ውብሸት ሰንደቁ
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተገነባው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሰሞኑ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል አመራሮች ተገኝተዋል።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እየተገነባ ያለው የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ በከፊል ምርት ማምረት ጀምሯል። በ294 ነጥብ 5 ሄክታር ላይ የተገነባው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢትዮጵያን ቀጣይ አቅጣጫ የሚያሳይ ነው ተብሎለታል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልዩ የሚያደርገው የግብርና ምርቶችን ማቀነባበር ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው። ይህ ለእንደ ኢትዮጵያ ዓይነት የግብርና መር ኢንዱስትሪ ተከታይ ታዳጊ ሀገራት ወደሚቀጥለው ግባቸው ለመሸጋገር የሚያደርጉትን ጉዞ አጋዥ ነው። በፓርኩ እስካሁን ከተገነቡት 11 የምርት ቦታዎች ውስጥ አራቱ በማምረት ላይ ናቸው።
ስምንት ተጨማሪ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር እና ሌሎች ፍላጎቶችን በመፍጠር የማሽን ተከላ ከተጠናቀቀ በኋላ ምርት ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሆኑም በፓርኩ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል። በፓርኩ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በአቮካዶ ዘይት፣ በማር እና በቡና ማቀነባበር ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
በቀጣይም በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን፣ የወተት ተዋጽኦዎችን፣ ሥጋ፣ ዶሮ፣ ቡና እና ጥራጥሬዎችን እንደሚያቀነባብሩ ተገልጿል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየርና ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በይርጋዓለም የተገነባው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልጠዋል።
ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ አጠቃላይ ወጪው 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን በመጀመሪያ ምዕራፍ 11 ሼዶችን ተገንብተው ተመርቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሲዳማ ለረጅም ዓመታት ተንከባክቦ ያቆየውን የእንግዳ ተቀባይ ባህሉን በተደረገላቸው አቀባበል መረዳታቸውን ተናግረው በተለይ በባህላዊው የዳኝነት ሥርዓት እውነትን በመፍራትና ተረጋግተው ነገሮችን በመከባበርና በንግግር መፍታት መቻሉ ከክልሉ አልፎ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።
የሀገራችንን ሥም በአሉባልታ እያነሱ የሚያጠለሹ ያጠነክሩናል እንጂ ኢትዮጵያን አያፈርሱም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአርሶ አደሩን ህይወት ለፖለቲካ ፍጆታ ብሎ የሚቀጥፉና ደምን የሚያፈሱ ቡድኖች ከሲዳማ አብሮነት ባህል መማር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ የምረቃ ስነስርዓት ላይ እንደገለፁት የአግሮ ፕሮሰ ሲንግ ዘርፉን ዕድገት በማፋጠን ሀገራችን ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ልማት ለምታደርገው መዋቅራዊ ሽግግር መሳካት፣ የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃና የሀገርን ኢኮኖሚ ከፍ በማድረግ ረገድ ሚናቸው ላቅ ያለ ነው።
የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የአምራች ኢንዱ ስትሪዎችን ልዩ ባህሪ የተከተለ በመሆኑ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችና ባለሙያዎች ለማፍራት ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የተወገዘው የፕሮጀክት አፈፃፀም መጓተት በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንዳይደገም በተደረገው ከፍተኛ ክትትል ሥራው ፍሬ አፍርቷል ያሉት ሚኒስትሩ ሀገሪቱ በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆና ለተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ወደ ውጭ የምንልካቸው ምርቶች ጥሬ ሀብቶች በመሆናቸው ከዘርፉ ከፍተኛ ውጤት እንዳናገኝ ሲያደርገን መቆየቱን ነው የገለጹት። የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከማስቻሉም ባሻገር ለዜጎቻችን ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ይናገራሉ።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በዘርፉ ለማሳደግ በተሠራው ሥራ በ2003 ዓ.ም 4 ነጥብ 5 ከነበረበት እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ 6 ነጥብ 5 ብቻ ከፍ ማድረግ መቻሉ የዘርፉን ዕድገት ዘገምተኛነት እንደሚያሳይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። አክለውም ችግሩን ለመቅረፍ በውጭ የሚገኘውን ምንዛሪ ለመጨመርና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚደረግ ሽግግር የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ አንዱ ማሳያ መሆኑን አክለዋል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ክልል ያለው ውስን መሬት ቢሆንም ትልቅ የሰው ኃይል መኖሩን ጠቅሰው ዜጎች ለገበያ የሚያበቃቸውን ሙያ በመሠልጠን ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል። የክልሉ ነዋሪ አርሶ አደር ይህን የተመረቀውን የይርጋዓለም የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚፈልገውን የግብርና ግብዓት በማቅረብ ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም በእርሻውም ሆነ በጓሮው በማልማት ፋብሪካው የሚፈልገውን ምርት ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል። ባለሀብት እና ነጋዴውን ህብረተሰብ ለመሳብ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በትኩረት መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩ ወልዴ ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 152 ሼዶችን የመያዝ አቅም እንዳለው ገልጸው፣ ለ100 ሺህ ዜጎች በቀጥታ እና 300 ሺህ ለሚሆኑት በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት ።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በይርጋለም የሚገኝ አግሮ ፕሮሰስንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል።
ክልሉ በግብርና ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም መንግሥት ግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባት ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር ሚናውን እንዲወጣ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ለፓርኩ የሚሆኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ሥራ ተጠናቅቋል ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርክ አራት የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች አሉ ያሉት ሥራ አስኪያጁ በአጠቃላይ 152 ሼዶች ለመገምባት እንደታቀደና ይህንን በአንድ ጊዜ ገምብቶ መጨረስ ስለማይቻል በአሁኑ በመጀመሪያ ዙር የተጠናቀቁ ሼዶች አልቀው ወደ ሥራ ለማስገባት ማስመረቅ አስፈልጓል ብለዋል።
የቡና፣ የወተት፣ የማር እና የመሳሰሉት ወደ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ሥራ በመግባት አገልግሎት ሲሰጡ መቆየቱን አስታውሰው የአቡካዶ ዘይት ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ 17 ጊዜ ወደ ውጭ መላክ መቻሉን ገልፀዋል።
በክልሉ የሚታየው የግብርና ምርቶች አቅም የላቀ መሆኑን እንዲሁም ፀጥታና ሰላም ጉዳይ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ስለሆነ ገንዘባቸውን በዚህ ፓርክ ውስጥ በመግባት ኢንቨስት ለሚያደርጉት መንገዱ ክፍት መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
መሪዎች ስለ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም ስለ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚናገሩት በተጨማሪ ጠቀሜታቸውን በሚዛኑ ለማየት በዘርፉ ያሉ ምሁራንን አስተያየት ምን እንደሚሉ ማዳመጥ ተገቢ ይሆናል። አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው። አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምን ጠቀሜታ አላቸው ስንል ጠይቀናቸዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንዲህ ይላሉ፡- አግሮ ኢንዱስትሪ ሲባል የግብርናውን ዘርፍ (አግሪካልቸራል ሴክተርን) እና የኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚያገናኝ ድልድይ ነው። የአግሪካልቸራል ሴክተር ውስጥ ያሉትን አካላት ማለትም ገበሬዎችን እና የኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚመራውን ኢንዱስትሪያሊስት የሚያገናኝ ነው አግሮ ኢንዱስትሪ። አግሮ ኢንዱስትሪዎች ሲኖሩ ጥሬ የሆነውን ምርት የሚያመርተው ገበሬ በቀጥታ ገበያ ያገኛል።
ለምሳሌ ብናነሳ አቦካዶን ፕሮሰስ አድርጎ የሚያቀርብ ኢንዱስትሪ ካለ አቡካዶ የሚያመርተው ገበሬም ተጠቃሚ ይሆናል። በተመሳሳይ ሽንኩርት፣ ወተት፣ ድንችና የመሳሰሉትን ፕሮሰስ የሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች በበዙ ቁጥር እነዚህን የሚያመርቱ ገበሬዎች ምርታቸውን የሚገዛቸው ስለሚያገኙ በቀጥታ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ገበሬ ለምርቶቹ ገበያ አገኘ ማለት ነገ ከነገ ወዲያ ምርቶቹን በጥራትና በብዛት ለማምረት ዕድል ይፈጠርለታል።
አግሮ ኢንዱስትሪ ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች የሚለ የው የሚያመርታቸው ምርቶች አብዛኞቹ የሚበሉ ምርቶች መሆናቸው ነው። ይህ ኢንዱስትሪ እንደዚህ ዓይነት ምርቶችን በብዛት በአመረተ ቁጥር ደግሞ የምግብ ዋጋ ግሽበት ይቀንሳል። ምክንያቱም ፍላጎቱ እንዳለ ሆኖ አቅርቦት ከፍ ሲል ዋጋ ወደታች የመውረድ አጋጣሚዎች ስላሉ ነው። በመሆኑም የዚህ ዓይነት ኢንዱስትሪዎች መኖር የዋጋ ንረትን በእጅጉ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
የአግሮ ኢንዱስትሪዎች መኖር በሁለት ረገድ ጥቅሞችን ያበረክታል። የመጀመሪያው ለገበሬው ትልቅ የገበያ ዕድል መፍጠሩ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለምርት ተጠቃሚው ዋጋ እንዲቀንስ ማስቻሉ ነው። በዚህ መንገድ ገበሬው ገቢ ያገኛል ከተሜው ደግሞ ዋጋው ሳይወደድና ሳይንርበት በቀላሉ ምርቶችን የማግኘት ዕድል ይፈጠርለታል።
ይህም ሲጠቃለል የአግሮ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ለማድረግና የሀገርን ዕድገት ለማፋጠን ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪም አግሮ ኢንዱስትሪ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር አወንታዊ ሚና ይጫወታል። ይህ የሚሆነው በዋናው በኢንዱስትሪው ውስጥ ተቀጥረው ሊሠሩ ከሚችሉት ሠራተኞች ባሻገር በገበሬዎች ማሳ ላይ በርካታ ምርት ለማምረት ሲባል ተጨማሪ ጉልበት ተጠቅመው ማምረት ስለሚጀምሩ ነው።
የአግሮ ኢንዱስትሪ ሌላኛው ጥቅሙ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት መቻሉ ነው። ለምሳሌ ታሽገው ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ የሚውሉት የጁስ መጠጦች በአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊዘጋጁ የሚችሉ ናቸው። ማንጎ ይርጋ ዓለም ተመርቶ ከዚያም በይርጋ ዓለም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮሰስ ተደርጎ የሚቀርብ ከሆነ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ሳታወጣ ህዝቡም በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን እንዲያገኝ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ መንገድ አግሮ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ከቻሉ የሀገር ውስጥ ፍጆታን መሸፈን ብቻ ሳይሆን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ተጨማሪ ጥቅሞች ሊገኙበት የሚችል ዘርፍ ነው።
በመጨረሻም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አግሪካልቸራል ኢንዱስትሪዎች ለግብዓትነት የሚጠቀሟቸው ምርቶች በብዛት በሚመረቱባቸው አካባቢዎች መስፋፋት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የሆነ የማንጎ ምርት አለ፤ ይህን ለመጠቀም ምርቱን እንደግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በዚያ አካባቢ ቢገነቡ፤ በተመሳሳይ ከፍተኛ የእንስሳት ምርት ባሉባቸው አካባቢዎችም ከወተትና ሥጋ ልማት ጋር የተያያዘ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ቢሰማሩ ኢንዱስትሪዎቹ ውጤታማ ይሆናሉ። ነገር ግን ለፖለቲካ ግብዓትነት ተብሎ በክልል ደረጃ እየታሰበ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማልማት ሥራ የሚከናወን ከሆነ ኢኮኖሚካሊ አዋጭ ላይሆን የሚችልበት ዕድል ይፈጠራል ሲሉ አሳስበዋል።
በይርጋዓለም የተገነባው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከፊል ገጽታ፤
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013