ግርማ መንግሥቴ
እንደ መታደል ሆኖ ስለ ድሬ ያልተባለ የለም። ከድሮው ከዘመነ ጋሪ ጀምሮ እስከ አሆኗ ዘመነ ባጃጅ ድረስ ሁሉም ስለ ድሬ እሚለውን ሁሉ እያለ ነው።
ድምፃዊው በድምፁ፤ ሰአሊው በብሩሹ፤ ፀሀፊው በብእሩ ስለ ድሬ ያላለው የለም። ይህ ደግሞ የሚቀጥል እንጂ የሚቆም አይደለም። ይህ ጽሑፍም ከእነዚህ ሁሉ የቀጠለና ታሪኩን ወቅታዊ የማድረግ ስራ አካል ነውና በዚሁ ስምምነት እንቀጥል።
ድሬዳዋ ከሁለቱ የኢትዮጵያ ከተሞች አስተዳደር አካባቢዎች አንዷ (በድሮዎቹ ስርአታትም ከአዲስ አበባ ቀጥላ የአገሩቱ ሁለተኛዋ መዲና) ናት፤ በሌላ አገላለፅ ሌላኛዋ አዲስ አበባ ማለት ነው። (በ1999 በተካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃ መሰረት ከአጠቃላይ የአስተዳደሩ ነዋሪ መካከል ከሁለት ሶስተኛው በላይ በከተማዋ ነዋሪ ነው።)
አቶ መርሻ ናሁሰናይ በተባሉ ባለውለታዋ መቆርቆሯ (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1894-1898፤ እኤአ ከ1902 – 1906) የሚነገርላት ድሬዳዋ ቆርቋሪዋና የመጀመሪያ አስተዳዳሪዋን ሁሌም የምታስታውስ ሲሆን ለዚህም በተለያዩ ህትመቶቿ ላይ የምታሰፍራቸው ሀሳቦቿ ምስክሮች ናቸው።
ድሮ ድሮ (ልጅ ሆነንም ሆነ ከእኛ ቀደም ያሉት) ድሬ የምትታወቀው በሞቀና በደመቀ ንግዷ፤ በደራና ጎመራ ቢዝነሷ ሲሆን ለዚህ ደግሞ “ባቡሬ” ቀዳሚና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። (“ባቡሬ”ን ከስለሺ ደምሴ ዜማ የተዋስኩት የሀሳብ ማንሸራሸሪያ ነው፤ “ባቡሬ / ይዞኝ ገባ ድሬ” እንዲል።)
ከተመሰረተ ከሐያ ዓመታት አድካሚ ስራ በኋላ በ1911 ተሰርቶ የተመረቀው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት በአዲስ አበባና ጂቡቲ መካከል ጉዳዬ ብሎ ከሚያስተናግዳቸው ከተሞች ያለ ምንም ተወዳዳሪ ድሬዳዋ የምትገኝ ሲሆን የድሬ ሁለመና ሲነሳ “የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት”ን ማንሳት የግድ ነው፤ የድሬና ድሬዳዊያን የአኗኗር ዘይቤና የኑሮ ፍልስፍናን ካነሱ ይህንኑ ድርጅት (በቀድሞው ስሙ ፍራንኮ-ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ድርጅት) ሳያነሱ ማለፍ አይቻለዎትም። የድሬ እንቅስቃሴ ባቡር ነው፣ የድሬ ኢኮኖሚ ባቡር ነው፤ የድሬ ጉሮሮ ባቡር ነው፤ የድሬ የውጭና የውስጥ ግንኙነት ባቡር ነው። “ባቡሬ / ይዞኝ ገባ ድሬ” እንዲል ድምፃዊው።
ድሬና ባቡሬ፤ ንግዷንና ባቡሬን፤ ስልጣኔዋንና ባቡሬን፤ ትራንስፖርቷንና ባቡሬን፤ አጠቃላይ ማንነቷንና ባቡሬን ለያይቶ አይደለም ለይቶ እንኳ ማሰብ የሚታሰብ አይደለም። (በመሀል ከተማው የተንጣለለውና ከ30 ዓመታት በላይ የተወረረ ከተማ መስሎና ተዘግቶ የተቀመጠውን የድርጅቱን ጣቢያና ሽንጣም ጊቢውን በአይነ ህሊናዎ ይመለከቱ።)
ከዚሁ ከባቡርና ባቡሬ ጋር በተያያዘ ወደ አሁኑ ዘመን ስንመጣ አዲሱን የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር መስመር እናገኛለን።
መስመሩ አዲስ የተዘረጋ ሲሆን ከበፊቱ በጣም ለየት የሚያደርገውና ድሬዎችን ብዙም ያላስደሰተው ጉዳይ መስመሩ ከከተማው ውጪ 12 ኪሎ ሜትር ላይ እንዲያልፍ መደረጉ ሲሆን፤ እንደዛም ሆኖ ባቡር የገደላትን ድሬ ባቡር ያነሳታል የሚለው የተስፋ ድምፅ ከሁሉም ጎልቶ የሚሰማ ድምፅ ነውና እኛም ለድሬ ይህንኑ እንመኝላታለን፤ “ባቡሬ / ይዞኝ ገባ ድሬ”ም እንላለን።
ስለ ድሬዳዋ ሲነሳ ከማንም በፊት ቀድሞ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያዊያን እሴት የሆነው፤ ከግላዊነት ያፈነገጠው የማህበራዊ ህይወት ጉዳይ ነው።
ከዚህ አኳያ ምንም እንኳን አሜሪካንና ድሬን ማወዳደር ያላቻ . . . አይነት ነገር ቢሆንም የሚተያዩበትና የማይተያዩበት ጉዳይ ካለ ግን ማንሳቱ ክፋት የለውም።
አሜሪካ ከምትታወቅባቸው እሴቶቿ ዋናው የሄደን ሁሉ “አስምጦ” (“አቅልጦ”ም ይሉታል) የማስቀረት ብቃቷና ማንም ከማንም ሳይል ሁሉም እኩል መኖር መቻሉ ሲሆን፤ ይህም “melting pot” የሚል ማእረግንና መታወቂያን አስገኝቶላታል። ከዚህ አኳያ ድሬንም በዚሁ መነፅር ስንመለከታት ተመሳሳይ ሆና ነው የምናገኛት። እንደ ብዙዎች የአይን እማኝነት ድሬ የገባ ተመልሶ ይወጣል ማለት ዘበት ብቻ ሳይሆን ከቶም የሚታሰብ አይደለምና ነው።
ከዚህ አኳያ ከአሜሪካ ጋር ስናስተያያት ከሌላ ማለትም ከ”ግላዊነት” እና “ማህበራዊነት” አኳያ ካስተያየናቸው ሁለቱንም በሁለት ጎራ ቆመው ነው የምናገኛቸው። በዚህ በኩል ምንም አይነት የጋራ ነጥብ የላቸውም። ምን ማለታችን ነው፤ የአሜሪካኖች የኑሮ አተያያቸውም ሆነ ፍልስፍናቸው “ግላዊነት” (ኢንዲቪጁዋሊዝም)ን መሰረት ያደረገ፤ ድሬዎች ግን ያለ ሰው እማይሆንላቸው መሆናቸው ነው። (ጉዳዩ ሰፋ ላለ ጥናት መነሻ ሊሆን ስለሚችል በዚሁ እንለፈው።)
ድሬ ከማህበራዊ ህይወትም ሆነ አብሮነት አኳያ የምታራምደው ፖሊሲ “በሰላም አብሮ የመኖር” (peaceful co-existence) ፖሊሲን ሲሆን ይህም በመርህ ደረጃ አለምን እንዲገዛ የሚፈለግ ጽንሰ ሀሳብ ለብዙዎች ባይሳካም ለድሬ ግን ተሳክቶላት እየኖረችው ትገኛለች።
እንደተመለከትነው አብሮነት ለድሬ እሴቷ ነው። ስራ ባህሏ ሲሆን ጉራማይሌነት (በተለይ ከቋንቋ እና ሀይማኖት አኳያ) ጌጧ ነው።
በድሬ በአገር በቀል እውቀትነታቸው እጅጉን የሚታወቁት እሴቶቻችን አሁንም ከነ ሙሉ ጤንነታቸው የሚገኙ ሲሆን ለዚህም መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ መከባበር፣ መደጋገፍ፣ አብሮ መብላት፣ አብሮ መጠጣት እና የመሳሰሉትን መጥቀሱ በቂ ነው። (አሁን ካለንብት ክፉ ዘመን አኳያ ይህን ለማመን የሚቸገር ካለ የምንመኝለት አንድ ጥሩ ነገር ቢኖር ብቅ ብሎ በትንሹ አንድ ሳምንት ድሬን እንዲጎበኝ ብቻ ነው። ከዛም እያልን ያለነውን በአምስቱም የስሜት ህዋሳቱ ያጣጥመዋል።)
በድሬ “እኛ/እነሱ” የሚባል ከፋፋይ ፍልስፍናና የአንድነት ጠር የሆነ አስተሳሰብ ጭራሽ አያገኙም (አያወራን ያለነው ስለድሬዎች እንጂ ስለ ግለሰ(ቦች) አለመሆኑን ልብ ይሏል)። ላጭር ጊዜም ቢሆን ተዟዙሬ እንደተመለከትኩት በድሬ በ”እኛ” እና “እነሱ” የተነሳ ምንም አይነት ንቁሪያም ሆነ ንትርክ፤ አለያም ውዝግብ አልተመለከትኩም። እንግዳ መቀበል፤ በተቀበለችው ፍጥነትም ማላመድና ማዋሀድ (እንደ አሜሪካ “melting pot” ማለት ነው) መለያዋ ነው። ለምን ቢሉ ድሬ ሄዶ ከተመለሰው ይልቅ እዛው ቀለጦ የቀረው ይበልጣልና ነው።
ድሬ እድገቷ የኋልዮሽ ቢሆንም ንቃትና ቅልጥፍናዋ፤ ተግባርና እንቅስቃሴዋ፤ ሳቅና ፈገግታዋ ከኋላዋ ተነስተው ካደጉት፤ ብጤ ከተሞቿ ቢበልጥ እንጂ ያነሰ አይደለም።
እነዚህ ብቻም አይደሉም፤ ድሬዎች የመኖር ፍልስፍናቸው ካደረጓቸው እሴቶቻቸው መካከል አንዱ “መተማመን” ስለ መሆኑ እዛ ሆኖ ለተመለከተ አሻሚ አይደለም። ድሬ ውስጥ እርስ በርስ መተማመን ጎልቶ ይታያል። ባዶ ሱቅ ጥሎ ረጅም ሜትሮችን ለሌላ ጉዳይ መሄድና ዘግይቶ መምጣት ብርቅ አይደለም። ምን ይህ ብቻ፤ ይህ ፀሀፊ ቆይታ ባደረገበት ገንደ ቆሬ አካባቢ በምግብ ቤቶች “ቦኖ” የሚባል ነገር የለም። አንዳንድ ቀንማ የምግብ ቤቱ ባለቤትም አይኖርም። የምግብ ቤቱ አስተናጋጆች ግን ሁሉም ስራቸውን ይሰራሉ። ሁሉም በየፊናው ያቀርባል፤ ሂሳቡን በየፊናው ይቀበላል። መጨረሻ ላይ ሁሉም የየራሱን ሂሳብ አውጥቶ ይቆጥርና “እኔ የሸጥኩት ይሄንን ነው” የሚል በሚመስል አይነት ሂሳቡን ለባለቤቱ ያስረክባል። እንደ እነዚህ አይነት የአኗኗር ፍልስፍናዎችና ዘይቤዎች ብዙ ናቸው። እንደ አጠቃላይ ሸፍጥ፣ ሸር፣ ውሸት፣ ክህደት፣ ማጭበርበር . . . ለድሬዎች አልተፈጠሩም ማለት ነው። በቃ ህይወት በድሬ እንዲህ ናት።
በድሬ ከምሽቱ ሁለትና ሶስት ሰዓት ላይ ምን የመሰለ ስማርትፎን (የእጅ ስልክ) ከኪስ/ቦርሳ (ወንድም ይሁን ሴት) አውጥቶ በማናገር (አዲስ አበቤዎች ይህን እንዳይሰሙ) ኮራ ጀነን ብሎ ዎክ ማድረግ ምንም የሚያስደንቅ ነገር የለውም። ወደ ከዚራ አካባቢ ብቅ ቢሉ ይህንን እስኪገርሞት ድረስ ይመለከታሉ። ሞባይል ከጣሉም ብዙም ላይሰጉና መልሰው ሊያገኙት እንደሚችሉ ማሰብ የተለመደና ጓደኛችንም የገጠመው ጉዳይ ነውና ማመን መተማመን በድሬ ሞልቷል። (ይህን ስንል ግን አሸዋ ሜዳ ታክሲ ተራን ይጨምራል እያልን አይደለም። እዛ ሲደርሱ እራሳቸው ድሬዎች “ተጠንቀቁ” ይሉዎታልና አይስጉ።)
በድሬ ከሌሎች ለየት የሚሉ በርካታ ነገሮች ሞልተዋል። እንዘርዝራቸው ብንል መሀል ድረስ እንኳን መዝለቅ አንችልም። ሰውየው “ያለን እድል” እንዳለው ሁሉ እኛም ያለን እድል ነካ ነካ ማድረግ ብቻ ሲሆን፤ ከሚነካኩትም አንዱ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ የባህል (ኪነት) ቡድን አባላት ናቸው።
በድሬ ኪነት አባላት ሲያቀነቀኑ የሚሰሙ የኪነ ጥበብ ስራዎች፤ በተለይም ዜማዎች በሌሎች አካባቢዎች እንደምንሰማው በአንድ ነጠላ ጉዳይ፣ ነጠላ ቋንቋ፣ ነጠላ ብሄር ወዘተ ላይ የተንጠለጠሉ ሳይሆኑ አካታች ናቸው። ሁሉም ብሄር ይወደሳል፤ ሁሉም ሰው ይደነቃል፤ ሁሉም ቋንቋ ይቀነቀናል፤ ሁሉም ሃይማኖት ይከበራል ወዘተ። ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ በአንድ ማእቀፍ ውስጥ ነውና ከማንም እና ምንም በላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይነግሳል። ለአገራችን ሰላም ይዘንብ፣ ፍቅር ይነግስ፣ እድገትና ብልፅግና ይስፋፋ ዘንድ በኪነት ቡድኑ አባላት አንደበት ይቀነቀናል። (በዚሁ ዓመት የተለያዩ በክልሉ ሲካሄዱ የነበሩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ ከየክልሎች ወደ ከተማዋ የመጡ እንግዶችን በተመለከተ በተዘጋጁ የአቀባበል ፕሮግራሞች ላይ የታየው ይሄው ነው።)
ድሬን ከሌሎች ልዩ ከሚያደርጓት አንዱ የአየር ንብረቷ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ሙቀቱ 89 ዲግሪ ፋራናይት መተንፈሻ ሁሉ ጠፍቶ ነበር።
እዚህ ላይ አንድ መጥቀስ የሚያስፈልግ አቢይ ጉዳይ ቢኖር የአረንጓዴ ልማት ጉዳይ ሲሆን፤ እሱም የወደፊቱን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች መሰራት ያለባቸው መሆኑን ማመለክት ነው።
የቀድሞው ትውልድ በተከላቸው ዛፎች የዛሬው ትውልድ መኖር ከቻለ የነገውስ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል። በመሆኑም ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ የእፅዋት ዝርያዎችን በማፈላለግ ማፅደቅና አሳሳቢ የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ያስፈልጋል።
ሌላው ከሌሎች ከተሞቻችን ሁሉ ድሬን ልዩ የሚያደርጋት በአገራችን የኮብልስቶን ታሪክ ቀዳሚ የመሆኗ ጉዳይ ነው።
ከተማዋ እምብርት ላይ ቆሞ እንደሚገኘውና ለመታሰቢያነት የቆመው የኮብልስቶን ሀውልት ላይ ተፅፎ እንደሚነበበው ድሬ ኮብልስቶንን እንደ አንድ የልማቷ አካል አድርጋ ያስገባችው በ1935 ነው። ይህም በከተማዋ የተገነቡ ኮብልስቶን መንገዶች የተዋጣላቸው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የሚገርመው ነገር ኢትዮጵያ ኮብልስቶንን ገና አሁን ያወቀች ይመስል አንዴ ጀርመን አንዴ ጣሊያን ሲባል መከረሙና የረባ ልምድ እንኳን መቅሰም አለመቻሉ ነው።
የድሬ ገፅታ ብዙ ነው። መሀል ከተማዋን ያየ አሸዋ ሜዳ ሲሄድ ቢለወጥበት አይገርምም። በአሸዋ ሜዳና ታይዋን አዳራሽ ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ ነው። ከሁሉም ለየት የሚለው ግን ብዙም የማይነገርለት ከአልባሳት ባለፈ ያለው ንግድ ነው።
ይህ ንግድ በአብዛኛው ምግብና ምግብ ነክ የሆኑት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አይነቱም ብዙ ነው። ዝርዝሩ ብዙ ሲሆን ከሁሉም የሚገርመውና ምናልባትም ውጪ አገር መኖሩ ሲነገር የምንሰማው ከፈጣን ምግቦቹ መካከል አንዱ ጭማቂ (ጁስ) መሆኑ ለሁሉም ሰው፤ በተለይም ኪሱ ላላበጠ ነዋሪ ምንኛ አስፈላጊና የተመጣጠነ ምግብን ለማግኘት እንደሚረዳው አያጠራጥርም። ይህን በይበልጥ ለመረዳት አዲስ አበባን ማሰብ ያስፈልጋል። አዲስ አበባ ጁስ የሀብታሞች ብቻ ሊሆኑ ትንሽ ከቀራቸው የምግብ አይነቶች አንዱ እየሆነ ነውና ነው።
እዚሁ አሸዋ ሜዳና አካባቢው ላይ ለየት ያለ ነገር የሚታይ ሲሆን እሱም የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ ነው። ብዙ ምግብ ቤቶች ከደንበኞቻቸው ጋር እንደ ዋዛ የሚለያዩት በፍጥነትና መዘግየት መካከል ባለው ልዩነትና ለጊዜ ባላቸው አረዳድ ምክንያት ነው። ድሬዎች ይህን የፈቱ ይመስላሉ። እንዴት? ለሚለው በረከቦት መሰል ምድጃ በአንድ ጊዜ ከ20 እና 25 በላይ ድስቶችን (በተለይ የፉል) መጣድና ማውጣት የመጣ ሰው በመጣበት ፍጥነት መስተናገድ እንዲችል የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሳቸው ነው። (ፈጠራውን በማየት እንጂ በዚህች ፅሁፍ መግለፅ ከባድ ነው።)
በድሬ እንደሌሎች ከተሞች የግንባታ ማእበል አይኑር እንጂ፤ ውሀ በፈረቃ ይሁን እንጂ፤ የቴክኖሎጂ ልማት በስፋት አይታይ እንጂ፤ የስራ እድል እጥረት ይስተዋል እንጂ፤ ኮቪድን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥንቃቄ አስፈሪና አስደንጋጭ ይሁን እንጂ፤ የወጣት መዝናኛ ማእከላት በሚፈለገው ልክ ይኑሩ አይኑሩ ለማወቅ አስቸጋሪ ይሁን እንጂ፤ እንደ ሌሎች ያገሪቱ ክፍሎች ሁሉ በኑሮ ውድነት ማእበል ትናጥ እንጂ ወዘተ ወዘተ በድሮው ባቡር መስመር መቋረጥ የተገፈፈችውን ግርማ ሞገስ አሁን በተዘረጋው አዲሱ ኢትዮ-ጂቡቲ መስመር (ምንም እንኳን ከከተማዋ 12 ኪሎ ሜትር እርቆ የተዘረጋ መሆኑ ብዙዎችን ቢያሳዝንም) የህዳሴ ጉዞዋን ትጀምራለች የሚል ተስፋ በብዙዎች አለ።
ወደ ማጠቃለሉ እንምጣ። “ድሬና የአኗኗር ፍልስፍናዋ” ብለን ስንነሳ እነዚህንና እዚህ ያልጠቀስናቸው ሌሎች በርካታ ማህበረ-ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ታሳቢ አድርገን ሲሆን፤ ባጭሩ የድሬዎች የአኗኗር ፍልስፍና በፍቅር፣ አብሮነት፣ መተሳሰብ፣ መተባበር፣ በሰላም አብሮ መኖር፣ መደጋገፍ፣ መረዳዳት፣ አቃፊነት፣ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ቀለል ያለ ህይወትን የመምራት (Simplicity)፣ “አለማካበድ”፣ እኩልነት፣ አልማጅነት/አስማጭነት ወዘተ ወዘተ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለማፅናት፤ ይህ ሁሉ ደግሞ መሰረቱ አገር በቀል እውቀት መሆኑንና ሳይሸራረፍ እዚህ መድረሱን ከስሩ ለማስመር በማሰብ ነው። በዚሁ ከቀጠለችም ድሬ እንደነ ኒው ዮርክ ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ የሰው ልጅ ዝርያዎች በሰላም አብረው የሚኖሩባትና ከ800 በላይ ቋንቋዎች ያለ ምንም ችግር የሚነገሩባት ከተማ በመሆን ዓለም አቀፍ ሽልማት የማታገኝበት ምክንያት የለምና ያንን ቀን በጋራ እንጠብቃለን። በአራት ቀን የከተማዋ ቆይታ መነሻነት ይህን ጽሑፍ ስናዘጋጅም ምኞታችንም ይሄው መሆኑን ጭምር መናገር ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2013