርጉምም የለውም።
ከለውጡ በኋላ ሸሽተው መቀሌ ሲገቡ ትልቅ ስህተት ተሳሳቱ። ቀጥሎ ብልጽግና እየለመናቸው ከብልጽግና ጋር አልቀጥልም ሲሉ ደግሞ በሌላ ስህተት ተሳሳቱ። ቀጥለው ደግሞ የማይነካውን ቀይ መስመር አልፈው ሰሜን ዕዝን ሲመቱ ሦስተኛ ስህተት ሰሩ ፤ ሦስት ጊዜም ሳይነቁ የአሁን ደግሞ ሽምቅ አራተኛ ስህተት ነው ።
አንዴ የስህተት መንገድ ከጀመርክ ማቆሚያ የለውም። አያዋጣምና ህዝቡ በፍጥነት ከዚህ ስህተት መውጣት አለበት። እየተጎዳ ያለው የትግራይ ህዝብ ነው። የእነሱ የተሳሳተ እሳቤና ስልት ምንድነው የነበረው ፣ ውጊያውን ጎንደር እናደርገዋለን ምናምን የሚል ነው፣ ጎንደርስ ቢካሄድ ሰው ነው የሚጠፋው። ውጊያ በኢትዮጵያ እስካለ ድረስ የሚያጠፋው ኢትዮጵያዊያንን ነው። ስለሆነም አይጠቅምምና በፍጥነት ተረባርበን የትግራይን ክልል እንድናደራጅና ህዝባችንን ካለበት መከራና ችግር እንድናወጣ ያስፈልጋል።
እኛ የምንፈልገው ከአሥር እና ከአስራ አምስት ሰው አይበልጥም። ለአስራ አምስት ሰው ተብሎ ክልል መታመስ የለበትም። እነሱን ለህግ በማቅረብ ለተቀረው ሚሊሺያ ምናምን ምህረት ይደረግለታል። ወደ አገሩ ገብቶ ሥራውን መስራትና በፍጥነት ክልሉን ማደራጀት ነው የሚያስፈልገው። እኛ ሁሉንም ሰው የማሰርም ሆነ የመጠየቅ ፍላጎት የለንም። የትግራይ ህዝብ ይህን ተገንዝቦ በፍጥነት ወደ ሰላሙ እና ክልል ወደ ማደራጀት እንድንገባ ድጋፍ ቢያደርግ መልካም ነው። በየቦታው ያላችሁ የትግራይ ሰዎች ግዴታ የለባችሁምና እኛን አትውደዱን ግን ትግራይን እንድናደራጅ ተባባሪ ብትሆኑ በጣም ጥሩ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
ሱዳንን በተመለከተ
የሱዳን ህዝብ ወንድም ህዝብ ነው። በኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር የቆመ ህዝብ ነው። አሁንም ኢትዮጵያን የሚወድ ህዝብ ነው። እኛ ጦርነት የማንፈልገው ከኤርትራ ተምረን ነው። ከኤርትራ ጋር ተጣላን፣ ተዋጋን በመቶ ሺዎች ገደልንና መጨረሻ ላይ ጉዳዩን የተባበሩት መንግሥታት ወስዶት የምታውቁት ነው የሆነው። አሁንም ብንገዳደል የሆነ ጊዜ አቁሙ ተብሎ ሌላ ኃይል መግባቱ አይቀርም። የሱዳናዊውም ሆነ የኢትዮጵያዊው ሞት ኪሳራ ነው።
ሱዳን አሁን ባለችበት ሁኔታ ከጎረቤት አገር ጋር ለመዋጋት የሚያስችል ነገር ላይ አይደለችም ፤ በጣም ብዙ ችግር አለባት። ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታም ከሱዳን ጋር ለመዋጋት ብዙ ችግር አለባት። ስለሆነም ጦርነት ለሁለታችንም አያስፈልገንም። ችግሮችን በሰላም በንግግር መፍታት ነው የሚሻለው። ያ ተጀምሯል ይፈታል ብዬም አስባለሁ።
ከሱዳን ጋር ያለው ጉዳዩ የቆየ ነው። በ1902 በአፄ ምንሊክና በእንግሊዝ ሰዎች መካከል የተደረገ ድርድር ነው የወሰን ማካለል ጉዳይ ነው ። ሱዳን ነጻ ሳትወጣ
በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ 1950ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ላይ መለስተኛ ንግግሮች ተደርገዋል። በመርህ ደረጃ ይህን ተቀብለን እናስተካክላለን በሚል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በንግግር ያለ ጉዳይ ነው። እንደተባለው በእኛ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ኮሚቴ በእነሱ በኩልም ሚኒስትሪያል ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ ጀምረን ነበር፣ ላለፈው አንድ ዓመት ምናምን ገደማም ሄደንበታል ።
በሰላም ማስከበር ዘመቻው ወቅት የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ ገብቷል፤ ወደማይገባ ነገርም ሄዷል። እኛ ለዛ የሰጠነው ምላሽ በሁለቱ ህዝብ መካከል ውጊያ አያስፈልግምና በንግግር በውይይት እንፍታው የሚል ነው። እንፍታው ስንል ግን የእኛ አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል፣ማሳቸው ተቃጥሏል፣ ቤታቸው ተቃጥሏል በደል ደርሶብናል ያም ሆኖ ውጊያ ስለማይጠቅመን አንዋጋ እያልን ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሱዳን ከሌሎቹ ጋር ወዳጅነት ፈጠረች ለተባለው ሱዳን ከኢንዶኔዥያ፣ ከባርባዶስ፣ ከሲሼልስ፣ ከቡልጋሪያ ጋር ወዳጅ መሆን ትችላለች። የኢትዮጵያ ጠላት መሆን ግን አትችልም። ሱዳን የሚለው ቃል በዓረብኛና ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በግሪክኛ አንድ ነው ትርጉሙ። አንድ ህዝብ ነን። የትም አገር ሄዳችሁ ሱዳናዊ ብታዩ በአማርኛ ነው የምታወሩት።
ኑቢያ ነው፤ ኢትዮጵያን ከሱዳን መለየት አይቻልም። ሌላ ጋር ወዳጅ መሆን ግን ይቻላል፤ ችግር የለውም። እኛም ከሌላ ጋር ወዳጅ መሆን እንችላለን ሱዳንን ጠላት ማድረግ ግን አንችልም። በብዙ ነገር አንድ ህዝቦች ነን ተዋደን ተከባብረን አብረን የኖርንና ወደፊትም አብረን የምንኖር።የወዳጅነት ችግር የለብንም። ከማንም መወዳጀት ይቻላል። ያ ወዳጅነት ኢትዮጵያን ጠላት ለማድረግ ከሆነ ግን አንድ ህዝብ የሚለይ ስለሆነ አይጠቅምም ዋጋም የለውም።
ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ
ህዳሴን በሚመለከት ህዳሴ ዘርፈ ብዙ የሆነ ችግር ያለበት ነው። በገንዘብ ሆነ በዲፕሎማሲ ያለው በጣም በስፋት የሚነሳ ነው። በየጊዜው የሚነሱና የማያቋርጡ ችግሮች ጀርባቸው ሲፈተሽ ሄዶ ሄዶ ህዳሴ አለበት። የኢትዮጵያን አቋም ግልጽ ለማድረግ ኢትዮጵያ ግብጽን የመጉዳት ፍላጎት ፈጽሞ የላትም። ኢትዮጵያ ሱዳንን የመጉዳት ፍላጎትም ፈጽሞ የላትም። ኢትዮጵያ እነሱ ሳይጎዱ መጠቀም ነው የምትፈልገው።
በዛኛው በኩል ያሉ ወንድሞቻችን እንዲገነዘቡ የምንፈልገው እኛ ጨለማ ውስጥ መኖር አንፈልግም። አምፖል ነው የምንፈልገው። የእኛ ብርሃን ወደ እነሱ ይጋባ ይሆናል እንጂ አይጎዳቸውም። ከአባይ ጋም ተያይዞ ለሚነሱ መከራከሪያ ሀሳቦች ዓባይ ወደ ካርቱም ሄዶ ናይል ከሚባለው ውሃ ጋር የሚቀላቀለው ከሰማንያ አምስት በላይ ገባር የውሀ አካላት ያለው ነው ።
የተከበረው ምክር ቤት ሊገነዘብ የሚያስፈልገው የኢትዮጵያ መንግሥት የዓባይን ውሃ ባለፈውም አልገደበም በሚቀጥለው ክረምትም አይገድብም። የተከለከልነው ዝናብ አትገድቡ ተብለን ነው። የዓባይን ውሃ ብንገድብማ አሁን ዛሬ እንገድብ ነበር፤ ዓባይ እኮ ዛሬም እየፈሰሰ ነው።
ከጣና የሚሄደው ውሃ ባለፈው ወር ነበር፣ የዛሬ ሦስት ወር ነበር አልነካነውም እኛ እኮ የምንለው ክረምት ላይ ዝናብ ሲዘንብ ከሚዘንበው ዝናብ ቢበዛ አምስት ከመቶ እንጠቀም ነው። እናስቀር ብንልም አንችልም ማስቀረት በጣም ብዙ ስለሆነ። ዝናብም አትጠቀሙ ማለት ይህ ትንሽ ይከብዳል።
ብዙ ጊዜ ሲነገር ዓባይ ተገደበ ይባላል። አልገደብንም እንዳትሳሳቱ። ዓባይ ከጣና የሚወጣው ዓመቱን ሙሉ ሁሌ እንደፈሰሰ ነው።በክረምት ወራት ግን ከሁሉም ተፋሰስ የሚፈሰው ውሃ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ከእርሱ ትንሽዬ ለማስቀረት ነው ጥረት ያደረግነው። ጣናን አትጠቀሙ ተብለን፣ ዝናብ አትጠቀሙ ተብለን እኛ ታዲያ እንዴት እንሁን። አሁን ደግሞ ደመና እያዘነብን ነው እሱንም ካልተጠቀምን ችግር ነው። እና ህዳሴን ስንሰራ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የለንም። እንዲያውም ኢነርጂ ላይ አብረን ኢንቨስት ብናደርግ ጥሩ ነው ።
ኢትዮጵያ ለኢነርጂ ልማት ጥልቅ አቅም ያላት ሀገር ነች። ኢነርጂ ላይ አብረን ኢንቨስት እያደረግን እርሻ ላይ ደግሞ ከሱዳን ጋር ኢንቨስት እያደረግን አብረን ብናድግ ጥሩ ነው። እኛ ፍላጎታችን አብረን ማደግ ብቻ ነው። በቴክኒክም በገንዘብም ብዙ እየተፈተንባቸው ያሉ ጉዳዮች ቢኖሩትም ህዳሴ ግድቡን ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል በገባነው መሰረት እናሳካዋለን። ይህ የሚታጠፍ ሀሳብ አይደለም።
በሚቀጥለው ክረምት ውሃ አያያዝ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ውሃ እንዴት እንደሚሞላ ሳትፈርም ውሃ ባትይዝ የሚል ጥያቄ ይነሳል። አትፈርምም እየተባለ እንደሚነገር አውቃለሁ። የግብጽና የሱዳን መንግሥት ዝግጁ ከሆኑ ውሃ አሞላልን በሚመለከት ኢትዮጵያ ነገ ጠዋት ለመፈረም ዝግጁ ናት። እኛ ውሃ የምንይዘው በህግ ነው። በሚታወቅ ስርዓት ነው ውሃ የምንይዘው።
ነገር ግን ውሃ አሞላሉንና ኦፕሬሽኑን አንድ ላይ እንነጋገር ከተባለጊዜ ስለሚወስድ በዚህ ውስጥም የሚያከራክር ጉዳይ ስላለ የዘንድሮ ክረምት ያልፋል። የተከበሩ የግብጽ ወንድሞቻችን እንዲገነዘቡ የምንፈልገው የዘንድሮ ክረምት ማለፍ ማለት አንድ ቢሊዮን ዶላር እናጣለን ማለት እነደሆነ ነው። ይህንን ከየት አባቴ አመጣዋለሁ። በትግራይ አንድ ቢሊዮን ዶላር አጥፍቼ እንደገና ደግሞ እዚህ ውሃ ባለመያዝ አይመችም፤ አይቻልም እሱ አስቸጋሪ ነው። እናም ውሃውን እንይዛለን ውሃ ከመያዛችን በፊት የሚደረግ ድርድር ካለም ዝግጁ ነን።
ወንድሞቻችን እንዲጎዱ ስለማንፈልግ ውሃ ስንይዝ እነሱን በማይጎዳ መልኩ መሆኑን ደግሞ እርግጠኛ ሆነን እንሰራለን። ስድስት ቢሊዮን ዛፍ እንተክላለን እሱም ዝናብ ይጨምራል። ይሄ ደመና ማዝነብ ቅድም አነሳሁላችሁ እንጂ ሁለት ቴክኒክ ነው ያለው። አንደኛው ከምድር ወደ ሰማይ በሚተኮስ ጨዋማ ንጥረ ነገር ነው የሚዘንበው። ሁለተኛው አየር ከደመና በታች በማብረር እነዛን ነገሮች በመርጨት ነው ዝናብ የሚዘንበው። በጣም የሚገርማችሁ በቴክኖሎጂው ዝናብ በዘነበ ቁጥር የደመና ቁጥር ያድጋል። ስለዘነበ የሚጠፋ እንዳይመስላችሁ።
እና ኢትዮጵያ ውስጥ ዝናብ እየበዛ ይሄዳል። በዚህም የእኛ ጎረቤቶች ሁሉም በቂ ውሃ ያገኛሉ፣ በቂ ውሃ እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ህዝብ በነጻ ችግኝ ተክሎ እየሰራ ነው። እኛም ደግሞ እንድንለማ እነሱም ትብብር እንዲያደርጉልን በሰላም ብቻ ጉዳዩን እንዲያዩት መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ህዳሴን በሚመለከት ግን የፈለገው ፈታኝ ነገር ቢኖር በተገባው ቃል መሰረት የሚፈጸም ይሆናል።
ምርጫን በተመለከተ
ምርጫን በሚመለከት የዘንድሮው ምርጫ በመደበኛ ሁኔታ የሚካሄድ አይደለም። ቅድም እንዳነሳችሁት አንደኛ ሶሻል ሚዲያ የሚባል ነገር አለ። እኔ እንኳን ወደ እዚህ ቢሮ ስመጣ ከ270 በላይ ብሎገሮች ተዘግተው ነበር። አሁን ሁሉም ክፍት ነው። ክፍት ብቻ ሳይሆን ቀላቢም አለው። ለእነዚህ ኃይሎች የሚቀልብ ብዙ ሰው አለ። የፖለቲካ ምህዳሩም እንደምታውቁት በንጽጽር ሰፍቷል። ድሮ የምናውቀው አይነት ነገር አይደለም ያለው። ቅድም እንዳነሳነው የትርክት መራራቅም አለ። በእነዚህ ምክንያቶች የሚቀጥለው ምርጫ በጣም ወሳኝ፣ ነገር ግን ፈታኝ ነው።
በዚህ ምርጫ ለመወዳደር ፈልገው ዝግጅት እያላቸው የሚወጡ ፓርቲዎችን በሚመለከት መንግሥት ከግማሽ መንገድ በላይ ሄዶ አነጋግሯል፤ ለምኗል፤ ደግፏል። አንወዳደርም ያሉ ፓርቲዎችን እኔ አነጋግሬያቸዋለሁ። አስፈላጊውን ድጋፍ እናድርግላችሁ ተወዳደሩ እንዳትወጡ ብለናቸዋል ፤ ሽማግሌም ልከንባቸዋል። ታስታውሱ እንደሆነ ሊወጡ የሚያስቡ ኃይሎች አሉ ብዬ ነግሬያችኋለሁ።
እንዳይወጡ ለምነናል። ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ ኦፌኮ እናግዛችሁ ተወዳደሩ ብዬ እንዳይወጡ እኔ አናግሬያቸዋለሁ። አሁን በቅርቡ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበዋል። ምርጫ ቦርድ የእነዚህን ፓርቲዎች ጥያቄ ይቀበላል የሚል ተስፋ አለኝ። ማድረግ አለበት ብዬም አምናለሁ።
ማንም የፖለቲካ ፓርቲ ሊወዳደር ፍላጎት ካለው ደግፈን አግዘን እንዲወዳደር ማድረግ አለብን። የሆነ ህግ ጠቅሰን ከመግፋት ህጉን ከፍተን ማስገባት እንደሚሻል በጽኑ አምናለሁ። ምርጫ ቦርድም ይህን እንደሚያደርግ ተስፋ አለኝ።
የዚህ ምርጫ ዋነኛ ዓላማ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ ሁሉም ፓርቲዎች በእኩል የሚወዳደሩበት ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት ነው። በዚህም ዓላማችን ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ብንሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ እንኳን ደስ አለህ የሚል ቃል አሁን ካለው መንግሥት ተሰምቶ የስልጣን ሽግግር የሚደረግባት ኢትዮጵያን ማየት ነው።
ብናሸንፍ በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲሆንና ኮሮጆ ላለመስረቅና እንቅፋት ላለመሆን በመቶ ሺዎች የእኛነድ ካድሬዎች አሰልጥነናል። የእኛ ድል ምርጫውን ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን ማድረግ ነው። ያው ድሮም ስለነበርን እናውቀዋለንና ብዙ ሙከራ እየተደረገ ነው። ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ይሆናል የሚል ተስፋ አለን።
ዴሞክራሲን በሚመለከት ዴሞክራሲ እኛ ጋር አበበና አደገ የሚሉ አገራትንም መለስ ብሎ ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል። ዴሞክራሲ የሂደትና የባህል ለውጥ ውጤት ነው። የአንድ ምርጫ ውጤት አይደለም። አንድ ምርጫ ምንም ያክል የጠራ ቢሆን ዴሞክራሲን በተሟላ መልኩ አያረጋግጥም። ምርጫ ግን ዴሞክራሲ እንዲፈጠር ዋና መሰረት ነው። ለምሳሌ አሜሪካኖች ሲጠየቁ 300 ዓመት የቆየ ዴሞክራሲ አለን ይላሉ። በንድፈሀሳብና በስነጽሁፋቸው ።
አሜሪካ ሀገር ውስጥ ለ150 ዓመታት ሴቶች ለመምረጥ አይፈቀድላቸውም ነበር። ከተፈቀደላቸውም በኋላ ለመምረጥ ሳይሆን ለመመረጥ ደግሞ 250 ዓመት አስፈልጓቸው ነበር።
በእኛም ሀገር ሁሉም ነገር በአንድ ጀምበር እንደማይሆን የእነዚህ ሀገራት ታሪክ ያሳያል። በሂደት ግን እየዳበረ እየዳበረ የተሻለ ዴሞክራሲ ይኖራል የሚል እምነት አለ፤ በአንድ ምርጫ ሁሉን መመለስ ባይቻልም። እንደተባለው እርቅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ኢትዮጵያውያን ይቅር መባባል አለብን። የትላንትናውን ረስተን የበለፀገች ሀገር መፍጠርም ያስፈልጋል።
ለዚህ የእርቅ ኮሚሽን፣ የሰላም ሚኒስቴር ፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰፋፊ ጥረቶች እያደረጉ ነው። ይሄን ደግፈን የተሸከምናቸውን ወደ ኋላ የሚጎትቱን ጥለን ይቅር ተባብለን ተስማምተን ወደፊት መራመድ ያስፈልጋል። ሀሳቡም ትክክል ነው፤ ስራውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። እንግዲህ እናንተም እንዳነሳችሁት ህዝቡም እንደሚለው ትእግስት በዛ እርምጃ የማይወስድ መንግሥት ነው የሚል ወቀሳ ከኢትዮጵያ ጫፍ ጫፍ ሲስተናገድ ነው የመጣው።
የገጠመን ፈተና ከፓርቲዎች አንፃር የልምድ ጉዳይ ነው። ፓርቲዎች የለመዱት ምርጫ ማጀብ ነው እንጂ በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ አይደለም። የህወሓትን ምርጫ ሲያጅብ የነበረ ሁሉ ዛሬ ላይ በምርጫ አልወዳደርም ቢል የምርጫ አጃቢነት ስላለበት እንጂ የዘንድሮው ምርጫ በምንም መመዘኛ ካለፈው ምርጫ ስለሚያንስ አይደለም። የለመደ አመል ከገዳም ያስወጣል እንደሚባለው የልምድ ጉዳይ ሆኖ እንጂ።
በሩጫ ውስጥ የሚያሯሩጡና የሚሮጡ ሰዎች አሉ። አሯሯጭ የሚከፈለው ስላሯሯጠ ብቻ ነው፤ ማሸነፍ የእሱ ግብ አይደለም። ዓላማው አሸናፊውን ሰው በተሻለ ፍጥነት እንዲገባ ማድረግ ነው። ስለሆነም አሯሯጮች እኛ ሩጫ አልለመደብንም ቢሉም የልምድ ጉዳይ እንጂ ለውድድር አሁን ያለው ጊዜ ድሮ ከነበረው ስለሚያንስ አይደለም።
ኦሮሞና አማራ ተጣልተዋል እንትና ሞቷል ቢባልና የፈለገም ቢሆን ምርጫው ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ አድርጎ የሚፈልገውን መንግሥት መርጦ አሁን ካለበት ጣጣ ወጥቶ ወደፊት መሄድ አለበት።
እነዚህ ሰዎች ምርጫ እናድርግ ሲባል አይ ምርጫ መደረግ የለበትም፤ ምርጫ ይቅር ሲባል አይ የሽግግር መንግሥት እንፍጠር ይላሉ። እንደዚህ አይነት አጭበርባሪነት እስከመቼ ይቀጥላል። ምርጫ መደረግ አለበት በዚህም ህዝቡ የራሱን መሪ፣ የፈለገውን ይመርጣል። ከተመረጠ በኋላ ያ መንግሥት ማስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች አስተካክሎ ሀገር ያለማል።
ዝም ብሎ እየተድበሰበስን መቀጠል አስቸጋሪ ነው። በውስጥም በውጭም ብዙ መከራ እያመጣ ያለውም ይሄ ነው። ብዙ መታረም ያለባቸው ጉዳዮች አሉና በምርጫ ህዝቡ ከመረጠ በኋላ ጉዳዮቹ ይታረማሉ።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግን በህፃናት ጫወታ መስለን ብናየው ፤ ህፃናት ተስማምተው ጨዋታ ከጀመሩ በኋላ አንደኛው ህፃን እንደሚሸነፍ ሲያውቅ የገነቡትን ቤት ፍርስርስ ያደርጋል፤ እናም ሌላኛው ህፃን እፍርታም ይለዋል። እነዚህ እፍርታም የፖለቲካ ሰዎች ናቸው ጫወታ የሚያበላሹት።
እፍርታም ፖለቲከኞች ቶሎ ብለው ወደ መርጫ ገብተው ምርጫ ቦርድ አግዟቸው የተሻለ ምርጫ እንድናካሂድ ማገዝ አለባቸው። በምርጫ መወዳደር በራሱ ትልቅ ድል ነው ብለው መቀበልም አለባቸው። እኛ ግን በተደጋጋሚ እንዳልኩት ሁለቴ አናስብም ከተመረጥን በንፅህና እናገለግላለን ካልተመረጥንም ለቀን እንሄዳለን።
እናግዝ እያልን በሰበብ በአስባቡ መውጣት ግን ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ይገድላል፤ የሚጠቅምም አይደለም። አንዳንዶች እዚህ አንወዳደርም ካሉ በኋላ ልክ ሰዎች አዘውን ምርጫ እንደምናደርግ ወይም አዘውን ምርጫ እንደምናቆም ሰዎች ጋር ለአቤቱታ ይሄዳሉ። እንደዛ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደረግም። ምርጫውን በተሻለ መጠን ዴሞክራሲያዊ አድርገን ብንጠቀምበት ይሻላል።
ወሰንን በተመለከተ
ወሰንን በሚመለከት ብቻ ሳይሆን ድንበርንም አልፈታንም። ቅኝ ገዥዎች ባሰመሩት የድንበር መስመር ግማሹ ኦሮሞ ኬንያ ግማሹ ኢትዮጵያ፤ ግማሹ ሶማሌ ጅቡቲ ግማሹ ኢትዮጵያ ወዘተ የከተተ ነው። ለሰላም ሲባል ነው የሚኖረው እንጂ ችግር አለበት። ትክክለኛ መስመር አይደለም። የወሰንም ችግር አለ ፤ወሰንን ከከለልን ገና 30 ዓመታችን ነው። ስለሆነም ችግሩን ቀስ እያልን እየፈታን እንሄዳለን ። መሬቱ ተቆርሶ አይሄድም። የት ይሄዳል? ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው።
ስለሆነም ቀስ እያልን በተረጋጋ መንፈስ እየፈታን መሄድ ያስፈልጋል፤ ችግሩ ሁሉም ጋር አለ። ደቡብ ክልል ውስጥ ከዞን ዞን ብዙ ጥያቄ አለ፤ በክልል ደረጃ፣ በወረዳ ደረጃ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፣ ኦሮሚያ ውስጥ በከተማና በአጎራባች ቀበሌዎች ይነሳል። ኦሮሚያ ውስጥ በከተማና በገጠር ቀበሌዎች መካከል ይነሳል። በአጠቃላይ የወሰን ጉዳይን ቀስ ብለን እየተረጋጋንና በህግ አግባብ እየፈታን ብንሄድ ነው የሚጠቅመን።
ግጭቶችን በተመለከተ
መተከል ላይ በርካታ ስራዎች ሰርተናል፤ በጣም ብዙ ውይይቶች ስናካሂድ ነበር ። 81ሺ አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው መልሰናል ፣ 3 ሺ200 የታጠቁ ሰዎች በድርድር ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ አድርገናል ፣ ከ10ሺ በላይ ሚልሺያ አሰልጥነናል፤ ከ183 ቀበሌዎች 170ዎቹን በአዲስ መልክ አደራጅተናል። አሁንም ይቀራል ተፈናቅለው ያልተመለሱ አርሶ አደሮችና ቤታቸው የተቃጠለባቸው አሉ።
አሁንም ሰፊ ጥረትና ስራ እንዲሁም እርቅ እና ስምምነት ማድረግ ይፈልጋል። እሱን እየሰራን ነው፤ ማጠናከር ይፈልጋል። አሁንም ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ እዚያም ሁኔታዎች እንዲበላሽ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ ። ነቅተን ተባብረን የብሄርና ምናምን ጉዳይ ሳናነሳ እንደ አንድ ህዝብ ሆነን ነገርየውን በሂደት ማረም፣ ማስተካከል ያስፈልጋል።
ከከሚሴ ጋር በተያያዘ ትላንት ሙሉ ቀን ማታም እስከ ምሽት ብዙ ሰዓት በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ስንነጋገር ነበር። የከሚሴ አካባቢ የኦሮሚኛ ተናጋሪዎችን ስታገኝ በቃ ኦሮሞዎች አለቁ፤ የአማራ ልዩ ኃይል ጨፈጨፋቸው የሚል ሪፖርት ነው የሚመጣው። የአማራው ሰው ደግሞ ሪፖርት ሲያደርግ ሸኔ የሚባል ኃይል ጨፈጨፈ ነው የሚለው።
እኔ የመለስኩላቸው የከሚሴ ህዝብ የወሎ ህዝብ ነው የወሎን ህዝብ አይጨፈጭፍም፤ የወሎ ህዝብም አይጨፈጭፈውም፤ ወንድሙ ነው። መሀል እየገባን የምናባላው እኛ ነን። ህዝቡ ህዝቡ እኛ ሳንፈጠርም ነበር፣ ወደፊትም ይኖራል። በዚህ ሂደት የደበደበ ያቆሰለ ካለ በህግ ይጠየቃል። ነገር እንዳይፋፋም እንስራ፤ አናባብሰው፤ ጥሩ አይደለም። ለወሎ ህዝብ ከከሚሴ በላይ በእምነትም በባህልም በታሪክም የሚቀርበው የለም፤ ከሚሴም እንደዚሁ። ከሚሴ ከወሎ ውጭ ግንጥል ጌጥ ነው።
እነዚህ አንድ ህዝቦች ናቸው፤ በሰከነ መንገድ ሁለቱም ጋር ሰው እንዳይጎዳና ክፍፍል እንዳይፈጠር አንድ ሆነው ተከባብረው ወደ ልማት እንዲሄዱ ማድረግ ነው የሚጠበቅብን። ልዩ ኃይልም የራሱ ህዝብ ነው፤ የራሱን ህዝብ መጨፍጨፍ እንዴት ያደርገዋል። ከጭፍጨፋ በኋላ እኮ መልሶ የአማራ ክልል ነው። እንደዚህ አይነት በጣም ወደጫፍ የሄደ ነገር ሰከን ብሎ ማየት ጠቃሚ ይሆናል። ጠቃሚ የሚሆነው በስክነት ሞት መቀነስ ስለሚቻል ነው። በእያንዳንዱ ሞት ውስጥ በትክክል ያለውና የሚነገረው ይጋነናል።
ሰው የራሱ ብቻ ጠበቃ ሆኖ ስለሚቆም ትግራይ ስትሄዱ ጉሙዝ ስትሄዱ በየቦታው እንደዛ ነው ይህ አይጠቅመንም፣ ሰላም እና የጋራ ልማት ያስፈልጋል። በኦሮሞና በአማራ መካከል ወሎም ይሁን ወለጋ ሸዋም ይሁን ጎጃም ግጭት ካለ ጠላት ይጠቀማል እንጂ ኦሮሞም አማራም አይጠቀምም። ይህን አስቦ በትብብርና በሰከነ መንገድ ማየት ይሻለናል።
እባካችሁ በዘር መባላት ፣ በእምነት መባላት አይመጥነንም ፤ ታሪካችን አይደለም፤ አይፈቅድልንም ። ጥፋት ያስከትላል ለጠላቶቻችን ሲሳይ ያደርገናል፤ ጥንቃቄ እናርግ። ይህን የምታራግቡም ኃይሎች እባካችሁ ኢትዮጵያን በማባላት ጥቅም አታገኙም። ሰክናችሁ ለማየት ሞክሩ። ተነስ አማራ ተነስ ኦሮሞ የምትሉ ኃይሎች ጥንቃቄ አድርጉ።
እነዚህ ህዝቦች ተነስተው ቢባሉ ትልቅ ጥፋት ይፈጠራል፣ ጥቅም የለውም። በሰከነ መንገድ ማየት ግን ለሁሉ ይበጃል። መንግሥት አስፈላጊውንና የሚችለውን ሁሉ ከህዝቡ ጋር ሆኖ ያደርጋል። ችግር የሆነብን ግን እዚም እሳት እዚያም እሳት እሳት እያጠፋን መቼ ነው ሌላውን ስራ የምንሰራው የሚለው ነው።
በየአካባቢው እያንዳንዱ ዜጋ ሰላምን ለማምጣት ፣ችግር እንዳይፈጠር ተባብሮ መስራት ይኖርበታል ። እኛ አንድ ሚልዮን ጦር የለንም። ያለንን ጦር ሁሉ ቦታ ልንበትነው አንችልም። ይህን ታሳቢ ያደረገ ስራ እንሰራለን እናንተም ደጋፊ ሁኑ። በከሚሴም በፌዴራልና በክልል ኮሚቴዎች አዋቅረን ልከናል፤ ይረጋጋል ህዝቡ መረጋጋት ያውቅበታል። እኛ ማጋጋሉን ከተውን ይሰክናል። ለነበረው ጥፋት ደግሞ እንደ ጥገፋቱ ልክ ሁሉም በህግ ይጠየቃል ። ነገሩን በሰከነ መንገድ ብናየው ጥሩ ነው።
ልዩ ኃይልን በተመለከተ
የልዩ ኃይልን በሚመለከት ቀደም ብሎ ኮሚቴ ተቋቁሟል፤ ልዩ ኃይል ህገ መንግስታዊ አይደለም። ግን ተቋቁሟል ። የአማራ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሲዳማም ክልል ሆኖ ልዩ ኃይል ላደራጅ እያለ ነው። ከሲዳማ በኋላ ደግሞ ዞኖችና ከሚሴም ልዩ ኃይል ላቋቁም ማለቱ አይቀርም ። ገንዘብ በልዩ ኃይል ፈጅተን እንዴት ነው ብልፅግና የሚመጣው።
እንዴት ነው የሚሆነው ለሚለው ጥናት ከተጠና በኋላ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለውን አይተን በህግ አግባብ ማስተካከያ ይደረጋል። ኃይሉን አንበትነውም፤ ኃይሉን የምንጠቀምበትን መንገድ ግን ጥናቱ የሚያመጣውን ውጤት አይተን እንወስናለን። አስፈላጊ ነው የሚለውንና ከልክ በላይ ተለጥጦ እንዳይሄድ ሁሉንም በህግ አግባብ ማየትና በሰከነ መንገድ መሄድ ነው ለኢትዮጵያ የሚበጃት።
ነገር ሲሰበሰብና ሲደመር ብዙ ግጭትና ግድያ ብዙ ክፉ ዜና አለ፤ በየቀኑ እንቅልፍ የሚነሱ በርካታ ነገሮች አሉ። በሌላ መንገድ ብዙ ጥሩ ዜናና ብልፅግና አለ። እንተባበር እንደመር፣ እንተጋገዝ የኢትዮጵያ መለወጥና ማደግ የሚጎዳው ኢትዮጵያዊ የለም። የኢትዮጵያ ውርደት ግን አንተ የትም ብትሆን ያዋርድሃል። እዚህ ባትኖርም። ብቻህን ሀብታም ብትሆን የድሀ ሀገር ህዝብ ተብለህ ትዋረዳለህ። ተባብረን ወደ ሰላምና ልማት እንሂድ።
ይሄንን በማድረግ ችግሮቻችንን ማርገብና መቀነስ እንችላለን የሚል ተስፋ አለኝ። የተከበረው ምክር ቤትም ከዚህ አንፃር ድጋፉን ቢያደርግ የተሻለ ስራ ለመስራት እድልና ልምድ ተገኝቷል የሚል እምነት አለኝ። በጥቅሉ ያሉትን ችግሮች እየቀነስን መልካም ነገሮች እያስፋፋን የተሻለች ኢትዮጵያን እንፈጥራለን የሚል ተስፋ አለኝ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013