ወርቅነሽ ደምሰው
በርካታ ዜጎች በተለያዩ ዓለማት ካሏቸው የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ በዲያስፖራ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ ሀገራት መካከልም ተጠቃሽ ናት፡፡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ አባላት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ሲሆን ከምንም በፊት ሀገራቸውን የሚያስቀድሙ ሀገር ወዳድና ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡
እነዚህ በባዕድ ሀገር እየኖሩ ዘወትር ሀገራቸውን የሚናፍቁ የዲያስፖራው አባላት ካላቸው የአገር ፍቅር ባሻገር ሁልጊዜ በችግሯ በደስታዋ ለመድረስ የራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ሩቅ ሆነውም ቢሆን ለሀገራቸውን ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ በመስጠት እያንዳንዱን የልማት ስራ በመደገፍ አገር ፈተና ላይ የወደቀች ሲመስላቸውም ከጎን በመቆም አለኝታ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩና እያስመሰከሩ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም ማሳያ ከሆኑት ነገሮች መካከልም ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች እንዲሁም በኮቪዲ- 19 ወረርሽኝ መከላከያ የሚሆን የገንዘብ የግብዓትና የሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ድጋፍ በማድረግ ለሀገር ያላቸውን ፍቅር በተግባር አሳይተዋል እያሳዩም ነው። በኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለሚፈናቀሉ ዜጎች ከሚያደርጉት የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ከወገኖቻቸው ጎን መቆም የቻሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ሆነዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በኢትዮጵያ ላይ የሀሰት ዘመቻ በመክፈት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ጫና በማሳደር ተጽዕኖ ለመፍጠር የሀሰት ክሶችን ሲያቀርቡ የነበሩ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃንን በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ይህንን ያልተገባ ድርጊትና ተግባር ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረግጠው በማስረዳት በሚኖሩባቸው የዓለም አገራት ሁሉ ከፍተኛ የሆነ ጥረትን አድርገው ቀላል የማይባል ውጤትንም ለማስመዝገብ ችለዋል፡፡
እነዚህ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በዓለም አደባባይ ወጥተው ለሀገራቸው ጽምፅ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ በኒውዮርክ፣ በብራስልስ፣ በአውስትራሊያ፣ በጄኔቫ በመሳሳሉት ሀገራት እንዲሁ በአፍሪካ በተለያዩ ቦታዎች በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ይህ አቋማቸው በግልጽ ታይቷል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ያለውን ጣልቃ ገብነት እና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማደናገር በኢትዮጵያ ላይ ህጋዊ ያልሆነ ጫና ለማድረግ የሚሞክሩ ሀይሎችን አውግዘዋል ፡፡
ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎቹ ያደረጓቸው ሰልፎች ምዕራባውያን መንግስታት የሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነቷን ለማስጠበቅ የምትወስደውን እርምጃ ከመደገፍ ባሻገር በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት የለባቸውም የሚሉና በኢትዮጵያውያን መካከል ትብብርና ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ መልዕክት የተላለፉበት እንደነበር ተመልክተናል፡፡
የኢትዮጵያውያኑ ያሳዩት የሀገርና የወገን ፍቅር እጅግ የሚያስደምም ነበር፡፡ ለኢትዮጵያም መጻኢ እድል ብሩህ የተስፋ ብርሃን ያበራም ሆኗል፡፡ በተለይ በሀገራቸው ተስፋ ቆርጠው የነበሩት የዲያስፖራ አባላት የተያዘው የለውጡ መንገድ በሀገራቸው ተስፋ ሰንቀው ከጎኗ እንዲቆሙ እያደረጋቸውም ያመላክታል፡፡ ምንም እንኳን መፍረሷን የሚመኙ አካላት መኖራቸውን እያየን ቢሆንም እውነትን ከተደበቀችበት አንጥረው አውጥተው ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማሳወቅ የሚችሉ የሀገር ብርቅዬ ልጆች መኖራቸው የማይካድ ነው፡፡ በዓለም አደባባይ የሀሰት በትረ መክተው አክሽፈዋልና፡፡
በተለይ መንግስት በትግራይ ክልል ከወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ ምክንያታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በኢትዮጵያ ላይ ለመፍጠር እየሰሩ ያሉ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን መኖራቸው ይታወቃል። ነገር ግን እነዚህ አካላት የኢትዮጵያን መልካም ስም በሚያጎድፍና በሚያጠለሽ መልኩ ሀሰተኛ መረጃ ሲነዛ ዝም አላሉም ይልቁንም ነገርን ከስሩ ብለው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ከሳሾቻችን እንዲረዱት አደረጉ እንጂ በዚህም ትልቅ ውጤት በመምጣቱ ኢትዮጵያ በስደት ባሉ ልጇቿ ኮርታለች።
እነዚህ የዲያስፖራ አባላት የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፤ ትውልድ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሀገር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማስገንዘብ ሰፊ ስራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡ ኤጀንሲ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ተገቢ ያልሆነ ጫና ለመመከት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በሀገሪቱ ላይ የሚፈጸመውን ተገቢ ያልሆነ ጫና ለመቀልበስ ጥረት እያደረገ መሆኑን የሚናገሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ናቸው፡፡ መንግስት በትግራይ ክልል የትኛውም ቡድን የከፋ ጉዳት እንዳይገጥመው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ትክክለኛ መረጃ ለዓለም እያደረሱ አይደለም ብለዋል። በመሆኑም ኤጀንሲው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲይዝ ዲያስፖራውን የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ወይዘሮ ሰላማዊት ገለጻ ኤጀንሲው ይህን ተገቢ ያልሆነ ጫና ለመቀልበስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር እየሰራ ነው። በተጨማሪም የሚዲያ ባለቤቶችና ለሚዲያ ቅርብ የሆኑ ሰዎች፣ የዲያስፖራ ሚዲያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያዊያን የትግራይ ክልልን የተመለከቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን እንዲመክቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያብራራሉ።
በዚሁ መሰረት በአሜሪካ፣ በካናዳና በጄኔቫ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሠላማዊ ሠልፍ በማካሄድ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል። የሠላማዊ ሠልፎቹ መልዕክት በዋናነት ማንም ሶስተኛ ወገን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችል ያመላከተ እንደሆነም አንስተዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ሠልፍ ከማድረግ ባለፈው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና ለመንግስታት እውነታውን እንዲረዱ ፊርማ አሰባስበው መላካቸውን ጠቅሰው። በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዝኛና በዓረብኛ ቋንቋዎች ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚያንፀባርቁ ጽሁፎችን እየጻፉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም የዲያስፖራው ማሕበረሰብ በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የሶስተኛ ወገን ጫና ለመመከት መትጋት እንዳለበት ማስገንዘባቸው ባለፈው ሳምንት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
እነዚህ በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉ ለሀገራቸው ዘብ የቆሙ ኢትዮጵያዊያን፤ ትውልድ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መቼም ቢሆን ከኢትዮጵያና ከወገኖቻቸው እንደማይለዩ ያሳዩበትም ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013